Saturday, 17 July 2021 14:27

ህወኃት ህፃናትን ለጦርነት መጠቀሙ አነጋጋሪ ሆኗል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  አና ጎሜዝ ድርጊቱ በጣም አስደንጋጭ ነው ብለዋል
                              
             ህወኃት እድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ለጦርነት መጠቀሙ እንዳሳሰባቸው የቀድሞው የአውሮፓ የፓርላማ አባልና የ97 ምርጫ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ የነበሩት አና ጎሜዝ ተናገሩ፡፡
ከ15 ዓመታት በላይ የአውሮፓ ፓርላማ አባል እንደነበሩ የሚታወቁት አና ጎሜዝ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ በሰሜኑ ጦርነት ህፃናት መሳሪያ ታጥቀው መመልከታቸው እንዳስደነገጣቸው ጠቁመዋል፡፡
ህጻናትን ለጦርነት መጠቀም አሳዛኝ ድርጊት ከመሆኑም በላይ አለማቀፍ ወንጀል መሆኑን ያሰመሩበት አና ጎሜዝ፤ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ነገር አሳሳቢ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል፡፡
ከህፃናት ወታደሮች የፎቶ ምስል ጋር ባስተላለፉት መልዕክታቸውም፣ ጦርነቱ ረሃብን ጨምሮ በርካታ ሰብአዊ ቀውሶችን ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ አለማቀፍ  ተቋማት ጦርነቱ በሚቆምበት ሁኔታ ላይ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም ዲሞክራሲና እውነተኛ ልማት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል - አና ጎሜዝ፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ራሱን የትግራይ መከላከያ ሃይሎች ብሎ የሚጠራው ቡድን፣ “ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ; እንደሚገኝ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡


Read 14878 times