Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 08 September 2012 11:33

የ5 ደቂቃ ስራ በ15 ቀን... “ሃዘንን በስራ መወጣት” እንዲህ አይደለም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ የ7ሺ ኮንዶምኒዬም ቤቶች እጣ የወጣው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው። እጣው እንደወጣ፤ ወዲያውኑ ዝርዝር መረጃውን የመስተዳድሩ ዌብሳይት ላይ መጫን ይቻል ነበር - ሁሉም ሰው በኢንተርኔት እንዲያየው። መረጃውንና የስም ዝርዝሩን ዌብ ሳይት ላይ መጫን የአምስት ደቂቃ ስራ ነው። በእርግጥ የቴሌ የኢንተርኔት አገልግሎት ቀርፋፋ መሆኑን እናውቅ የለ? እሺ ይሁን... ነገርዬው 15 ደቂቃ ይፈጃል እንበል። ግን እንዳያችሁት፤ መረጃው ዌብሳይት ላይ ሳይጫን፤ 15 ቀን አለፈው። እንዲህ ነችና “የኢንፎርሜሽን ዘመን”!

“የአምስትና የአስራ አምስት ደቂቃ ስራ፤ ለምን 15 ቀን ፈጀ?” የሚለው ጥያቄ ትልቅ እንቆቅልሽ ነው። የእጣውን መረጃ (የስም ዝርዝሩን) ዌብ ሳይት ላይ መጫን፤ ለከተማው መስተዳድር ከብዶት ይሆን? ሊሆን አይችልም። የአንድ ቀን ስልጠና በተሰጠው ሰራተኛ ሊከናወን የሚችል ስራ ነው። ይህችን ታክል ብቃት በመስተዳድሩ ውስጥ ይጠፋል? ጠፍቷል ከተባለ፤ ዋናው ጭንቀታችን ስለ ኮንዶምኒዬም እጣ መሆኑ ይቀርና... እስከነጭራሹ መስተዳድር የሚባል ነገር ስለመኖር አለመኖሩ ወደ መጠየቅ እንገባለን። ስለዚህ፤ “ይህችን ታክል ብቃትማ ጨርሶ ሊጠፋ አይችልም” ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ሶስት ወይም አራት “ፋይሎችን” ዌብሳይት ላይ መጫን፤ ለመስተዳድሩ ከባድ ዳገት ይሆንበታል ብሎ ማሰብ ራሱ እጅግ ከባድ ነዋ።

እና ታዲያ ምክንያቱ ምንድነው? ምናልባት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞት ከተፈጠረው ሃዘን ጋር የተያያዘ ይሆን? በእርግጥ፤ በሃዘኑ ምክንያት የመንግስት መስርያ ቤቶች አልተዘጉም። በየእለቱ በሚዲያ የሰማነውም፤ “ሃዘናችንን በስራ እንወጣዋለን” የሚለውን ሃሳብ ነው።

እንዲያም ሆኖ፤ በበርካታ የመንግስት መስርያ ቤቶች፤ በርካታ ስራዎች ሲጓተቱና ሲስተጓጎሉ ሰንብተዋል - በሃዘኑ ሰበብ። በተለይ ዳተኞችና ሰነፎች፤ የአገሬውን ሃዘን እንደ ጥሩ ሰበብ የቆጠሩት ይመስላል። ምናልባት፤ የኮንዶምኒዬሙ እጣ የዚህ ሰበብ ሰለባ ሆኖ እንደሆነስ? እጣው ከወጣ በኋላ፤ ወዲያውኑ በደቂቃዎች ውስጥ በኢንተርኔት ማሰራጨት እየተቻለ፤ እንዲያ የሚዘገይበትና ድምፁ የሚጠፋበት ሌላ ምክንያት ይኖራል?

የእጣው ስም ዝርዝር ለማየት ሲጠባበቁ የነበሩ ሰዎች፤ መረጃው ሲዘገይባቸው ማጠያየቃቸው አልቀረም። ከእሁድ ጀምሮ የዘገየው የእጣው ስም ዝርዝር፤ በአምስተኛው ቀን ሃሙስ እለት በኢንተርኔት እንደሚለቀቅ ነበር የተነገራቸው። ከሁለት ሳምንት በፊት ሃሙስ መሆኑ ነው። ግን እንደተባለው አልሆነም።

በእርግጥ፤ በማግስቱ አርብ እለት፤ የመስተዳድሩ ዌብ ሳይት ላይ፤ “የሰባተኛው ዙር የኮንዶምኒዬም እጣ አሸናፊዎች” የሚል መሪ ርዕስ (Link) ገብቷል። መሪ ርዕሱን ወይም ሊንኩን ስትከፍቱ፤ የአሸናፊዎቹን ስም ዝርዝር ታገኛላችሁ ማለት ነው። ሲከፈት ግን ምንም የለም። እንደገና ሌላ ሳምንት፤ ሌላ ሃሙስና አርብ መጣ። “የእጣ አሸናፊዎች” የሚለው መሪ ርዕስ አልተለወጠም። እዚያው እንዳለ ነው። የተለወጠ ነገር ቢኖር፤ መሪ ርዕሱ ሲከፈት፤ “በቅርብ ቀን” የሚል ፅሁፍ እንዲታይ ተደርጓል (coming soon ይላል።) አንዲት መረጃ ዌብ ሳይት ላይ ለመጫን፤ ከ5 ደቂቃ በላይ ከፈጀ፤ ጭራሽኑም ከ15 ቀን በላይ ሲዘገይ ያስገርማል። ጭራሽ፤ እንደ ትልቅ ግንባታ “በቅርብ ቀን” የሚል ፅሁፍ ተለጥፎበት ሲጓተት ደግሞ፤ “ነገር እየተበላሸ ይሆን?” ያሰኛል። “ሃዘናችንን በስራ እንወጣዋለን” የሚለው የብዙዎች ንግግር በተግባር ሲታይ፤ እንዲህ ጥቃቅን ስራዎችን እንደ ግዙፍ ፕሮጀክት ማጓተት ከሆነ፤ ሌላ ትልቅ ሃዘን ይሆናል። “ቢሆንም፤ ‘ነገር ተበላሸ’ አያሰኝም” የሚሉ እንደሚኖሩ እገምታለሁ። እውነት አላቸው። በመንግስት መስርያ ቤት ውስጥ፤ ስራዎችን ማጓተትና ማንዛዛት ለአገራችን አዲስ ነገር አይደለም። የለመድነው ነባር ባህላችን ስለሆነ፤ “አሁን፣ ምንም የተበላሸ ነገር የለም፤ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር እንደድሮው ነው” ሊባል ይችላል። እውነት ነው። “በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሞት የተፈጠረውን ሃዘን በስራ እንወጣዋለን፤ ጀግና አይሞትም” የምንል ከሆነ ግን፤ በሰበብ አስባቡ ስራ የማጓተት ነባር ባህልን አቅፎ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። ስራን የማቀላጠፍ አዲስ ባህል ለመፍጠር መጣጣር ያስፈልጋል። ቢያንስ ቢያንስ፤ ጥቃቅን ስራዎችን አለማጓተት! የ5 ደቂቃ ስራዎችን ለማከናወን፤ 15 ቀናትን አለማጥፋት! ለማንኛውም የእጣው ስም ዝርዝር በዚህ ሳምንት ማክሰኞ እለት በመስተዳድሩ ዌብ ሳይት ላይ ተጭኗል።

 

 

Read 2843 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:46

Latest from