Monday, 19 July 2021 00:00

ከከፋ ችግር ተጋፍጦ የመውጣት (RESILENCE) አንድምታ

Written by  አበበ
Rate this item
(4 votes)

   ማብቂያ የለሹ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት
                       
                     ኢትዮጵያ አገራችን በችግር አዙሪት ውስጥ የተዘፈቀች ይመስላል። ዋናው የችግሩ ምንጭ ከወያኔ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ምርጫውና የዓባይ ወንዝ ነገርም ዕረፍት የሚነሱ ጉዳዮች ሆነው ከርመዋል። ችግሩን ይበልጥ ያወሳሰበው  ደግሞ ማብቂያ የሌለው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው። በተለይ ደግሞ ከወያኔ ጋር በተያያዘ ጣልቃ ገብነቱ ሉአላዊነትን እስከ መዳፈር የመዝለቁ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በፓርላማ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው  ነበር፦ “,,,እትዮጵያ አትፈርሰም፣ አትሸነፍም፣ አትወድቅም። ያለፍንበት ፈተና ሁሉ የሚያሳየው (Resilient) ሕዝብና አገር መሆናችንን ነው።”
ከዚህ በመነሳት Resilient ማለት ምን ማለት እንደሆነና የተግባር መገለጫዎቹን በአጭሩ ከተመለከትን በኋላ፣ሃሳቡ በህግ ማስከበሩ ዘመቻ፣ በምርጫው ወቅትና በህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ላይ እንዴት በተግባር እንደዋለ እናያለን።
*Resilent፡- Bouncing back from hardship (ግርድፍ ትርጉሙ፡- “ከከፋ ችግር ተጋፍጦ መውጣት” ማለት ነው።)
የተግባር መገለጫዎቹም፦
አስቸጋሪውን እውነታ ከመካድና ከመሸሽ ይልቅ፣ ሁኔታውን መረዳትና አምኖ መቀበል፤ በችግሩ ከማዘንና ከመረበሽ፣ በውስጡ ትርጉም ያለው ነገር መፈለግና መፍትሄው ላይ ከማተኮር በተጨማሪ በዛሬ ችግራችን ታፍነንና ተደፍቀን እንዳንቀር፣ የዛሬን ችግር ለወደፊቱ እንደ መደላድል (ድልድይ) በሚያገለገል መልኩ ማየት፤ እና በመጨረሻም ችግሩን የተለየ ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለመቋቋም፣ በእጅ የሚገኝን ማንኛውንም ነገር (ሃብት) ሌሎች ከሚያስቡትና ከሚገምቱት ውጪ ባልተለመደ መልኩ ለተለየ አገልግሎትና ተግባር መጠቀም መቻል ማለት ነው።
ነገሩን በምሳሌ ለማቅረብ የአድዋ ጦርነትን ማየት ይቻላል፦
አውሮጳውያን አፍሪካን ለመቀራመት በወሰኑት መሠረት፣ ጣልያን ኢትዮጵያን የመውረሯ ነገር በፍጹም ሊቀየር የሚችል ሃሳብ አይደለም። ለኢትዮጵያውያን ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ከመረዳትና አምኖ ከመቀበል ዉጪ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። ስለዚህ ምን በደልናቸው? ምን አጥፍተን ነው? እያሉ የነሱን ምክንያት ለማወቅ ጊዜ ከማባከን ይልቅ፤ የከፋውን እውነታ በመቀበል፣ ከሆነ አይቀር እንግዲህ የመጣው ይምጣ በሚል መንፈስ መፍትሄው ላይ በማተኮር ጦርነቱን በቁርጠኝነት ለመዋጋት ከመዘጋጀት ውጪ ሌላ መንገድ አልነበረም። የተደረገውም ይኸው ነበር።
