Saturday, 24 July 2021 00:00

የኬንያው የራይድ ኩባንያ የኢትዮጵያን ገበያ ሊቀላቀል ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 - በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 5.ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ታውቋል
            - የአገልግሎት አድማሱን ወደ ምግብ ማድረስና የክልል ከተሞች ያስፋፋል ተብሏል።


          “ሊትል” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የኬንያው የራይድ ኩባንያ በቅርቡ የኢትዮጵያን ገበያ በመቀላቀል አገልግሎቱን በአዲስ አበባ እንደሚጀምር ተገለፀ። ግዙፉ  የቴሌኮም ኩባንያ “ሳፋሪኮም” እና  ሌሎች በርካታ የኬንያ ኩባንያዎች እስካሁን ለውጭ የንግድ ተቋማት ተዘግቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀል ተከትሎ ነው “ሊትል” በአዲስ አበባ አገልግሎት ለማቅረብ የተነሳሳው ተብሏል።
የ“ሊትል” ዋና ስራ አስፈጻሚ ካማል ቡድሃብሃቲ ለኬንያው “ቢዝነስ ዴይሊ” እንደተናገሩት፤ ኩባንያው በመጪዎቹ  አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ 5 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሚያደርግ ሲሆን በዕድገት ትንበያው ላይ ተመስርቶ ተጨማሪ የ5 ሚ.ዶላር መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ  ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡
በኬንያ ዩጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ውስጥ ከሚንቀሰቀሱት “ኡበር” እና “ታክሲፋይ” የተሰኙ ዓለማቀፍ የራይድ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር የሚፎካከረው “ሊትል” የኢትዮጵያ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
ኩባንያዎችንና ግለሰብ ተጠቃሚዎችን በደንበኝነት ታላሚ አድርጎ ወደ አገልግሎት የሚገባው  የራይድ ኩባንያ፤ 2 ሺ ሹፌሮችን እንደሚቀጥር “ቢዝነስ ዴይሊ” ዘግቧል። በኋላ ላይም ምግብ የማድረስ (food delivery) እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
“ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በእይታ ትኩረታችን ውስጥ ነበረች” ብለዋል- ዋና ስራ አስፈጻሚው  ከ“ቢዝነስ ቱዴይ” ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
“የኬንያው ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ማምራቱን ስናይ፣ እኛም ገበያውን ለመቀላቀል ድፍረቱን ተቀዳጀን፡፡ እዚያ ሰፊ ገበያ ነው ያለው፤ እናም አገልግሎታችንን በዚያ አገር የማስፋፋት ትልቅ ዕድል መኖሩን ተገነዘብን” ሲሉ አስረድተዋል-ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡
 “ሊትል” ኩባንያ በቅርቡ “ቴሌብር” የተሰኘውን የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ከጀመረውና በመንግስት ባለቤትነት ከሚመራው ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በአጋርነት እንደሚሰራ ተዘግቧል፡፡
“አንዳንድ ግሩም የኢትዮጵያ አጋሮች አሉን፡፡ በጣም ግዙፍ የሆነ  ገበያ እንዳለ ይሰማናል፤ በዚህ ሥፍራ ስኬት ለመቀዳጀት ደግሞ የበለፀገ አገር በቀልና ባህላዊ ዕውቀት ይዘው ከሚመጡ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት መስራት ይኖርብናል” ሲሉም አክለዋል ሚ/ር ቡድሃባቲ  በቃለ ምልልሳቸው፡፡



Read 1090 times