Saturday, 17 July 2021 15:31

የመሻገር ሲቃ

Written by  ደራሲ- ኢቫን ካንኪር (ዩጎዝላቪያ) ተርጓሚ- ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(4 votes)

   በእያንዳንዱ ምሽት ታዳጊዎቹ ወደ መኝታቸው ከመሄዳቸው በፊት ሰብሰብ ብለው ማውጋት ይወዳሉ፡፡ በሰፊው ምድጃ አጠገብ ተቀምጠው ወደ አዕምሮአቸው የመጣውን ነገር ሁሉ ያንሾካሹካሉ። በደብዛዛው መስኮት በኩል ወደ ክፍሉ የሚያጮልቁትን የምሽት ፍዝ አንጸባራቂ ብርሃናት ህልም በተሞሉ ዓይኖቻቸው ይመለከታሉ፡፡ በእያንዳንዷ ጥጋጥግ የፀጥታ ጥላዎች ግር የሚሉ እንግዳ ተረቶችን ተሸክመው ይገዝፋሉ፡፡
ወደ አዕምሮአቸው የመጣውን ነገር ሁሉ ቢናገሩም ቅሉ ወደ አዕምሮአቸው የሚመጡት የጸሐይ ብርሃንና ግለት (የስሜት) ከፍቅርና ተስፋ ጋር የተጠላለፉባቸው ታሪኮች ናቸው፡፡ ለእነሱ የሚቀጥለው ጊዜ በሙሉ አንድ ረጅም የደመቀ ክብረ በዓል ነው፡፡  በገና እና በፋሲካ በዓል መካከል እንኳን የሁዳዴ ጾም የለም፡፡ እዚያ የሆነ ቦታ በአበቦች ካሸበረቀው መጋረጃ ጀርባ የምልዓተ ሕይወት እርግብግቢት፣ ትርታ ሁሉ በጸጥታ ከብርሃን ወደ ብርሃን ይንቆረቆራል፡፡
ቃላት በለሆሳስ ይነገራሉ፤ በከፊል ብቻ ግንዛቤ መረዳት ይወሰድባቸዋል። የትኛውም ተረት መነሻም ሆነ ቅርጽ፣ የትኛውም ተረት መቋጫ የለውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ ጊዜ አራቱም ልጆች ያወራሉ። ሆኖም ማንኛቸውም አይደናገሩም፡፡ ሁሉም ዓይኖቻቸውን ትኩር አድርገውና ተመስጠው የእያንዳንዱን ቃል ግልጽና እውነተኛ መሆን፣ የእያንዳንዱ ተረት ጉልህና ሕይወታዊ መልክ፣ የእያንዳንዱ ተረት ሞገስ ያለው አጨራረስ በብሩህና በጣም አስደሳች በሆነው ጸዳል በኩል መንፈሳቸውን ሰብስበው  ይመለከታሉ፡፡
የምሽቱ የሰከረ ድንግዝግዝ ብርሃን መልካቸውን ከማመሳሰሉ የተነሳ የአራት ዓመቱን ታዳጊ ቶንቼክ ከታላቋና አስር ዓመቷ ሎይዝካ መለየት አይቻልም፡፡ ሁሉም ቀጭን ጠባብ ፊቶችና ትላልቅ የተበለጠጡ ወደ ውስጥ የሚመለከቱ ዓይኖች አሏቸው፡፡
