Saturday, 17 July 2021 14:33

ኤች አይቪን ለመግታት፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብር፣ የጋራ ሃላፊነት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ኤችአይቪ ኤይድስ በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚለውን ለመገመት ያስችላል በማለት የፌዴራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ቀደም ሲል ያወጣውን መረጃ ልናስነብባችሁ ለህትመት ብለነዋል፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020/ አዲስ በኤችአይቪ ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ አንድ ሺህ ሰባት መቶ አስራ አምስት (11,715) ደርሶ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020/ በኤችአይቪ ኤይድስ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ስድስት መቶ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰላሳ ስድስት (622,236) ነበር፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2020/ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር አስራ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሰማንያ አምስት (12,685) መሆኑን የፌዴራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በድረ ገጹ ለንባብ ብሎታል፡፡ መረጃው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2013/የወጣ ነው፡፡
የፌዴራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በአዋጅ ቁጥር 276/1994 የተቋቋመ ኤች አይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀሱ የፌደራልና የክልል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ በማስተባበር፣ የስራ ቅንጅት እንዲኖር ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ሌሎች ተዛማጅ ስራዎችን በመስራት፣ የኤች አይቪ ስርጭትንና የሞትን ምጣኔ በመቀነስ፣ መድሎና መገለልን በማስቀረት፣ እንደ ሀገር ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ የሚጠበቅበት መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
በዚሁ መሰረት ይህንን ሀገራዊ ጉዳይ የሚያሳካ፣ በየአምስት አመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘ ጋጀት፣ አፈጻጸም መርህ በማበጀት፣ በየግማሽ አመቱ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች፣ ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገምገም፣ የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ ተጨበጭና በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ኤች አይቪ/ኤድስ እንደ ሀገር በህብረተሰቡ ላይ አጥልቶ የነበረውን የሞት ድባብ፣ ህመምና ስቃይ፣ መገለልና መድሎ፣ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል፡፡
ምንም እንኳን በዚህ መልክ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ በተገኘው ስኬት በመርካት፣ አሁናዊ ሁኔታውን በሚገባ ባለመረዳትና በመዘናጋት፣ ኤች አይቪ/ኤድስ ዛሬም በየዓመቱ ለአስር ሺዎች ሞት ምክንያት እየሆነ መሆኑን እያስተዋልን አይደለም። አሁንም እንደ ትናንቱ ወጣቱና አምራች የሆነው ሀይል በአዲስ በኤች አይቪ እየተያዘ መሆኑን እየተገነዘብን አይደለም፡፡ የስርጭት ምጣኔው አስጊና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም የከፍተኛ አመራሩም ሆነ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ትኩረትን አሁንም በሚፈለገው ልክ ሊያገኝ አልቻለም ሲሉ የተናገሩት የፌዴ ራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ሓላፊ የነበሩት ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ ናቸው፡፡
ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በስነስርአቱ ላይ ከተናገሩት ውስጥ የሚከተለውን ቀንጨብ አድርገን ለንባብ ብለነዋል፡፡ ‹‹ኤች አይቪ ኤድስን ስርጭት በመግታት ረገድ አግባብ ያላቸው አካላት በሙሉ ለችግሩ ይበልጥ ትኩረት በመስጠት፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የማህበረሰብ ንቅናቄዎችን በስፋት በማካሄድ፣ ጤናማ አመለካከትና ባህሪ እንዲዳብር፣ የመከላከል ስራውን በተቀናጀ ሁኔታ በመስራትና ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ራሳቸውን ከኤችአይቪ እንዲከላከሉ ማድረግና አስፈላጊውን ድጋፍና ክብካቤ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ በተደረገው ሰፊ ርብርብ፣ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት፣ በተገኘው ውጤት በመርካትና በመዘናጋታችን ምክንያት የሁሉም ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ተሳትፎና ርብርብ መቀነሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሄንኑ ተከትሎ በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዲስ በቫይረሱ የመያዝና በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች የመሞት ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት የኤች አይቪ/ኤድስን ጉዳይ በማካተት፣ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት በሚችልበት ደረጃ መስራት የሚገባቸው ቢሆንም በታሰበው ልክ በትኩረት ባለመሰራቱ ተጠባቂው ውጤት እየመጣ አይደለም። የክልል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤቶች፣ በሁሉም ተቋም፣ ኤች አይቪ/ኤድስ ጉዳይ ተካቶ፣ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ፣ ተግባራዊ እንዲሆን በመከታተልና በመቆጣጠር ለመምራት ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነት ያለባቸው ቢሆንም እዚህ ግባ የሚባል ስራ እየሰሩ አይደለም፡፡
