Tuesday, 27 July 2021 17:48

ድንክዬዎቹ

Written by  ድርሰት፡- ማርክ ኮኔሊ ትርጉም፡- ቃለ-ኦዝ ጥቁሬ
Rate this item
(2 votes)

  “ሙሉ ስምህን ለክቡር ፍ/ቤቱ ብትናገር?”
“ፍራንክ ዋይንጋርድ እባላለሁ”
“የመኖሪያ አድራሻ?”
“ኒውዮርክ፤ 57ኛው መንገድ”
“በምንድን ነው የምትተዳደረው?”
“በአንድ የቲያትር ቡድን ውስጥ መድረክ የማስዋብ ስራ እሰራለሁ”
“የጀምስ ድዌል ቀጣሪ ነበርክ?”
“በእርግጥ ቀጣሪው ባልባልም የእሱ አለቃ ግን ነበርኩ። ሁለታችንም ለዋና አዘጋጁ ሚስተር ቤንደር ተቀጥረን እናገለግል ነበር”
“ቴዎዶር ሮቤል የተባለውን ግለሰብ ታውቀው ነበር?”
“አዎ ጌታዬ”
“እሱም ከእናንተ ጋር ይሰራ ነበር?”
“የለም ከእሱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው የዛሬ አንድ ወር አካባቢ ለአዲሱ ትያትራችን ፤ልምምድ ስንጀምር ነው። በቲያትሩ ውስጥ አንድ ድንክ ሰው የሚጫወትበት ሚና በመኖሩ ጂሚና እሱ ከሌሎች ድንክዬዎች ጋር ለቦታው ለመወዳደር መጥተው ነበር፡፡ ያኔም ሮቤል ከሌሎች ድንኮች በቁመት ከፍ ይል እንደነበር አስተውያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ያለፈው ማክሰኞ በራቸውን ሰብረን እስከገባንበት ቀን ድረስ በድጋሜ አይቼው አላውቅም፡፡”
“በሩን ሰብራችሁ ከገባችሁ በኋላ ምን አጋጠማችሁ?”
“ሁለቱም እክፍሉ ጥግ ወለሉ ላይ ተዘርረው ነበር፡፡ የቤቱ አከራይ ሚስስ ፓይክ ከእኔ ጋር ነበረች፡፡”
“ህይወታቸው አልፎ ነበር?”
“አዎ ጌታዬ”
“ሚስተር ዋይንጋርድ ለመሆኑ አንተ መኖሪያህ ኒውዮርክ ሆኖ ሳለ ወንጀሉ በተፈፀመበት ቀን እዚህ ጀርዚ ከተማ ምን ልታደርግ መጣህ?”
“ሰኞ እለት ጂሚ ስራ አለመግባቱን ስረዳ ወደ ቤቱ ስልክ ደውዬ ነበር፡፡ ስልኩን ያነሳችው ሚስስ ፓይክ ጂሚና ሮቤል ተያይዘው መውጣታቸውን ስትነግረኝ ከሁለቱ አንዱ ከተመለሱ  እንዲደውሉልኝ መልእክት አስቀመጥኩ፡፡ በኋላ ማክሰኞ ዕለት ሚስስ ፓይክ ራሷ ደውላ የነጂሚ ክፍል ከውስጥ እንደተቀረቀረና በሩን ደጋግማ ለብዙ ጊዜ ብታንኳኳ የሚከፍትላት እንዳጣችና በሁኔታው በጣም እንደተደናገጠች ነገረችኝ። እኔም የሆነ ነገር ሆነው ይሆናል ብዬ ክፉ ጠርጥሬ በባቡር በመምጣት ቀትር ላይ እዚህ ደረስኩኝ። ከዚያም ከሚስስ ፓይክ ጋር ተባብረን በሩን በመገንጠል ክፍላቸው ገባን፡፡”
“ይሄንን ቢላዋ ከዚህ በፊት አይተኸው ታውቃለህ?”
