Saturday, 17 July 2021 14:35

“ካብ ጎረቤት ትረኽቦ ፈታዊኻ ፀላኢንከ ትወልደልካ ኣዴኻ”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

              (ወዳጅህን ከጎረቤትህ ታገኛለህ ጠላትህን እናትህ ትወልድልሃለች!)

           በትግራይ ወርዒ በሚባል በረሃ ውስጥ ሁለት ወንድማማቾች ሽፍቶች ነበሩ፡፡ ክፉ ደግ አይተው አብረው ያደጉ ናቸው፡፡ ብዙ ባልንጀሮችና ተከታዮች አፍርተዋል፡፡ ታላቅም  ታናሽም በተከታዮቻቸው መካከል የየራሳቸው ቡድን መስርተዋል፡፡ የየቡድኑን የጎበዝ አለቃም ሾመዋል፡፡ በየጊዜው ከግብረ-አበር ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዘረፋ ያካሂዱ ነበር። አንድ ቀን እስከነ ተከታዮቻቸው ከደጋ ተምቤን ቆላ ወርደው፣ አሳቻ ቦታ መርጠው፣ እንደ ልማዳቸው አድፍጠው ሲጠባበቁ አያሌ ሸቀጥና የዐረብ ንብረት በግመል ጭኖ የመጣ የነጋዴ ቅፍለት (Caravan) ያጋጥማቸውና ሙልጭ አድርገው ይዘርፉታል፡፡
 ከዚያም የተዘረፈው ይከፋፈል ይባላል፡፡ ታላቅዬው እስከነ አሽከሮቹ “ይሄ ንብረት በሙሉ ለእኔ ቡድን ይሰጥና በሚቀጥለው የምንዘርፈው ደግሞ ለአንተ ቡድን ይሁን”  የሚል አዲስ የብልጠት ሀሳብ አመጣ፡፡ ትንሽዬውም በጣም ተናደደና “በምንም ዓይነት የእኩል መሆን አለበት” ብሎ አሻፈረኝ፣ ሞቼ - እገኛለሁ አለ፡፡
ታላቅ ታናሽን ካልገደለ እንደማያርፍ በማመን ዘወር ብሎ መሳሪያውን ያቀባብላል፡፡ ይህንን ሁኔታ ያስተዋለ የታናሽዬው የጎበዝ አለቃ የሆነ፣ ባዳ ሰው ለታናሽዬው በጩኸት እንዲጠነቀቅ ምልክት ይሰጠዋል፡፡
ተኩስ ሲጀመር ያ የጎበዝ አለቃ ቀድሞውንም ተዘጋጅቶ ነበርና ታላቅዬውን ቀንድቦ ይጥለዋል፡፡  የታላቅዬው ወገኖች ይሸነፋሉ፡፡
ታናሽዬውም፤ ያን የጎበዝ አለቃ ጠርቶ፡-
“ካብ ጎረቤት ትረኽቦ ፈታዊኻ
ፀላኢንከ ትወልደልካ ኣዴኻ”
(“ወዳጅህን ከጎረቤትህ ታገኛለህ
ጠላትህን እናትህ ትወልድልሃለች”)
አለና  “በል ንብረቱን በሙሉ ሳታዳላ አከፋፍል” ብሎ አዘዘው፡፡
*   *   *
ዕድሜያቸው፣ አስተዳደጋቸው፣ የተማሩበት የትምህርት ሥርዓት፣  የታገሉበት ርዕዮተ- ዓለም፣ የኖሩበት የትግል ታክቲክና ብልጠት፣ የሚመኙት የረዥም ጊዜ ስትራቴጂና ግብ እጅግ ተቀራራቢ የሆኑ ወንድማማቾች፣ ሥጋ- ዘመዶች፣ ወንድም  አከል ጓደኛሞች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና መንግስታት እጅግ የተለየና ተዓምራዊ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር አዋላጅ ቢመጣ አማላጅ፣ አዋዳጅ ቢመጣ አጣማጅ፣ አወቅሁሽ ናቅሁሽ መባባላቸው፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚል የዕኩይ- ፉክክር ማድረጋቸው የማይቀር ነው፡፡ የአንድ እናት ልጆች ናቸውና፡፡ የአንድ አስተሳሰብ ጥንስሶች ናቸውና፡፡  ስለሆነም ለመራራቅ መተዛዘብ፣  ለመነካካት መቀራረብ ይቀናቸዋል፡፡ ቀላሉን ያወሳስባሉ፡፡ ውስብስቡን ያናንቃሉ፡፡ “ምን አለ?” ሳይሆን፣ “ማን አለ?” እና “የማን ሰው ነው?” ይሆናል የጨዋታው ህግ፡፡ በየትኛውም አጀንዳ ላይ አንዱ እሚለውን ለማፍረስ ሌላው ሳይተኛ ያድራል፡፡
