Saturday, 08 September 2012 10:47

ማሪ

Written by  ትርጉም ፡ ነገደ ጌ.
Rate this item
(11 votes)

“The Idiot” ከሚለው የፊዮዶር ዶስቶየቭስኪ ድርሰት ተቀንጭቦ የየቀረበ)

“…አሁን ሁላችሁም በከፍተኛ ጉጉት ተሞልታችሁ እንደምታዳምጡኝ ይሰማኛል፡፡” ሲል ሊዮን ኒኮላየቪች ንግግሩን ጀመረ፡፡ “ማለቴ የማጫውታችሁ ታሪክ እንደጠበቃችሁት ሆኖ ሳታገኙት ስትቀሩ በኔ መበሳጨታችሁ አይቀርም፤ …ቀልዴን አይደለም፡፡” አለ በፈገግታ እየገረመማቸው፡፡

“በጄኔቭ ጐዳናዎች ላይ ልጆች ሲጫወቱ መመልከት የተለመደ ትዕይንት ነው፡፡ በአራት አመት የጄኔቭ ቆይታዬ፣ እኔም አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት ከልጆች ጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ …እኔ ያረፍኩበት ቤት መንደር ነዋሪ ሕፃናት በአቅራቢያ ባለ ት/ቤት ይማሩ ነበር፡፡ እኔ በፍፁም አስተማሪያቸው አልነበርኩም፡፡ ጁልስ ቲቦት የተባለ መምህር ነበራቸው፡፡ በተለየ መንገድ አስተምሬያቸው ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን እንደ አስተማሪ እንዲያዩኝ አልፈልግም፡፡ ከነሱ ጋር ጊዜዬን ከማሳለፍ ውጭ ሌላ ምንም የምሰራው ነገር አልነበረኝም፡፡

…ለማወቅ የሚያጓጓቸውን ነገር ስነግራቸው አንድም ነገር ሳልደብቃቸው ነው፡፡ በኋላ ልጆቹ በዙሪያዬ እየከበቡ ከኔ አልለይ ስላሉ ወላጆቻቸውና የመንደሩ ሰው በሙሉ አለመጠን ይበሳጩብኝ ጀመር፡፡ በዚህም ምክንያት የት/ቤቱ ኃላፊ ዋና ጠላት ሆንኩ፡፡…ይገርማል በመላ ጄኔቭ ሰዎች እንደ ጠላታቸው የቆጠሩኝ በነዚህ ልጆች የተነሳ ነው፡፡ የግል ሃኪሜ ሺንድለር እንኳ ሳይቀር ጀርባውን አዙሮብኝ ነበር…፡፡ ነገር ግን ሰዎቹን እንደዚህ አለመጠን የረበሻቸውና ያስፈራቸው ነገር ምንድነው? አዎ ልጆች ሁሉም ነገር ሊነገራቸው ይችላል፡፡ አንድም ነገር ሳይቀር ሁሉንም ነገር መረዳት ይችላሉ፡፡ አንድም ሳይቀር ነገር ግን የማይሸፈነው እውነታ፣ ማለትም ትልልቆቹ ሰዎች፣ አባቶችና እናቶች፣ ስለልጆቻቸው የሚያውቁት እጅግ በጣም ጥቂት መሆኑ ሁልጊዜ ያስደነግጠኛል፡፡ ልጆች እድሜያቸው ገና ነው ወይም ነፍስ አላወቁም ተብሎ ነገሮችን ከፊታቸው ማሸሽ እጅግ ሊታዘንለት የሚገባ ያልታደለ አስተሳሰብ ነው!...ልጆች ሁሉንም ሲረዱ፣ አባቶቻቸው በእድሜአቸው ምክንያት ምንም እንደማይገባቸው ሲቆጥሯቸው በፍጥነት ማስተዋላቸውስ! ትልልቅና የበሰሉ ሰዎች እጅግ አስቸጋሪ በሚሉዋቸው ጉዳዮች ላይ እንኳን አንድ ልጅ በጣም ጥሩ አማካሪ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያቅታቸዋል፡፡…በመስኮትህ ላይ አርፎ በደስታና በሙሉ ልብ የሚመለከትህ አንድ ትንሽ ወፍ ስታይ ስሜትህን ከፊቱ ልትደብቅ አትችልም፤ ልታታልለው ብታስብ እንኳ ውስጥህ በሃፍረት ሲሸማቀቅ ይሰማሃል፡፡ በምድር ላይ ከወፍ የተሻለ ነገር ስላላየሁ፤ ልጆችን ወፎች እያልኩ እጠራቸዋለሁ…፡፡