“አዎን ጌታዬ፡፡ ወንጀሉ የተፈፀመበት ቢላዋ ነው። ከጂሚ በድን አንድ ጫማ ያህል ርቆ ወለሉ ላይ ወድቆ ነበር፡፡”
“ቅድም ክፉ ጠረጠርኩ ብለህ ተናግረህ ነበር፡፡ ይሄንን ዘግናኝ ድርጊት አስቀድመህ ታውቅ ነበር ማለት ነው?”
“ፈፅሞ አላውቅም ነበር፡፡ ጂሚ የሆነ ችግር የደረሰበት ነው እንጂ የመሰለኝ እንዲህ አይነቱን ሁኔታ ፈጽሞ አልጠበቅኩም፡፡ እሱ ሰሞኑን አለመጠን ፈርቶና  ተክዞ ነበር። ሮቤል ደግሞ ጂሚን ከደረሰበት ጭንቀት ለማውጣት ብዙም እንደማይጥር አውቅ ነበር፡፡”
“በሁለቱ ሰዎች መሀል ፀብ ቢጤ ነበራ?”
“የለም ፀብ እንኳን አልነበራቸውም። ብቻ ሁለቱም ጥልቅ ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። በእርግጥ ሮቤል መጨነቅ የጀመረው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ሮቤል የጂሚን ድንክ እህት አግብቶ ነበር፡፡ እሷ ከሞተችበት ማለትም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ጂሚና ሮቤል ሚስስ ፓይክ ቤት ተከራይተው አብረው ይኖሩ ነበር፡፡”
“አንተ ይሄን ሁሉ ታሪክ እንዴት ለማወቅ ቻልክ?”
“ጂሚና እኔ በጣም ተቀራርበን ነበር። ጥሩ ፀባይ ያለው ሰው ከመሆኑም በላይ ስራውን ከሰጠሁት በኋላ እንደ ባለውለታ ነበር የሚያየኝ፡፡ ለቲያትሩ የፈለግነው አንድ ሰው ብቻ ሆኖ ሳለ የድንኮቹ ወኪሎች ግን አስራ አምስት ያህል ድንኮችን ወደኛ ላኩ፡፡ ዳሬክተሩ ሚስተር ጌርድ ስራ ስለበዛበት እኔ እንድመርጥ ባዘዘኝ መሰረት ከሁሉ የሚያንስ የነበረውን ጂሚን ልመርጠው ቻልኩ፡፡ ከተዋወቅን በኋላ እድሉን ለሱ በመስጠቴ በጣም እንደተደሰተ ነገረኝ። ጓደኛሞች ከሆንን በኋላ ስለ እህቱ ባልና ስለሁሉም  ነገር ያጫውተኝ ነበር፡፡”
“በእሱና በእህቱ ባል መሀከል ቂም በቀል እንዳለስ አጫውቶህ ያውቃል?”
“ፈፅሞ አጫውቶኝ አያውቅም። ከሮቤል ጋር ጠንከር ያለ ቃል ተለዋውጠውም እንኳን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ እንደውም እሱ እንደነገረኝ ከሆነ በጣም ከመውደዱ የተነሳ ባለው አቅም ሁሉ ይረዳው ነበረ፡፡ ሮቤል ያለስራ ባሳለፋቸው ወቅቶች የኖረው በጂሚ ድጋፍ ነው፡፡ በቁመቱ መጨመር ምክንያት የሮቤል ህይወት እንዴት ሊበላሽ እንደቻለ ጂሚ ነግሮኛል፡፡”
“በቁመቱ መጨመር? ምን ማለትህ ነው?”
