Tuesday, 27 July 2021 00:00

የማሊው ፕሬዚዳንት ከግድያ ሙከራ አመለጡ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 መሪዋ የተገደሉባት ሃይቲ አዲስ ጠ/ ሚኒስትር ሾማለች


           በማሊ ከወራት በፊት በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ባለፈው ማክሰኞ በመዲናዋ ባማኮ በሚገኝ መስጊድ በሶስት ታጣቂዎች ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ማምለጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመዲናዋ ባማኮ በሚገኝ አንድ መስጊድ በተዘጋጀ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የጸሎት ስነስርዓት ላይ እያሉ ሁለት ታጣቂዎች ስለት ከያዘ ሌላ ተባባሪያቸው ጋር በመሆን የግድያ ሙከራ እንዳደረጉባቸው የጠቆመው ዘገባው፣ የደረሰባቸው ጉዳት ይኑር አይኑር በይፋ የታወቀ ነገር አለመኖሩን አመልክቷል፡፡
ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ጥቃቱ ከተሞከረባቸው ከሰዓታት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ነገርዬው የስራው አካል ነው፤ ምንም ችግር አልደረሰም ሲሉ ጉዳዩን ቀለል አድርገው መናገራቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
የ38 አመቱ ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ባለፈው ነሃሴ ወር በመሩት መፈንቅለ መንግስት ፕሬዚዳንት አቡበከር ኬታን በማስወገድ ጊዜያዊ መንግስት መስርተው አገሪቷን ሲመሩ እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከ3 ወራት በፊት ደግሞ ራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስ ከሳምንታት በፊት ታጣቂዎች በመኖሪያ ቤታቸው ባደረሱባቸው ጥቃት  መገደላቸውን ተከትሎ በባላደራ መሪ ስትተዳደር የቆየቺው ሃይቲ ባለፈው ማክሰኞ አሪየል ሄንሪን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሾመች ሲሆን፣ ሄንሪ አዲሱን ካቢኒያቸውን በማስተዋወቅ እስከ ቀጣዩ ምርጫ አገሪቱን የሚያስተዳድር መንግስት እንደሚመሰርቱ በቃለ መሃላ ስነስርዓቱ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡
አገሪቱን ላለፉት 5 አመታት ያስተዳደሩትን ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስን የገደሉት ታጣቂዎች ማንነት አሁንም ገና በግልጽ አልታወቀም ያለው ዘገባው፣ ፖሊስ 26 ያህል ተጠርጣሪዎችን አስሮ በመመርመር ላይ እንደሚገኝና ከእነዚህም መካከል አስራ ስምንቱ የቀድሞ የኮሎምቢያ ጦር አባላት፣ ሶስቱ ደግሞ ሃይቲና አሜሪካውያን መሆናቸውንም ገልጧል፡፡








Read 2561 times