Saturday, 24 July 2021 00:00

የህወኃት ቡድን የሚፈጽመው የሰብዓዊ ድጋፍ የማደናቀፍ ድርጊት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲወገዝ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአሸባሪው ህወሃት የሚፈጸመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመለከተ።
ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤የኢትዮጵያ መንግስት አርሶ አደሩ እንዲያርስና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ፣ የአሸባሪው ህወሃት ትርፍራፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን ችግር ውስጥ እንደከተቱት አስታውቋል፡፡
የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከተላለፈበትና የአገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌና ሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዲወጡ ከተደረገበት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት በነበረው ሁኔታ የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኮሚቴ በሶስት ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።
ከዚያ በተጨማሪም ለስርጭት የተዘጋጀ 400 ሺህ ኩንታል ስንዴ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተከማችቶ እንደነበር ገልጿል። 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅም ህዝቡ እንዲጠቀምበት በሚል በክልሉ ዲፖዎች ውስጥ ተከማችቶ እንደነበር ጠቅሷል።
አጋሮችና አለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በክልሉ ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ በመንግስት መፈጠሩን ያወሳው መግለጫው፤ መንግስት አሁንም ቢሆን ለህዝቡ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የብሔራዊ ደህንነትን ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እንዲያርፉ በማድረግ የተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፈቃድ መሰጠቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ በአዲስ አበባ በኩል የማለፍ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው የማይጣስና የሚከበረውን የአገር ደህንነትን ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነ አመልክቷል። ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሁለት በረራ ማድረጉንም አስታውሷል። በከባድ መኪና የሰብአዊ ድጋፉ በአፋር ክልል በኩል እንዲጓጓዝ እየተደረገ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ መዘግየትን ለማስቀረትና የተቀላጠፈ የፍተሻ ስራ እንዲከናወን ለማድረግም ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሷል።
ከቀናት በፊት የሰብዓዊ ድጋፍ ከሰመራ አባላ መስመር ሲያጓጉዙ የነበሩ መኪናዎች ላይ በአሸባሪው ህወሃት አማካኝነት የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዘው መግለጫው፤ በቡድኑ አማካኝነት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍን በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር ያለመታከት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ምግብና መድሃኒት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሰራም አረጋግጧል። ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋርም በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

Read 949 times