Saturday, 31 July 2021 00:00

የህዳሴ ኃይቅና ኃይል፣ የጠፈር ሽርሽርና ሮኬት፣ የኦሎምፒክ ልህቀትና ንግስ... ምን ለያቸው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • በ1 ሜትር ውፍረት፣ በ4 ሜትር ቁመት፣ ኢትዮጵያን ዞሮ የሚመለስ ግንብ ቢኖር አስቡት። ለዚህ የሚበቃ ኮንክሪትና ድንጋይ ነው - ለህዳሴ                        ግድብ ግንባታ የዋለው። እንዲያውም ይተርፈራል
          • ፋልኮን ሄቪ የተሰኘው ሮኬት፣ ከምድር ለመምጠቅ 4,000 ኩንታል ነዳጅ ይጠቀማል። ግማሽ ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እንደማለት ነው። ግማሽ  ያህሉ ለ3 ደቂቃ በረራ አይበቃውም።
                             


            የተቀደሰ ተግባር፣….
 አንድም ኑሮን ለማደላደል ነው - እንደ ህዳሴ ግድብ ግንባታ። ኤሌክትሪክ  ለኑሮ የማይሆነው ነገር የለማ መብራት፣እሳት፣ ሞተር፣ ፋብሪካ፡፡
አንድም ወደ ከፍታ ለመምጠቅ ነው  - ይሄ የፈር ቀዳጅ ግለሰቦች ስራ ነው፡፡ ከሱስ በማይተናነስ የሙያ ፍቅርና በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማበብ እንደጀመረው የጠፈር ቢዝነስ።
አንድም መንፈስን ለማደስ ነው። ድንቅ ነገርን፣ በተለይም የብቃት ልህቀትን አድምቆ ለማሳየት - በየ4 ዓመቱ እንደሚደገሰው የኦሎምፒክ ንግሥ።
በሌላ አነጋገር፣ ምን እንደለያቸው ለመግለፅ፣ የተቀደሰ ተግባር፣ አንድም አካላዊ፣ ወይም አእምሯዊ አልያም መንፈሳዊ ነው እንላለን።
ምንስ አንድ አደረጋቸው?
አካላዊ፣አእምሯዊና መንፈሳዊ ብለን አንዱን ከሌላው ለይተን ብንመነዝራቸውም፣…. በአንዱ ውስጥ ሌላውም አለ። እንዲያውም፣ ሊነጣጠሉ አይችሉም። ከተቀደሰ ሃሳብ ያልመነጨ፣በተቀደሰ ሙያ የማይፈፀም፣ በተቀደሰ ስብዕና የማይፀና፣አንዳችም የተቀደሰ ተግባር የለም። የሕይወት ልምላሜ፣ ሶስቱን ገፅታዎች ያጣምራል፡፡ የአእምሮ፣ የአካል፣ የመንፈስ ህብር ነው። ይሄም አንድ ያደርጋቸዋል። የህዳሴ ግንባታ፣ የጠፈር ቢዝነስ፣ የኦሎምፒክ ንግስ... የቅዱስ ህልውና ገፅታዎች ናቸው።
በቀጥታ ለኑሮ እንዲያገለግል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ የተሰራውን  ግድብ ተመልከቱ፡፡ ከኑሮ ገፅታ በተጨማሪ ልህቀትን አግዝፎ የሚያሳይና መደነቅን የሚያፈልቅ መንፈሳዊ ገፅታ አለው፡፡ ድንቅ የጥበብ ግንባታውንና እውን የሆነውን ኃይል በማየት ብቻ እርካታን ያገኙበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የኦምሎፒክ ድግስን አስተውሉ፡፡ መንፈስን የሚያድስ የድንቅ ብቃት ንግስ ነው ኦሎምፒክ፡፡ ግን፣መንፈሳዊ ድግስ ነው፡፡ መንፈሳዊ ቢሆንም ግን፣ እህልና ውሃ ባያቀርብልንም፣ በቀጥታ ለኑሮ የሚጠቅሙ ገፅዎችም አሉት፡፡ ለውድድር ሳይሆን ለጤንነት ተነስተው የሚሮጡ ሰዎች በኦሎምፒክ ማግስት ይበረክታሉ።
