Saturday, 17 July 2021 14:45

በXXXII ኦሎምፒያድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ከ7ሺ በላይ የህክምና ባለሙያዎች ይሰማራሉ
      • ከትኬት ሽያጭ የሚገኘው 810 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታጥቷል
      • ከ9500 ሰዓታት በላይ ስርጭት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል
      • እስከ 30 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኗል


            ጃፓን የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ አንድ ሰሞን ቀርቶታል፡፡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሳሳቢነት ቶኪዮ ከተማ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ  ስትሆን ኦሎምፒኩ በሚካሄድባቸው 16 ቀናትም አዋጁ ይፀናል፡፡  የኦሎምፒኩ አዘጋጆች በቅድሚያ ከ10ሺ በላይ ዶክተሮችና ነርሶች በተጠንቀቅ እንደሚቆሙ አሳውቀው ነበር፡፡ ኮቪድ 19 በጃፓን ውስጥ በሚያሳየው ወቅታዊ  ሁኔታ የህክምና ባለሙያዎቹ ብዛት ወደ 7ሺ ተቀንሶ የኦሎምፒኩን ደህንነት ለመጠበቅ ይሰማራሉ ተብሏል፡፡ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂድ ሱጋ በኮቪድ 19  ተለዋዋጭ ባህሪይና ተላላፊነት ሳቢያ  ከባድ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ለተመልካቾች ዝግ የሆነበት ምክንያት የአዳዲስ ቫይረስ ዝርያዎች መገኛ እንዳይሆን በመስጋት መሆኑንም አሳውቀዋል ፡፡
ከጃፓን ህዝብ 80 በመቶው ኦሎምፒኩ ሲካሄድ ወረርሽኙ ቢባባስስ በሚል ስጋት ያለፈውን ዓመቱን ሙሉ ሲቃወም ቆይቷል፡፡ የጃፓን መንግስትን የሚተቹ ፓርቲዎች ፣ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት፤ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር እና ሌሎችም የቶኪዮ መስተዳድር አደጋውን ለመጋፈጥ መወሰኑን እየተቹ ናቸው፡፡  ዋና አዘጋጇ የቶኪዮ ከተማ ብቻ ሳትሆን በአቅራቢያዋ የሚገኙት ሌሎች ከተሞች ካንጋዋ፤ ሳያቲማ እና ቺባ በሚያኳሂዷቸው የኦሎምፒክ ውድድሮች ተመልካቾችን ማስተናገድ አይፈቀድላቸውም፡፡ ከወረርሽኙ በፊት የኦሎምፒኩ እስከ 9 ሚሊዮን  ትኬቶችን ለሽያጭ ለማቅረብ እቅድ ነበራቸው፡፡ ይሁንና የኦሎምፒኩ የውድድር ስፍራዎች ለስፖርት አፍቃሪዎች በመታገዳቸው በትኬት ሽያጭ የሚገኘውን ከ815 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አሳጥቷል፡፡   206 አገራት የወከሉ 15ሺ ኦሎምፒያኖች እና ከ50ሺ በላይ ልዑካኖቻቸው በቶኪዮ 2020 ላይ ተሳታፊ ናቸው፡፡ 33 የኦሎምፒክ ስፖርቶች 339 የኦሎምፒክ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በተለያዩ የጃፓን ከተሞች የተገነቡ 41 የውድድር ስፍራዎች ያስተናግዷቸዋል፡፡ ቤዝቦል እና ሶፍት ቦል፤ ካራቴ፤ ስፖርት ክላይምቢንግ፤ ሰርፊንግ እና ስኬት ቦርድን በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄዱ ይሆናሉ፡፡ ኦሎምፒኩ ከዓለም የተለያዩ ክፍሎች የሚገቡ ስፖርት አፍቃሪዎችን   ባለማስተናገዱ የጃፓን ቱሪዝም ተጎጂ ይሆናል፡፡ ከኮሮና በፊት በተለይ በ2019 እኤአ ላይ ከ51.9 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ጃፓንን በመጎብኘት ከ43.6 ቢሊዮን ዶላር ወጭ አድርገው ከፍተኛ ገቢ አስገኝተዋል፡፡  በ2020 እኤአ ላይ ግን  የጎብኝዎች ቁጥር እስከ 40 ሚሊዮን እንደሚደርስ ተጠብቆ በኮሮና ወረርሽኝ  የቱሪስቶች ብዛት ወደ 4.12 ሚሊዮን የወረደ ሲሆን 2021 እኤአ ከገባ በኋላ ጃፓንን የጎበኙት ከ78ሺ በታች ናቸው፡፡
ኦሎምፒኩ ለስፖርት አፍቃሪዎች ዝግ ሆኖ መካሄዱ በርካታ የስፖርት አካላትን ቅር አሰኝቷል፡፡ በተለይ በስፖንሰርሺፕ የተሳተፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኦሎምፒክ ውድድር ስፍራዎች ላይ ስፖርት አፍቃሪዎች አለመገኘታቸው አዳዲስ ደንበኞችን የሚያፈሩበትን እድል ስለሚያሳጣቸው ደስተኞች አይደሉም፡፡ ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኦሎምፒኩ ለ1 ዓመት ከተራዘመ በኋላ  ስፖንሰሮችን ተጨማሪ ክፍያ መጠየቁም አልተዋጠላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች  በሚቀጥሉት የኦሎምፒክ መድረኮች በስፖንሰርነት ለመግባት ማቅማማታቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በዋና አጋርነት የሚሰሩ ከ14 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች  ለኦሎምፒኩ የ4 ዓመት የስራ ዘመን እያንዳንዳቸው 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍለዋል፡፡ የስፖርቱ መድረኩ በ1 ዓመት ከተሸጋሸገ በኋላ እያንዳንዳቸው ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተደርገዋል፡፡በነፍስ ወከፍ ከ25 እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል በተከታይ ደረጃ የነበሩት ስፖንሰሮች ደግሞ እያንዳንዳቸው 5 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ሂሳብ እንዲፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ከ70 በላይ የጃፓን ኩባንያዎች ቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክን ስፖንሰር ያደረጉ ሲሆን እስከ 3.3 ቢሊዮን ዶላር መክፈላቸው በኦሎምፒክ ታሪክ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
