Print this page
Thursday, 15 July 2021 00:00

የስብሐት የአርባ ዓመታት ቁዘማ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)


           "--በእርግጥም የርባገረዱ ልጅ እግሩ ስብሃት፣ እንደ ካህሊል ለዓለምና ለሕይወት አይናፋር ነበር፡፡ ግን ተስፋዬ ገሠሠን፣ ሰለሞን ደሬሳን፣ ሀና ይልማን፣ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ ወዳጆቹ ተራ በተራ እጁን ይዘው እየሳቡ ወደ ሕይወት ይሉት የሚያዳፋ አዙሪት አንደረደሩት፡፡--"
             
            የአንዳንድ ሰዎች ሕይወት የሆነ ገጽ የጎደለው፣ ደራሲው የማይታወቅ የጠፋ መጽሐፍ የሚመስል ገጽታ አያጣም፡፡
‹ይመስላል ከተማው
አሮጌ መጽሐፍ ግማሽ ገጽ የጠፋው›
እንዲል ገጣሚው ደምሰው መርሻ…
ሕይወታቸው የቱንም ያህል ቢጻፍ የቱንም ያህል ቢለፈፍ ግን የተሟላ መልዕክት የለውም፡፡ እነሱ የተጻፈላቸውን የተነገረላቸውን አይደሉም፡፡ #ይሄን አይደለሁም፤ እኔ እኮ እንዲህ ነኝ; አይሉም- በጭጭታ ግዴለሽ መስለው ሲሲፐሳዊ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ሕይወታቸው የሆነ ግር የሚል ያልተዳሰሰ ስንኩል ገጽታ አያጣም፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ለእኔ፣ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ነው፡፡
እኔ ስብሐት ለአብን በአካል አላውቀውም፡፡ ብቻ በርሱ ዙሪያ የነበሩ ሚካኤል ሽፈራው ዓይነት ደቀ መዛሙርቱ ስለ እርሱ የሚወረውሯቸውን ስብርባሪ ትርክቶች እንደ ቢራቢሮ ሳሳድድ ነበር፡፡ ግን እጠይቃለሁ፤ በእውን የስብሐት ለአብ ዕብደት የሚመስል፣ ግርታ የታከለበት የዝግመት ኑረት - ልሕቀት ወይስ ውድቀት? በእኔ እይታ ስብሐት በዕድሜ ዘመን ሙሉ የሚሳሳለትን መጫወቻ በጭካኔ ተነጥቆ፣ ረዳት አጥቶ እንደሚነፈርቅ ህጻን ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ይህን ትግሉን እንደ ምጥቀት ተቀብለው አጠገቡ ተቀምጠው ከአንደበቱ የሚወጡ ጣፋጭ ማባበያ ቃላትን እየቀለቡ፣ ያስተጋቡልን ትንታጎች አንዳቸውም እንኳን በነፍሱ የሚፍገምገምበትን ምክንያት ያወቁት አይመስልም፡፡