እንዲያም ሆኖ፣ የኦሎምፒክና ውድድሮች ዋና ባሕርይ መንፈሳዊ ነው፡፡ የብቃት ልሕቀትን በማሳየት መንፈስን ማደስ፣ነው ክቡር የኦሎምፒክ መንፈሳዊ አላማ፡፡  የዛለ የደከመ፣ የደበዘዘ የደረፈሰ መንፈስን ማደስና ማንቃት፣ ማንጻትና ማፍካት ነው። የኦሎምፒክ ውድ በረከት፡፡ ደግሞም፣ ከምትሃት የማይተናነስ ነው ሃያልነቱ ለነገሩ፣ ምትሃት የማይመስል ድንቅ ተግባር የለም።

የሕዳሴ ግድብ “ጉዶች”
ሌላውን ሁሉ ትተን፣ የኤሌክትሪክ መብራት ብቻ ብናይ እንኳ፣ አስራሚ ነው። ስንትና ስንት ጋራና ሸንተረር አቆራርጦ፣ በመቶ በአምስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ባለው ዋና ማብሪያ ማጥፊያ በመተማመን ነው፤ ማታ ቤታችን የማይጨልመው።
የተዘረጉት የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ከሰው ጣቶች የበለጠ ውፍረት የላቸውም። የሚንቀሳቀስ፣ የሚጎርፍ ነገር አይታይባቸውም። ነገር ግን፣ የማያንቀሳቅሱት፣ የሚያሾሩት ነገር የለም። ባትሪውን ይሞላልሉ፣ አምፖሉን ያበራሉ፣ ምጣዱንና ምድጃውን ይለኩሳሉ፤ ያግላሉ። የቴሌቪዥኑን አይን ይከፍታሉ። በእልፍ ልሳን ያናግራሉ። ባቡሩን ያስጋልባሉ። ወፍጮውን ፋብሪካውን ሲያሽከረክሩ ውለው ያድራሉ - ደከመኝ፤ ሰለቸኝ የለም። የሕዳሴ ግድብ፣ የ20 ሚሊዮን ሰራተኞች ያህል ነው ጉልበቱ። ቀን ከሌሊት ያለ እረፍት የሚሰራ። እንዲሁ ሲታይ፣ ለልብስ ማንጠልጠያ ከተዘረጋ ሽቦ አይደለም፡፡ ግን፤ ብርሃን ይሆናል፣ እሳትና ግለት ይሆናል። ብረት ማቅለጫ ይሆናል። ኮንተይነር ተሸካሚ ክሬን እየሆነ ያነሳል ይጭናል። ማሽኖችን ያሽከረክራል። ፋብሪካዎች ያንቀሳቅሳል። ወደር የሌለው ምትሃት ይመስላል።
የዚህ ሁሉ መነሻ፣ የዛሬ 150 ዓመት የተገለጠ የእውቀት ግኝት ነው። በማግኔቶች መሃል የሚንቀሳቀስ ሽቦ ውስጥ፣ የኤሌክትሪክ “ምትሃት” ይፈጠራል። የተጠቀለለ ሽቦ ውስጥ ኤሌክትሪክ ሲተላለፍ ደግሞ፣ የማግኔት “ምትሃት” ይፈጠራል። የማይክል ፋራዳይ የሳይንስ ግኝት ነው።
በእርግጥ፣ የማግኔትና የኤሌክትሪክ ባህሪያት አዲስ የሰው ፈጠራ አይደሉም። ጥንትም የነበሩ ዘላለማዊ የተፈጥሮ እውነታዎች ናቸው። የማይክል ፋራዳይ ልህቀት፣ የእውቀት ግኝቱ ነው። የተፈጥሮ እውነታዎችን አስተውሎ መርምሮ አጣምሮ ተገነዘበ፡፡ የራሱ ገንዘብ አደረጋቸው።  ይሄው፣የአእምሮ ገንዘብ፣ወደ ቤተ ሙከራ ቴክሎጂ ቢመነደግም፣ከዚያ አላለፈም-በፋራዳይ ዘመን፡፡ ገና ለኑሮ የሚሆን አንዳችም የሚቀመስ እህል፣ጠብ የሚል ውሃ አልወጣውም፡፡ ያኔ ገና ለመኖሪያ ቤት መብራት ለፋብሪካዎች  የልብ ትርታ ለመሆን አልበቃም፡፡ የአእምሮ ገንዘብና የፈር ቀዳጅ የሙያ ፍቅር እንጂ፣ ገና ኪስ የሚገባ ገንዘብ የኑሮ መተዳደሪያ አልሆነም ነበር፡፡
