Tuesday, 27 July 2021 13:32

ዮንሴ ዓለማቀፍ የጤና ማዕከል ከ40.ሚ በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ሊያከናውን ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማእከል በ1.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ከ40 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ለማከናወን  ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን በላከው መግለጫ አስታወቀ፡፡
በተደረሰው የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማዕከል፤ “ብሔራዊ ዘመቻ ለእውቀት አመለካከትና ባህሪ ለውጥ ስለ ህዝብ ብዛትና ተዋልዶ ጤና (በኢትዮጵያ ውስጥ የተመጠነ፣ደስተኛና ውጤታማ የሆነ ቤተሰብ ፕሮጀክት ሁለት)ን እ.ኤ.አ 2023 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ተግባራዊ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ የሚያከናውነው ከኮሪያ ዓለማቀፍ የትብብር ኤጀንሲ፤(ኮይሳ) በተገኘ 1.7 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በአዲስ አበባና ድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በአማራ፣ኦሮሚያ፣ሶማሊያ፣ትግራይና የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ውስጥ የሚተገበር መሆኑ ተጠቁማል፡፡
ፕሮጀክቱ ዮንሴ ዓለም ዓቀፍ የጤና ማዕከል በ12 ሚሊዮን ዶላር እየተገበረ የሚገኘው ጥቅል ፕሮጀክት አንድ ክፍል ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል በልማት ዕቅዱ ፑል ፈንድ አማካኝነት በኦሮሚያና ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ስድስት ወረዳዎች እንዲሁም በጌዲዮና ጉጂ ዞኖች ውስጥ በመተግበር ላይ  ሲሆን የዚሁ ፕሮጀክት ሌላኛው ክፍል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ በተመደበለት 2 ሚሊዮን  ዶላር እየተገበረ እንደሚገኝ ማዕከሉ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ዮንሴ ዓለም አቀፍ የጤና ማዕከል የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በሚገኘው ዮንሴ ዩኒቨርስቲ ዎንጁ ካምፓስ ውስጥ የተመሰረተና በዓለም አቀፍ የህብረተሰብ ጤና ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ኢንስቲቲዮት ሲሆን ዓለማቀፍ ድህነት እንዲቀንስና በዓለማቀፍ የሕዝብ ጤና ላይ ከ2030 የልማት ግቦች ጋር በተገናዘበ መንገድ አስተዋፅኦ ማድረግን ዓላማው ያደረገ ተቋም ነው፡፡


Read 2400 times