Sunday, 11 July 2021 18:33

ፍቅር አለማማጁ!

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(0 votes)

 አድማስ ትውስታ

          ፍቅር አለማማጁ!
                          

           እኔና ቤቲን ያገናኘን እንጀራ ነው፡፡ እህል ውሃ። Destiny ወይም እጣፈንታ ልትሉት ትችላላችሁ፡፡ እኔ የድርጅቱ የሂሳብ ሹም ሆኜ በተቀጠርኩ በመንፈቄ፣ ቤቲ ፀሐፊዬ ሆና ተቀጠረች፡፡ የሚያስደነግጥ  መልክና ቁመና የላትም፡፡ ግን ከዚያ የማይተናነስ ቀልድና ጨዋታ አዋቂ ናት፡፡ ወንዶችንም ሴቶችንም እኩል መማረክ የሚችል አንደበት ተችሯታል፡፡
እኔንም የማረከችኝ በዚሁ አንደበቷ ነበር። ቤቲ ሲበዛ ቀልደኛ ናት፡፡ የዕድል ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ ቦታዋ የእኔ ቢሮ ሳይሆን የኮሜዲ መድረክ ነበር። እሷ ከመጣች በኋላ መ/ቤታችን የሳቅ አዝመራ ሆኗል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አስደንጋጭ ቀልዶች ትናገራለች፤ አጥንት ከሥጋ የሚለያዩ፡፡ በቀልዶቿ ደንግጠው የሸሹ ግን አላየሁም፡፡ ከልጅነት ባልንጀራዬ ከቢኒ በቀር፡፡
እኔና ቢኒ እንደወንድማማቾች ነው ያደግነው። አንድ ሰፈር ብይ ተጫውተን፣ አንድ ት/ቤት ተምረናል፡፡ ዩኒቨርስቲ ስንገባ ተለያየን፡፡ እሱ ኢንጂነሪንግ ሲያጠና፣ እኔ አካውንቲንግ አጠናሁ። እሱ ባህርዳር ሥራ አግኝቶ ሲሄድ፣ እኔ አዲስ አበባ ቀረሁ፡፡ እሱ ከሥራ ባልደረባው ጋር ፍቅር ሲጀማምር፣ እኔ የፍቅር ጓደኛዬን አለምኩ፡፡ በሁለተኛ ወሬም፣  ቤቲን ጣለልኝ፡፡
ቢኒ በዓመቱ ነው ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስከፍለውን የባህርዳር ሥራውን ጥሎ ሸገር የመጣው፡፡ ምን ሥራውን ብቻ! ፍቅረኛ ያላትንም ጭምር እንጂ፡፡ የድሮ ሸጋ ባህርዩንም ባህርዳር ጥሎት የመጣ ይመስለኛል፡፡ ተግባቢና ተጫዋች የነበረው ቢኒ፤ በዓመት ጊዜ ውስጥ እልም ያለ ተጠራጣሪ ሆኖ ነው የመጣው፡፡ ብዙ የእሱ ያልነበሩ እንግዳ ጠባዮችም አምጥቷል፡፡ መቆጣት መነጫነጭ፣ ማማረር እና ሌሎች…
የሆኖ ሆኖ ግን አዲስ አበባ መምጣቱን ከሰማሁ ጊዜ ጀምሮ ፍቅረኛዬን ላስተዋውቀው ብዙ ለፋሁ። ለእኔ የበኩር ፍቅረኛዬን ለልጅነት ባልንጀራዬ ማስተዋወቅ ትልቅ ትርጉም ነበረው፡፡ ሸጋ የህይወት ጓደኛ መምረጤን እየነገረኝ፣ ቢያደንቅልኝ ደስታዬ ነበር፡፡ ድሮ የማውቀው ቢኒ ደግሞ የአድናቆት ስስት የለበትም፡፡ አሁን እሱ ራሱ መች ጭራው ተይዞ! ከስንት ጊዜ በኋላ እንደምንም እሺ አሰኘሁት፡፡
