Monday, 19 July 2021 00:00

ወወክማ:- እሴቶቹን ይጠብቅ! ትውልዳችንንም ይመጥን !!

Written by  አበባው ፍስሃ (የ4 ኪሎው)
Rate this item
(1 Vote)

   ዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ታትማ ለንባብ በበቃችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ”ህብረተሰብ” አምዷ፡- የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስትያናዊ ማህበር /ወ.ወ.ክ.ማ/ “ማኔጅመንት” “ ግልጽ ደብዳቤ፡- ለጠ/ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አዲስ አበባ” ብሎ የፃፈውን አጭር ደብዳቤ ደጋግሜ አነበብኩት፡፡
በግሌ ገና ከልጅነቴ አንስቶ በ4 ኪሎ ወወክማ በአባልነት በተለይ በተዋልዶ ጤናና በሥነ-ጥበባዊ የወወክማ ፕሮግራሞች በአስተባባሪነትና በተሳታፊነት ለዓመታት ቆይቻለሁ፡፡ ምንም እንኳ ዛሬም ከወጣትነት ክልል ያልወጣሁ ቢሆንም የወወክማ የዓመታት ቆይታዬ ዛሬ ላይ ላለሁበት ግላዊ ኑሮም ሆነ መደበኛ ሥራዬ መሠረት የሆነኝ ወጣት ነኝ፡፡
በወወክማ መሣተፍና ማህበርተኛ ሆኖ መዝለቅ መከባበርን፣ እውነተኝነትን፣ የጋርዮሽ ህይወት መኖርን፣ አለማዳላትን፣ ሠብዓዊነትንና በጎ አድራጊነትን ያላምዳል፤ የዕለት ከዕለት የማህበሩ ፕሮግራምና መርሃ ግብሮቹ ደግሞ አካልን፣ አእምሮንና መንፈስን ያጎለምሳሉ፡፡
እኔ የማውቀው፣ ያጣጣምኩትና ለዛሬው እኔነቴ ጭምር መሠረት የሆነኝ ወወክማ ይህ ዓይነቱን ነው፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ማኔጅመንት” ነኝ ያለው አካል የፃፈው ደብዳቤ በጣም አጭርና እውነታውን አብራርቶ ያቀረበ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
ፈር መያዣ፡- ስለ 4 ኪሎ ወወክማ ህንጻ /ቅጥር/ ግቢ
የ4 ኪሎ ወወክማ በአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ ንግሥና በ    1942 ዓ.ም አፄው አሜሪካንን ጎብኝተው እንደተመለሱ በአሜሪካን ወወክማ /YMCA/ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ የወወክማ ንብረት ነው፡፡ በዘመነ ደርግ ያካለ አንዳች አዋጅ በፖለቲካዊ ውሳኔ ወወክማ እንዲፈርስ ተደርጎ የማህበሩ ንብረቶችም በ “ቀላጤ” ተወርሰው በወቅቱ ለስፖርት ኮሚሽን እንዲሰጡ ተደረገ፡፡
በ1984 ዓ.ም ለተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የወወክማ ልጆች ባቀረቡት ጥያቄ ማህበሩ እንደገና እንዲቋቋም በያኔው የሽግግር መንግሥት ፕሬዝዳንት በአቶ ታምራት ላይኔ ተፈቀደ፡፡ ማህበሩ እንደገና ከተቋቋመበት ማግስት አንስቶ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የማህበሩ የቀድሞ ንብረቶች እንዲመለሱ /ወላይታ፣ አድዋ፣ አዳማ፣ ደብረብርሃንና ጥያቄ መቅረብ ጀመረ፤ ሆኖም “የፕራይቬታይዤሽን ኤጀንሲ” የተባለው መስሪያ ቤት ለወወክማ የንብረቶች ይመለሱልኝ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አልተቻለውም /ኤጀንሲው በደርግ ዘመን በአዋጅ ቢሆንም ያለአግባብ የተወረሱትን እያጣራ የመመለስ ስልጣንና ኃላፊነት ብቻ ስለነበረው የወወክማን ጥያቄ ማስተናገድ አልተቻለውም ነበር/ ይሁንና እንደገና የተቋቋመው ወወክማ በቀድሞ ዓላማ ላይ በመመስረት በብሔራዊ ማህበሩና በቅርንጫፎች አማካኝነት ንብረቶችን ከማስመለስ ጥያቄው ጎን ለጎን በርካታ ተግባራቶችን እየከወነ ቆይቷል፡፡