በዚያ ምሽት ግን የሆነ ያልታወቀ ነገር ካልታወቀ ቦታ ከሀይለኛና ቁጡ እጆቹ ጋር ወደ ብሩህና አስደሳቹ ብርሃን ገብቶ በተረቶች፣ በበዓላትና በአፈ ታሪኮች መካከል ጨካኝ ሆኖ ታየ፡፡ ደብዳቤው (ፖስታው) አባትዬው በኢጣሊያ አፈር ላይ መውደቁን የሚገልጽ ዜና አስከትሎ መጣ። የሆነ የማይታወቅ፣ አዲስ፣ እንግዳ የሆነ፣ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሚያስቸግር ነገር ገጠማቸው፡፡ እዚያው ቆሟል፤ ረጅም ሰፊ ቢሆንም፣ ነገር ግን ዓይን፣ ፊትም ሆነ አፍ የለውም፡፡ ሁኔታው ከምንም የማይመሳሰል፣ ጩኸት ከበዛበት ሕይወትም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከመንገድ ላይ፣ ከምድጃው ወጋገንም ሆነ ከተረቶቹ የማይገጥም ነገር ነበር፡፡  
ምንም የማያስደስት በተለየ ሁኔታ የማያሳዝን ሙት ነገር ይመስላል፡፡ ምንም ዓይኖች ስለሌሉት ከየት እና መቼ እንደመጣ ሊያብራራ የሚችል አንደበት የለም፡፡ ልክ ከግዙፍ ግንብ ፊት እንደቆሙ ሁሉ ከዚያ አንድስ የሚያህል ጣዕረ ሞት እንግዳ ሁነት ፊት ትሁትና አይናፋር መስለው ያለ ንቅናቄ ቆሙ፡፡
‹‹ግን መቼ ነው የሚመለሰው?›› አለ ቶንቸክ በመገረም፡፡
ሎይዝካ ጎንተል አድርጋውና በቁጣ ስሜት ተመልክታው፤
‹‹ከወደቀ እንዴት ተመልሶ ሊመጣ ይችላል?›› አለችው፡፡
ሁሉንም ዝምታ ዋጣቸው፡፡ እዚያ ግዙፍ ጥቁር ግንብ ፊት ቆሙ፡፡ ከግዙፉ ነገር ባሻገር ምንም ማየት አልቻሉም፡፡
‹‹እኔም ወደ ጦርነት እሄዳለሁ›› ሳይጠበቅ የሰባት ዓመቱ ማቲቼ አሳወቀ፡፡ ሁኔታው ልክ ትክክለኛውን ሀሳብ እንዳገኘ ሰው ነበር።
‹‹በጣም ትንሽ እኮ ነህ!›› የአራት አመቱ ቶንቼክ ገሰጸው፡፡  
ደቃቃዋና ህመምተኛዋ ሚልካ በእናቷ ግዙፍ የአንገት ልብስ ተውጣና የመንገደኛ ሻንጣ መስላ ከሆነ የጨለማው ጥግ በዚያ ስስ ቀጭን ድምፅዋ፤
‹‹ጦርነት ግን ምን ይመስላል? ማቲቼ ንገረን? ታሪኩን ንገረን?››
ማቲቼ አብራራ፡፡
‹‹ደህና፣ ጦርነት ማለት እንዲህ ነው። ሰዎች በጩቤ ይወጋጋሉ፤ በሰይፍ ይሞሻለቃሉ፤ በጠመንጃ ይገዳደላሉ። የበለጠ ሰው መውጋትሽ፣ መቆራረጥሽ ስኬት ነው፡፡ ይህን ስላደረግሽ ማንም ምንም አይልሽም፡፡ ምክንያቱም የሚደረገው እንዲያ ነው፡፡ ጦርነት ማለት ይሄ ነው፡፡››
‹‹ግን ለምንድን ነው እርስ በእርስ የሚቆራረጡት የሚሞሸላለቁት?›› ሚልካ ነበረች፡፡
‹‹ለንጉሱ ነዋ!›› አለ ማቲቼ… ሁሉም በዝምታ ተሸበቡ፡፡     
በደብዛዛው ርቀት በፈዘዙ ዓይኖቻቸው ስር የሆነ ግርማ ያለው አንፀባራቂ ነገር ድንገት ብልጭ አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቡራኬ ላይ እንዳሉ ሁሉ ትንፋሻቸው እንዳይሰማ ሆነው ደንዝዘው ተቀመጡ፡፡ የተጫናቸውን ከባድ ዝምታ ለመስበር በሚመስል ሁነት ማቲቼ በፍጥነት ሀሳቡን ሰብስቦ፤