 

“ነገር ግን እንደ እውነታው ከሆነ፣ በአጠቃላይ የምኖርበት መንደር ሰዎች በተለይ በአንድ አጋጣሚ እጅግ ተበሳጭተውብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የመምህሩ ቲቦትም ቅናትና ምቀኝነት ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኖ ነበር፡፡ …በመጀመሪያ ህፃናቱ እርሱ የሚላቸውን አንድም ሳይሰሙ፣ እኔ የምነግራቸውን ግን እንዴት በቀላሉ እንደሚረዱት ሲያይ ጭንቅላቱን በማነቃነቅ እጅግ ይገረም ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶ፣ እኔም ሆንኩ እሱ ምንም ነገር ልናስተምራቸው እንደማንችልና ይልቁንም እነሱ እኛን (ትልልቆቹን) የሚያስተምሩ እንደሆኑ በነገርኩት ጊዜ ግን ይስቅብኝ ጀመር፡፡ ህይወቱን ከልጆች ጋር ያሳለፈ ሰው ሆኖ ሳለ፣ ምን እንደሚያስቀናውና ለልጆቹ የኔን ተራነት የሚያወሱ ታሪኮችን እንዴት ሊያወራ እንደቻለ በፍፁም ያልገባኝ ነገር ነው፡፡

የነፍስ ቁስለት የሚታከመው በልጆች መንፈስ ነው…፡፡ …አስታውሳለሁ፣ በህይወቱ በአጠቃላይ እጅግ የተከፋ አንድ ታካሚ ወደ ሺንድለር ክሊኒክ ይመጣ ነበር፡፡ በምድር ላይ ታይቶ እማይታወቅ አስቀያሚ እጣ ነው፡፡ ወደ ክሊኒክ የመጣውም በሽታው እንደ እብደት ተቆጥሮ የባለሙያውን ክትትል ፍለጋ ነው፡፡ እንደኔ አስተያየት ግን ታካሚው ፈጽሞ የአዕምሮ ችግር አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን በከባድ ውጥረት የሚሰቃይ ሰው ነበር፡፡ …በቃ! የሱ ጉዳይ ይኸው ነው፡፡ በመጨረሻም እነዚህ ልጆች ለርሱ ምን ማለት እንደሆኑ ብታውቁ ኖሮ…! ስለዚህ ሰው በሌላ ቀን ሰፋ አድርጌ አጫውታችኋለሁ፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር እንዴት እንደጀመረ ልንገራችሁ፡፡

በመጀመሪያ ልጆቹ አልወደዱኝም ነበር፡፡ ከሰውነቴ መግዘፍ በላይ ራሴን የማልንከባከብ እጅግ ግድየለሽ ነበርኩ፡፡ የመልክም መስህብ እንደሌለኝ አውቃለሁ፡፡ በገዛ ሀገራቸው መጤ መሆኔም ሌላ የማልክደው ሃቅ ነው፡፡