ከየጎራቸው ውጪ ያለው ህዝብ ቢመክራቸው በጄ አይሉም፡፡ ማተቤን ማተብህ አድርግ፣ ለእኔ ዕምነት አደግድግ፣ ማለትን እንደ አሠርቱ ትዕዛዛት ሊያስጠኑት ይጣጣራሉ እንጂ ሁሉን መርምረህ የሚበጅህን አንተ ዕወቅ አይሉትም፡፡ በልዩነቶቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በአንድነቶቻቸው ላይም ይጣላሉ፡፡ መጣላትን እንደ ዓላማ የያዙ እስኪመስለን ድረስ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ- የሚሉም ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ድርጅት እንጂ አገር የላቸውም፡፡ ከቶውንም “ተመሳሳዮች  ይገፋፋሉ፣ ተቃራኒዎች ይሳሳባሉ” የሚለውም የሳይንስ ህግ አይገዛቸውም፡፡ በምንም ስለ ምንም ጉዳይ አይደማመጡምና። ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ አንድ ተንኮል ተግተው፣ አንድ ምሥጢር ተጋርተው አድገው እኒህ ወንድማማቾች እንደምን ሊፋቀሩ ይቻላቸዋል? ለህዝቡ፣ ለጋራ-ቤታችን፣ ለአገሩ፣ ለአህጉሩ፣ ለሉሉ ስንል ተሳስበን እንደር፣ ደግ ደጉ ይታየን ቢባሉ ልሣን ለልሣን ማን ተግባብቶ?
“ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት”
እንዲል መፅሐፈ-ተውኔት ይጠፋፋሉ፡፡ በቋንቋ መጠፋፋት ወደ አለመግባባት፣ ወደ አለመቻቻልና ወደ መቂያቂያም ከዚያ አንድያውን ወደ መፈጃጀት ያመራቸዋል፡፡ ይሄ ለሀገር አይበጅም፡፡ ሁሉን ከልብ ካላረጉት ከጊዜያዊ ታክቲክነት አያልፍም፡፡
“መርሃ ግብር አውጣ፣ ልዩነት አውጣጣ፣ አማራጭ አምጣ፣ የአማራጭ አማራጭ አዋጣ፣ እንደምንም አናት ውጣ..” ነው ነገሩ፡፡ ብቻ ይኸንንም አታሳጣ! ከማለት በቀር መቼም ምርጫም አማራጭም የለም፡፡
ተመራጩ፣ አስመራጩ፣ አማራጩ፣ ታዛቢውና ሀሳዊ- ተመልካቹ በሙሉ፣ በአንድ ልብ እንዲያስቡ፣ ህዝቡን ትተው በንብረቱ የማይጣሉና ራሳቸውን ሳይሆን የአገሪቱን ህልውና ማዕከል የሚያደርጉ ተሟጋቾች ለማግኘት ማለም ይገባናል፡፡ አለበለዚያ ከስንት ዘመን በፊት እንደተባለው ዛሬም “ጠላታችንን እናታችን እንደምትወልድልን” ከማየትና ከመታዘብ ሌላ መላም ላይኖረን ነው፡፡ ለማንኛውም፤
እናት ብዙ ልጆች አሏት
ያም “እናቴ” ያም “እናቴ” ብሎ ሚላት፡፡
ያም በፍቅር እንዳያንቃት
ያም በቅናት እንዳይነክሳት
ያ ከሥሯ እንዳይነቅላት
ያም ባፍጢሟ እንዳይተክላት
ሰብሰብ ብለህ ሰብስባት!!
ብሎ አደራን ማጥበቁ ሳይሻል አይቀርም፡፡

Read 16155 times