Print this page
Saturday, 17 July 2021 14:27

ኢትዮጵያን ጨምሮ 6 ሃገራት የከፋ የሰብአዊ ጥቃትና የዘር ማጥፋት እየተፈጸሙባቸው ነው - የአሜሪካ መንግስት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የአለም ሃገራት የከፋ የሰብአዊ ጥቃትና የዘር ማጥፋት እየተፈጸሙባቸው መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዓመታዊ ዘር ማጥፋትና ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት ሪፖርታቸው፤ ኢትዮጵያ  ቻይና፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ ደቡብ ሱዳንና ማይናመር የዘር ማጥፋትን ጨምሮ ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸሙባቸው ያሉ ሃገራት ናቸው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል መንግስታቸው የዘር ማጥፋት እንዲሁም የጭካኔ  ድርጊቶች ተፈጽመዋል ብሎ እንደሚያምን ያስታወቁት የውጭ ጉዳይ ሃላፊው፤ ለዚህም መንግስታቸው  የእርዳታ ገደብን ጨምሮ የቪዛ ክልከላ እርምጃዎችን በህወኃት አመራሮችና በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ማሳለፉን አስታውሰዋል፡፡
በቻይና ሁለት ግዛቶች ሃይማኖትን መነሻ ባደረገ ጥቃት የዘር ማጥፋት ድርጊት መፈጸሙን እንዲሁም  በበርማ ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙንና መንግስታቸው የተለያዩ የማዕቀብ እርምጃዎችን መውሰዱን አውስተዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ሚዛኑን የሳተ መሆኑን በመቃወም የአንድ ወገን ጫናዎች እንዲቆም የሚጠይቅ የትዊተር ዘመቻ በመላው አለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡
ይህ መሰሉ የትዊተር ዘመቻ አሜሪካና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለማቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያን በተመለከተ የያዙት አቋም እስኪቀየር ድረስ እንደሚቀጥል የዘመቻው አስተባባሪዎች ጠቁመዋል፡፡

Read 14610 times