Saturday, 17 July 2021 15:37

“የዓለም ህዝቦች ለመዳን ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ጀርመናዊው ኡዌ (ባንተን) ሸፈር፤ ድምፃዊ፤ ጊታር ተጫዋችና የሩት ሮክ ሬጌ ሙዚቃ አርቲስት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ማይክ የጨበጠው በ19 ዓመቱ ሲሆን “ባንተን” የሚለውን ቅፅል ስም ያወጡለት የሙያ ባልደረቦቹ የጃማይካ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ በስነግጥም የተካነ የሙዚቃ አጫዋች ወይም ዲጄ መሆኑን በማድነቅ ነው ቅፅል ስሙን የሰጡት፡፡ ኡዌ "FREE YOUR MIND" በሚል ስያሜ አዲስ  አልበሙን  ከወር በፊት ለዓለም ገበያ አቅርቧል፡፡ ሙዚቃዎቹ የተሰሩት ሶስቱን አህጉራት አፍሪካ፤ አሜሪካና አውሮፓን በማካለል ሲሆን በተለይ ኮስታሪካ፤ ኢትዮጵያ፤ ጀርመን፤ ጃማይካና ደቡብ አፍሪካ ላይ ቀረፃዎች ተከናውነዋል፡፡ ከሰላሳ በላይ ሙዚቀኞችና ከስምንት የተለያዩ አገራት ተሳትፈውበታል፡፡ በጀርመንና በአውሮፓ ስሙ የናኘው የሬጌ አሳታሚ ጋንጃማን የአልበሙን ሚክሲንግና ማስተሪንግ የሰራው ሲሆን በዲጂታል የሙዚቃ አውታሮችና በሲዲ አሳትሞ ለዓለም ገበያ ያቀረበው ደግሞ ራስታ ያርድ ሬከርድስ ነው፡፡
‹‹ፍሪ ዩር ማይንድ›› ለኡዌ አራተኛ የሙዚቃ አልበሙ ሲሆን የመጨረሻ አልበሙን “ሜንታል ዋር” ካሳተመ ከ9 ዓመታት በኋላ ለገበያ የቀረበ ነው፡፡ ዘፈኖቹ በእንግሊዘኛ፤ በጀርመንኛ፤ በፓቶዋ እና በአማርኛ ዜማዎች መቀንቀናቸው አልበሙን ልዩ ያደርገዋል፡፡ አብረውት የሰሩት ድምፃውያን የበርሊኑ ጋንጃማን፤ የኢትዮጵያው ራስ ጃኒ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው አፍሪካ ሴሌ ናቸው፡፡
አርቲስቱ በመላው አውሮፓ በተለይ ጀርመን ውስጥ በሬጌ ሙዚቃ ስሙ የገነነ ሲሆን በካሬቢያን ቅኝት የተሟሹት ዜማዎቹ፤ ጥልቅ እሳቤ ያላቸው ስንኞቹና ምርጥ የሙዚቃ ቅንብሮቹ ተወዳጅነትን አትርፈውለታል፡፡ በአዲስ አልበሙ “ፍሪ ዩር ማይንድ” ላይ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት (Ark of the covenant) በሚል ርእስ ሁለት ሙዚቃዎችን በሬጌ እና ደብ  ስልቶች፣ ከታዋቂው የኢትዮጵያ ሬጌ ሙዚቀኛ ራስ ዮሃንስ (ራስ ጃኒ) ጋር በመጣመር ሰርቷቸዋል፡፡ ኡዌ ባንተን ከሚኖርበት የጀርመን ከተማ ቢሌፌልድ ከግሩም ሠይፉ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


