Saturday, 17 July 2021 14:32

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈተነበት የተናጠል ተኩስ አቁም

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

   የፌደራሉ መንግስት በአሸባሪነት በፈረጀው የህውኃት ታጣቂ ቡድን ላይ ሲወስድ የቆየውን ህግ የማስከበር እርምጃ በማቆም ሠራዊቱ የትግራይ ክልልን ለቆ እንዲወጣ ከወሰነበት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በህወኃት ታጣቂ ቡድን እየተገደሉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁን ያወጀበትንና ሰራዊቱን ከክልሉ እንዲወጣ ያደረገበትን ምክንያት ሲገልፅም፤ ወቅቱ የእርሻ  በመሆኑ አርሶአደሩ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የእርሻ ሥራውን እንዲሰራና ህዝቡም የፅሞና ጊዜ እንዲያገኝ ታቅዶ የተወሰነ እንደሆነ ቢያስታውቅም፤ አለም አቀፉ ማህረሰብ፣  በህውኃት ታጣቂ ሃይሎች የሚወሰደውን የሃይል እርምጃ አላወገዘም።
በመንግስት የተወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅና ሰራዊቱን ከክልሉ የማስወጣት እርምጃ ግን እንደታሰበው ለህዝቡ የተረጋጋ የእርሻና የፅሞና ጊዜ ሊሆንለት አልቻለም። አለምአቀፉ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ ከሚያሳድረው ያልተገባ ወከባና ጫናም የሚያስታግስ አልሆነም። ይልቁንም ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ ሲወተውቱ የከረሙት አሜሪካና አውሮፓ ህብረት “ኢትዮጵያ ያወጀችው የተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው፤ ህዝቡን ከብባ እያስራበች ነው፤ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው” ሲሉ ሌላ ውንጀላ  ፈጠሩ።
የአውሮፓ ህብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነሩ ጃኔዝ ሌናርቺክ ይህንኑ መግለጫቸውን በህብረቱ “ኢዩ ኦብዘርቨር” መፅሔት ላይ “ኢትዮጵያ ክሬቲንግ ፋሚን ኢን ትግራይ” (የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ሰው ሰራሽ ረሃብን እየፈጠረ ነው) በሚል ርዕስ እንዲታተም አደረገ።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሰሞኑን በዚሁ ጉዳይ  ላይ በሰጡት መግለጫም፤ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስና ህዝብም የምርት ሰዓት ሳያልፍበት ወደ እርሻ ሥራው እንዲገባ እንዲያደርግ በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሲጠየቅ ቢቆይም የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃው በመንግስት ሲወሰድ ግን ማንም በአዎንታዊነት ሊቀበለው አልፈለገም ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል።
መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ በአለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በአዎንታዊ  አለመታየቱ ብቻም ሳይሆን እርምጃው በሰጠው ዕድል ተጠቅሞ አሸባሪው የህወኃት ኃይል የትግራይ ክልልን የሞት ቀጠና አድርጓት ሰንብቷል። መከላከያ ክልሉን ለቆ ከወጣበት ከሰኔ 21  ጀምሮ “ለመንግስት ድጋፍ ሲያደርጉ ነበሩ” የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። በእስር ቤቶች ታጉረዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ “በህግ ማስከበር ሰበብ ንፁሃንን እየገደለ ነው የሚል ውንጀላ በየጊዜው ሲያቀርቡ የነበሩት ምዕራባውያን አገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ግን በህወሃት ቡድን ስለሚገደሉ ንፁሃን ዜጎች ትንፍሽ ያሉት ነገር አለመኖሩ ትዝብት ላይ እንደጣላቸው ብዙዎች ይናገራሉ። ታጣቂ ሃይሉ የሚወስደውን ኢ-ሰብአዊ እርምጃ ከማውገዝና ታጣቂው ሃይል ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ከማሳሰብ ይልቅ በክልሉ የኢንተርኔት የስልክ፣ የመብራትና መሰል አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ እንዲደረግ፣ ወደ ክልሉ የተቋረጠው የአውሮፕላን በረራና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር ተደጋጋሚ ጥያቄ ሊያቀርቡና በመንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ሲሞክሩ ታይተዋል። ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማድረስ አለመቻሉን በመግለፅ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር የታተሩት ምዕራባውያኑ፣ መንግስት “በሩን ለእርዳታ ሰጪዎች ክፍት አድርጌአለሁ- ተገቢውንም ድጋፍ አደርጋለሁ። የሚል ምላሽ ቢሰጥም ሰብአዊ እርዳታዎችን እንሰጣለን፤ እርዳታውንም እናስተባብራለን ያሉ  ወገኖች ደብዛቸው ጠፍቷል። ሰሞኑን ደግሞ እነዚሁ ወገኖች የኢትዮጵያ  መንግስት ወደ ክልሉ ይዘን የምንገባውንና የምናወጣውን ነገር ሊፈትሽና ሊመለከት አይገባም” የሚል ቅድመ ሁኔታ ይዘው ብቅ ብለዋል። ሆኖም ቅድመ ሁኔታው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ውድቅ ተደርጓል።
ይህንን ሁኔታም አስመልክቶ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምበሳደር ሬድዋን ሁሴን ሲናገሩ፤ “የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ወገኖች መንግስት የወሰደውን አዎንታዊ ውሳኔ ተቀብለው ድጋፍ ማድረግ ሲገባቸው፣ ውሳኔውን  ከማድነቅ የጎደለውን ከመሙላትና ከማሳሰብ ይልቅ አፍራሽና አሉታዊ ምክንያት በመደርደር የውሳኔውን አነስተኛነት ለማሳየት መንቀሳቀሳቸው አሳዛኝ ነገር ነው ብለዋል።
ከሰሞኑ ደግሞ የህወኃት ታጣቂ ቡድን ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናት በአደንዛዥ እፅ በማስከር ወደ ውጊያ ማሰማራቱ በአደባባይ እየታየ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ አላወገዘም፡፡ የህወኃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ባለፈ አለም አቀፍ ስምምነቶችን በመጣስ ህፃናቱን  ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑ በታዋቂ  ዓለማቀፍ ሚዲዎች ላይ ሳይቀር በምስል ተደግፎ  ቢዘገብም፣ አይተው እንዳላዩ መሆንን መርጠዋል። በኢትዮጵያ  መንግስት ላይ ተደጋጋሚ ጫና ሲያሳዳድሩ የቆዩት አሜሪካና አውሮፓ ህብረት መንግስት በወሰደው የተኩስ አቁም  ውሳኔ በተደጋጋሚ ተፈትነው ወድቀዋል። ኒውዮርክ ታይምስ “የትግራይ ሀይሎች የፌደራሉን መንግስት ጦር ከትግራይ ያስወጡበት መንገድ” በሚል በሰራው ሰፊ ዘገባ የህፃናት ተዋጊዎች ምስል ይዞ ወጥቷል፡፡
ኤኬ-47 መሳሪያ በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ወደ ጦር ግንባር ሲገሰግሱ የሚያሳይ ምስል ያወጣው ዝነኛው ኒውዮርክ ታይምስ፤ የህወኃት ቡድን  ህጻናትን በጦርነት ላይ ማሰማራቱን ከመተቸት ይልቅ  ማድነቅና ማጀገን መምረጡ  ከሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠና ሚዛናዊነቱን የሳተ ነው ሲሉ የፖለቲካ ልሂቃን ነቅፈውታል። ከመንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ ወዲህ ያለውን ጠቃቀስን እንጂ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በጦርነቱ ወቅት ተከስቷል ያለውን የትግራይ ሰብአዊ ቀውስና የሰላማዊ ሰዎች ግድያን ሲያወግዝ፣ የማይካድራውን የጅምላ ጭፍጨፋ ሳያነሳ ማለፉ ብዙዎች የዓለምቀፍ ማህበረሰቡን ዓላማ እንዲጠራጠሩት አድርጓቸዋል፡፡
የውጭ ሚኒስትር ዴኤታው በሰሞኑ መግለጫቸው ይህንኑ ነው በአፅንኦት የገለፁት፡፡ በእርግጥም የመንግስት የተናጥል የተኩስ አቁም  ውሳኔ፤ ዓለማቀፉን ማህበረሰብ ክፉኛ ፈትኖታል።

Read 14751 times