በመጨረሻም ስለ ጣሊያን ሥልጣኔ፣ ስለ መሳርያቸው ዘመናዊነት ወዘተ ከመጨነቅ፣ ”ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት”፣ እንደሚበልጥ ለዚህም በክብር ተዋግቶ ማለፍ “የጀግንነት መገለጫ” ሆኖ ቀረበ። ከሚታሰበውና ከተለመደው ውጪ በጣልያን በኩል የተፈጠረው አስቸጋሪውና የከፋው የጦርነት አደጋ፣ በኢትዮጵያውያን በኩል ለጦርነት የተለየ ትርጉም ተሰጠው። የአገር ክብርና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር የሚገለጽበት፡ የአገር ውለታ የሚከፈልበት ነገር ሆነ።
በዘመናት መካከልም እትዮጵያውያን ለነፃነታቸውና ለአንድነታቸው የፈሰሰ ደምና የተከሰከሰ አጥንት እንዳለ እንዲያውቁ አደረጋቸው። በተያያዘ ሁኔታ “የአልበገርም ባይነት” መንፈስን በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ አዳበሩት። እንደ አድዋ ሁሉ በማይጨው፣ በካራማራ፣ በባድመ ለአገር ሉአላዊነትና አንድነት ክብር ሲባል ብዙ ጀግኖች ተሰው። ኢትዮጵያውያን የከፋ ችግርን ተጋፍጦ ማለፍን (resilient) በጦርነት ውስጥ ተለማመዱት። በተለይ ለአገር መሞት ዛሬም ድረስ ክብር ሆኖ ዘለቀ። ስሜቱ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ/ት ደም ውስጥ ታተመ። ለዚህም ነው ህዝቡ “ክተት ሠራዊት” ሲባል ሆ! ብሎ የሚነሳው። ይህንን መንፈስ ለመረዳት የግድ ኢትዮጵያዊ መሆንን ይጠይቃል። ለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን ከከፋ አደጋ ውስጥ የምንወጣው።
በርግጥ “የባንዳነት መንፈስ” ቀድሞም ነበር። አሁንም አለ። መገለጫዎቹም የጁንታው ቡድን አባላት ዓይነት ሰዎች ናቸው። ወያኔ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ የዘረኝነት አስተሳሰብን በመዝራት ሊያጠፋው የሞከረው ይህንን የቆራጥነት፣ የነፃነትንና የአንድነትን መንፈስ ነው። ወያኔ ለውጪ ኃይሎች የማጎብደድ ባህሪ ያዳበረው የባንዳነት ሥሪት በመሪዎቹ ውስጥ ስለነበረ ነው።
የሠራዊቱ ችግርን ተጋፍጦ የመውጣት ገድል
መከላክያ ሠራዊቱ በወያኔ ደርሶበት ከነበረው “ድንገተኛ መብረቃዊ ጥቃት” ተብሎ ከተሰየመ አስደንጋጭና አሰቃቂ በተንኮል የተሞላ ጥቃት ያገገመበትና ወደ መልሶ ማጥቃት የተሸጋገረበት ፍጥነት፤ ሠራዊቱ ከከፋ ችግር ተጋፍጦ የመውጣት  (Resilient) ባህሪ ያዳበረ መሆኑን ያሳያል።
የመከላከያ ሠራዊቱ በሶስት ሳምንታት ውስጥ የወያኔን አከርካሪ ሙሉ ለሙሉ የሰባበረው ሲሆን፣ በውጤቱም የወያኔ ዋና ዋና መሪዎች ተገድለውና ወያኔም ጥቃቱን መቋቋም ተስኖት የሽምቅ ውጊያ ለማድረግ ወደ በረሃ እንዲወርድ አስገድዶታል፡፡ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የውጭ ሚዲያዎች፣ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ በውጭ የሚኖሩ የወያኔ ደጋፊዎች ጩኸት እጅግ የበረታ ነበር። ከሁሉም ግን የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ሚዛኑን እየሳተ የመጣበት ወቅት ነበር። ወያኔም የውጊያ ስልቱን በመቀየር ተዋጊዎቹን ሕዝቡ ውስጥ ማስረግና ሕዝቡንም በማስገደድ ሠራዊቱን መፈታተኑን ተያያዘው።
