Monday, 19 July 2021 00:00

ትውልድ የሚቀረፀው በንባብ ነው!

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

      “ጳጉሜን እናንብብ” የሚል መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው
                        
             ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፍልውሃ አካባቢ ነው። የአንደኛው ደረጃ ትምህርታቸውን አፄ ገላውዲዮስና ሽመልስ ሀብቴ  ት/ቤቶች ውስጥ ተከታትለዋል።
የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ”ግሎባል ስተዲ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽን” የመጀመሪያ ድግሪያቸውን፣ በሶሽዮሎጂ የማስተርስ ድግሪያቸውን አግኝተዋል። በህንዱ የስሪሣይ ዩኒቨርስቲ በ”ጆርናሊዝም ኤንድ ማስ ኮሚዩኒኬሽን” የትምህርት ዘርፍ የተከታተሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም  የዶክትሬት ድግሪያቸውን በሶሽዮሎጂ እየተማሩ ነው። በኒው ጀኔሬሽን ዩኒቨርስቲ በመምህርነት በመስራት ላይ ይገኛሉ።
ወላጅ አባታቸው ኢንጅነር አባይነህ መሸሻ በልጃቸው የወደፊት ህይወት ላይ መሰረት መጣል የጀመሩት ገና በለጋ ዕድሜቸው ላይ እንደነበር ያስታውሳሉ። “የማንበብ ባህል እንዲኖረን፣ ራሳችንን ከንባብና ከዕውቀት ጋር እንድናቆራኝ መሰረቱን የጣለው እሱ ነው። አባታችን ገና ከሕፃንነት ዕድሜያችን ጀምሮ እንድናነብ በተለያዩ መንገዶች ይገፋፋን ነበር። ሰውን ሰው የሚደርገው ማንበብ ነው። ራሳችሁን በንባብና በዕውቀት ካነፃችሁ ማንም ቢገፋችሁ አትወድቁም”  እያለ ይመክረን ነበር። ይህ ሁኔታም በእኔ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው የሚሉት ኢንጂነሩ፤ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የኢንጂነርነት ሙያ ተክነውበታል።  ከ20 ዓመታት በላይ በሙያቸው ላይ በመስራትም የተለያዩ ህንፃዎችን ት/ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችንና ልዩ ልዩ የመኖሪያ ቤቶችን ሲገነቡ ቆይተው የተመረቁበትን ሙያ በይደር አቆይተው ተመልሰው ት/ቤት ገቡ።
ለትምህርት ሁልጊዜም የሚረፍድ ጊዜ የለም። አባቴ ያስተማረኝ ነገር ትምህርትና ዕውቀትን ጊዜ እንደማይገድበው ነው። እና እስከ መጨረሻው ህይወቴ ድረስ እማራለሁ” የሚሉት ኢንጅነር አልአዛር፤ ከትምህርት ቤት ካገኙት ዕውቀት በበለጠ በንባብ ያገኙት እንደሚልቅና  ይህንንም  ወደ ትውልዱ ውስጥ ለማስረፅ አበክረው እንደሚተጉ ይናገራሉ።
“ሀገር ማንበብ አለበት። ትውልድ የሚታነፀው በንባብ ነው። አገራችን ለዓመታት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ቆይታለች” ያሉት ኢንጂነሩ፤” ከዚህ ችግር ሊያላቅቋ    ትና መጪው ጊዜዋን ብሩህ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ልጆቿን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች አጥታለች። ይህ አስከፊ ታሪካችን አንድ ቦታ ላይ ሊቆም ይገባል። አንባቢ፣ ጠያቂና ተመራማሪ ትውልድ ሊፈጠር ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል ይላሉ?” የሚል እምነት አለኝ የሚሉት ኢንጅነር አልአዛር ከተለያዩ ወገኖች በልግስና ያገኙዋቸውን መፅሐፍት ጨምሮ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በግዥ፣ በስጦታና በተለያዩ መንገዶች ያሰባስቧቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ መፃሕፍት “ሸገር የመፅሐፍት መደብር” የሚል ስያሜ በሰጡት መደብራቸው ለአንባቢያን አቅርበዋል።
 ከዚህ በተጨማሪም ከ15ሺ የሚበልጡ መፃሕፍትን ለችግረኛ ልጆችና ለወጣት ማህበራት በስጦታ አበርክተዋል። በቤተ መፃህፍታቸው ከሚገኙትና ለሽያጭ ከቀረቡት ከእያንዳንዱ መፃሕፍት ሽያጭ ላይ 5 በመቶውን ለመሰረት በጎ አድራጎት ማህበር ለመለገስም  ቃል ገብተዋል። ይህም አንድም ትውልዱ ራሱን ከመፃሕፍትና ከንባብ ጋር እንዲያስተዋውቅ ለማገዝ ሲሆን ሌላው ደግሞ የበጎ አድራጎት ማህበራቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ለመደገፍ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ተማሪዎች እረፍት በሚሆኑባቸው የክረምት ወራት ላይ የንባብ ባህልን ለማዳበር መሰራት  እንደ አለበት ይመሰክራሉ። ይህንኑ የንባብ ባህልን ማዳበርን አስመልክቶ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚችል ሰፋ ያለ ፕሮግራም “ጳጉሜንና ንባብ” በሚል መሪ ቃል፤ በመጪው ጳጉሜ ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በሚገኙበት ሰፊ ፕሮግራም ለማካሄድ እየተዘጋጁ እንደሆነም ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል። ከ672 በላይ እናቶችን ከእነልጆቻቸው በመንከባከብ ላይ የሚገኘው የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት ተወካይ አቶ ሚካኤል አባይነህ፤  “ስጦታው በድርጅቱ የሚረዱት ህፃናት የማንበብ ባህል እንዲያዳብሩ ከማገዙም ሌላ  የማካፈልና የመረዳዳትን እንደ ባህል እንዲያጎለብቱም ያግዛቸዋል” ብለዋል
“ያነበበ ትውልድ ራሱን ያንፃል፤ ራሱን ይቀይራል። ይህም  በተቋማችን እውን እንዲሆን ለተደረገልን ስጦታ በእጅጉ እናመሰግናለን” ብለዋል አቶ ሚካኤል፡፡
“ጳጉሜን እናንብብ” በመላው አገሪቱ የንባብ ጊዜ እንዲሆን፣ የመፃህፍት ልገሳና ሌሎች ከንባብ ጋር የተያያዙ ምርሃግብሮች ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኢንጅነር አልአዛር ለዘዲስ አድማስ ጠቁመዋል።

Read 12096 times