Saturday, 31 July 2021 00:00

በዘንድሮ ክረምት 2 ሚ. ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተጠቆመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

አደጋውን ለመቋቋም የ3.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ያስፈልጋል
                                
              እስከ ነሐሴ መጨረሻ ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሎ በሚጠበቀው የዘንድሮ ክረምት፣ 2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
ጠንካራ ቅዝቃዜና ዝናብ እያስተናገደ የሚቀጥለው የክረምቱ ወቅት፣ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 56 ዞኖችና 244 ወረዳዎች የከፋ የጎርፍ ስጋት መደቀኑ ተገልጿል።
የጎርፍ አደጋ ስጋቱ በጋምቤላ ሁለት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ 10  ያህል ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ከ45 በላይ ወረዳዎች፣ በአማራ ክልል 4 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች፣ በሶማሌ ክልል 8 ዞኖች ላይ፣ በአፋር በዞን 1 እና ዞን 2 በሚገኙ ወረዳዎች፣ በትግራይ 2 ዞኖች፣ በደቡብ ክልል 8 ያህል ዞኖች፣ በሲዳማ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች፣ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በዘንድሮ ክረምት ለጎርፍ አደጋ  ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሏል።
የጎርፍ አደጋው ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም፣ የ3.6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የጎርፍ አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለአደጋው ተጋላጭ ይሆናሉ የተባሉ አካባቢዎች በተለይም ዝቅተኛና ተዳፋታማ ቦታ ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ለቅድመ አደጋ መከላከል ሥራዎች ንቁና ተባባሪ  እንዲሆኑ ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል።



Read 7844 times