Saturday, 17 July 2021 14:23

አባይን ያላየ ….ሄዶ ማየት ይችላል

Written by  ሳህሉ
Rate this item
(1 Vote)

  አድማስ ትውስታ

              ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች 1ኛ  እየወጣች በአጠቃላይ ድምር መጨረሻ የሆነችበት ምክንያት አንድ አጎቴ ስለ ጣሊያን ወረራ ሲያወሩ ፈረንጅ ኢትዮጵያን ለመያዝ ዘወትር የሚመኝበትና የማይተኛበት ምክንያት፣ “ይህን እንደዋዛ የምናየውን ዋርካ ሁሉ እነሱ በሀገራቸው ፉርኖ ስለሚያደርጉት ወይም ወደ ፉርኖነት ስለሚለውጡት ነው” ሲሉ እሰማ ነበር። ዋርካ ጥሩ ነገር ቢሆንም ከዋርካ ፉርኖ እንደማይሰራ የገባኝ ቆይቶ ነው - በልጅነት የተሰማ ነገር በቀላሉ ከአይምሮ አይወጣምና። ይሁንም ግን ታዲያ ያኔ የቀየዬን ዋርካዎች ብዛትና ትልቅነት ሳይ የዚያን ሁሉ ዋርካ ለፋርኖነት መዋል ሚስጥር የተረዱ ፈረንጆች አገራችንን ለመያዝ የሚመኙበትን ምክንያት ግልጽ አድርጎልኝ ነበር።
በልጅነት ወራት ይህን ማመንና መቀበል፤ ችግር አይሆን ይሆናል። የሚያስቸግረው አድጎ፣ ተምሮ፣ ትልቅ ሰው ከሆኑም በኋላ ያ የልጅነት እምነት  ሳይለወጥ ሲቀር ነው። አጎቴ ያሉትን ቢሉና ቢያምኑም ችግር አይሆን ይሆናል። አልተማሩም፣ ከገጠር አልወጡም። የሚያስቸግረው ተምሮና ሰልጥኖ እንደ አጎቴ ማሰቡ ሲቀጥል ነው።
ፕሮፌሰር መስፍን አንድ ጊዜ ሲጽፉ እኛ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የመረጃ ጥላቻ አለን ብለው ነበር። ከፓርላማው አንስተው እስከ ሊስትሮና እረኛው ድረስ ያለ መረጃ ለመናገር የሚገደን አይደለም። ለትልቅ አገራዊ ጉዳይ ሆነም ወዲያ ማዶ መንደር በተከሰተ ነገር መረጃ ፍለጋ የሚታክት የለም። እኛም እንዲያው በደፈናው ብቻ  “ህዝቡ ይህን ይወዳል ያን ይጠላል” እየተባለ፣ ሀገራችን በሆነው ነገር አንደኛ በሆነው ነገር ሁለተኛ እየወጣች ፣ጠላት እንደተመኛት፣በተፈጥሮ ሀብት እንደ በለፀገች፣ ህዝቦቿ ከዓለም ተለዠይተው ኩሩ እንደሆኑ፣እግዜር እንደወደዳትና እንደባረካት ይኸው አላንዳች ጥቅም አለን። ለምን ቢሉ በእኛ ሀገር የሰፈራችንን ምንጭ ለማድነቅና ለመኩራራት አባይ ይኑር አይኑር ማወቅ ስለማያስፈልገን ነው።
እርግጥ ነው የሀገራችን ህብረተሰብ አፋዊ ህብረተሰብ ነው። ህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን ፅሁፉም ሳይቀር አፋዊ ነው። በአፈ ታሪክ አድገን ኖረናል። ታዲያ ግን ይህ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር “ወርቃማው አፈ ታሪካችን” የሚሉት ነገር ላዩን የዋህ ይምሰል እንጂ  ቀላል ነገር አይደለም። ህዝብ ያለ አፈ ታሪክ ኖሮ አያውቅም። ስላለፈ እሱነቱ ደግ የሚቃኘውና ለነገው አዳሩ ደግ የሚመኘው በአፈ ታሪኩ ነው።