32ኛው ኦሎምፒያድ ከስፖርት አፍቃሪዎች ድባብ የሚርቅ ቢሆንም  በቲቪ ስርጭት ከፍተኛውን ትኩረት ሊያገኝ ይችላል፡፡ በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ኦፊሴላዊ የኦሎምፒክ የብሮድካስት አገልግሎት OBS እና በዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች የላቀ ተሳትፎ ከፍተኛ ድምቀት ይኖረዋል፡፡ ታላላቅ የብሮድካስት ኩባንያዎች ታላቁ የስፖርት መድረክ  በረቀቀ ቴክኖሎጂ ልዩ የስርጭት ሽፋን እንደሚሰጡት  የሚጠበቅ ሲሆን ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የብሮድካስት መብት ገቢው 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ ኦቢኤስ ተብሎ የሚጠራው የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የብሮድካስት አገልግሎት ከ8100 በላይ ሰራተኞችን በማሰማራት ከ9500 ሰዓታት  በላይ የስርጭት ሽፋን እንደሚኖረው የታወቀ ሲሆን ከዚሁ ስርጭት 4ሺ ሰዓታት የሚሆነው የቀጥታ ስርጭቶችና የሽልማት ስነስርዓቶች ናቸው፡፡ ኦሎምፒኩ በዓለም ዙርያ በ220 አገራት በሚኖረው የቲቪ ስርጭት ላይ ከኦሎምፒክ የብሮድካስት አገልግሎት ጋር ከ29 በላይ የብሮድካስት ባለመብቶች እና  ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ የብሮድካስት ተቋማት በጋራ ይሰራሉ፡፡ በመላው አሜሪካ የብሮድካስት መብቱን የያዘው ኤንቢሲ NBC በስርጭት ሽፋኑ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ኤንቢሲ ከ2021 እስከ 2032 እኤአ የኦሎምፒክ ስርጭትን ለመስራት 7.75 ቢሊዮን ዶላር የከፈለ ሲሆን  ከቶኪዮ 2020 ስርጭቱ በተያያዘ በሚሰራቸው ማስታወቂያዎች ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያገኝ ይጠብቃል፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ ዘገባዎች 32ኛው ኦሎምፒያድ ከ57 ዓመታት በፊት ቶኪዮ ካስተናገደችው 18ኛው ኦሎምፒያድ እና ከ5 ዓመታት በፊት ሪዮ ዲጀኔሮ ካዘጋጀችው 31ኛው ኦሎምፒያድ ጋር በማነፃጸር ይመለከቱታል፡፡ በ1964 እኤአ ላይ ጃፓን  18ኛውን ኦሎምፒያድ ያስተናገደችው ከ2ኛው ዓለም ጦርነት 19 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ በሳተላይት የቴሌቭዥን ስርጭት ያገኘበትና ባለቀለም ምስሎች የተላለፉበት ወቅት ነበር፡፡  በ40 የተለያዩ አገራት የስርጭት ሽፋን በማግኘት ከ600 እስከ 800 ሚሊዮን ተመልካቾችን የታደሙት የ1964 ቶኪዮ ኦሎምፒክ በያንግዜ ምንዛሬ ከ1.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከብሮድካስት መብት ገቢ ሆኖበታል፡፡  በሌላ በኩል የብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ በ2016 እኤአ ላይ ያስተናገደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ 11.5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደሆነበት ይታወሳል፡፡ ከ500ሺ በላይ ቱሪስቶች ኦሎምፒኩን ምክንያት አድርገው ብራዚልን የጎበኙ ሲሆን የኦሎምፒክ ውድድሮችን ለመታደም ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ትኬቶች ተሸጥዋል፡፡
32ኛው ኦሎምፒያድን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ጃፓን ከሰባት ዓመታት በላይ ነው የተንቀሳቀሰችው፡፡ በአጠቃላይ ኦሎምፒያዱ እስከ 30  ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኖበት ከምንግዜም ውድ የኦሎምፒክ መስተንግዶዎች ተርታ ገብቷል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የፈጠረው የ1 ዓመት ሽግሽግ በዝግጅቱ ላይ ተጨማሪ 3 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኗል፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛውን በጀት ወጭ በማድረግ የመጀመርያው ተጠቃሽ በ2014 እኤአ ላይ የራሽያዋ ሶቺ ያዘጋጀችው የክረምት ኦሎምፒክ 55 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበት ነው፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ቤጂንግ ያስተናገደችው 29ኛው ኦሎምፒያድ እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበታል፡፡


Read 397 times