በመጀመሪያ እየተጠቋቆሙ ይስቁብኝ ነበር…ማሪን በድብቅ ስስማት ካዩኝ በኋላ ግን ድንጋይ ይወረውሩብኝ ጀመር፡፡ አንዴ ብቻ ነበር የሳምኳት…ምን ያስቃችኋል አትሳቁ እንጂ፡፡” በሚያዳምጡት ከንፈር ላይ የሚመጣውን ፈገግታ ለማየት የመጨረሻዎቹን ዓረፍተ ነገሮች በፍጥነት ነበር የተናገራቸው፡፡ “ጉዳዩ በጭራሽ የፍቅር አልነበረም፡፡ ምን ያህል ያዘነችና የተከፋች ፍጥረት መሆኗን ብታውቁ ኖሮ፤ ሁላችሁም እኔ በዚያን ጊዜ እንደተሰማኝ አይነት ሃዘን ታዝኑላት ነበር፡፡ ከአሮጊቷ እናቷ ጋር እኔ በምኖርበት መንደር ትኖር ነበር፡፡ እድሳት የሚያስፈልገው አንድ ትንሽ አሮጌ ጐጆ ለሁለት ከፍለው፣ በአንደኛው መስኮት በኩል አሮጊቷ የጫማ ክሮች፣ ትንባሆና ሳሙና ትነግድ ነበር፡፡ አሮጊቷ ምንም ጥቅም የሌላት መናኛ ሴት ነበረች፡፡ ለምሳሌ ሁልጊዜ አንድ ቦታ ቆማ እንቅስቃሴ ካለማድረጓ የተነሳ እግሯ አብጦ ያስቸግራት ነበር፡፡ ማሪ ቀጭንና ደካማ የሃያ አመት ሴት ልጇ ነች፡፡ በቀን በቀን ከቤት እቤት እየዞረች ቤት ለመጥረግና ለመወልወል፣ ግቢ ለማጽዳት እና ከብት ለማገድ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስምምነት ካደረገችላቸው ቤተሰቦች ጋር እየሰራች ምግቧንና ጥቂት ገንዘብ ታገኛለች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በመንደሩ የሚያልፍ ፈረንሳዊ ነጋዴ አስኮብልሎ ከወሰዳት በኋላ ራቅ ያለ የማታውቀው ሃገር ላይ ጥሏት ጠፋ፡፡ ልብሷ እላዩዋ ላይ ተበሳጥሶና የጫማዋ ሶል ተበሳስቶ፣ የምትበላውን ከመንገደኛ እየለመነች እንደምንም ቤቷ ደረሰች፡፡ ለአንድ ሳምንት ያህል በእግሯ ተጉዛ፣ በየመንገዱ እያደረች በመምጣቷ ብርድ መቷት በሃይል ታስል ነበር፡፡ እግሮቿ በመቧጠጣቸው የተነሳ ቆዳዋ ተገሸላልጦ፣ እጆቿም በልዘውና አብጠው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን…በፊት ያልነበረ ውበት ለብሳ የበለጠ ቆንጆ ሆነች፡፡ አይኖቿ ብቻ…ለስላሳ፣ ደግና ንፁህ ነበሩ፡፡ ከብዙ ጊዜ በፊት…በስራ ላይ እያለች፣ በድንገት በከፍተኛ ድምጽ መዘመር በመጀመሯ፣ አብረዋት የነበሩ ሰዎች ምን ያህል እንደተገረሙና እንዳውካኩ ልረሳው አልችልም፡፡ ሁሉም “ማሪ ዘፈነች፡፡ ማሪ ዘመረች” እያለ ሲተራመስ ወድያውኑ መዝሙሩን አቋርጣ መናገር አቆመች፡፡ በነዚያ ጊዜዎች ሰዎች ለርሷ እጅግ ርህሩህ ነበሩ፡፡ ታማና ተዋርዳ ስትመጣ ግን አንድም ያዘነላት ሰው አልነበረም፡፡ ሰዎቹ እጅግ ጨካኝና አስከፊ ነበሩ፡፡

 

 

Read 6180 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:03