“በአንዳንድ ድንኮች ላይ የሚከሰት ድንገተኛ ክስተት ሰምቻለሁ፡፡ መጀመሪያ የሰማሁት ከጂሚ ጋ  ነበር፡፡ ብዙዎቹ ድንኮች ለአስራ አራት ወይም ለአስራ አምስት አመታት ያላቸውን ቁመት ይዘው  እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ይኖራሉ። አንዳንዶቹ ግን 30 ዓመት ሲሞላቸው ለሁለተኛ ግዜ ማደግ ይጀምራሉ፡፡ በሚቀጥሉት አንድ ወይም ሁለት ዓመታት ከአንድ ጫማ ወይም ከዚያ ትንሽ ከፍ ያለ ቁመት ከጨመሩ በኋላ እድገታቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያቆማሉ። ሆኖም ከዚያ በኋላ ተመልሰው ድንክዬ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እናም የሚፈልጋቸው አይኖርም። ሮቤልም የዚህ እጣ ተቋዳሽ በመሆኑ ከስራው ሊባረር ችሏል፡፡ ጂሚ እንደነገረኝ እና  ከሚስስ ፓርክ እንደሰማሁት ሮቤል በሁኔታው ክፉኛ ማማረር ያዘወትር ነበር፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ ኒው ዮርክ ያለው ወኪሉ ጋር ቢመላለስም ለእሱ የሚሆን ስራ ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ከዚያም ተመልሶ ወደ ጀርሲ ይመጣል። ጂሚ ስራውን እኛ ጋር ከጀመረ በኋላ ብዙውን ጊዜ ኒው ዮርክ ስለሚቆይ ሮቤል የሳምንቱን አብዛኛውን ቀናት በብቸኝነት ያሳልፍ ነበር፡፡ ወደ መጨረሻ አካባቢ ወደ ኒውዮርክ መመለሱን ጭራሹኑ አቆመ፡፡ ጂሚ ግን ሁልጊዜ  ቅዳሜ ወደ ጀርሲ መጥቶ ሊያጫውተውና ሊያዝናናው እየሞከረ እስከ ሰኞ ድረስ አብሮት ይከርማል፡፡ እሁድ እሁድ በእግር ከተንሸራሸሩ በኋላ ሲኒማ የመግባት ልምድ ነበራቸው፡፡ ሮቤል የቁመታቸውን መበላለጥ የበለጠ የተገነዘበው በጎዳና ላይ አብረው ሲንሸራሸሩ ነው ብዬ እገምታለሁ። ለሁለቱም ሞት ምክንያት የሆነውም ይህ ይመስለኛል፡፡”
“ይህን ለማለት ያስደፈረህ ምክንያት ምንድን ነው?”
“መልካም፤ ቅድም እንደተናገርኩት ጂሚ ለሮቤል በማዘን እሱን ለማስደሰት ከልቡ ይጥር ነበር፡፡ ሁለቱም ቢሆኑም ጂሚ  ምንግዜም ቢሆን ስራ እንደማያጣ ሮቤል ግን  ፈፅሞ ተስፋ እንደሌለው በሚገባ ተረድተውታል፡፡ ጉዳዩ የተጀመረው የዛሬ ሶስት ሳምንት ሰኞ ቀን ነበር፡፡ እኔ ከመድረኩ ውጪ ሳለሁ ጂሚ በጠባቡ መተላለፊያ ሲመጣ አየሁት፡፡ ለወትሮው በፈገግታ ተውቦ ምርኩዙንም እያወዛወዘ ሲመጣ አውቀው የነበረውን ጂሚ፤ ፊቱ ክብድ ብሎና ጭጎጎት መስሎ ሳየው ምን እንዳጋጠመው ጠየኩት፡፡
“ባክህን አቶ ዋይንጋርድ ደህና አይደለሁም፡፡ በጣም ፈርቻለሁ” አለ፡፡
“ለምን?” አልኩት፡፡