 ይህ ክፋት ባልኖረው ነበር። ክፋቱ ግን  ዛሬም ገሀዱን በገሀድ አይን ማየት አልችልም ብለን በቅኔ ጉልበት መኖራችንን ስንቀጥል ነው። ቅኔ ሲባል የቤተ ክርስያኑ ቅኔ ለማለት አይደለም። በምሳሌ ለማብራራት ያህል፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከላሊበላ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቆ ውጪ ሀገር ተሸጦ ቆይቶ ኋላ ተገኝቶ ወደ ሀገሩ የተመለሰው “አፍሮ አይገባም” የሚባለው ትልቁ የላሊበላ የወርቅ መስቀል በገና በዓል ወቅት ለህዝብ ወጥቶ ሲታይ ካህናቱ ምዕመኑን “እልል በሉ፣ ዓለምን ባርኮ  የተመለሰው የቅዱስ ላሊበላ መስቀል ይህ ነው” ይሉ ነበር። እንግዲህ ይህ የመስቀሉን ተሰርቆ ውጪ ሀገር ተሸጦ መመለስ እንደ ክፉ አጋጣሚ ሳይሆን እግዜር ሆን ብሎ በመስቀሉ ታምራት ሊሰራና ዓለምን ሊባርክ እንዳደረገው አድርገው ከመተርጎማቸው የመጣ ነው። የቅኔ ጉልበት ማለት ይህ ነው። ክፉን አጋጣሚን ወደ ላቀ መለኮታዊ ተልዕኮ የመለወጥ ሀይል አለው። ለጉዳታችን ውበት ሰጥቶ ያፅናናል።
እና እኛም ይህ ክህሎት የተፈጥሮአችን አካል ሆኗል። የመስቀሉ ታምር የእምነት ጉዳይ በመሆኑ በእምነት የምንቀበለው እንጂ፣ እንዴት? ውስጥ የሚያገባባን አይደለም። ነገር ግን ከእምነቱ ማዶ የእለት ተእለት አለማዊ ኑሮአችንና አስተሳሰባችን በዚህ ዓይን የተቃኘ ይመስላል።  እናም ኢትዮጵያን በቅኔ አይናችን ስናያት ለምለም ናት፣ በተፈጥሮ የበለፀገች በማዕድ የከበረች፣ ለጠላት የምታጓጓ ሀገር ናት። ችግሩ የሚመጣው ለእነዚህ ሁሉ ተጨባጭ መረጃ አምጡ የተባለ ጊዜ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ በዘፈን ውስጥ ካልሆነ በቀር ለምለም አይደለችም። እርግጥ ነው ሀገሬ ደረቅ ናት ተብሎ አይዘፈንም። ሰሀራ በረሀ ውስጥ ያሉ ሀገሮችም ቢሆኑ ስለ ሀገራቸው ውበት ይዘፍናሉ- ለምለም ናት ሀገሬ ብለው ባይሆንም በሌላ። ዳሩ ግን እውነቱን  ማወቅ እስከዚህ የሚጎዳ ነገር የለውም። እናም በስፋት ኤርትራን የምታህለው እንግሊዝ ኢትዮጵያን በደን ብዛት ትበልጣታለች። የማዕድኑም ነገርም ቢሆን እንደዚያው ነው።  የመሬት ውስጥ ነገር ባይታወቅም እስከ ዛሬ ባለው በእርግጠኝነት የሚታወቅ ያለን የተፈጥሮ ሀብት መሬት ብቻ ነው።
የአገር መውደድ ምልክት ይሁን ወይ እንደተባለው የመረጃ ጥላቻ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አንደኛ ወይም ሁለተኛ የማናስወጣበት ነገር እየጠፋ መጥቷል። ሌላው ቀርቶ ተለቅ ያለ ቤተ ክርስቲያን ሲሰራ ቤተ-ክርስቲያኑ ተስርቶ ሳያልቅ ወዲያው የሚወራው ወሬ ከአፍሪካ አንደኛ ወይም ሁለተኛ መሆኑ ነው። ለዚህ ደግሞ ምንም አይነት መረጃ መጥቀስም ሆነ ማንበብ አያስፈልገንም። የመቀሌው መስፍን ኢንጂነሪንግ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ነው ተብሎ ተፅፏል። ነገር ግን በቅርቡ የድርጅቱ ሰራተኞች ወደ ሱዳን ለስራ ሄደው የሱዳንን መኪና መገጣጠሚያ በጎበኙበት ወቅት እዚያ ሊበትኑት አዘጋጅተውት ከነበረው የድርጅታቸው ማስታወቂያ ብሮሸር ውስጥ “መስፍን ኢንጂነሪንግ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ ነው” የሚለውን አረፍተ ነገር እየደለዙ በማጥፋት ለመበተን ተገድው ነበር። ለምን ቢባል ድሮውንም ያለምንም መረጃ በሳይሆን አይቀርም ያሉት ነገር ስለነበር ነው።
