Sunday, 25 July 2021 00:00

ኢትዮጵያ እጇን አትሰጥም!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ግብፆች ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባሰቡና በተናገሩ ቁጥር የሚገልጹት “ግብፅ በአረብ አብዮት እየተናጠች ባለችበት ጊዜ ውስጥ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ሳታስፈቅደን አትጀምርም ነበር” እያሉ ነው። ይህን የሚሉት ኢትዮጵያ ቱኒዝያ ላይ የዐረብ አብዮት እንዲቀጣጠል እንዳላደረገች ሁሉ ግብፅም እንዲገባ እንዳላደረገችው ሳያውቁት ቀርተው አይደለም። ማመንና መቀበል ያቃታቸው ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ባለ የውሃ ሃብቷ ላይ የፈለገችውን ለማድረግ ሙሉ  ስልጣኑ በእሷ እጅ ብቻ ያለ መሆኑን ነው። እነሱ እንደ ማንገራገሪያ የሚጠቀሙበትን እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተዋዋሉት የውሃ ክፍፍል ውል በኢትዮጵያ ዘንድ ዋጋ የሌለው መሆኑን መረዳት ስለሚቸግራቸውና ስለሚጨንቃቸውም ነው - ምክንያት የሚደረድሩት።
በተፋሰሱ የላይኛው አገሮች ላይ “የማይጣስ ድምፅ (ቬቶ ፓወር)” ሰጥቶናል የሚሉት ይህ ውል በኢትዮጵያ ጫማ ስር ወድቆ በተደጋጋሚ መደቅደቁን እያዩ ማመን ስለሚቸግራቸውም ነው እንዲህ የሚቅበጠበጡት።
በተለያየ ጊዜ እንደገለጽኩት፤ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለመወያየትና ለመመካከር የተነሳችው ግድቡ በሁለቱ ሀገሮች ላይ የሚያስከትለው የከፋ ጉዳት እንደማይኖር ለማሳመንና ለማግባባት በማሰብ ነበር። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ በእነሱ ለመታመን የተጀመረው ጉዳይ መልኩን ለውጦ ድርድር ሆነ። ድርድሩንም ቢሆን ኢትዮጵያ በክፉ አይን አላየችውም፤ በቅንነት ቀጥላበታለች።
ሁለቱ ሀገሮች ግን ልባቸው በክፋት የተሞላ ሆነ። ነገር የጀመሩት ኢትዮጵያ ይሄን ያህል ግዙፍ ግድብ ምን ይሰራላታል? መጠኑን ለምን አትቀንስም? በማለት ነው። እሱን እምቢ ሲባሉ ግድቡን የውሃ መሙላት ጊዜ እስከ 21 ዓመት እንዲዘገይ ጠየቁ። ይህ ይሆንላቸው ዘንድም ድርድሩን ወደ አሜሪካ ወሰዱት። ታዛቢ የነበረችው አሜሪካ ራሷን አደራዳሪ ብቻ ሳይሆን የመደራደሪያ ውል አርቃቂ አድርጋ ሾመች። ወትሮም ነገሩ ያላማራት ኢትዮጵያ፣ አሜሪካ ያዘጋጀችው ሰነድ ጨርሶ የሚስማማት ባለመሆኑ #በጉዳዩ መክሬበት ልመለስ; ብላ ረቂቅ ውሉን ለአርቃቂዎቹ ለአሜሪካኖች አስታቅፋቸው አዲስ አበባ ገባች። ኢትዮጵያ ልትቀበለው ያልፈለገችውን ረቂቅ ውል ሱዳንም ሳትስማማበት ቀረች። ግብፅ ብቻ ፈረመችው። ራሳቸውን እንደ እውነተኛ ተደራዳሪ አድርገው የሚቆጥሩት ግብጾች ይህንን ውል በመፈረማቸው እየፎከሩ እየተኩራሩበት ይገኛሉ።
“የግብፅና የሱዳን አሳሪና አስገዳጅ ስምምነት” ካልተፈጸመ የሚለው ጩኸት የአሜሪካውን ድርድር ኢትዮጵያ ውድቅ ካደረገችውና ጥላ ከወጣች በኋላ የተፈጠረ ወይም የተጀመረ ይመስለኛል። እነሱ አስገዳጅ የሚሉት ውል ምን ምን እንደሚይዝ የታወቀ ነገር የለም። የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎችም ሰሞኑን በሰጧቸው መግለጫዎች ሀሳቡ ድፍን ቅል የሆነባቸው መሆኑን ተናግረዋል። እንደ እኔ ግን ሱዳን ከሶስትና ከአራት ወር በፊት “ኢትዮጵያ ግድብ መስራት ብትፈልግ እንድትሰራ መፍቀድ አለብን” ስትል የሰጠችውን መግለጫ እንደ አንድ አመልካች መውሰድ ይቻላል። እነሱ የፈለጉት “እኛ በፈለግነው ጊዜ ተነስተን ግድብ የምንሰራ ህዝቦች፣ እነሱ እኛ ለምንሰራው ግድብ ፈቃድ ሰጪዎች” መሆኑን ነው። ይህ ጨርሶ አይታሰብም፤ ደግሞም አይሞከርም።
