Monday, 19 July 2021 00:00

“ይሄ ፈተና ኢትዮጵያ የፀና መሰረት ኖሯት እንድትወጣ ያደርጋታል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


                ከምርጫው ምን አተረፍን ?
ከምርጫው ያተረፍነው ነገር ቢኖር የነበረው አገዛዝ የስልጣን ዘመኑ አልቆ ስለነበር "ያልተመረጠ መንግስት ነው እያስተዳደረ ያለው" የሚሉ አስተያየቶችን ያስቀረ መሆኑ ነው፡፡ ሃገር ቢያንስ በህጋዊ አካል እየተመራች ነው፡፡ በዚህም ሲናፈስ የቆየውን ብዥታ አስቀርቷል፡፡ ሌላው በርካታ ተወዳዳሪ የነበርን ፓርቲዎች በምርጫው አሸናፊ  ለመሆን ብዙ ደክመናል፤ ነገር ግን ህብረተሰቡ አሁን ሃገሪቱ ለገጠማት ተግዳሮት በስልጣን ላይ ባለው መንግስት እንድትሻገርለት እንደሚፈልግ ያሳወቀበት ምርጫ ሆኖ  ነው የታየኝ፡፡
የብሔራዊ እርቅና መግባባት
እንደ ፓርቲ አጠቃላይ ሁኔታዎችን የገመገምንበትን መግለጫ አውጥተናል፡፡ መንግስት አሁን በሃገሪቱ ካሉ ችግሮች አንፃር እስከ መንግስት ምስረታው መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ዝም ብሎ መቀመጥ የለበትም ባይ ነኝ፡፡ ገዢው ፓርቲ አሁን ባለው ሁኔታ አብላጫውን መቀመጫ  አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ ሃገር አሻጋሪ እርምጃዎች ውስጥ  መግባት አለበት፡፡ የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን ይገባዋል የምለው የብሔራዊ እርቅና መግባባት ነው፡፡ ይሄንን ሁኔታ ለመፍጠር መስከረምን ወይም የመንግስት ምስረታ ቀንን ሳይጠብቅ ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡ እኛ እርቅ ስንል ብዙዎች ወደ ኋላ ይጎትቱናል ምክንያቱም የኛ መታረቅና መግባባት ለሌላው አይመቸውም፡፡ በተለይ ምዕራባውያን ኢትዮጵያውያን ተባብረው በጋራ ሃገራቸውን ለማሳደግ መነሳታቸው ያስደነግጣቸዋል፡፡ ለነሱ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው የሚሆንባቸው፡፡ ስለዚህም የሚፈልጉት ሁሌም በጦርነት አዙሪት  ውስጥ እንድንቆይ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ባለው የሰሜኑ ጦርነት  መሹለኪያ ቀዳዳ አጥተው  ነው እንጂ ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች የመሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ እልቂትን እንደሚደግሱልንና የማንወጣው ማጥ ውስጥ እንደሚከቱን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ አንፃር ለዚህ መንግስትም ሆነ ለህብረተሰባችን ሊያዋጣ የሚችለው ሆደ ሰፊ መሆንና እልህን ትቶ ከማንኛውም አካል ጋር ተቀምጦ መነጋገርና ወደ እርቅ መምጣት ነው፡፡ አሁን ላይ ጦርነቱን የትግራይ ህዝብና የአማራ ህዝብ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የትግራይና የአማራ ህዝብ ደግሞ አብሮ የኖረ አብሮ ሃገር የመሰረተ፣ ለሃገር ምስረታ አብሮ  የሞተ ህዝብ ነው፡፡ ይሔ ህዝብ እውነትን ወደ ጎን ብሎ የግለሰቦችና የእኩያን ፍላጎት መወጣጫ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ አንፃር መንግስት አሁኑኑ የተሻሉ ሽማግሌዎች መርጦ ወደ እርቅ መንገድ መሄድ አለበት፡፡ በዚህ እርቅ ላይ ምዕራባውያን ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። ምዕራባውያን እናስታርቅ ብለው አንድም ሠላም ያወረዱበት ሀገር የለም፡፡ ምክንያቱም እነሱ በዚህ መሃል ሁሌም የተለየ ተልዕኮ አላቸው፡፡ ዓላማቸው ያልተነካን አንጡራ ሃብት በመውሰድ ሃገር ለመበታተን ስለሆነ የእነሱ ጣልቃ ገብነት ፈፅሞ አያስፈልግም። ቻይና እኮ ያመለጠቻቸው በበር መዝጋት ፖሊሲዋ ነው፡፡  እኛም በር  ዘግተን በሃገር ሽማግሌዎቻችን የጥሞና ጊዜ ወስደን ከውጊያ ሁሉም ወገን መመለስ አለበት፡፡
ከእልህ መለስ ብሎ ለእርቅ ዝግጁ መሆን
እውነት ለመነጋገር እነ እገሌ እርቅ አይፈልጉም የሚሉ ሰዎች እንዴት አድርገው እንደተረዷቸው አላውቅም፤ እርቅ የማይፈልግ አካል የለም፡፡ “የኔ ሃሳብ ትክክል ነው፤ ያንተ ትክክል አይደለም” የሚል የመገፋፋት ሁኔታ ነው ያለው እንጂ እርቅ የማይፈልግ አካል የለም፡፡ ችግሩ ያለው  ለምሳሌ “ኦነግ ሸኔ አጥፊ ነው፤ ህወሃት አጥፊ ነው፤ እርቅ አይገባውም” ተብሎ በአንድ ወገን ሲደመደም ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማንኛውም  ድምዳሜ ላይ አለመድረስ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እነማን ያስታርቁ ለሚለው እርግጥ ነው ባለፉት ጊዜያት በተሰሩ ስህተቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎችም ያለማክበርና ያለማመን ሁኔታ አለ፡፡ ይሁን እንጂ ከረቫት ያላሰሩ ነገር ግን ስለ እርቅ በሚገባ የሚያውቁ የአማራም፣ የኦሮሞም፣ የጋሞም፣ የወላይታም የሌላውም የሃገር ሽማግሌዎች አሉ፡፡ ሁለተኛ እነዚህ  እስኪቀራረቡ የአፍሪካ ህብረት አለ፡፡ አፍሪካውያን አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና የኛ ህልውና ነው ብለው ከልባቸው የሚያምኑ አፍሪካውያን አሉ፡፡ በእነሱ በኩል መቀራረብ ይቻላል፡፡ አንዴ ከተቀራረቡ ራሳቸውም መነጋገር ይችላሉ። ዋናው መቀራረቡ ነው፡፡ እኔ የሚደንቀኝ ጦርነትን የመጀመሪያ አማራጭ አድርገን እንኳ እርቅን እንዴት ሶስተኛና አራተኛ አማራጭ ማድረግ እንዳቃተን ነው፡፡
ማንም ማንንም ሳይፈርጅ ሃገርን ህልውና  አደጋ ውስጥ በማይከት መልኩ ሁሉም ሰው ለእርቅ መቀመጥ አለበት፡፡ አንዳንዶች ህወኃት፣ ሸኔ መካተት የለባቸውም የሚል ነገር ያነሳሉ፤ ታዲያ ማን ነው የሚታረቀው? እርቅ የሚያስፈልገው ለፀብ ከሆነ ፀበኛው ማን ነው? የተጣላ ነው  የሚታረቀው።  ሁሉም የተጣላ አካል ነው ለእርቅ መቀመጥ ያለበት፡፡ በዚህ የእርቅ ሂደት ወንጀለኛ የሆኑ ሰዎች በጋራ ስምምነት ለህግ ይቀርባሉ፡፡ ይቅር መባል ያለባቸው ይቅርታ ይደረግላቸዋል ማለት ነው፡፡
በታሪካችን መንግስታት የተወሳሰቡ ፈተናዎች ገጥሟቸዋል፡፡ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለመበታተን በርካታ ድግስ ደግሰውልን ነበር፤ ነገር ግን አባቶቻችን ያንን በብልህነት ነው የተወጡት፡፡ ቀድሞም የኢትዮጵያ ፈተና የሁለት መንገድ ነበር፤ በባንዳና በአፍሪካውያን፡፡ ይሄን ሴራ ግልጽ አድርጎ ከጎናችን ማሰለፍ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ፈተናም እንደውም ኢትዮጵያ መሰረቷ የፀና ሆና እንድትወጣ ያደርጋታል የሚል እሳቤ ነው ያለኝ፡፡


Read 1417 times