እንዲህ እንዲህ እያለ በአፍሪካ በሩጫ አንደኛ ነን፣ በመርካቶ ትልቅነት አንደኛ ነን፣በሸራተን አንደኛ ነን፣ በአየር መንገድ፣በጦር ሀይል፣በአየር ሀይል፣ በከብት ብዛት፣ በቡና ምርት፣ በተማረ የሰው ሀይል፣ በኩሩነት፣በጀግንነት በወንዝ፣በተራራ፣በዳሎል፣ በንፁህ አየር፣ በብሔር ብሔረሰብ፣በእንግዳ ተቀባይነት፣ በጥንታዊ ታሪክ ባለቤትነት፣ ክርስትናን በመቀበል…. ወዘተ አንደኛ ነን። እነዚህን ብዙዎቻችን በእየለቱ የምንላቸውና አምነን የምንቀበላቸው ናቸው። ነገር ግን ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሁለቱ ብቻ ትክክል ቢሆኑ ነው። የተቀሩት ገሚሱ ውሸት፣ ጭራሽ ደረጃ ተሰርቶበት የማያውቅና ለውድድርም አመቺ ያልሆነ ነው። አሁን በቀደምለት በFM  ሬዲዮ የሸራተን ጋዝ ላይት በዓለም ሁለተኛ ነው። አንደኛው የኒውዮርኩ ነው ሲባል ተሰምቷል። ማን አወዳደረው? እንዴት ተወዳደረ? የተባለና የታወቀ ነገር የለም።
የሚገርመው ነገር ታዲያ በዚህ ሁሉ ነገር አንደኛና ሁለተኛ እየወጣን በአጠቃላይ ዕድገት መጨረሻ የመሆናችን ነገር ነው። የሚጋጭ ነገር ነውና። እውነቱ ግን አብዛኛውን ደረጃ እራሳችን ለራሳችን ስለምንሰጥና ስንሰጥም ደግሞ ስለሌላው አለም ምንም ካለማወቅና ለማወቅ ካለመፈለግ የተነሳ ስለሆነ ነው። አንድ እውቅ የታሪክ ምሁር “ኢትዮጵያ ለአንድ ሺ ዓመት እሷም አለምን ዘንግታ፣ አለምም እሷን ዘንግቶ የኖረች ሀገር ናት” ያለው ነገር እስከዛሬ ርዝራዡ ያለ ነው የሚመስለው። በዚህ መረጃ ሞልቶ በተረፈበት ዘመን አንኳ የተማረው ሰው ራሱ አንድ ነገር ከመናገሩ በፊት “እኛ የት ነን ሌላው የት ነው?” ብሎ የመጠየቅ ፍላጎት የለውም። ፖለቲከኛውም ቢሆን ከአስር ሰው አስተያየት ተነስቶ የሀገሪቱን ህዝብ ፍላጎት ለመተንተን አይጨንቀውም። ወይም ደግሞ የአዲስ አበባን ሰው የሽንት ቤት ችግር አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር አድርጎ ማቅረብ አይገደውም። ቁጥር ጠቅሶ፣ ቦታ ጠቅሶ የሚሟገት ከስንት አንድ ቢገኝ ነው። ቁጥሩም ደግሞ ተዘጋጅቶ አይገኝም።
ብቻ ዛሬም አፋዊ ህብረተሰብ ነንና ነገራችን ሁሉ በስማ በለው ነው። በፓርላማ ውስጥም ጥያቄ ሲጠየቅ እንደው በደፈናው “ህዝቡ እንዲህ ያወራል። በደንብ አስባችሁበታል ወይ?” ነው። ጋዜጠኛውም ሲጠይቅ “ምን ይሰማዎታል?” “ለኢትዮጵያ ምን መልዕክት አለዎት?” “ምን አስደናቂ ገጠመኝ አለዎት?” ነው። ታዲያ ይህ በመረጃ ያለመታገዝና በነሲብ የመሄድ ጉዳይ ስለ ሐገራችን ካለን ውስጣዊ ግምት ጋር ተያይዞ ሁሉን ነገር፣ ሁሉን ችግር በሴራ አይን እንድንመለከት ያደረገን ይመስላል፡፡ በፊት ኢትዮጵያ ድሀ አይደለችም እንላለን፣ ቀጥለን ኢትዮጵያ እንድታድግ ማንም አይፈልግም እንላለን። ከጥንት ጀምሮ ጠላት ሲመኛት የኖረ፤ አንዴ አረቦች፣ አንዴ አሜሪካኖች በአይነ ቁራኛ እንደሚያዩን ሴራውን እንዘረዝራለን። አሜሪካ፤ ኢትዮጵያ  በአፍሪካ ቀንድ ሀያል ሀገር እንድትሆን አትፈልግም። አረቦች የኢትዮጵያን ነዳጅ እንዳይወጣ አሻጥር ይሰራሉ።  ፈረንጆች ሁሌ ተረጂ እንድንሆን ይፈልጋሉ። ስለዚህ በእነዚህ ተፅዕኖ ሳቢያ ማደግ አልቻልንም። በእነዚህ ዙሪያ በየቦታው የሚተነተነው የሴራ አይነት ብዙና እረቂቅ ነው። አሜሪካና ፈረንጆች እንዲህ በዓለም የመጨረሻ ደሀ የሆነችን ሀገር አንቀው በመያዝ ምን የሚጠቀሙት እንዳለ ለማንም ሊቅ በቀላሉ ግልጽ የሚሆን አይመስልም። ቢያንስ ግን ለኛ  የድህነታችን ችግር በእኛ ምክንያት እንዳልሆነ ያፅናናል። ቁጭትም ይሰማናል። ኢትዮጵያ የብዙ ጠላት አይን ያረፈባት ሀገር መሆኗም ስለ ሀገራችን መልካም ስሜት ይፈጥርብናል። እንደግ፣እንስራ ብንልም ስለሚያሰናክሉብን  አርፈን ተረጋግተን ውስጣዊ ኩራታችንን ሳናጣ በቁጭትና ንዴት  ረክተን እንቀመጣለን። ይህም እንግዲህ የቅኔያችን  አካል፣ የቅኔያአችን ጉልበት ነው- መከራና ችግርን ወደ ውበት ለውጦ ማየት ማስቻል።
