Sunday, 25 July 2021 00:00

የቀድሞ ሠራዊት አባላት ለመከላከያ ሠራዊት ነገ በአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ ያደርጋሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት በነገው ዕለት ለአገር መከላከያ ሠራዊት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ 4 ሰዓት የአብሮነትና የድጋፍ ሠልፍ ያደርጋሉ፡፡  
የድጋፍ ሠልፉን ያስተባበረው የኢትዮጵያ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መቶ አለቃ በቀለ በላይ ስለ ሁነቱ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ "የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ እኛም  ከእናንተ ጋር ነን የሚል መልዕክት ያለው የአብሮነት ድጋፍ ነው" ብለዋል፡፡
"እኛ የአሁኑ መከላከያ ሠራዊት እርሾ ነን" ያሉት መቶ አለቃ በቀለ፤ "አሁንም ሰራዊቱን በማንኛውም ተሳትፎ ለማጠናከርና ለመደገፍ ያለማወላወል ዝግጁ ሆነን ከመንግስት የሚቀርብልንን ጥሪ እንጠብቃለን" ብለዋል፡፡
አሁን ያሉት የኢትዮጵያ ውድ ልጆች የተሰባሰቡበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው ያሉት መቶ አለቃው፤ በዚሁ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው ስውር ጥቃት ሁሉ የኢትዮጵያ ጥቃት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"የሃገር ጉዳይ እድሜ አይገድበውም፤ መከላከያ በፈለገን ቦታ ሁሉ  ከጎኑ ሆነን ለእናት ሃገራችን ያለንን ሁሉ ሳንሰስት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን" ብለዋል፤ ሃላፊው ለአዲስ አድማስ፡፡
“ኢትዮጵያ አትፈርስም ምክንያቱም ዛሬም ሰው አለ!” በሚል መሪ መፈክር በሚካሄደው የድጋፍ ሠልፍ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የቀድሞ ሠራዊት አባላትና አመራሮች ተገኝተው ለመከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት ያሳያሉ ተብሏል፡፡
“በሀገር አንድነት ለመጣ ሃይል ዛሬም ክንዳችን ብርቱ ነው” ያሉት መቶ አለቃ በቀለ በላይ፤ ያለንን ወታደራዊ ልምድና እውቀት ሁሉ ተጠቅመን ሃገራችንን ከጠላቶቿ ለመከላከል የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡


Read 11362 times