Tuesday, 20 July 2021 00:00

የ‹‹ጥቋቁር አናብስት›› - (ቀያይ ስህተቶች

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(2 votes)

     ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ..ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ ስነ-ጽሁፋዊ ትርጉም ስራዎች በስፋት ለንባብ በቅተዋል፡፡ በተለይ ለተርጓሚዎች  ወረርሽኙ  ከማደናቀፍ ይልቅ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ ይመስላል፡፡
የስመ-ጥር ግለሰቦችን ስንት የተደከመበት ስራ በለብ-ለብ ትርጉም እያጣደፉ እንካችሁ የሚሉን ፀሃፍት፤ እዚህም-እዚያም እየተነሱ ነው፤ እንዲያውም አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ የመጽሐፍ ገበያው የንግድ-ዘይቤ ይመስላል፡፡ እዚህ በስም የማልጠቅሳቸው መልካም የጥበብ ትሩፋታቸውን አንብበን ያከበርናቸው የጥበብ ሰዎች ሁሉ አዲሱ ‹‹ፋሽን›› የሆነውን የ‹‹ትርጉም ቢዝነስ›› ተቀላቅለዋል፡፡ ትርፋማነቱ አዋጭ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሁንና የኑሮ ውድነት ባመጣው አዙሪት  የትርጉም ስራ ላይ ከመንጠልጠል ጣጣ ወጥተው፣ ወደ ነባር ፈጠራዎቻቸው ፀሃይ ሳትጠልቅ፣ ጀንበር ሳታዘቀዝቅ መመለሳቸው ህልም ይመስላል፡፡
በኢትዮጵያ የትርጉም ስራ ውስጥ በብዛትም-በጥራትም ለህዝባቸው በማቅረብ ባለ-ውለታዎቹ..ከትናንትናዎቹ..ማሞ ውድነህ፣ አማረ ማሞ፣ መስፍን አለማየሁ፣ ሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም.. የመሳሰሉ.. ሁሌም የወርቃማ ዘመን ምልክቶቻችንን እንድንናፍቅ የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ-መነሻ በዘመነኞቹ ተርጓሚዎች ላይ የሳንሱር መቀስ ግድ የሚልበት፤ ተስፋችን ተሟጦ ያለቀበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የዚያኑ ያህል ውስን ቢሆኑም ዛሬም በጣት የሚቆጠሩ ከልብ በመነጨ መሰጠት ለህዝብ (ንቃተ ህሊና፣የንባብ ደረጃ) ይመጥናል ያሉትን ታሪክ-ነክ ማስታወሻዎች፣ የጉዞ ሰነዶች፣ ግለ-ታሪኮች የተረጎሙልንን በማይናቅ ድካማቸው አንረሳቸውም፡፡
ሞልቪየር
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ደራሲያንን ህይወትና ስራዎቻቸውን በጥልቀት ያጠኑ የሥነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች በምንጭነት ይጠቀሙበታል፤ ግልጋሎቱ የላቀ ነው ሲሉም ያወድሱታል፡፡ ውስን በሆነው የአማርኛ ሥነ-ጽሁፍ ለመዳሰስ ያለው አስተዋጽኦ ይህ ነው አይባልም። ዘሪሁን አስፋው በ‹‹ሥነ-ጽሁፍ መሠረታውያን››፤ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ነባር ደራስያን ስራቸውን ለስነ-ጽሁፍ መማሪያነት የተጠቀመበትን ያህል፤ህይወታቸውን ደግሞ አንድ ‹‹ኖርዌጅያን›› ነጭ ሊጠበብበት ሞክሯል.. ሩዶልፍ ኬ ሞልቪየር፡፡