ኤችአይቪ/ኤድስ በየደረጃው ያለው አመራር አጀንዳ አለመሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ስላደረገው፣ እአአ በ2030 ኤድስ የማህበረሰባችን የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተቀ መጠውን ራዕይ እንዳናሳካ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡
በመሆኑም ሀገርን መውደድ ከወንዝ ከተራራው፣ አጠቃላይ ያደግንበትን መንደርና አከባቢ ከመውደድ በዘለለ ሰውን መውደድ በመሆኑ፣ ባለን ውስን ሀብት ተክክለኛ፣ ደረጃውን የጠበቀና በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያለው የኤች አይቪ ኤድስ መረጃ፣ ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ፣ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖችንና በኤድስ ምክንያት ያለ አሳዳጊ የቀሩ ህጻናትን ተገቢ፣ ማህበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ፣ ስነልቦናዊ ድጋፍ በመስጠት፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን ከኤች አይቪ ለመከላከልና በራሳቸው የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ አቅም እንዲኖራቸው በማስቻል ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡
ኤችአይቪን ከስርአተ ጾታ እና የኤችአይቪ ምላሽ አኩዋያ አንድ ጥናት መደረጉን ዶ/ር ጽጌረዳ ሰኔ 7/2013 ዓ/ም ይፋ አድርገዋል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት በሀገራችን ልጃገረዶችና ሴቶች በትምህርት፣ በጤና አገልግሎት፣ በመሰረታዊ የኑሮ ፍላጎትና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ከአጠቃላይ ማህበረሰቡ ጋር ሲነጻጸር የተጎዱ መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አውስተው መንግስት የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ከህገ መንግስት ጀምሮ ጠንካራ የሴቶች ፖሊሲ በማውጣትና እንዲተገበሩ በማድረግ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል። ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የተሰጠውን ኃላፊነትና ተግባር መሰረት በማድረግ ይህ የዳሰሳ ጥናት እንዲከናወን ያደረገ እንደሆነና በጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን በመተንተን ኤች አይቪ የማህበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን በሚተገበረው ዘርፈ ብዙ ምላሽ ላይ በሚከናወኑ ተግባራት ባለድርሻ አካለት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የእናቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ተ/ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ልጅዓለም እንደገለጹት ላለፉት አስር ወራት በተከናወነው የዳሰሳ ጥናት የተለያዩ ውጤቶች እንደተገኙ ገልጸው የኤች አይቪ ስርጭት ምጣኔ ከስርዓተ ፆታ የፍትሐዊነት ችግር፣ የኤች አይቪ ምላሽ ስርዓተ ፆታን በሚፈለገው ልክ ያላካተተ እንደሆነ በተጨማሪም የስርዓተ ፆታ ጉዳዮችን ተደራሽ ለማድረግ የተመደበ በጀት በግልጽ አለመታወቁ በዳሰሳው ወቅት ከተገኙ ዉጤቶች መካከል እንደሆኑ አንስተው የተገኘው የዳሰሳ ውጤትን መሰረት በማድረግ በቀጣይ የተለያዩ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ዶ/ር ጽጌረዳ እንደገለጹት አንድ ሀገር፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ጤናማና አምራች የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የጤናው ዘርፍ ስኬት ፈርጀ ብዙ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ በጤናው ዘርፍ ያልተሳካላቸው ሀገሮች፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን፣ ማህበራዊ ፍትህን፣ የዳበረ ዴሞክራሲን ያረጋግጣሉ ተብሎም አይወሰድም፡፡ ኤች አይቪ/ኤድስ የሚያስከትለው ቀውስ ደግሞ ከጤና ችግርነቱ ባሻገር፣ ስነ ልቦናዊ ስብራት ጭምር ነው፡፡
በመሆኑም አሁን ካለንበት አዙሪት ውስጥ ለመውጣት፣ የቀጣዩን አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በተሟላ መንገድ መገንዘብና መተግበር ይጠይቃል፡፡ እስትራቴጂክ ዕቅዱ እ.ኤ.አ በ2025 ያስቀመጥናቸውን አንኳር ግቦችና በ2030 የያዝነውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዱ ዋና ዋና የአ ፈጻጸም አቅጣጫዎችን የያዘ፣ የባለድርሻ አካላትና፣ የአጋር ድርጅቶችን፣ የከፍተኛ አመራ ሩንና ባለሙያውን የተቀናጀ አሰራር፣ ጠንካራ ቁርጠኝነትን፣ የነቃ ተሳትፎና ሀገርን ከኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት ለመታደግ፣ የላቀ ተነሳሽነትን የሚጠይቅ ነው። ለተግባራዊነቱ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከወዲሁ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
ምንጭ፡-የፌዴራል ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ድረ ገጽ

Read 14735 times