ሌላው ባህሪያችን ደግሞ “ብቸኛና የመጀመሪያው” የሚለውን ነገር መውደዳችን ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ ተለይታ የምትታወቅባቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በአድዋ ከአፍሪካ ብቸኛ ናት። በፊደልም እንዲሁ፡፡ ቡና የተገኘባት፣ አባይ የፈለቀባት፣ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ሀገር ናት፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉት ጥቂት ነገሮች በከፈቱት በር የተነሳ ግን ሀይለኛ “የብቸኛና የመጀመሪያ” አፍቃሪዎች ሆነናል። እናም በየጊዜው እውነቱ ከውሸቱና ከግምቱ ጋር እየተቀላቀለ ብቸኛና የመጀመሪያ የሆንበት ነገር እየበረከተ መጥቷል። የጥንታዊው ታሪክ ነገር ሲነሳ እንኳን የአፍሪካ የስልጣኔ  ማዕከል አድርገን ነው እራሳችንን የምናየው። መቼም ግብጽ አፍሪካ አይደለችም ካልተባለ በስተቀር ይሄ አስቸጋሪ ነገር ነው። ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ ልዩ ነገሮች ያሏት ሀገር ነች። ሁሉም አገር ደግሞ ይብዛም ይነስም የራሱ የሆነ ልዩ ነገር፣ ልዩ ታሪክ አለው። እኛ ልዩ ባህል አለን ብለን ስንኮራ ሌላው ልዩ ባህል የሌለውና የማይኮራበት እስኪመስለን ድረስ ነው። በራስ መኩራት ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን በራሳችን የምንኮራ  እኛ ብቻ እስኪመስለን አይደለም። ይህ የሚመጣው ስለ ሌላው ካለማወቅና ለማወቅ ካለመፈለግ  ብቻ ነው። ለምሳሌ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይወዳታል እንላለን። ባርኳታልም እንላለን። አባባላችን የሚሰጠን ስሜት  ከሌሎቹ ሁሉ  ለይቶ እንደሚወዳት ነው። ለዚህ ግን ምንም ምድራዊ መረጃ  ማቅረብ የምንችል አይመስለኝም። ምክንያቱም እነ ስዊድን፣ እነ ጃፓን እነ ካናዳ አሉ። እንዲህ የበለፀጉት እግዚአብሔር ባይወዳቸው አይመስለኝም።
በጥቅሉ ወደ ውስጣችን በትክክል ለማየት በፊትም ይሁን ኋላ ዙሪያችንን ማየቱ ይጠቅመናል፣ ያስፈልገናል። በተጨባጭ እውቀት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ያስፈልገናል።  ከአፍሪካ በብዙ ነገሮች አንደኛ ወጥተን ጦም ብናድር  ጥቅም የሌለበት  ጨዋታ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም አንደኝነታችንም የመጣው ስለነሱ ካለማወቅ በመሆኑ ነው።
 ዛሬ ዘመኑ ሌላ ነው። አባይን ያላየ የሰፈሩን ምንጭ ቢያደንቅ ይቅር የሚባልበት ምክንያት የለም…. ሄዶ ማየት ይችላልና። ሌላ ባይጠቅመው በስህተት ከመኩራራት ይተርፋል።       
 ምንጭ (አዲስ አድማስ፤  ግንቦት 2 ቀን 1995 ዓ.ም)


Read 3348 times