ሞልቪየር በኢትዮጵያ ለ14 አመት ያህል እንደኖረ ይነገርለታል፡፡ የሀገራችንን ባህል፣እምነት፣ ስነ-ልቦና ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ አማርኛ ቋንቋን እንደ-ተወላጅ የሚያቀላጥፉ ምሁር ናቸው፡፡ ሰውዬው በሞያቸው መምህርና የታሪክ አጥኚ ከመሆናቸው ጎን ለጎን፣ ሥለ- ኢትዮጵያ ባህልና አኗኗር በማጥናት Tradition and change in Ethiopia እና ሌሎችም ሥራዎችን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በዚህም አበርክ,ቷቸው አድናቆትና አክብሮት የተቸራቸው ፀሐፊ ናቸው፡፡ በሀገራችን "የበጎ ሰው"ን ጨምሮ ለአለም-አቀፍ ሽልማትም የበቁ ምሁር ናቸው፡፡
በእኚህ ምሁር ስለተጻፈውና ብዙ ስለተባለለት ታላቅ ስራ The black Lion መጽሐፍ ብዙ ጊዜ እብሰለስል ነበር፡፡ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለማንበብ ብርቱ ጉጉት ካደረብኝ አያሌ ጊዜያት ተቆጥረዋል፡፡ ይሄ ናፍቆቴ እውን የሚሆንበት ጊዜ ግን በዚህ ፍጥነት ቅርብ አልመሰለኝም ነበር፡፡
ጥቋቁር አናብስት
ባለፈው ለምርጫ መዳረሻ ሰሞን.. የቅዳሜ ጋዜጣና መጽሄቶችን ለመግዛት በብሔራዊ በኩል አልፋለሁ፡፡..ድንገት መሬት ላይ ሸራ አንጥፈው ለገበያ ከተዘረጉ መጽሃፍት መካከል.. በጥቁር ልባስ የተደጎሰ አዲስ መጽሃፍ አይኔ ገባ፤ ሽፋኑ ላይ ከኢትዮጵያ ታላላቅ - መሪዎች እስከ የከባድ-ሚዛን ደራሲያን ፎቶ ትኩረቴን ሳቡት፤ እንደ-ቀልድ ርዕሱን ሳማትር አይኔን ለመጠራጠር ዳዳኝ፤ የደራሲውን ስም ሳነብብ ደስታና ድንጋጤ መንትያ ሆኖ ተላተመኝ፡፡ አዎ መጽሐፉ እራሱ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜያት ወደ ‹‹እናት ቋንቋው አማርኛ›› ተመልሶ ለማንበብ ስናፍቅ የነበረው የዶ/ር ሞልቪየር TheBlack Lion (ጥቋቁር አናብስት) በሚል ርዕስ ‹ቴዎድሮስ ሸዋንግዛውና ኤፍሬም ጀማል በተባሉ ሁለት ፀሃፍት ወደ አማርኛ ተመልሷል፡፡
ተርጓሚዎቹ
ተርጓሚዎቹ ጥሩ የሚባል የስነ-ጽሁፍ ፍላጎትና መሰጠት አላቸው፤ሆኖም ይህንን ስራ ለመተርጎም የሚያስችል ብቃቱ ግን የላቸውም፡፡ ሥነ-ጽሁፍ በገበያ-ተኮር ስልት በ‹‹ደመ-ነፍስ›› የጀማሪ መፈንጫ መሆኗ እንኳን የስነ-ፅሁፍ ቤተሰብ ለሆነ ይቅርና ለማንም ያስቆጫል፡፡ እግር-በእግር እየተከታተለ ቀንድን የሚል ሁነኛ ‹‹ሀያሲ›› መጥፋቱ፣ ለዚህ አይነቱ ‹‹ቀይ ስህተት›› መንገድ ጠርጓል ማለት ይቻላል፡፡ ልጆቹ "በዚህ ታላቅ ስራ የትርጉም ዘርፉን ለመቀላቀል" በሚል እጃቸውን ለማፍታታት ደፍረዋል፡፡ ይሁንና በታላቅ ከበሬታ ለካበተ ባለ-ልምድ ተርጓሚ እስኪያነሳው ባለበት ሊቆይ እንጂ እጅ-ሊሟሽበት የሚገባ ስራ አልነበረም፡፡ ለኔ የ"ጥቋቁር አናብስት"..ትርጉም አንባቢ ‹‹ጠያቂ አእምሮ›› የለውም ከሚል የተሰነዘረ ጥቃት ነው፤ የጥቃት ሙከራው የተቃጣብን ደግሞ ጋሼ ‹‹ሳህለ ስላሴን›› ሽፋን በማድረግ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ጎኑም ይኸው ነው፡፡ ጋሽ ሳህለ ስላሴ በገለልተኝነት ቸልታ፣ በፀጥታ ከመመልከት ውጪ የልጆቹን ስህተት ነቅሶ በማውጣትና በማሳየት እንዲሁም በመጠቆም ሊታደጉት ብርቱ ጥረት አላደረጉለትም፤ ለምን ትኩረት እንዳልሰጡት ለማወቅ ዳገት ሆኖብኛል፤ ከእድሜ መግፋት ይሁን.. ተተኪ ለማፍራት ከመነጨ የዋህ ምኞት ግልጽ አይደለም፡፡