‹‹እኔም ወደ ጦርነት እሄዳለሁ፡፡ ጠላቶቼን እፋለማቸዋለሁ፡፡›› አለ፡፡
‹‹ጠላት ግን ምን ይመስላል? ቀንድ አለው እንዴ?›› ድንገት ሚልካ በቀጭን ድምፅዋ ጠየቀች፡፡
‹‹አለው! አለው እንጂ ከሌለውማ ምኑን ጠላት ሆነ፡፡›› የተበሳጨ በሚመስል ጉልህ በሆነ ድምጽ ቶንቼክ መለሰላት፡፡ ሆኖም ማቲቼ ራሱ ትክክለኛውን መልስ አላወቀውም፡፡
‹‹ቀንዶች… ያለው አይመስለኝም፡፡›› በሚርበተበትና ዝግ ባለ በሚቆራረጥ ድምጽ መለሰ፡፡
‹‹እንዴት ቀንድ ሊኖረው ይችላል፡፡ ጠላት እኮ እንደኛው ሰው ነው፡፡›› ሎይዝካ ባለመቀበል ድምጽዋን አሰማች፡፡ መልሳ አሰብ አድርጋ ሌላ ሀሳብ ጨመረች፤
‹‹ብቻ ነፍስ የለውም!››
ረዘም ካለ ዝምታ በኋላ ቶንቼክ ጥያቄ አቀረበ፤
‹‹ግን ሰዎች በጦርነት ላይ እንዴት ነው የሚወድቁት? ልክ እንደዚህ ወደ ኋላ?›› አወዳደቁን አሳየ፡፡
‹‹ይገድሉታል!›› ማቲቼ አብራራ፡፡
‹‹አባቴ ጠብመንጃ ሊያመጣልኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡››
‹‹ከወደቀ እንዴት ጠብመንጃ ሊያመጣልህ ይችላል?›› ሎይዝካ ለዘብ ባለ ቁጣ መልስ ሰጠችው፡፡
‹‹እና እንዲሞት አድርገው- ገደሉት?››
‹‹ገደሉት!››
የማይታመን ዝምታና ሀዘን በሰፊው በተበለጠጡ የታዳጊ ዓይኖቻቸው በኩል ወደ ጨለማው፣ ወደ ሆነ የማይታወቅ ነገር፣ ወደ ልብ፣ ወደ አዕምሮ አፈጠጠ፡፡  
በተመሳሳይ ሰዓት ከጎጆው በር ውጭ አግዳሚ ወንበር ላይ ወንድና ሴት አያቶቻቸው ቁጭ ብለው ነበር፡፡ የመጨረሻዎቹ የምሽት ደማቅ ቀይ ጸዳል የተላበሱ የፀሐይ ጨረሮች ጨለምለም ባለው የግቢው መናፈሻ ቅጠላቅጠሎች ላይ አብረቅራቂ ጨረሮቻቸውን ፈንጥቀዋል፡፡ ከፈረስ ጋጣው በኩል ከሚሰማው መጎርነን የጀመረ፣ ጉርምርምታ የሚመስል፣ የተራዘመ፣ የታፈነ የመንሰቅሰቅ ልቅሶ በስተቀር ምሽቱ ፀጥ ያለ ነበር፡፡ ይሄው ልቅሶ እንስሳቱን ለመንከባከብ በሚል ወደ ጋጣው የሄደችው የልጅ እግሯ እናት የሀዘን እንጉርጉሮ መሆኑ የሚጠረጠር አይደለም፡፡ ሁለቱ እድሜ የተጫናቸው ሰዎች ልክ ከዚህ በፊት ለዓመታት፣ ለረጅም ዘመናት አድርገውት የማያውቁ ይመስል አንዱ የሌላውን እጅ አጥብቆ ይዞ ጭብጥ፣ ኩርምትና ጥግትግት ብለው፣ ምንም ሳይናገሩ እንባ በሌላቸው በተራቆቱ ዓይኖች ደንገዝገዝ ያለው ወገግታ ላይ አፍጥጠው ተቀመጡ፡፡     


Read 1653 times