የተቀጣጠርንበት ሆቴል ቀድመን የደረስነው እኔና ቤቲ ነበርን፡፡ ከ20 ደቂቃ በኋላ ቢኒ መጣ። ከወደፊቷ የትዳር አጋሬ ጋር አስተዋወቅሁት፡፡ እሱቴ! አልሞቀውም አልበረደውም፡፡ ቤቲ ከፍቅር ጋር የተገናኙ ቀልዶችን በተከታታይ አዘነበችልን። ብዙዎቹን እኔ ራሴ ሰምቻቸው አላውቅም፡፡ ይሄን ሁሉ ያደረገችው የልጅነት ባልንጀራዬ ዘና እንዲልና የመግባባት ስሜት ለመፍጠር ነበር፡፡ ግን አልተሳካላትም፡፡ በቀልዶቿ የምንስቀው እኔና እሷ ብቻ ነበርን፡፡ ቢኒ ተሳስቶ እንኳን ጥርሱን ብልጭ አላደረገም። እሷ ግን ተስፋ ሳትቆርጥ በኩመካዋ ገፋችበት፡፡
“ምነው…የተደበርክ  ትመስላለህ? እኔ እኮ መቼ ተዋውቄው ስል ነው የከረምኩት”
አለችው፤ ዓይን ዓይኑን እያየችው፡፡ ደንገጥ አለና ተመለከታት፤ ኮስተር ብሎ፡፡
“የምሬን ነው… ትላንት ሳሚ እንደቀጠረህ ሲነግረኝ ጉጉቴ ጨመረ፤ የቀጠሮ ሰዓቱ አልደርስ አለኝ” ስትል አከለችለት፡፡ ይኼኔ የተለጎመው አፉ ተፈታ፡፡
“ምነው በደህና?” ጠየቃት፤ በጥርጣሬና በጉጉት ስሜት ተሞልቶ፡፡
“ምን መሰለህ… ሳሚ፤ ፎቶህን ሲያሳየኝ በአካልም እንዲህ ከሆነ ወደ እሱ እቀየሳለሁ ብዬው ነበር…” አለች ቤቲ - በዓይኗ እየጠቀሰችኝ፡፡ እንዲህ አይነት ኩምክና ለእኔ የተለመደ ስለሆነ ምንም አልመሰለኝም፡፡ ቢኒ ግን እንደአራስ ነብር ቱግ አለ፡፡ የባሰ አታምጣ ማለት ይሄኔ ነው፡፡
“የሴት ቀልደኛ ደሜን ነው የምታፈላው!” እያለ ከተቀመጠበት ተነሳ “ሳሚ፣ ህይወቴን ያበላሸችብኝ እንደዚህች ያለችው ፎጋሪ ነኝ ባይ ናት…እቺም ጉድ እንዳታደርግህ!” አለና ከሆቴሉ የማምለጥ ያህል ተጣድፎ ወጣ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን እምብዛም ድንጋጤ የማይጐበኛት ቤቲ፤ ለአፍታ በዝምታ ተውጣ ቀረች፡፡ ለማጫወት ያደረገችው ሙከራ እንዲህ በጠብ ይጠናቀቃል ብላ አላሰበችም ነበር፡፡
“ሳሚዬ ፈተናውን ወድቋል… አንተው ትሻለኛለህ!” ስትል እየቀለደች፣ ከንፈሬ ላይ ከንፈሯን አሳረፈች፡፡
*   *   *
ከወር በኋላ ቢኒ ጋ ደውዬለት እንድንገናኝ ጠየቅሁት፡፡
“የሴት ቀልደኞች እጣ ክፍሌ አይደሉም … ካለች ግን ከበር ነው የምመለሰው!” ሲል አስጠነቀቀኝ፡፡
ባህርዳር በመሃንዲስነት በተቀጠረበት የግል ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ለጥቂት ወራት እንደሰራ ነበር አንዲት ልጅ እግር መሃንዲስ ከሌላ ቅርንጫፍ ተዛውራ፣ ወደ እነቢኒ ክፍል የመጣችው። ማህሌት ትባላለች፡፡ አለቃው እንደቀልድ “አለማምዳት” ብለው ለእሱ አስረከቡት፡፡ እሱ ግን የምር አደረገው፡፡
የኪስ ቦርሳውን አውጥቶ ሁለት ፎቶዎቿን አሳየኝ፡፡ ውበቷ እንደሰማይ ክዋክብት ይንቦገቦጋል። በዚያ ላይ ሽቅርቅር ናት! ቢኒ እሷን ማለማመድ ዋናው ስራው አድርጐት ቁጭ አለ፡፡ ጠዋት ከቤት ወደ ቢሮ ይዟት ይመጣል-በኮንትራት ታክሲ፡፡ በሻይ ሰዓት አብሯት ነው፡፡
