Saturday, 31 July 2021 00:00

“መንግስት ህወኃትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግድ ይገባል” - ተቃዋሚ ፓርቲዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የአማራ ክልልን የክተት አዋጅ ተቀብሎ አባላቱ እንዲዘምቱ መመሪያ ያስተላለፈው መኢአድ፤ የመላው ኢትዮጵያውያን አንድት ድርጅት፤ “የፌደራል  መንግስቱ ህወኃትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግድ ይገባል” አለ።
የአማራ ከልል ያስተላለፈውን የክተት አዋጅ ጥሪ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል፤ የገለጸው ፓርቲው፤ “በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር በህወኃት ሃይል የከፋ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ጠቁሙ፤ ይሄን አደጋ መመከት ብቻ ሳይሆን ስጋቱን እስከ መጨረሻው ማስወገድ የሚቻለውም ሁሉም በአንድነት ሲቆም ነው ብሏል፡፡”
የመኢአድ ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ  ላይ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ “ህወኃት እያደረሰ ካለው ጥፋት አንፃር የአማራ ክልል ያደረገው የክተት ጥሪ እንዲያውም የዘገየ ነው፤ ሁሉም ይሔን ጥሪ   በፍጥነት ተቀብሎ፣ በሃገር አድን እንቅስቃሴው ላይ ሊሳተፍ ይገባል” ብሏል፡፡
መላ አባላቱና ደጋፊዎቹ የመክተት ጥሪውን እንዲቀበሉ ጥሪ ያቀረበው መኢአድ፤ በተለይ በርካታ አባላቱ ወታደራዊ ልምድ ያላቸው እንደመሆኑ የሚደረገውን የሃገር ማዳን እንቅስቃሴ በእጅጉ ያግዛሉ ብሎ እንደሚያምን በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያ ለጥሪው አዋንታዊ ምላሽ በመስጠት አሸባሪው ትህነግንና መሰሎቹን በአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጠራርጎ ለማጥፋትና ለፍርድ ለማቅረብ የሚደረገውን ዘመቻ  እንዲቀላቀል የጠየቀው ፓርቲው፤ መንግስትም  ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግሮ ጦርነቱ በአጭሩ የሚቋጭበትን ሁኔታ እንዲፈጥር ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ የአማራ ክልል ያወጀውን የክተት ጥሪ አመራሩና አባላቱ ተቀብለው ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ እንደሚያደርጉት የገለፀ ሲሆን ጦርነቱም ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል።
ትህነግን ለአንዴና በመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይገባል ብሏል አብን በመግለጫው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ም/ቤትም የመንግስትን የክተት ጥሪ እንደሚደግፍ በህወኃት ላይ የሚደረገው ዘመቻ ሊቀላጠፍ እንደሚገባው ገልጿል፡፡

Read 738 times