Saturday, 17 July 2021 14:51

አደገኛው የኮሮና ዝርያ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት 104 አገራትን አዳርሷል

Written by 
Rate this item
(0 votes)


              ዴልታ በመባል የሚታወቀውና በፍጥነት በመዛመትም ሆነ በገዳይነቱ ከሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እንደሚልቅ የተነገረለት አደገኛው የኮሮና ዝርያ በአለም ዙሪያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ እንደሚገኝና የከፉ ወረርሽኞችን ሊያስከትል እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በጥቅምት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በህንድ የተገኘው ዴልታ የተባለው የቫይረሱ ዝርያ ወደ ሌሎች የአለማችን አገራት በፍጥነት በመሰራጨት እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ወደ 104 አገራት መግባቱን የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ባለፈው ሰኞ ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
እስካለፈው ሳምንት በነበሩት አራት ተከታታይ ሳምንታት በአለማቀፍ ደረጃ የኮሮኖ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመር ማሳየቱን ያስታወሱት የድርጅቱ ዳይሬክተር፣ ለአስር ሳምንታት ቅናሽ ሲያሳይ የዘለቀው የሟቾች ቁጥርም ባለፈው ሳምንት ጭማሬ ማሳየቱን በመግለጽ ለዚህም ዴልታ የተባለው ዝርያ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ሲጂቲኤን እንደዘገበው፤ ዝርያው በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋባቸው ካሉት አገራት አንዷ በሆነችው አሜሪካ ለወራት ቅናሽ ሲያሳይ የቆየው የቫይረሱ ስርጭት ባለፉት ሳምንታት ጭማሬ ማሳየት የጀመረ ሲሆን በየቀኑ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች አማካይ ቁጥር ከአንድ ወር በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በተለይ በሰሜናዊ አካባቢዋ በሶስተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ መፈተን በጀመረችው አፍሪካ አጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ባለፈው ረቡዕ ከ6 ሚሊዮን ማለፉን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፣ የሟቾች ቁጥርም ወደ 154 ሺህ መጠጋቱንና በአህጉሩ ከ37 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች መሰጠታቸውንም አመልክቷል፡፡
በኡጋንዳ ባለፈው ሳምንት ብቻ የኮሮና የእንቅስቃሴ ገደብ ህጎችን ጥሰዋል የተባሉ ከ2 ሺህ 180 በላይ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡

Read 1528 times