ተርጓሚዎቹ.. ጥሞና እርቆት.. ከመጽሃፍት ለተኳረፈው፣ የማህበራዊ ሚዲያው አለም ከደም-ስሩ ለተዋሀደው ትውልድ እንግዳ አይደሉም፡፡ በዚህ ማህበራዊ ትስስር የራሳቸውን ገጽ በመክፈት ‹‹ጥበብ ነክ›› ጽሁፎችን በማስነበብ ጥሩ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ተከታዮችም አሏቸው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያቸው ምስጋና ዘንቦላቸዋል፣ አድናቆት ጎርፎላቸዋል፡፡ ውዳሴ ከቸሯቸው ከያኒያን መካከል እንደ ሙያ አባታቸው የሚቆጥሩት ታታሪውና ትጉሁ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ አንዱ ነው፡፡
አድናቆት በወለደው ተነሳሽነት በመገፋፋት የበኩር ስህተታቸውን በሞልቪየር The black Lion አንድ ብለዋል፡፡ ይህ ታሪካዊ ስህተት ሳያንስ.. ለተከታዮቻቸው.. “ምንም እንኳን ለናንተ ፍቅርና አክብሮት ብታንስም እጅ-መንሻ ትሁናችሁ..? ሲሉ በመግቢያቸው ሊመፃደቁ ዳድቷቸዋል፡፡ ሳያውቁ ስህተት መስራት የወግ ነው.. አያስወቅስም፣ አያስከስስም። ይስማዕከ ወርቁ ‹‹ደህንነቱ›› ውስጥ ‹‹የማይሳሳት ሰው ታሪክ የሌለው ነው ሲል ጽፏል፡፡ ከስህተት ለታረመ መሳሳት የታሪክ አንድ አካል እንጂ ጠፍቶ ለመቅረት ምክንያት እንዳልሆነ ይስማዕከ ነግሮናል፤ እያወቁ ለስህተት መነሳት ግን ቢያንስ ሊያስተች እንደ-ሚችል ተርጓሚዎቹ በሳል መካሪ ያሻቸዋል፡፡ ለነዚህ ልጆች አንባቢ ማለት ፔጃቸውን ተቀላቅሎ የሚለጥፋትን ጽሁፍ የተከታተለ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት መግቢያውን ብቻ ማንበብ በቂ ነው፡፡
ደጋፊ ለማስደሰት ሲባል ለእጅ መንሻ የሚሆን አፀፋ ማሰብ ያባት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የማይጠፋ ንብረት፣ የማይሞት ሀብት፣ የረዥም ዘመን ነዋሪ የሆነውን መጽሀፍ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ የይድረስ-ይድረስ ማስደጎስ ግን ተገቢ አይደለም፡፡
መጽሐፉ ለፌስ-ቡክ የታሰቡ የሚመስሉ በወጉ ያልታሹና ያልተፈተጉ፤ ቃል በቃል ወደ አማርኛ የተመለሱ ታሪኮች ታጭቀውበታል፡፡.. የህሩይ ወ/ስላሴ፣ የአሰፋ ገብረ-ማርያም፣ የወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሃንስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን መሰል በየትኛውም ዘውግ የተፃፉ ድርሳናትም ሆኑ የጥበብ ስራዎች ለአደባባይ ስለ መብቃታቸው የሚነደው ‹‹ቀንደኛ ተቃዋሚ ነኝ›› ሲል ጽፎ ያነበብኩት አንድ ደራሲ አውቃለሁ፤ እርሱም ደረጄ ነው፡፡ ደራሲና ሀያሲ ደረጄ በላይነህ፤ ዶ/ር አብይ አህመድ በፌስ-ቡክ ላይ በለቀቋቸው ግጥሞች