በወቅቱ በተለይም ከኢትዮጵያ የ2ተኛው ሚሊኒየም በዓል አከባበር አንስቶ የማህበሩን ንብረቶች ለማስመለስ ጥረቶች ተጠናክረው በመቀጠላቸው በ2001 ዓ.ም ከቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠ/ሚኒስትር ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር የኢትዮጵያ ወጣቶች የንቅናቄና የተሳትፎ ኮንፈረንስ በተካሄደበትና በመላው ሃገሪቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለእይታ በበቃ የውይይት መድረክ፣ የወወክማ ወጣት ተወካዮች ባቀረብነው “የማህበራችን ንብረቶች ይመለሱልን” ጥያቄ አቶ መለስ ዜናዊ “አላግባብ የማህበሩ ንብረቶች የተወሰዱ ከሆነ መመለስ ይኖርባቸዋል፣ ይመለሳሉም” የሚል ቀና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከዚሁ ቀና ምላሽ በኋላ በወቅቱ በ4 ኪሎ ወወክማ የምንሳተፍ ወጣቶች ከ4 ኪሎ ወወክማ የቦርድ ሥራ አመራር አካላት ጋር በመቀናጀት ለጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ደብዳ በመፃፍ ጥያቄ አቅርበን ደብዳቤውም በወቅቱ የአቶ መለስ ዜናዊ የማህበራዊና ህዝብ አደረጃጀት አማካሪ በሆኑት በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ አማካኝነት አዎንታዊ ምላሽ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ እጅጉን በሚያሳዝንና በሚያሳፍር መልኩ በዚያን ወቅት የወወክማን ብሔራዊ ማህበር በቦርድ አባልነት የሚመሩ አንድ ግለሰብ /ስማቸውን መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም/ የጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሠራተኛ በመሆናቸው ይህንኑ የ4 ኪሎ ወወክማን ደብዳቤ አዎንታዊ ምላሽ ከእነተሰጠበት ሰነድ ጋር ከጠ/ሚንስትር ጽ/ቤት የሚኒስትሮች ም/ቤት መዝገብ ቤት እንዲወጣ አደረጉት፡፡
ቀጥሎ በዚሁ የደብዳቤያችን አላግባብ ከጠ/ሚ/ጽ/ቤት መውጣትን አስመልክቶ በ4 ኪሎ ወወክማና በብሔራዊ ወወክማ የቦርድ አመራሮች መካከል አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ከዚህም ባሻገር በ4 ኪሎ ወወክማ ተጽፎ ለጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የገባውን ደብዳቤ ያስገባሁትም ሆነ የምከታተለው እኔ ስለነበርኩ የብሔራዊ ማህበራችን የቦርድ አመራሮች አብነት ጆሣንሰን አካባቢ በነበረበው የአዲስ ከተማ ወወክማ ጽ/ቤት አስጠርተው የፍ/ቤት ያህል አቁመው አፋጠጡኝ፡፡
ከብዙ ክርክርና ኃይለ ቃል የታከለበት ማዋከብ በኋላ “4 ኪሎ ወወክማ ቅርንጫፍ ነው፤ የወወክማን ንብረት የመጠየቅ ስልጣንም ሆነ ኃላፊነት የለውም፤ እኛ እንደ ሀገር ሁሉንም የተነጠቁ (የተወረሱ) የወወክማ ንብረቶችን እናስመልሳለን!” ተብሎ በ“አርፈህ ተቀመጥ” ማስጠንቀቂያ ተለያየን፡፡
የወወክማ “ማኔጅመንት” አጭር ደብዳቤ ውስንነቶች
በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ኮሚቴ አልተቋቋመም፤ ይመለስለት ተብሎ ተወሰነ እንጂ የውሳኔ ሃሳብ አልቀረበም፡፡ በደብዳቤው መጠየቅ የነበረበት “ውሳኔው ይፈፀም!” መሆን ነበረበት፣