ሁኔታውን በጥሞና ሲከታተል የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በድንገት አንድ ውሳኔ አሳለፈ። ሁኔታው ድንገተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጆሮ ጭው የሚያደርግ፣ በድንጋጤ ዓይን የሚያስጎለጉልና እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ውሳኔ ነበር። ውሳኔውም “ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የተናጥል የተኩስ አቁም አድርጌአለሁ” የሚል ነበር።
ውሳኔው የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአስደነገጠው በላይ ለምዕራባውያን ድንገተኛ ነገር ነበር። “ተደራደሩ አልን እንጂ ተኩስ አቁማችሁ ውጡ አላልንም” ማለት ጀመሩ። ግን ለምን? የምዕራባውያኑና የወያኔ ዕቅድ ሠራዊቱንና መንግሥትን የጦርነት አዙሪት ውስጥ በማስገባት በተራዘመ ጦርነት ማሰላቸትና የአገርን ኢኮኖሚ በማዳከም ጫና ለመፍጠር ነበር።
የመንግሥት ውሳኔ ለሕዝቡ፣ ለምዕራባውያንና ለወያኔ አስደንጋጭ የሆነበት ምክንያት፤ መንግሥት Resilient ባህሪ በመላበሱ ነው። ይህም ማለት አስቸጋሪውን እውነታ ከመካድ ይልቅ ሁኔታውን በመረዳትና አምኖ በመቀበል፤ እኛም (ሕዝቡ) ሆንን ምዕራባውያን ፍጹም ያልጠበቅነውን ውሳኔ በመወሰን ችግርን እየተጋፈጡ ማለፍ የሚለውን (resilient) መንገድ በተግባር አከናወነ።
የምርጫው ነገር
መጀመርያ ላይ ህዝቡ ለምርጫው ብዙም ትኩረት አልሰጠውም ነበር። ምርጫውን ተከትሎ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ግን ዙርያ ገባውን አርብቦ ነበር። የአብዛኛው ሰው ትኩረት የምርጫ ቦርድ ነፃነት እስከ ምን ይዘልቃል የሚል ነበር። የመራጮች ምዝገባ ቁጥርም በጣም አነስተኛ ነበር። ሁኔታዎች ግን በፍጥነት ተቀያየሩ። የሆነው እንዲህ ነበር። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ (election) ብቻ ሳይሆን ሕዝበ ውሳኔም (referendum) ጭምር ነበር። ይህንን ለመገንዘብ እንዲረዳን የምርጫንና የህዝበ ውሳኔን ትርጉም በአጭሩ እንመልከት።
ምርጫ፤ ሕዝቡ ግለሰብ ዕጩዎችን (ተወካዮችን) ወይም ፓርቲዎችን ለፖለቲካ አመራርና ለሕዝብ ቢሮዎች አስተዳዳሪነት ድምጽ በመስጠት የሚመርጥበት መንገድ ነው። ሕዝበ ውሳኔ (referendum) ማለት ደግሞ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ጥያቄዎች/ጉዳዮች ተለይተው ከቀረቡ በኋላ በቀረበው ነገር ላይ ሕዝቡ ድምጹን በመስጠት የሚወስንበት መንገድ ነው።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ (election) ሲሆን፤ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት፣ የአንዳንድ ተቃዋሚዎች ሁኔታና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች የተራገቡ ወሬዎች ምርጫው የሁከት መነሻ እንደሚሆን ከመላ ምት ያለፈ ግምት እንዲፈጠር የተመቻቸ መደላድል ፈጠሩ። ይህ የሕዝቡን ሥነ ልቡናዊ ውቅር ያላገናዘበና የሕዝቡን አገር በቀል ዕውቀት የዘነጋ ወሬ ባልተጠበቀ ፍጥነት ምርጫውንና ሕዝበ ውሳኔን መሳ ለመሳ አመጣቸው።