“ማደግ ጀምሬያለሁ” ብሎ መለሰልኝ። እንዲህ ያለኝ ልክ በሚገድል ክፉ በሽታ መያዙን እንዳወቀ ሰው ሀይለኛ ድንጋጤ ፊቱ ላይ እየታየበት ነበር፡፡ ነገሩ አስገረመኝ።  “ጂሚ ጤነኛ ነህ እንዴ? አረዘምክም፤ያው የድሮ ሚጢጢ ጂሚ ነህ” እያልኩት ልቀላልድበት ሞከርኩ፡፡ እሱ ግን  ፊቱን የበለጠ ከስክሶት “የለም እኔ አድጊያለሁ፤ 31 ዓመት ሊሆነኝ ነው፡፡ አባቴም በዚህ እድሜው ቁመት ጨምሮ ነበር፡፡ እሱ ግን ብር ስለነበረው በወቅቱ ምንም ችግር አልገጠመውም፡፡ እኔ ግን ምንም የለኝም፡፡ የግድ መስራት አለብኝ” አለኝ ፡፡
“ቁመትህ ምን ያህል ይረዝም ነበር?” ብዬ ጠየኩት።
“35 ኢንች” አለኝ
“ታዲያ ለምን በሜትር ለክቼ ምን ያህል እንደጨመርክ አታውቅም?; ብለው በድንጋጤ ወደ ኋላው እየሸሸ፤
“አልፈልግም፤ በጭራሽ ያን ማወቅ አልፈልግም” ብሎ ትቶ ወደ መልበሻ ክፍል እየተጣደፈ ሄደ፡፡ ሳምንቱን ሙሉ አለመጠን ተደብሮ ነበር ያሳለፈው። ሰኞ ቀን ፊቱ ገርጥቶና እንደ ኖራ ነጭ ሆኖ መጣ። ወደ መልበሻ  ክፍል ሜካፕ ለመቀባት ደረጃውን ሲወጣ ጠብቄው ክንዱን ያዝኩት። መንጭቆኝ ይሄዳል ብዬ ብጠብቅም፣ መልዕክቱ ያልገባኝ አይነት ፈገግታ ፈገግ እያለ ዝም ብሎ ቆመልኝ፡፡
“እዛ የእህትህ ባል ጋር ነበርክ አይደለም?”  ብዬ ጠየኩት፡፡
“አዎ” አለኝ፡፡
“ለምን ከእሱ አትርቅም? እሱ እንደሆነ ሰባራ እድሉን ከማማረር ሌላ ምንም የማያውቅ ሰው ነው። ከእሱ ጋር በመዋል የራስህን ህይወት እያጨለምከው እንደሆነ ገብቶሃል?” ብዬ የተሰማኝን መከርኩት፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ፀጥ ብሎ ምንም ሳይናገር ከቆየ በኋላ እንዲህ አለኝ፡-
“ሮቤል እኮ ብቸኛ ነው፡፡ ጓደኛ ይፈልጋል። ወጣም ወረደም ችግሩ ያለው ከእሱ ጋር ሳይሆን እኔው ራሴ ጋር ነው፡፡ ከአሁኑ ሁለት ኢንች ያህል እረዝሜያለሁ።” በመገረም እንደ አዲስ ከላይ እስከ ታች ተመለከትኩት። ከተረበሸ ገፅታው በስተቀር  ምኑም ምኑም ያው የድሮው ጂሚ ነበር፡፡
“ተለክተህ ነው ያወከው?” ብዬ ጠየኩት።
“አልተለካውም” አለኝ፡፡
“ታዲያ በምን አወክ? ናና ልለካህ” እያልኩ ብወተውተውም፣ በጣም ስላስፈራው ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም ሳምንቱን ሙሉ ሲሸኘኝ ከረመ፡፡ ቅዳሜ ለት ማታ ወደ ቤቱ ለመሄድ ሲዘጋጅ ከኋላው ደርሼበት ደህንነቱን ስጠይቀው ደህና እንደሆነ ቢነግረኝም፣ እንደ እውነቱ ከሆነ ከምንግዜውም በላይ ፊቱ ገርጥቶ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ በህይወት ያየሁት እንግዲህ ያኔ ነው፡፡;
“ዘበኛው ጎርሲትዝ ሬሳዎቹ በክፍሉ ጥግ እንደነበሩ መስክሯል፡፡ መጀመሪያ እናንተ በሩን ገንጥላችሁ ስትገቡም እዛው ነበሩ?”
