Print this page
Sunday, 18 July 2021 00:00

የዙማ እስር የፈጠረው ነውጥ ደቡብ አፍሪካን ለከፋ ውድመት ዳርጓታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸው ባለፈው ሃሙስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው የቀሰቀሱት ተቃውሞ ወደ ከፋ ብጥብጥ፣ ሁከት፣ ግድያና ዝርፊያ አምርቷል፤ እስከ ረቡዕ ድረስም 72 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡
ከ1990ዎቹ ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተ የከፋ ነውጥ እንደሆነ የተነገረለትና ዙማ ከተወለዱበት ካዙል ናታል ግዛት የተነሳው ነውጥ ወደተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶችና ከተሞች መስፋፋቱን ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲርል ራማፎሳ አገሪቱን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ ከ2 ሺህ 500 በላይ የጸጥታ ሃይሎችን ቢያሰማሩም ከነውጠኞች ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አለመሆኑንና ሁከትና ብጥብጡ ዝርፊያና ግድያው ግን ለቀናት ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ቢቢሲ፣ ሰኞ ዕለት ብቻ 200 ያህል የገበያ ማዕከላት መዘረፋቸውንና ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ የተለያዩ አገራት ስደተኞች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ አፍሪካውያን በተለይ ረቡዕ ዕለት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአገሬውና የተለያዩ አገራት ዜጎች መጋዘኖችን፣ መደብሮችን፣ የመንግስትና የህዝብ ተቋማትን መዝረፋቸውን የዘገበው ሮይተርስ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት በእሳት መጋየታቸውን፣ ሆስፒታሎችና የኮሮና ቫይረስ ክትባት የሚሰጥባቸው ማዕከላት መዘጋታቸውን፣ ጎዳናዎችና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መዘጋታቸውን አመልክቷል፡፡
በጆሃንስበርግ፣ ሱዌቶና ደርባንን በመሳሰሉ አካባቢዎች ዘራፊዎች ተደራጅተውና መሳሪያ ታጥቀው በመሰማራታቸው የጸጥታ ሃይሎች ድርጊቱን ለማስቆም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ እስከ ረቡዕ ዕለት የአገሪቱ ፖሊስ በመላ አገሪቱ ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን እንዳስታወቀም አመልክቷል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ነውጠኞች የገንዘብ መክፈያ ማሽኖችን በመስበር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መዝረፋቸውንና ሆቴልና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ በርካታ የንግድ ተቋማት መዘረፍና መቃጠላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአመጽና ብጥብጡ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ተጎጂ መሆናቸውንና በዚህም ከ130 ሺህ በላይ ሰዎች ከስራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ መነገሩንም አስረድቷል፡፡ ቴኪዊኒ በተባለ ግዛት ብቻ 1.09 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንብረት ውድመት መድረሱንም ለአብነት አንስቷል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ዜጎችን ለሞት የዳረገውንና የንብረት ውድመት ያስከተለውን ብጥብጥ፣ ጋጠወጥነትና ዘገባ ያወገዙ ሲሆን፣ ወንጀለኞች በአፋጣኝ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ ህዝቡ ወደመረጋጋት እንዲመለስና ህግ እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።
ተደራራቢ የሙስና ክሶች ተመስርተውባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የ79 አመቱ ጃኮብ ዙማ የተመሰረቱባቸውን ክሶች በተመለከተ ችሎት ቀርበው ምላሻቸውን እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ጥሪ ቢደረግላቸውም፣ በተደጋጋሚ በእምቢተኝነት ፍርድ ቤት ሳይገኙ በመቅረታቸው የአገሪቱ ከፍተኛ የህገ መንግሥት ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት የ15 ወራት እስር ቅጣት እንደጣለባቸውና እስራቸው እንዲዘገይ ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ ተደርጎ ለእስር እንደተዳረጉ የሚታወስ ነው፡፡


Read 2615 times
Administrator

Latest from Administrator