ዙሪያ በሰራው ሂሳዊ ቅኝቱ፤ለዶክተሩ ስንቅ ሊሆን የሚችል “ምክር” አስታጥቋቸዋል፡፡.. ምክሩ ከላይ ካነሳሁት ሀሳብ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ነውና እዚህ ብጠቅሰው ጉዳዩን የበለጠ ያጠናክረዋል፡፡ .. (ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለምን ተፃፈ ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ወደ መጽሃፍ ሲመጣ ግን ጥንቃቄ ያሻዋል። ገንዘብ ከፍለን ስለምንገዛውና የማይጠፋ ቋሚ ሰነድ በመሆኑም እንተቸዋለን፡፡ (አዲስ አድማስ ቅጽ 21 ቁጥር 1076) በርግጥ ምክሩ ማህበራዊ ሚዲያው ላገነናቸው፣ በጭብጨባ ተውጠው ለሚጠፋ ዘመነኞች ሁሉ በተለይ (ቴዎድሮስ እና ኤፍሬም) ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በታች ከመፅሐፉ ውስጥ በዋነኝነት ክፍተቶችና ስህተቶች ናቸው ባልኳቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥቆማዬንና ምልከታዬን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
በአንድ-ወቅት በተርጓሚዎቹ ጥምረት የተከፈተ “Book for all” በሚል በማህበራዊ-ትስስር ገጽ የራሳቸውን እና የሌሎችን ፀሃፍያን በፌስ-ቡክ ግድግዳ ላይ ለቅመው የሚያሰፍሩትን መጣጥፎች ለአንድ-ወር ልቤን ከፍቼ በጥሞና ለመከታተል ሞክሬ ነበር፡፡ ከዚያ በላይ መግፋት ግን አልቻልኩም፤በወጉ ያልታረሙና ለመነበብ የማይገፋፉ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው አታከቱኝ፡፡ ከወር በላይ በደንበኝነቴ መቀጠል ተሳነኝ፡፡ በዚያው ጠፋሁ፡፡ እስከ ዛሬ አልተመለስኩም፡፡
ልጆቹ ለመተርጎም ገና አቅምና ጉልበታቸው ያልጠነከረ፣ የልምድ-ማነስ የሚታይባቸው  እንደሆኑ በግልፅ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ በርግጥ እንደ-ጅምር ለመተርጎም ያደረባቸው ቅንና የዋህ ፍላጎት ላያስወቅሳቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ‹‹ልምምዱ›› በእንደዚህ አይነት ዘመን-ተሻጋሪ ስራ መሆን አልነበረበትም፡፡ የክብር ዶ/ር ሳህለስላሴ በአርትኦቱ መሳተፍን ‹‹ለምን›› ስል መጠየቅ የፈለኩትም ለዚህ ነው፡፡..በዚህ ረገድ የራሷ ፊደል እንዳላት ሀገር ካሰብን ሁላችንም የሞልቪየር ባለ-እዳዎቹ ነን፤ ሀገር-በቀል ሀብቶቻችንን ቆፍሮ በአእምሮ ልቀት፤በግል ትጋት ለውጤት ብሎም ለአደባባይ አብቅቷቸዋል፡፡ ከመጀመሪያው ትውልድ ተነስቶ (በህይወት የሌሉትን ታሪካቸውን በመቆፈር) እስከ ‹‹ዘመናዊ የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ›› ጅማሮ (የአፈወርቅ ገ/እየሱስ ‹‹ጦቢያ››ን ልብ ይሏል) የደራሲያንን ህይወትና ስራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ረገድ The black Lion ወደር የሌለው ስራ ነው፡፡