በደብዳቤው ላይ “ወወክማ በደርግ ሥርዓት ከአዋጅ ውጪ ያለ አግባብ የተወረሰው 4 ኪሎ አካባቢ የሚገኘው ህንፃ…” ይላል፡፡ ዳሩ ግን ዘርዘር ተደርጎ መብራራት ነበረበት ማለትም ከአዋጅ ውጪ ሲባል በምን አግባብ? (ማለትም በ“ቀላጤ” ወይንም በፖለቲካ ውሳኔ የተወረሰ መሆኑ መገለጽ ነበረበት)
በ2001 ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ ወጣቶችን ሲያወያዩ እንደሚመለስ በይፋ መግለፃቸው፣ የአቶ መለስ የማህበራዊና ህዝብ አደረጃጀት አማካሪ የነበሩት አቶ ኃ/ማርያም ደሣለኝ ጉዳዩን ይዘውት እንደነበር፣ ብሎም አጠቃላይ የማስመለስና የመመለስ ሂደቱ ተብራርቶ መገለጽ ነበረበት፣
ያን ጊዜ /በ2001 ዓ.ም/ በ4 ኪሎ ወወክማ ለጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት በደብዳቤ የ”ይመለስልን” ጥያቄ ከቀረበ በኋላ በወቅቱ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፤ የወወክማን ንብረቶች በተለይም የ4 ኪሎ ወወክማን ህንጻ መመለስ እንደሚቻል በ2001 ዓ.ም በጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካኝነት በወጣቶች ኮንፈረስ ላይ መግለፃቸውን መነሻ አድርገው የፃፉትን ደብዳቤ መጥቀስም ሆነ ኮፒውን ማያያዝ ይገባ ነበር /ይህ የወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ ደብዳቤ ዛሬም ድረስ በ4 ኪሎ ወወክማ ቀደምት አባላት እጅ ይገኛል/
የአሁኑ ወወክማ “ማኔጅመንት” ይህንን ያህል ዓመታት ቆይቶ /በራሱ በተጻፈ ደብዳቤ እንኳ በ2004 የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ነበር ማለቱ ልብ ይባልልኝ / ዛሬ ላይ የስፖርት ኮሚሽን ህንፃ ለመስራት በ4 ኪሎ ወወክማ ቅጥር ግቢ ቁፋሮ ሲጀምር ከእንቅልፉ እንደባነነ አንድ ሰው “ከምስጋና ጋር ለወወክማ ይመለስ” ማለቱ ሳያንሰው ነጥሎ የ4 ኪሎ ወወክማን ህንፃ ይመለስ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ ተገቢነት የለውም፤ ሌሎቹ የወወክማ ንብረቶችስ? አብሮ መጠየቅ ነበረበት፡፡
ይህ ደብዳቤ የ4 ኪሎ ወወክማን ህንፃ መመለስ ባይቻል እንኳ መንግሥት የወወክማን ታሪክ፣ በሀገሪቱ ወጣቶች ላይ የተጫወተው አዎንታዊ ሚና ታሳቢ አድርጎ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችና ክልሎች ማህበሩ ለወጣቶች አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ማዕከላት ለመገንባት እንዲችል የመሬትና መሰል አቅርቦቶች እንዲሰጠው በአማራጭነት መጠየቅ ተገቢ ነበር፡፡
የወወክማ ትላንት
ወወክማ ለዛሬዋ ኢትዮጵያችን ዘመን አይሽሬ ባለውለታ መሆኑ አይካድም፤ አሁን አሁን እየጎለበቱ የመጡ የስፖርት አይነቶች በወወክማ የተጀመሩ፣ አማተርና ፕሮፌሽናል የስፖርት ባለሙያዎች በወወክማ ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው፡፡ (ለአብነት የዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድንን ጠንሳሹ ወወክማ ነው)፡፡
በተለያየ የሥራና የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገርን ያገለገሉ፣ ዛሬም ድረስ የሚያገለግሉ ጉምቱዎችና በርካታ ስኬታማ አርአያዎቻችን የወወክማ ፍሬዎች ናቸው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአድዋ ወወክማ፣ እንዲሁም የቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ የወላይታ ወወክማ አዘውታሪዎች ነበሩ፡፡