ማታ በውድ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እየጋበዘ ህልሟን፣ ተስፋዋንና ቅዠቷን ሰምቶ ወደ ቤቷ ይሸኟታል፡፡ የማታ ማታም አለማምዳለሁ ብሎ ተለማመዳት። በልቡ ፍቅር አረገዘ፡፡ እሷ ደግሞ ቀልዷና ቁምነገሯ አይለይም፡፡ እንደልጅነት ዘመኑ “ባሌ” እያለች ልታሳፍረው ትሞክራለች። ፍቅረኛ ይኑራት አይኑራት የሚያውቅበት ፍንጭ አልነበረውም፡፡ “አለማምዳት” ያለው አለቃው “ራት ልጋብዝሽ” ሲላት “ቢኒ ቦይፍሬንዴ ነው” ብላ እንዳስደነገጠችው ነግራዋለች፡፡ አንድ ቀን ያረገዘውን እንደምንም አምጦ ተገላገለው። ለማህሌት እውነቱን ነገራት፡፡ የሚገርመው ግን ነገርየው ዱብዕዳ አልሆነባትም፡፡ ቢኒ…“ጊዜ ስጠኝ፤ ላስብበት” ለቢኒ ይሄም ቢሆን አስፈንጥዞታል፡፡ ምላሿ አዎንታዊ ይሆን ዘንድም ነፍስ ካወቀ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ስለት ተሳለ፡፡
ወራት እንደዘበት ነጎዱ፡፡ በእርግጥ የተለመደው ግንኙነታቸው አልተቋረጠም። ግን ምላሽ የለም። ቢኒያም ፍቅሩን ልታረሳሳው የፈለገች ሁሉ መሰለው፡፡ ከራሱ ጋር ብዙ ከተማከረ በኋላ ፍቅሩን አስታወሳት፡፡ “ቢኒዬ… አልወሰንኩም እኮ!” አለችው፤ በሚንቆረቆር ድምጿ፡፡
“እስካሁን?” አላት፤ ተገርሞ፡፡
“ያጣደፉት ፍቅር…” የሚለውን ዘፈን በሚወድላት ድምጿ አቀነቀነችለት (አትቸኩል ለማለት!) ቢኒ ራሱን ታዘበ “እውነቷን እኮ ነው … ምን አጣደፈኝ?” አለ፡፡ ግን ምን ያህል ጊዜ እንደሚስፈልጋት ቢያውቅ አይጠላም ነበር፡፡
የዛን እለት እንደወትሮው ወደ ቤቷ ከሸኛት በኋላ ወደ ቤቱ አልሄደም፡፡ ቢመሽም ቤተክርስቲያን ሄዶ ፈጣሪውን ተለማመነ፡፡
ጠዋት ከእንቅልፉ የቀሰቀሰው የሞባይሉ ቴክስት ሜሴጅ (SMS) ነበር፡፡ እየተጨናበሰ ሞባይሉን ከኮመዲኖው ላይ አንስቶ መልሶ አስቀመጠው። ትንሽ ቆይቶ ግን ከአልጋው ላይ ተስፈንጥሮ ተነሳና ሞባይሉን አፈፍ አደረገ፡፡ የሜሴጅ ሳጥኑን የሚከፍተውን ቁልፍ ተጫነ፡፡ ዓይኑን አላመነም። ጽሑፉን ትክ ብሎ ተመለከተው፡፡ ያው ነው። “ቢኒዬ… የህይወት ዘመን ሽልማት ትፈልጋለህ? አሸንፈሃል! እኔን!!” ይላል - የማህሌት መልእክት። ስሜቱ ድብልቅልቅ አለበት፡፡ ደስታ… ድንጋጤ.. ጭንቀት… ብዙ ስሜቶች አፈኑት፡፡ ሁሉንም አስተናግዶ ሲጨርስ ወደ አቅሉ ተመለሰ፡፡ ስልክ ሊደውልላት ወይም መልእክት ሊልክላት አሰበ። ከዚያ በፊት ግን አንድ ነገር ትዝ አለው - ስለቱ! ከመቅፅበት ከአልጋው ወርዶ ልብሱን መለባበስ ጀመረ “ስለቴ ሰመረልኝ”ን በልቡ እያዜመ፡፡ በቀጥታ ያመራው ወደ ቤተክርስቲያን ነበር፡፡ ስለቱን የቤተክርስቲያኑ ሳጥን ውስጥ ለማስገባት ሲታገል፣ ሌላ ቴክስት ሜሴጅ አንቃጨለ። ስለቱን ታግሎ አስገባና ሞባይሉን ከኪሱ አወጣ፡፡ “ቢኒ…April the fool!” ይላል- የማህሌት ሁለተኛው መልእክት። “ዋት?!” ሲል አምባረቀና ሳያስበው የበረንዳው ደረጃ ላይ ዝርፍጥ አለ፡፡ ዘላለም ለሚመስሉ ሰዓቶች አልተነሳም፡፡ በነጋታው ራሱን ያገኘው አዲስ አበባ ወላጆቹ ቤት ነው፡፡
“ቀልድና ቁምነገር የምትቀላቅል ሴት አትመን!” አለኝ ቢኒ፤ ስንለያይ፡፡


Read 1251 times