የሞልቪየር ስራዎች ለኛ ‹‹ባዳ›› ሆኖብን እንጂ ለሌላው አለም ‹‹እንግዳ›› አይደሉም። እንኳን ‹‹ስነ-ጽሁፋችን›› ኢትዮጵያ የት እንዳለች እንኳን በተረሳችበት ሀያኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሞልቪየር የኢትዮጵያን ደራሲያን ‹‹እጅ ይዞ› ›ለአለም ህብረተሰብ ሲያስተዋውቅ፣ በጊዜው መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደከረመ በሞልቬር ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ መጽሃፉ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ብቻ ሳይሆን ስነ-ጽሁፍ እንዳላት፤ በውስጧም በፊደሎቿ ‹‹የሚፅፉ ደራሲያን ሁሉ አሉ›› ያስባለ ቅርስ ነው፡፡ ይህን እኛን ለሌላው አለም ያስተዋወቀን ‹‹ቅርስ››፤ ስህተቱን ብናልፍ እንኳ ጥንቃቄው ሊጓደል አይገባም ነበር፡፡
ዋነው-ነገር ሞልቪየር የተወልንን የሁላችንም ሀብት መሆኑን ተገንዝበው፣ ከቻሉ በድህረ-ገፃቸው አሊያም በሁለተኛ-እትም ህዝብን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ ለመታረም ልምምዱ ካለ የማይሻሻል ነገር የለም። እድሉም ቢሆን ሰፊ ነው፡፡ ሳይሳሳት እዚህ የቆመ የለም፡፡ አለማችን የማሰብ ብቻ ሳይሆን የመሳሳትም ውጤት ናት፡፡ እንዲያውም ከልማቷ ጥፋቷ ይበዛል፡፡ የመፅሃፍ ጥፋት በ‹‹ሂስ›› እንጂ በ‹‹ህግ›› አይዳኝም፡፡ ለማንም አቤት አይባልም፡፡ ሂስ ሲባል በዋነኝነት ስህተትን በመጠቆም ለማቃናት፣ለመገንባት እንጂ ለማፍረስ ብቻ ታልሞ የሚሰነዘር የማይክ-ታይሰን ቡጢ አይደለም፡፡ አንድን ግቡን የረሳ፣ሚዛኑን የሳተ የጥበብ ስራ ስህተቱን ለመንቀፍ የግድ ሀያሲ መሆንም አይጠበቅም፡፡ እንዲያውም የሚያስመሰግን ቅዱስ-ተግባር እንጂ የሚያስነውር እርኩስ ሴራ አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደ- ማሰብ አቅምና ደረጃችን እንጂ ‹‹ልክ›› ብሎ እውነትም ሆነ‹‹ልቅ›› ብሎ ስህተት እንደሌለ የስነ-ልቦና ተመራማሪዎች የሚያስረግጡት እውነት ነው፡፡ ስለዚህ መተራረም እንደ-ባህል ሊዳብር የሚገባው ስልጡን ስነ-ምግባር ነው፡፡
የ‹‹ሳህለ ሥላሴ-ሌላኛው መልካቸው››
በሞልቪየር ጥናት ውስጥ!
ሳህለ-ስላሴ ለአማርኛ ስነ-ጽሁፍ በትርጉም ዘርፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከማንም ጋር የሚወዳደር አይደለም። የኢትዮጵያን ህዝብ ባህል፣ ሥነ-ጽሁፍ አስተሳሰብ ለማበልፀግ የሚችሉትን ያህል አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአለም ስነ-ጽሁፍ ውስጥ የከበረ-ሥም ያላቸውን ዘመን አይሽሬ Clasic የውጭ ደራሲያን ለሀገራቸው አንባቢ በተዋበ ቋንቋ፣ ከእነ መንፈሱ ጥንቅቅ ባለ አማርኛ በማስነበብ ባለ-ውለታ ናቸው፡፡ ከ‹‹ወጣት ይፍረደው›› የግል ፈጠራ ልቦለዳቸው እስከ የእድሜ-ዘመን ማምሻ የመጨረሻ ስራቸው እስከ-ሆነው አነጋጋሪው በ‹‹እየሱስ ህይወት›› ላይ በሚያጠነጥነው የትርጉም ስራቸው የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ በአፍላ ወጣትነት ‹‹ፒያሳ›› ጊዮርጊስ አካባቢ አሮጌ መጽሃፍ መሸጫ፣ የእርሳቸውን ትርጉሞች በማሰስ ለማንበብ የነበረኝ ጉጉት የሚረሳ አልነበረም፡፡ ያኔ ጥሩ ‹‹የንባብ ትዝታ›› ከነበረኝና ጣፍጦኝ አንብቤ ከተደሰትኩባቸው የርሳቸው ትርጉሞች መካከል የ‹‹ፐርል በክ›› ስራ የሆነው ‹‹The mother›› በዚህ-አመት በድጋሚ ታትሞ ገበያ ላይ ማየቴ እጅጉን አስደስቶኛል፡፡