ይህንን ሁኔታ ከምርጫው ሂደት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ምርጫው ሊከናወን ጥቂት ቀናት እስኪቀሩት ድረስ የተመዘገበው የመራጭ ቁጥር አጥጋቢ አልነበረም። የተመዘገበውም ቢሆን በዕለቱ ተገኝቶ የመምረጥ ፍላጎቱ እምብዛም ነበር። በውጭ ኃይሎችና ሚዲያዎቻቸው፣ በአንዳንድ ተቃዋሚዎችና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች ይቀርቡ የነበሩ “ትንተናዎች” የተቀነባበረ ዘመቻ በሚመስል መልኩ ምርጫው ሠላምና መረጋጋትን በማወክ የአገሪቱን አንድነት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ በርግጠኝነት ይናገሩ ነበር። ሳይታወቃቸው ግን ሕዝቡን ወደ ምርጫ እየሳቡት ነበር። ሕዝቡ ሁኔታውን በአርምሞ ይከታተል ነበር። ቀስ በቀስ አንድ ነገር እያስተዋለ መጣ። ማንም ሳያስተምረውና ሳይነግረው የሚያውቀው አገር በቀል የሆነ ዕውቀትና ልምድ  አለው። የውጭ ሰዎች “ግልጽና በቅርብ የሚታይ አደጋ” (clear and present danger) የሚሉት ዓይነት ነገር እንዳለ ተገነዘበ።
በተደጋጋሚ እንደታየው አብዛኛው ሕዝብ የአገሩን ጉዳይ በተመለከተ ሳይነጋገር የሚግባባበት፣ ሳይሰበሰብ የሚስማማበት፣ በመንፈስ አንድ የሚሆንበት ምስጢራዊ ነገር አለው። አንድን አገራዊ ጉዳይ በተለይ ከአንድነትና ከሰላም ጋር የተያያዘ ከሆነ፣ በመጀመርያ ለብቻው ያሰላስለዋል፣ በመቀጠልም በቤተሰብ፣ በጓደኛሞች፣ በቅርብ ሰዎች፣ በአካባቢ እየቀጠለም በመንደርና በማኅበረሰቡ ደረጃ እንደ ዘበት በሚመስል መልኩ ነገሩን እያነሳሱ ይነጋገሩበታል፤ ያወጉታል፤ ይጫወቱታል፤ ይተክዙበታል። ከአልጋቸው (ከቁርበታቸው) ጋር ይመክሩበታል። በመጨረሻም በድንገት ሆ! ብለው ይነሳሉ። በአድዋ፣ በማይጨው፣ በካራማራ፣ በባድመ፣ የሆነው ይኸው ነበር። አሁንም በምርጫው ጊዜ በአዲስ አበባ የታየው ተመሳሳይ ነገር ነበር። ለመመዝገብ ዳተኛ የነበረ ሰው ሁሉ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት ግር ብሎ ተነሳ። ቀኑ ተራዘመ። ይህም አልበቃ ብሎ እንደገና ተራዘመ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ያልተመዘገቡ ተጸጸቱ። የነበራቸው አማራጭ የተመዘገቡ የቅርብ ሰዎቻቸው የምርጫው ቀን እንዳይቀሩ ዋና ጎትጓች መሆን ብቻ ነበር።
ረብሻ ይነሳበታል የተባለለት የምርጫ ቀን፣ ለሕዝቡ አልነጋልህ አለው። ከምርጫ ታዛቢዎችና ምርጫ አስፈጻሚዎች ቀድሞ በምርጫው ሥፍራ ተገኘ። ራሱ ሥነ ሥርዓት አስከባሪ ሆነ.። በሁኔታው የሕዝቡ ሥነ ልቡናዊ አሠራር ያልገባቸው ግራ ተጋቡ። ሕዝቡ ግን ምርጫውንም፣ ሕዝበ ውሳኔውንም አንድ ላይ ለማከናወን ነበር በነቂስ የወጣው። እስከ እኩለ ሌሊት ድምጽ ሲሰጥ የነበረው። ሕዝቡ የተለዩ ሁኔታዎችንና አጋጣሚዎችን መጠቀም የሚያውቅ፣ የዳበረ ማኅበራዊ ዕሴት ያለው መሆኑን በተግባር አረጋገጠ፡፡ በርግጥ የሰላምና የአንድነት ጉዳይ በዕለቱ ከተደረገው ፖለቲካዊ  ምርጫ (election) ጋር አብሮ ለሪፈረንደም አልቀረበም። ህዝቡ ግን አጋጣሚውን ተጠቀመበት።
በምርጫው ዕለት ፓርቲዎችንና ግለሰቦችን በምርጫው ህግ መሠረት መርጧል። እግረ መንገዱንም አንድነቱንና ሠላሙን ለማስከበር ቁርጠኛ መሆኑን በሕዝበ ውሳኔ (referendum) መልክ አሳይቷል። በርግጥ በሌላ አገላለጽ በፖለቲካው ምርጫ የሚያሸንፈው ፓርቲ የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ክቀረቡት ተወዳዳሪዎች የተሻለ ተመራጭ ሆኖ በሕዝበ ውሳኔ ተመርጧል እንደ ማለት ነው።
