Saturday, 31 July 2021 00:00

ህወኃት በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወኃት ቡድን በትግራይ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤ በስደተኞቹ ላይ የሚፈፀመው ጥቃት በእጅጉ እንዳሳሰበው አስታውቋል፡፡
ኤርትራውያን ስደተኞች ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ድርጅት መሥሪያ ቤት ደጃፍ ላይ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ነበር ተቃውሟቸውን ያሰሙት፡፡ ከመፈክሮቹ መካከልም “እኛ ስደተኞች እንጂ ወንጀለኞች አይደለንም”፣  “በብዙ  የተበደልን ስደተኞች ነን፤ ጉዳያችን በሦስተኛ ገለልተኛ ወገን ይታይልን”፣ “በኛ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት በአስቸኳይ መቆም አለበት”፣ “እኛ ስደተኞች ነን” እንዲሁም “እንደናንተው ሰው ነን” የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
በሰልፉ ላይ በርከት ያሉ ህፃናትም መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ከሰሞኑ 6 ኤርትራውያን ስደተኞች በህወኃት ሃይሎች መገደላቸውን የጠቆመ  ሲሆን የአሜሪካ መንግስት በበኩሉ፤ በስደተኞቹ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገልጧል፡፡  
የህውኃት ሃይሎች በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንዲሁም ዛቻ ከማድረስ በአስቸኳይ እንዲታቀቡም የአሜሪካ መንግስት አሳስቧል፡፡

Read 7861 times