በአለም ስነ-ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ታላቅ ከበሬታ የተቸራቸው ደራሲያን፣ የጥበብ ትሩፋታቸውን ለሀገራቸው ጥበብ አፍቃሪ በስፋት በማስተዋወቃቸው የምንሰጣቸው ቦታ ከምንም ባይወዳደርም፣ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችም እንዳሉበት መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ እርስ በርስ የሚጣረሱ ሁነቶችን ለተደራሲ የማጥራት ስራ የተርጓሚዎቹ ቢሆንም፣ በይሉኝታ ይሁን  ብስለትና ልምድ ከማነስ ጥያቄ ያስነሳል፡፡
ለምሳሌ ጋሽ ሳህለ-ስላሴ..ለሞልቪየር እንደነገሩት ከሆነ፤ ..ሁሉንም አይነት መጥፎ የሚባሉ ድርጊት ይፈፅሙ እንደ-ነበር አልደበቁትም፡፡ እንዲህ ሲሉ.. "ሲበዛ ነውረኛ ነበርኩ፤ ሴተኛ አዳሪዎችን እንደ-ልብ እጎበኛለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ከነበሩ ከአዲስ አበባ የውቤ በረሃ ሴተኛ አዳሪዎች ጋር ጥሩ ትዝታዎች አሉኝ፡፡ አየህ በዳንስ አብጃለሁ፤ ነፃነት ይሰጠኝ ነበር፡፡ ጥሩ እመገባለሁ፤ ከሌሎች ጓደኞቼ እጥፍ እበላ ነበር.. በርካታ ሴተኛ አዳሪዎችን አጣጥሜያለሁ፤ እነዚህ ሴቶች መልካም ሰዎች ነበሩ፡፡" (ገጽ 364) እዚህ ጋ የሳህለ-ስላሴ ሌላኛው አወዛጋቢ መልካቸው ብቅ ይላል፡፡ ለሞልቪየር ድፍረት በታከለበት ግልጽነት ሊነግሩት የወደዱትን ለኛ ለምን ሊሸሽጉ እንደፈለጉ ግልፅ አይደለም፡፡ የዚያን ጊዜው ወጣቱ ሳህሌ አድቬንቸር ይወድዳል፣ጀብድ መስራት ያስደስተዋል፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር ከውቤ-በረሃ እስከ ወንጂ-ስኳር ያሳለፉት ጊዜ ራሱን የቻለ የውቤ-በረሃ ገድል ነው። በራሱ ቁመና ቢፃፍ መጽሃፍ ይወጣዋል። ለዚያውም የጋሽ ስብሃት ለአብ የውቤ-በረሃ ዜና-መዋዕል የሆነውን ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› የሚያስንቅ፡፡ ይሁንና ‹‹ፍኖተ-ህይወት›› በተሰኘ ግለ-ታሪካቸው ውስጥ ይህንን አይነግሩንም.. አይን-አፋር መሆንን መርጠዋል፡፡ ወይም ወጥ በሆነና ራሱን በቻለ ሁኔታ ተጽፎ የተቀመጠም፣ ተርጓሚዎቹ ይህንን ፈትሸው ‹‹ፍንጭ›› ሊሰጡን ይገባ ነበር፡፡ ቃል በቃል አለባብሰው ከመተርጎም የዘለለ ምንም የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ጋሽ ሳህለ ስላሴ በጊዜው የወጣትነት ትኩሳት ሳይበርድላቸው፣ በፈረንሳይ ኤክስ-ፕሮቫንስ የህግ ትምህርት በሚከታተሉበት ወቅት ከመሰሎቻቸው ጋር ያሳለፉትን ለሞልቬየር ያጫወቱት፣ ለኛ ግን ከላይ በጠቀስኩት የህይወት ጉዟቸውን በሚዳስሰው መጽሃፋቸው የደበቁት ሌላ ታሪክ አላቸው። ይሄም ተመልሶ ከዚያን ጊዜ የዘመን-ተጋሪ አቻቸው የስብሃት ገ/እግዚያብሔር የፈረንሳይ ትርክት የሆነው‹‹ትኩሳት›› ጋር መሳ-ለመሳ ሊነፃፀር የሚችል ታሪክ ውስጣቸው እንዳለ እንረዳለን። በርግጥ ሣህለ-ስላሴ ከተረጎሙልን አያሌ-ስራዎቻቸው ጎን፣ በቂውን-ያህል ህይወታቸው ቢጠና፣ቢፈተሽ..