ሕዝቡ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የታየውን የሰላም መደፍረስ አደጋ ያስተናገደበት መንገድ ማለትም ፈጥኖ ሁኔታውን መረዳቱ፣ ችግር ሊፈጠር ይችላል ብሎ ከመረበሽ ይልቅ መፍትሄው ላይ ማተኮሩና ምርጫውን ባልተገመተ ሁኔታ ለሕዝበ ውሳኔ መጠቀሙ የከፋ አደጋን የማስወገድ ባህሪ (resilience) እንዳለው ያሳያል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ
የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በራስ አቅም (በሕዝብ ገንዘብና ድጋፍ) በመከናወን ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው። የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት እንደምታ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች የአፍሪቃ አገራት በተምሳሌትነት የሚቀርብ ነው። በራስ አቅም የተወሰነ ርቀት መጓዝ እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ሃሳብ ይዟል።
አፍሪቃውያን የሰው ኃይላቸውን፣ የተፈጥሮ ሃብታቸውን በተለይ መሬትና ውሃቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ከተጠቀሙ፤ ከምዕራቡም ሆነ ከምሥራቁ ዓለም የኢኮኖሚ ጥገኝነት ፈጥነው መውጣት ይችላሉ። የህዳሴ ግድብም የዚህ ጥረት ተግባራዊ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ፕሮጀክቱ “ተራ/መደበኛ ፕሮጀክት” ሳይሆን የነገውን የአፍሪቃ ተስፋ የመጠቆም አቅም ያለው ፕሮጀክት ነው።
ዓባይ ኢትዮጵያን በአንድ ወገን፣ ግብጽና ሱዳንን በሌላ ወገን አሰልፎ የሚያወዛግብ ወንዝ ነው። ኢትዮጵያ ለራሷም ሆነ ለሌሎች አፍሪቃውያን ታላቅ ተስፋን ሰንቃ፣ “የአፍሪቃውያንን ችግር በአፍሪቃውያን” የሚለውን መፈክር አስቀድማ “አለመግባባቱን” ለመፍታት ስትሞክር፤ ግብጽና ሱዳን ሁሉም ነገር ቀድሞ እንደነበረው ሊቀጥል ይገባል በሚል መንፈስ ላይ ታች ማለቱን መርጠዋል። አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ፣ አሁን ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ይዳኙን እያሉ ነው።
ግብጽ ወያኔን እንደ መሳርያ በመጠቀም ውስጣዊ አለመረጋጋት በመፍጠር ፕሮጀክቱን ለማዘግየት የሞከረችበት መንገድ ለራሱ ለወያኔ መጥፊያው ሆኖ አረፈ። ሱዳንና ግብጽ በየአገራቸው የሚቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማስታገስ የዓባይን ግርግርና ድርድር ይፈልጉታል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የህዝብ ድጋፍ መሠረቷ፣ ለአፍሪቃውያን የጋራ ተጠቃሚነትን  የምታሳይበት  ተምሳሌታዊ ፕሮጀክት አድርጋ ታየዋለች።
ኢትዮጵያ እንደ አገር ከህዳሴ ግድብ ያገኘችው ዋና ቁም ነገር፣ ህዝብና መንግሥት በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው አብረው እየወደቁ መነሳት እንደሚችሉ፣ አብረው ጎን ለጎን በጽናት መቆምን ወዘተ ሲሆን አብረውም ከከፋ ችግር ውስጥ ተጋፍጦ መውጣትን (resilience)፣እየተማሩ የሚገኙበት ፕሮጀክት መሆኑ ነው።