ይህ ሁሉ የሆነው ለስብሐት ለአብ የመጀመሪያ ምናልባትም የመጨረሻም ፍቅረኛው በነበረችው በንሸጣ ምንጩ (muse) ሀና ይልማ ምክንያት ነው። ስብሐት በ1977 ዓ.ም አካባቢ ለዶ/ር ታዬ አሰፋ እንዳጫወተው፤ ከሀና ይልማ ጋር ከመለያየቱ፣ እድሜው 32 ዓመት እንኳ ከማለፉ በፊት "ትኩሳት" እና "ሌቱም አይነጋልኝ"ን ጨምሮ አራት ወጥ ልብወለዶችና ሌሎች አጫጭር ልብወለዶችን ጽፎ ነበር፡፡ (ብሌን መጽሔት፣ ጥር 2007 ዓ.ም) ከሀና ይልማ ጋር ከተለያየ በኋላ በቀጠሉት ድፍን አርባ ዘመናት፣ ለእንጀራ ሲባል ጋዜጣ ላይ ከወረወራቸው ስብርባሪ ሀሳቦች ውጭ ምንም የታቀደ ቅርጽና ደርዝ ያለው መጽሐፍ አልጻፈም። በሀና ይልማ ህልሙን የኪነት ንሸጣውን የተዘረፈው ሰው፣ አጠገቡ ለነበሩት ግን የሆነ የተጃጃለ ካሪኬቸር (caricature) ገጸባህሪ ነበር፡፡
‹‹… በእኔ የደረሰብኝን ልጨምርልህ፡፡ እኔ ከገንዘብና ከህግ በስተቀር የሚገዛኝ የለም። ከዚያ በላይ ፍቅር ነው የሚረታኝ፡፡ ሐና ግን ለእኔ ከዚያም በላይ ነበረች፡፡ እንዴት ልንገርህ እናቴ ማለት ነበረች፡፡ በሕይወትህ አንዳንድ ጊዜ ሙሉ ሰው የምትለው ሰው ይከሰታል፡፡ ለእኔ ሀና ይልማ ሙሉ ሰው ነበረች፡፡ በውበትም ዓይኔ ነበረች፡፡ በአካል ቁመናም ጭምር…›› (ማስታወሻ፣ ዘነበ ወላ ገጽ 138)
ስብሐት ለሀና ይልማ የነበረው ፍቅር ብዙዎቻችን በሩቁ እንደምንረዳው ፍትወት በሚያሰግረው የመውደድ ሲቃ የተቀነበበ አልነበረም፡፡ አምልኮ ነው፡፡ የዘነበ ወላ "ማስታወሻ" ላይ ሀና አጠገቡ ጋደም ብላ የጻፈውን ሲያነብላት ‹‹you are my author ካለችኝ፣ ለእኔ በምድር ከዚህ የሚበልጥ ሽልማት የለም›› ይላል፡፡ ይህች የፍቅር አምላኩ፣ ዓለሙን ሙሉ ያደረገችለት ጣዖቱ ግን በአንድ የተረገመ አመሻሽ፣ አስር ሺህ ብሮችና የሞት መልዕክት የሚመስል የስንብት ደብዳቤ ብቻ ጥላለት በቅጡ እንኳን ሳትሰናበተው፣ የሚወደውን የሦስት ዓመት ልጁን ይዛ ከአገር ኮበለለች፡፡ ሀና ለስብሃት ምናልባት እንደ ነፍስ አጣማሪ (soulmate) ነበረች፡፡ ስብሃት ከዚህች ሴት ጋር የነበረውን ሕልም የሚመስል ግንኙነት ሲያጣ ነገሩ ዱብዳ ሆነበት፡፡ ለሕይወት መበርገጉን የሚያባብልበት መደበቂያ ፈለገ፡፡ በሰርጉ ዕለት ምናልባት ከሥብራቱ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶበታል፡፡ ወይ ከእነ ጭራሹ አልተጠገነም፡፡  