ለሌላ ጥናትና ምርምር በር-ከፋች ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በ1952 አካባቢ እርሳቸውና ሌሎች ጓደኞቻቸው በዚያ አስረሽ-ምቺው ተውጠው፣ ቅጥ-ያጣ ቅብጠታቸው ለብዙ ኪሳራ ዳርጓቸው እንዳለፈ ማወቅ ይቻላል። በፍቅር ህይወታቸው ብቻ ሳይሆን ለቀሪ ህይወታቸውም ከባድ የስነ-ልቦና ጠባሳ እንደተወላቸው እርሳቸው ባይነግሩንም በተለያዩ ጊዜ ከሚሰጡት ቃለ-ምልልሳቸው እንረዳለን፡፡ በአንድ ወቅት በ‹‹ፋና›› ኤፍ ኤም ከሀ እስከ ፐ በተባለ ፕሮግራም ላይ ከጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ ጋር በእንግድነት በነበራቸው ቆይታ.. ሚስት አግብተው፣ ትዳር ኖሯቸው እንደማያውቅ ሲናገሩ ማድመጤን አስታውሳለሁ፡፡ እንዲሁ በአለላ መጽሄት ላይ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ይህንኑ ደግመውታል፡፡ አግብቼ አላውቅም፤ፈላጊና ተፈላጊ መገናኘት አለባቸው፤ለመጋባት ብሎ መጋባት ልክ አይመስለኝም፡ ሲሉ ቅፅ 1 ቁ.2።
ጋሽ ሳህለ ስላሴ በግላጭ ባይነግሩንም እንኳን ዛሬ ላይ ያላቸው የህይወት ቅንጣት ከዚያን-ጊዜ የወጣትነት አውድ የተመዘዘ እንደሆነ ቃላዊ መረጃዎቻቸው ይጠቁሙናል፡፡ጋሽ ስብሃትም የነበረው የእርጅና ዘመን አወዛጋቢ የሰብእና መልኮቹ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ከወጣትነቱ ጋር የነበረውን ዝምድና፣ ከሳህለ-ስላሴ ጋር አዳብለን ካጠናን ተመሳሳይነቱ በይበልጥ ጉልህ ያደርገዋል፡፡
ሞልቬየር ይህን የኢትዮጵያ ደራሲያን የህይወት ስብስብ የፃፈው.. አንድም የዚያን ጊዜዎቹን ደራሲያን ከልብ በማድነቅ፤ ሁለትም የአፍሪካ ስነ-ጽሁፍ የትም አይደርስም ከሚል እምነቱ በመነሳት ለተቀረው አለም እንዲታወቅ ካለው መሻት የተነሳ ነው፡፡ (በቅኝ ገዥዎች የአፍሪካ ብሔራዊ መግባቢያ ቋንቋቸው ተጨቁኖ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡) ሞልቪየር የሀገራችን ተወላጅ እንዳለመሆኑ መጠን ብዙ የመረጃ ክፍተቶች ሊኖሩበት እንደሚችሉ እርግጥ ነው። ይህንንም እራሱ አምኗል..  በስማ-በለው የተሳሳተ መረጃ ሊደርሰኝ ይችላል፤ የመረጃ ምንጮቼንም በአግባቡ ላልረዳ እችላለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ.. ሲል ይፀፀታል፡፡ ይህን የመረጃ ክፍተት የመሙላት ተቀዳሚ የቤት ስራ የተርጓሚዎቹ ነበር፤ በቸልታ ተዘንግቷል፡፡ ሞልቬየር ይህን ድርሳን አጠናቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ያበቃው ወታደራዊ መንግስት‹‹ደርግ›› ገና ስልጣን ላይ እያለ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ አንዳንድ ደራሲዎች ሥለ-ስራቸውም ሆነ ስለ ህይወታቸው ከልብ እንዳያወሩ አግዷል፡፡ ከደርግ መወገድ በኋላ በደራሲያኑ ህይወትና ስራ ላይ ህዝብ በይፋ የሚያውቃቸው እውነታዎች ለማመሳከሪያነት መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ የራሱ የሞልቬየርን መረጃዎች አለባብሰው እንዳለ ከመተርጎምና ከመድገም የዘለለ በራሳቸው ጥረት ክፍተቱን ለመሙላት የሄዱበት መንገድ፣ የተዉልን ማስታወሻ የለም፡፡ (ክፍተቱ በግላጭ ተንሰራፍቶ የሚታየው በይልማ ሀብተየስ፤ በብርሃኑ ዘሪሁን፣በአቤ ጉበኛ፣ በበአሉ ግርማ፣ በስብሃት ገ/እግዚያብሔርና ሌሎችም ላይ ነው፡፡)
በግለሰብ ታሪኮች ላይ ያሉ ክፍተቶችን አንድ ሁለቱን ልጠቁም፡፡ ለአብነትም በዳኛቸው ወርቁ ታሪክ ላይ፤የአቶ ወርቁ ታዋቂው የህይወት ፍልስፍናቸው የ‹‹ራስህ አገልጋይ ካልሆንክ የሌላው ባሪያ ትሆናለህ›› የሚለውን.. ባሪያን.. በአገልጋይ ልዋጭ ተጠቅመዋል፡፡ ባሪያና አገልጋይ አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ማገልገል ላመኑት ወገን በታማኝነት መስራት ነው፡፡ ባርነት ሲባል ግን ያለ ግላዊ ምርጫና ፍላጎት፣ በጭቆና ለሌላው ጥቅም መስዋዕት ለመሆን መገደድ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ቀላል የሚመስሉ ብዙ ስህተቶችን መንቀስ ይቻላል፡፡
ሞልቪየር በዚህ ስራው ያካተታቸው ደራሲያን ስራቸውን ለተጨማሪ ግብአት እንዲሆን ማንበባቸው እንኳን ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ ንባቡ ቢቀር እንኳን የአማርኛ መዝገበ-ቃላት ለመጠቀም ንፉግ መሆናቸው ያስቆጫል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የዘመን-መንፈስ ለመረዳት በወቅቱ የተጻፉ መጽሃፍቶችን ማገላበጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የቤት ስራ ነበር። ይህ ስንፍና ሳይቀረፍ ከሞልቪየር ስም ጋር ለመነሳት መፍጠን ሊያስነቅፍ የሚችል መደዴ ግልብነት ነው፡፡ በዚያ ላይ የትርጉም ዘርፉን ብቻ ሳይሆን የሞልቪየርንም ድካምና ውለታ የሚያስረሳ ነው፡፡ እነዚህ መጽሃፉን ሊታደጉና ከነበረው የወቅቱ ስርአት ጋር አቆራኝተው ተነባቢ ሊያደርጉት የሚችሉ መጽሃፍት፣ እዚህም-እዚያም ተዘዋውሮ የመፈለግ ተነሳሽነት ማጣት እንጂ በድጋሚ የታተሙና በቀላሉ ገበያ ላይ ሊገኙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከፌስ-ቡክ (ሁካታና ግርግር) ራሳቸውን በማግለል ፋታ ጊዜ ወስደው፣ በሁለት ክፍል ለመነካካት በሞከርኳቸውና የሞልቪየር ስህተቶችና ‹‹የመረጃ ክፍተቶች›› ላይ ከሰሩ፤ እንዲሁም ተግባራዊ ለማድረግ ቅንነቱ ካለ በላቀ የትርጉም ዘርፍ እንኳን ለ"ሆሄ" ለ"በጎ ሰው"ም ደምፃችንን የማንሰጥበት ምንም ምክንያት አይኖርም። "ጥቋቁር አናብስት"ም ዘመን-ተሻጋሪና በቀላሉ የማንረሳው ቅርሳችን የማይሆንበት መነሻ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡


Read 1602 times