                  ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን መጎብኘትህ በቅርቡ ላሳተምከው አዲስ አልበም አስተዋጽኦ አድርጓል?
አዎም አይደለምም፡፡ አዎ፤ ምክንያቱም ለእኔ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ መምጣቴ ነበር፡፡ ጉብኝቱ ለእኔ በጣም ትልቅ ትርጉም ያለውና የመጀመርያውን ተሞክሮ ያገኘሁበት ነበር፡፡ ጉዞው የረዥም ጊዜ ምኞቴና እቅዴ ስለነበር ጉዞውን እንዳሳካ  የባረከኝን ልዑል እግዚአብሔርን  አመሰግነዋለሁ፡፡  እምነቴን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል።
አይደለም ስል ደግሞ ዋናው ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ ያለኝን አመለካከትና ትርጉም ጉብኝቱ አልቀየረውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ሁሉንም ነገር ለብዙ ዓመታት ስማረውና ሳጠናው ነው የኖርኩት። የሆነ ሆኖ፣ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የራስታ ማህበረሰቦችን በአካል ለመገናኘት መቻሌን እንደ በረከት እቆጥረዋለሁ፡፡ ከሁሉም  ጋር በግንባር መወያየትና መማማር መቻሌ ፍፁም አስደሳች ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ የኢትዮጵያ ጉብኝቴ በእምነት እንድጠነክር አድርጎኛል፡፡ እናም የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ በቅርቡ እንደገና እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት የሰራኸው ሙዚቃና የፃፍካቸው ግጥሞች እጅግ አስደማሚ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ሀሳቡ ከየት ነው የመነጨው? ለዓለምስ ምንድነው ፋይዳው?
የቃል ኪዳኑ ታቦት ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካነበብኩበት ጊዜ አንስቶ በአእምሮዬና በተመስጦዬ ውስጥ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት “ክብረ ነገስት” የተሰኘውን መፅሐፍ የጀርመንኛ ትርጉም ማንበቤም ሌላው ምክንያት ነው። በክብረ ነገስት ላይ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደመጣ ያነበብኩት ታሪክ ሁሌም ያስደንቀኛል፡፡ ምንም እንኳን ለኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ታሪክና ባህል ማዕከላዊ ሚና ቢጫወትም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለአብዛኛው የአለም ክፍል ምስጢር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን የምንኖረው በአንድ ወቅት ተሰውሮ የነበረው ነገር ሁሉ ወደ ብርሃን በሚወጣበት ዘመን ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዓለም ዙሪያ ያለውን ግንኙነት የሚያፋጥንባቸውን መንገዶች ፈጥሯል። ይህ ለበጎም ለክፉም ዓላማዎች ሊውል ይችላል፡፡ እውቀትና ጥሩ መልእክቶች በፍጥነት እንደሚሰራጩበት ሁሉ ለፖለቲካ ግጭት አደገኛ መቀስቀሻም ሊሆን ይችላል። በዚህ ውጥንቅጥ መሃል የእግዚአብሔር መልእክትና የሰው ልጅ መዳን ወደ አራቱ የዓለም ማዕዘናት መዳረሱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰዎች ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሲያውቁና በክብረ ነገስት ወደ ኢትዮጵያ የደረሰበትን ታሪክ ሲረዱ፣ አሥርቱን የእግዚአብሔር ትእዛዛት እውነተኛ ባህሪ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል፡፡
በዘፈኖችህ ውስጥ ኢትዮጵያን ደጋግመህ ጠቅሰሃል፡፡ በዓለም የሬጌ ሙዚቃ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ሚና እንዴት ይገለጻል?
በራስ ታፋሪያኖች እምነት፣ በሬጌ ሙዚቃ ልዩ መልእክት፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ጉልህ ሚና ትጫወታለች፡፡ መነሻው በጃማይካ፣ በካሪቢያንና በአሜሪካ ውስጥ ቢሆንም፤  በትራንስ አትላንቲክ የባሪያ ንግድ ወቅት  ወደ ምዕራቡ ዓለም የተጋዙት አፍሪካውያን ያመጡት ውጤት ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ እንደ ነቢይ የሚቆጠረው ማርከስ ጋርቬይ ወደ አፍሪካ እንድንመለከትና  በተከበረው አፍሪካዊ ማንነት ላይም አፅንዖት ሰጥቶ አስተምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በፋሺስት ወራሪዎች ጥቃት ሲሰነዘርባት በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ብዙ አፍሪካውያን ኢትዮጵያን ዳግም ነፃ ለማውጣት በተደረገው ትግል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ይደግፉ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ተወዳጁ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባደረጉት ጥረት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት መስራቾች አንዷ ሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ልጆች ለፍትህና ለእኩልነት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትግል ጠንካራ ተምሳሌትና ምልክት ሆኗል፡፡ እና አሁን በዓለም ዙሪያ በሬጌ ሙዚቃ ተወዳጅነት ሳቢያ ብዙ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክም ግንዛቤ እያገኙ መጥተዋል፡፡
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር እንዴት አብራችሁ ልትሰሩ ቻላችሁ?
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር የተገናኘነው በአዲስ አበባው ጥሩ ጓደኛዬ ራስ ሳም አማካኝነት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በጎበኘሁበት ወቅት ከራስ ሳም ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን፤ ከዛም በኋላ ወደ አውሮፓ በዛው ክረምት ላይ መጥቶ የሙዚቃ ስራዎቼን ባቀረብኩበት የሬጌ ጃም ፌስቲቫል ላይ  ተገናኝተን ብዙ ተጫውተናል፡፡
 በወቅቱ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ስለሰራሁት ዘፈኔ ለራስ ሳም ስነግረው፣ ኢትዮጵያዊ አርቲስት በአማርኛ ቋንቋ የዘፈኑን ታሪክ እንዲጫወት ማሰቤን ገለፅኩለት፡፡ ይሄን ጊዜ ከራስ ዮሐንስ ጋር እንድሰራው የጠቆመኝ ራስ ሳም ነው፡፡ ራስ ዮሐንስ ዘፈኑንና ሀሳቡን ስለወደደው ወዲያውኑ ስቱዲዮ ገብቶ ቀረፃውን በማከናወን የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ራስ ጃኒ እና ባለቤቱ ኢየሩሳሌም ሀብቴ እጅግ በጣም ግሩምና አፍቃሪ ሰዎች ናቸው፡፡ የሙዚቃውን ቀረፃ እውን ለማድረግ እንዲሁም ለሙዚቃ ቪዲዮው ስራ ቅን ትብብር አድርገዋል፡፡ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
በመጨረሻ  የምታስተላልፈው መልእክት…
በአንድ ወቅት በታሪክ ውስጥ ተደብቆ የነበረው ነገር ከእንግዲህ እንቆቅልሽ አይደለም፡፡ የዓለም ህዝቦች ለመዳን  ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ፡፡ ጠላቶቿ ብዙ ናቸው፣ ግን ልክ ቁራጭ ሻማ በብርሃኗ ጨለማውን እንደምታበራው ኢትዮጵያም እምነቷን ጠብቃ መቀጠል አለባት፡፡ ማንም ሰው ጊዜውን ማቆም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ በክፉም ላይ መልካም ድል እንደሚያደርግ እናምናለን። አንድነት ጥንካሬ ነው፡፡ ጸሎታችን ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዛሬም ለዝንተ ዓለምም እንወዳታለን።


Read 1666 times