“አዎን ጌታዬ”
“ሁለቱ ሰዎች ሊሞቱ የቻሉት ጂሚ ድዌል ቁመቱ በመጨመሩ ምክንያት ስራ ያጣ ይሆናል በሚል ፍርሀት ተገፋፍተው ተስፋ በመቁረጥ ራሳቸውን በራሳቸው አጥፍተው ነው ብለህ ታስባለህ?”
“የለም ጌታዬ! ነገሩ ፈፅሞ እንደዚያ አይደለም”
“ምን ማለትህ ነው?”
“እኔና ሚስስ ፓይክ ከክፍላቸው ስንገባ ቢላዋውን አይቼ በጣም ተገርሜ ነበር። ትልቅነቱ የስጋ ቤት ቢላዋ ያክል ነበር፡፡ ሚስስ ፓይክ ይሄ ቢላዋ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከኩሽናዋ ጠፍቶባት የነበረው የእሷ ቢላዋ እንደነበረም ነገረችኝ፡፡ ድንክዬዎቹ ወስደውት ይሆናል ብላ ግን ጨርሶም አልጠረጠረችም ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ እኔም ራሴ ቢላዋውን እነጂሚ የመስረቃቸው ነገር አልተዋጠልኝም፡፡ እዛ ክፍል ውስጥ ሳለሁ ግን ሁሉም ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ አልጋ ላይ ተቀምጦ የነበረውን አጭር ምርኩዝ አግኝታችሁታል?”
“ይሄ ነው?”
“አዎ እሱ ራሱ ነው፡፡ የጂሚን ቁመት መጨመር ጉዳይ ልቀበለው ያልቻልኩት ነገር ነበር፡፡ እናም ሚስስ ፓይክ ስለጠፋባት ቢላ ስትነግረኝ ነገሮችን አገጣጥሜ የሆነውን ሁሉ ደረስኩበት፡፡ ወንጀሉ ከመፈፀሙ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ጂሚ ቢላዋውን እክፍሉ የሆነ ቦታ ያገኘዋል፡፡”
“በአጋጣሚ ስትል ምን ማለትህ ነው?”
“ምክንያቱንም ቢላዋውን ከሚስስ ፓይክ ኩሽና የሰረቀው ሮቤል ነበር፡፡ እሱ ስራ ፈትና ብቸኛ ሆኖ  ሳለ የጂሚ ባለስራ መሆን በቅናት እሳት ሲያቃጥለው ኖሯል፡፡ እናም የጂሚን እድል ለማሰናከል አንድ ዘዴ መፈለግ ነበረበት፡፡ ጂሚ ዘወትር ይይዛት የነበረችውን ዱላ ለዚህ ተንኮል ብሎ በሰረቀው ቢላዋ በማያስታውቅ ሁኔታ ከስር በመከርከም ቁመቱን ቀስ በቀስ ማሳጠር ጀመረ፡፡ የዋሁ ጂሚም  ቁመቱን ከዱላዋ በጣም መርዘም በተገነዘበ ጊዜ ማደግ የጀመረ መስሎት አለቅጥ ተረበሸ፡፡ የሮቤል አላማም ተሳክቶ የቀድሞ ደስተኛ ህይወቱ ደፈረሰበት፡፡ ሆኖም አደጋው የደረሰ ዕለት ጂሚ ቢላዋውን ክፍል ውስጥ ሲያገኘው ሮቤል ለምን ስራ እንዳመጣው  በመጀመሪያ ሳይገረም አይቀርም፡፡ መቼም ሮቤል ነገሩን ሊነግረው ስለማይችል ራሱ ነገሩን ደርሶበት ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞም ሮቤል ነግሮት ይሆናል፡፡ ወጣም ወረደም ጂሚ የዱላው አናት ላይ ያለውን ትኩስ ግዝግዝ ያያል፡፡ በሮቤል ውለታ ቢስነት እብድ የሆነው ጂሚ በያዘው ቢላዋ ሮቤልን ወግቶ ከገደለው በኋላ የራሱንም ህይወት ለማጥፋት በቃ፡፡”
ምንጭ፡- (አዲስ አድማስ፤ ሐምሌ 1 ቀን 1992 ዓ.ም)


Read 1707 times