በኪነ-ጥበብ የሙያ ዘርፎች በርካታ ከዋክብቶቻችንን መዘርዘር የሚቻል ቢሆንም ስመ-ገናናው ጸሐፌ ተውኔት፣ ባለ ቅኔ ገጣሚና (አፍሪካዊ አንትሮፖሎጂስቱ) ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የቀድሞው ፕሬዚዳንት ደራሲ ጌታቸው በለጠ የወወክማ ፍሬዎች ናቸው፡፡
የወወክማ ዛሬ
ዛሬስ? መጠያየቅ ይኖርብናል፤ የምስረታ ታሪካቸው ከአስርና ከአስራ አምስት ዓመት ዕድሜ የማይዘሉ ማህበራት በውስጣዊ ጥንካሬ፣ በመዋቅራዊ አደረጃጀትና በብዙሃን ወጣቶች ተሳትፎ ረገድ የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘታቸውን እያስተዋልን ከሀገራችን የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሆነ ወጣት ትውልድ በበርካታ ችግሮች ውስጥ መዘፈቁ ገሃድ ሆኖ እያለ ሀገርን የመውደድ ምንነት፣ የራስን የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስን ጤንነት የመጠበቂያ መንገዶችን ማሳየት የሚጠበቅበት ወወክማ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ሊያከራክረን ከተገባም የወቅቱ የማህበሩ መፋዘዝ ነው፡፡
ለዚሁ ጽሑፌ መነሻ በሆነኝና የወወክማ “ማኔጅመንት” ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ፤ “በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ በትግራይ እንዲሁም በደ/ብ/ብ/ሕ በሚገኙ አስር ቅርንጫፎች …. ከ30 ሺ በላይ አባላትና በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም በየዓመቱ 80 ሺ የፕሮጀክት ተጠቃሚ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አቅፎ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በሲቪክ ተሳትፎ በአመራርነት ብቃት ላይ ሁለገብ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል” ብሎ ይዘረዝራል፡፡
በርግጥ ይህ ከላይ የተገለፀው የአሁኑ ወወክማ ቁመና ሃቅ ነው? አይመስለኝም! ምክንያቱም የወወክማ የአባልነትና የአመራርነት እሴት ከሰብዓዊነት ቀጥሎ ታማኝነትና ሃቀኝነት ነውና ሀቅ ሀቁን እንነጋገር፡፡ ለመሆኑ የ4 ኪሎ ወወክማ ጽ/ቤት የትና በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? አዲስ ከተማስ? የዑራኤሉ ቅርንጫፍስ? የወወክማ የወንዶችና የሴቶች እግር ኳስና የቴኒስና የባድሜንተር ቡድኖች የት ይሆን ያሉት? የዩዝ ካምፒንግ ፕሮግራምስ እየተተገበረ ነው? የአፍላ ዕድሜ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮግራም ምን ያህል አፍላ ወጣቶችን በተጨባጭ ከሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮች ታደገ? ዛሬ ላይ መንግሥታዊ ተግባር የሆነው በጎ ፈቃደኝነትና የወጣቶች ማህበራዊ አገልግሎት መርሃ ግብርን ያስተዋወቀውና ያስለመደው ወወክማ በበጎ ተግባራት ላይ የት ይሆን ሲሳተፍ ተፈልጎ የሚገኘው?
ከአፍሪካ ወወክማና ከዓለም አቀፍ ወወክማ ጋር ትስስር በመፍጠር ወርሃዊ ቀለብና የትምህርት ቁሳቁስ ያገኙ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወላጅ አጥና አካል ጉዳተኛ ህፃናትና ወጣቶች ዛሬም ወርሃዊ ቀለብ ይሰጣቸዋልን?