ግብፅና ሱዳን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የታላቁን ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት እንዳታካሂድ በማሰብ ለማስፈራራት አምስት ጊዜ የምድርና የዓየር ሃይል የተቀናጀ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል።
ኢትዮጵያን ጎትቶ ወደ ጦርነት ለማስገባት በማሰብም ሱዳን ድንበር ተሻግራ የኢትዮጵያን መሬት እንድትይዝ አድርገዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በማሰብ ድምጿን አጥፍታ ስራዋን ቀጠለች።
“ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ያለ ስምምነት ከተደረገ ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ማጣት ምክንያት ይሆናል” በማለት ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት ሶስት ጊዜ አጀንዳ አድርገው ያቀረቡት ግብፅና ሱዳን ሳይሳካላቸው መቅረቱም ይጠቀሳል። በፀጥታው ምክር ቤት ፊት ተገኝተው “እኛ እየገነባን ያለነው ለዓለም ስጋት የሚሆን የኒዩክሌር ማብላያ አይደለም፤ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ የሚውል የውሃ ግድብ ነው” በማለት የውሃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ስለሽ በቀለ፣ ሁለቱን አገሮች በአደባባይ አሳፍረዋቸዋል። የጸጥታው ም/ቤትም ጉዳዩ የልማት ጉዳይ በመሆኑ ሊወያይበትና አጀንዳ ሊያደርገው እንደማይገባም አስረግጠው ተናግረዋል።
ግብፆችና ሱዳኖች ተመልሰው ከተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በራፍ እንዳይቆሙ አድርገዋቸዋል። ሳይወዱ በግድም ወደ አፍሪካ ህብረት ድርድር እንዲመለሱ ሆነዋል። ይህም ኢትዮጵያ እጇን እንደማትሰጥ የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ እጅ እንደማትሰጥ ያሳየችበት ሌላው ተግባሯ “አሳሪ ስምምነት ሳንፈራረም ሁለተኛው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሌት አይካሄድም” እያሉ ሲደነፉባት ለነበሩት ግብፅና ሱዳን አስቀድማ ነግራ፣ አይናቸው እያየ ግድቡን መሙላቷ ነው።  ሌሎች መቶ ግድቦች ለወደፊት እንደምትገነባ ቀደም ሲል መናገሯ እዚህ ላይ ይታወሳል።
መጪዎቹ አዳዲስ ግድቦች በመንግስት ፕሮግራም የሚከወኑ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ደንቢ ዶሎ አጠገብ የዓለም ሎቶራል ፌዴሬሽን እንዳሰራው የቦርጣ ግድብ አይነት አንድ ሺ አንድ ግድቦችን  በክልል መንግሥታትና በሕዝብ አቅም መገንባት ይቻላል። በዚህ መንገድ የውሃ ሃብቷን ወደ ልማት በማስገባት ኢትዮጵያ እጅ የማትሰጥ ሀገር መሆኗን ደግማ ማሳወቅ ይኖርባታል።



Read 3175 times