በዚያች ምሽት ያነከሰው ልቡ በቀጠሉት አርባ ዘመናት እንኳን የተጠገነ አይመስልም። በቀጠሉት አርባ ዓመታት ምንም ግብ አልነበረውም፡፡ ለዕለት ውሎ ቁራሽ ዳቦና ጥቂት የጫት ዘለላ ካገኘ በቂው ነበር፡፡ በእርግጥ በየቅጽበታቱ በልቡ ላይ የደደረውን ቁዘማ ለማቅለል ርካሽ ፍትወትን ያሳድድ ነበር፡፡ በገባኝ ልክ ይህ መንጠራወዝ በሀና ምክንያት የገባበትን ወዲያው ወዲያው የሚያስደነግጥ፣ የባዶነት አዝቅት የማምለጥ የማያቋርጥና የማያባራ የሽሽት ጉዞ እንጂ ሴሰኝነት አልነበረም። ምናልባት በእያንዳንዷ ሴት እንስታዊነት ውስጥ የሚፈልገው ሀና ይልማን ይሆናል፡፡ ሲቆይ ግን ተሰላቸ ብለንም እናስብ፡፡
የግል ሕይወቱን በነጻነት ለሕዝብ በማቅረብ የምናደንቀው ስብሃት፤ ሀና ይልማን በተመለከተ ግን ይበልጥ ምሥጢራዊ የሆነ ይመስላል፡፡ ስለ ደረሰበት የልብ ስብራት አምልጦት በሚመስል ሁነት ለዘነበ ወላ ከነገረው ኩርማን እውነት ውጭ ለማንም፣ ምንም ያለ አይመስልም። ወይ የነገራቸው ሰዎች እናነበው ዘንድ አልከተቡልንም፡፡
‹‹… ደብዳቤዎቹ አሁን የሉም፡፡ ከዓመታት በኋላ እኔ የጻፍኩላትን ደብዳቤዎች ሰብስባ ሰጠችኝና ተለያየን፡፡ በዚሁ ጊዜ አብዮቱ ፈንድቷል፡፡ ደብዳቤዎቹ ለእኔ ጥሩ ትዝታ ቢኖራቸውም፣ እየቆየ ውስጤ የሚተራመሰውን ስቃይ መቻል አቃተኝ፡፡ ስለዚህ ለዜና እናት እንኪ እሳት ለኩሺበት ብዬ ሰጠኋት፡፡…›› ገጽ 142  
የጋሽ ስብሃት የዘመናት የቅርብ ወዳጅ ጋሽ ሥዩም ተፈራ፣ በቅርቡ በብሔራዊ ቤተ ተውኔት አጸድ ድንገት አግኝቻቸው የነገሩኝ ትዝብትም ይሄንኑ የሚያጎላ ሆኖብኛል። ‹‹ለእኔ ስብሃት አራት ዓይነት ሰው ነው፡፡ ስብሃት ሀና ይልማን ከማግኘቱ በፊት፣ ከሀና ይልማ ጋር፣ ሀናን ያጣ ሰሞንና፣ ስብሃት ሀናን ካጣ በኋላ…››     
በእርግጥም የርባገረዱ ልጅ እግሩ ስብሃት፣ እንደ ካህሊል ለዓለምና ለሕይወት አይናፋር ነበር፡፡ ግን ተስፋዬ ገሠሠን፣ ሰለሞን ደሬሳን፣ ሀና ይልማን፣ በዓሉ ግርማን የመሳሰሉ ወዳጆቹ ተራ በተራ እጁን ይዘው እየሳቡ ወደ ሕይወት ይሉት የሚያዳፋ አዙሪት አንደረደሩት፡፡ በአንድ ወቅት ድንጉጥ፣ እንግዳ፣ መድረሻ ቢስ ይመስል የነበረው ሰው፣ ቀስ በቀስ ሌሎችን ለማስጠለል እስኪበቃ ድረስ እንደ ዋርካ የሰፋ መሰለ፡፡
ሆኖም በእነዚህ ሁሉ አርባ ዘመናት ሀና ይልማን እንደ ድንገት ያጣው ስብሀት፤ ዘመኑን ሙሉ መጫወቻውን እንደተነጠቀ ህጻን ተጃጅሎ ወደ ውስጡ ሲነፈርቅ ነበር፡፡ የዶ/ር ዮናስ አድማሱና የደራሲና ተርጓሚ ሣህለ ሥላሴ ብርሃነ ማርያም የፍቅር ሕይወት ከስብሐት ጋር የሆነ የርቀት መመሳሰል እንዳለው ሳስብ ግር ይለኛል፡፡ ስብሃት መሻገር ችሎ በዚህች ሴት ምክንያት የደረሰበትን ባዶነትና ቁዘማ ቢከትበው ኖሮ፣ እንዴት የሚያስጎመጅ መጽሐፍ በወጣው ነበር፡፡ ያስቆጫል!


Read 1426 times