በእኔ ግላዊ እምነት የዛሬው ወወክማ ተጨባጭ ሁኔታው አሳዛኝ ነው፤ አባላትን ማበራከት፣ በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ የቀድሞ ወወክማ ልጆችን አደራጅቶ ማሳተፍ፣ መዋጮ የመሰብሰብ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችንና መርሃ ግብሮችን የማዘጋጀት፣ የቅርንጫፍ ማህበራትን ቁጥር የማበራከት፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትን የማጎልበት ሥራውን በአግባቡ እየከወነ ይሆን?
በዘመነ ደርግ ከህግ ውጪ (“በቀላጤ”) የተወረሱ የወወክማን ተቋማትና ንብረቶችን የማስመለስ በ2001 ዓ.ም የተጀመረን ጥረት፣ የ2004ቱን ሙከራ ከድኖ በማስቀመጥ ስሙንና የከ70 ዓመት በላይ አዛውንትነቱን የሚመጥኑ ታላላቅና ትውልዳዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትን የመከወንና የመሳሰሉት ወወክማዊ የቤት ሥራዎች ለምን ተዘነጉ?
የወወክማ አሳፋሪና ለዓመታት የዘለቀ ውስጣዊ አለመግባባት
የወወክማን 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ከማክበር ጋር በተያያዘ በአሁኑ የማህበሩ አመራርና በቀደምት አባላቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዛሬም ድረስ መፍትሔ አላገኘም፡፡ በማይቀየረውና ከቶውንም በማይለወጠው የወወክማ የወንድማማችነት ጥልቅ እሴት ላይ ተመስርቶ፣ ነባሩን የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ጠብቆ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ማካሄድ፣ ግልጽ፣ ነፃና አግባብነት ባለው መልኩ የሥራ አመራር አባላትን መምረጥ እየተቻለ የለብ ለብ፣ ፍፁም ሕገ-ወጥ የሆነ፣ የአባላትን ተሳትፎ ያላማከለና የቅርንጫፍ ማህበራትን መብት የነጠቀ አሰራር መከተል የአለመግባባቱ መሠረታዊ ምክንያቶች ሆነው ዛሬም ቀጥለዋል፡፡
በወወክማ መሳተፍ መንፈስን ማስከን፣ ቀልብን ማረጋጋት የሚቸር ከመሆኑም በላይ በነባሩ የወወክማ እሴቶች ላይ በጋራ ቆሞ ማናቸውንም ልዩነቶችና አለመግባባቶች መፍታት እየተቻለ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግና መገናኛ ብዙኃን ደጃፍ ድረስ የረገጠ ውዝግብ ተፈጥሮ ማየት አያሳፍርምን? ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፣ አለመግባባትም ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በተቧደኑበት የሚጠበቅ ነው፣ ታዲያ ምነው ዛሬ ላይ የወወክማ ማህበርተኞች በነባሩ ወወክማዊ እሴቶች ላይ ቆመው መፍትሄን አምጦ መውለድና መግባባት ተሳናቸው?
ችግሩ ግልጽ ነው!
ዋነኛውና የመጀመሪያው ችግር የወወክማን መተዳደሪያ ደንብ በተደጋጋሚ በ“አሻሽለነዋል” ሰበባ ምክንያት እየሰረዙ በመደለዝ ለጥቂቶች ተሳትፎና ለተቀጣሪ ፀሐፊ ፈላጭ ቆራጭነት እንዲመች መደረጉ ነው፡፡ ወወክማ የብዙኃን ማህበር እንጂ በጥቂቶች ብቻ የሚዘመር NGO (መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት) አይደለም!! ማህበር ከበጎ አድራጎት ድርጅት ይለያል! ወወክማም ማህበር እንጂ በጎ አድራጎት ድርጅት አይደለም፡፡
ከርቀት እንደምሰማው /የአንዳንዶችንም ትዝብት እንደተረዳሁት/፤ የዛሬው ወወክማ በጥቂቶች የሚዘወር፣ አሳታፊነት የሌለበት፣ በሥራ አመራር ቦርድ ለተቀጠረ ፀሐፊ ያልተገባ ግለሰባዊ ኃላፊነት የሰጠ፣ እንኳንስ አዳዲስ ማህበርተኞች ሊቀበል በቤቱ ያደጉና የቀደምት አባላትና አመራሮችን የሚገፋ፣ ለውይይትና ምክክር ፍላጎት የሌለው፣ ደንብና አሰራሮችን የሚጥስ፣ ዘመድንና ወዳጅን እየመረጠ የሚያቀርብ መሆኑ ሳያንሰው “በደንባራ በቅሎ…” እንዲሉ አንዲት እንኳ ፍሬ የሚያሳይ ብሎም በዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘንድ የሚታወቅና የሚነገርለት ፕሮግራምም ሆነ ተግባር የሌለው አንጋፋ ግን ደግሞ ፈዛዛና ደቃቃ ማህበር ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡
እናም የወወክማ ልጆች!