ማለቂያ ያጣው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ በማሳየት ላይ የሚገኙት ጣልቃ ገብነት በየትኛውም ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ለምን ለሚለው ጥያቄ ከኛ ይልቅ መልሱ ራሳቸው ጋር ይገኛል። በተለይ የአሜሪካ መንግሥት በአገራችን ላይ እያሳየች ያለው አቋም በጣም ግር የሚያሰኝ ነው። ሁሉንም መዘርዘር “የአዋጁን በጆሮ” ይሆናል። ጣልቃ ገብነታቸው አጠር ባለ መልክ ሲገለጥ “,,,የአገራችንን ሉአላዊነት የደፈሩበት መጠን፣ ሕዝቡን፣ መከላከያ ሠራዊቱንና መንግሥትን የናቁበት ልክ፤ ጉዳዩ ለህዝበ ውሳኔ ቢቀርብ ሕዝቡ በአንድ ድምጽ “አሁንስ በዛ” የሚል ድምጽ የሚሰጥበት ጉዳይ ይሆን ነበር።
ማጠቃለያ
የጽሁፉ ዋና መልዕክት የሆነው ችግርን ተጋፍጦ መውጣት (Resilient) ቃል/ሃሳብ ከላይ ከቀረበበት አውድ ውጪ በተለያየ ሁኔታ ሊቀርብ ይችላል። ለምሳሌ ጃፓኖች ተደጋግሞ ከሚያጋጥማቸው የመሬት መንቀጥቀጥ ችግር ጋር በተገናኘ ምክንያት ችግርን ተጋፍጦ የመቆም (resilient) ባህሪ አዳብረዋል። ቻይናዎች በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ተጋፍጦ የመቋቋም ባህሪ አላቸው።
ኢትዮጵያውያንም በነፃነታቸውና በክብራቸው ለሚመጣ ነገር፣ ተጋፍጦ የመቆም መንፈስ ያሳያሉ። ወያኔ ባለፉት 27 ዓመታት የዘረኝነት አስተሳሰብ በመዝራት ሊያጠፋ የሞከረው ይህንን ለነፃነትና ለክብር የመቆምን መንፈስ ነበር። የወያኔ መሪዎች ለውጭ ኃይሎች የማጎብደድ መንፈስ ያዳበሩበት ዋና ምክንያት፣ የባንዳነት ሥሪት በመሪዎቻቸው ባህሪ ውስጥ ስለነበረ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በጽኑ ልትጋፈጣቸው ከሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ የዘረኝነት አስተሳሰብና ድህነት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
የውጭ ኃይሎች/ምዕራባውያን የግል ጥቅማቸው ላይ በማተኮር የሌላውን አገርና ሰው መብትና ክብር የመጣስ አዝማሚያ ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት የተጋፋጭነት ባህሪ ካላቸው ሰዎችና አገሮች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ይገባሉ። አሁን በአገራችን በግልጽ የሚታየው ይህ ነው። ምን ይደረግ? ለሚለው ጉዳዩን በተለያየ መንገድ ለህዝበ ውሳኔ ማቅረብ ነው።
መከላክያ ሠራዊታችን በህግ ማስከበሩ ዘመቻ የመጀመርያው “መብረቃዊ ጥቃት” የተሰነዘረበት ጊዜ፣መንግሥት የአንድ ወገን ተኩስ አቁም የወሰነበት ሁኔታ፣ ሕዝቡም ምርጫውን እንደ ሕዝበ ውሳኔ ጭምር የተጠቀመበት መንገድ፤ ከችግር ተጋፍጦ የመውጣት መንፈስ (resilience) የተንጸባረቀባቸው አጋጣሚዎች ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ።
ማጠቃለያው ሲጠቃለልና ከችግር ተጋፍጦ የመውጣት ምስጢር (resilience) ተጨምቆ ሲቀርብ፦ እውነታውን መረዳትና መቀበል፣ ዛሬንና ወደፊትን ያስተሳሰረ መፍትሄ ላይ ማተኮርና ሌሎች ከሚያስቡትና ከሚገምቱት ውጪ ሃብትን (ረሶርስን) መጠቀም ናቸው።




Read 3485 times