ለወወክማ ዓላማዎች መቆም ካከታተመ፣ ከጀርባ የየራስ ድብቅ ፍላጎት ካለ፣ ከወወክማዊ እሴቶች ርቆ ወንበርንና ግለኛ ጥቅምን በማስጠበቅና በመንጠቅ ላይ ከተተኮረ ከ7 አስርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረን አዛውንት ማህበር ሞቱን ማፍጠን እንጂ ሌላ ረብ የለሽ ነገር አይፈይድምና፡-
ነባሩን ወወክማዊ እሴት ጠብቁ! የወወክማን መርሆዎች አክብሩና ልዩነቶቻችሁን አቻችሉ፣ ሰክናችሁ ተደማመጡና መፍትሔ አምጣችሁ ውለዱ!
“የያኔዎቹንና የትላንትናዎቹን የወወክላማ ልጆች ከያለንበት አሰባስበው፣ የተራራቅነውን አቀራርበው በቤታችን በጋራ እንድንታደም አድርገው ለማህበራችን የላቀ ጥንካሬ ያሳትፉናል!” ብለን ስንጠብቅ ውዝግባችሁን አካራችሁ አደባባይ በመውጣታችሁ በእጅጉ አዝነናል፡፡
ታሪክም፣ እኛም ሳናፍርባችሁ ወደ ቤተ-ወወክማ በመግባት በእሴቶቻችን ላይ በመቆም፣ የወወክማን የብዙኃን ማህበርነት አጥብቆ በመያዝ “ተግባብተናል! ኑ በጋራ ወወክማን እናጠንክር!” በማለት ትጠሩን ዘንድ ታናሻችሁ ጥልቅ መሻቴ ነው፡፡
ወወክማ የኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሁላችንም ነው!
ስለሆነም እኛ የዛሬዎቹን የሚመጥን ቁመና ይላበስ፣ የተቀዛቀዙና ከነአካቴው የተቋረጡ መርሃ ግብሮቹ ይጀመሩ፣ በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ወጣቶችን በአባልነት ይቀፍ! ቅርንጫፍ ማህበራቱ ከተወሸቁበት መንደር (ስርቻ) ይውጡ! በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ የያኔ የወወክማ ልጆች የሚሰባሰቡበት ስልት ተነድፎ ይተግበር! በተለይ ደግሞ ወወክማ እንደ ስሙ የእኛ የዛሬዎቹ ወጣቶች መሆኑን በፕሮግራሞቹ፣ በአሳታፊነቱና በአገልጋይነቱ ያረጋግጥ!!
(በነገራችን ላይ በዚሁ ሰሞን /ሰኔ መጨረሻ/ በምኖርበት አካባቢ “በወወክማ በክረምት በተዘጋጀ የስፖርት ስልጠና ወጣቶች 100 ብር በመክፈል ተሳታፊ ሁኑ፡፡” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ አይቼ ከልብ ማዘኔን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ በእኔ የወወክማ የተሳታፊነት ልምድ እንደ ኮሌጅ እያስከፈለ ስፖርታዊ ሥልጠና ሲሰጥ አይቼ አላውቅምና)
በድጋሚ! ወወክማ እሴቶቹን ይጠብቅ!!

Read 1646 times