እድሜና ምስጋና ለፈርቀዳጆች ይሁንና በዚያው ቀልጦ አልቀረም፡፡ ግንዛቤውና የእውቀት ግኝቱ ወደ እልፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እየተሻገረ፤ የህዳሴ ግድብ ላይ ደርሷል።
የሕዳሴ ግድብ”፣... እንደምናው፣ ዘንድሮም “የአባይ ማደሪያ” ሆኗል። ይሄ ለኑሮ የሚበጅ “ጥሩ፣ አመታዊ ሪፖርት ነው” ማለት ይቻላል። ግን ከዚያም በላይ ነው ትርጉሙ፡፡ ለኑሮ ብቻ ሳይሆን ለመንፈስም ነው በረከትነቱ፡፡
ለወትሮ፣ የአባይ ውሃ፣ እንደአመጣጡ የሚጎርፍ፣ ከማዶ እስከ ማዶ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደነፋ ጥሏቸው የሚሄድ ነበር። ምንስ አማራጭ አለው? የአባይ ጌታ፣ ቁልቁለት ነው፡፡ የአባይ ነጂ፤ የምዕተ ዓመታት ጋላቢ።
ጎጃም ባህርዳር አቅራቢያ፣ ከጢስ አባይ ፏፏቴ ብንጀምር እንኳ፣ የኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ፣  የቁልቁለት መዓት አይጣል ነው፡፡ ከ1200 ሺህ ሜትር ይበልጣል - ቁልቁለቱ።
ለሺህና ለእልፍ ዓመታት አባይን እያንደረደረ ሲያስጋልበው የነበረም፣ ሃይሉ ጌታ አጅሬው ቁልቁለት ነው፤ የማይጋፉት ዘላለማዊ የተፈጠሮ ህግ። “የመሬት ስበት” ብለን ልንጠራውም እንችላለን፡፡
አሁን፣ በህዳሴው ግድብ፣ አዲስ የእልፍ ዓመታት ታሪክ እየተፈጠረ ነው። አስከ አሁን ድረስ ያልነበረ የህዳሴ ኃይቅ ዛሬ በእውን ተፈጥሯል። ታዲያ፣ የተፈጥሮ ህግ ላይ በማመፅ አይደለም፡፡ ወይም የውሃና የቁልቁለት ዘላለማዊ  እውነታን በመሻር አይደለም። እንዲያውም፣ የሰው ልጆች፣ ድንቅና ብርቅ ታሪክ መስራት የሚችሉት፣ “በተፈጥሮ ህግ አይነኬነት” ላይ በመተማመን ነው።  እናም፣ከፊት ለፊት  ህዳሴ ግድብ የተሰኘ አዲስ ተራራ ስንገነባለት ውሃው ከገልቢያው ያርፋል። ግን አርፎ እንዲቀመጥ ብቻ አይደለም፤ ግደብ የተገነባው። ግድቡ፣ የውስጥ የጎርፍ መውረጃ አሸንዳዎች ፣ሰው ሰራሽ ፏፏቴዎች አሉት።
ውሃውን በዘፈቀደ የሚያንደረደሩ አይደሉም። መክፈቻ መዝጊያ አላቸው፣ የአቅጣጫና የፍጥነት መቆጣጠሪያ የተበጀላቸው ፏፏቴዎች ናቸው። ግድብ ውስጥ በተከፈቱት በተዘረጉት አሸንዳዎች፣ “ሰው ሰራሽ ጎርፍ” ቁልቁል ይምዘገዘጋል። ኃያልነቱ ያስደንቃል። በአማካይ፣ በአንድ ሴኮንድ 1.5 ሚሊዮን ሊትር  ውሃ ይጎርፋል።
በአንድ ሰዓት፣ ከ5 .4 ቢሊዮን ሊትር በላይ።
በቀን፣ 130 ቢሊዮን ሊትር፡፡
በወር፣ 3.9 ትሪሊዮን ሊትር፡፡
በዓመት፣ 46 ትሪሊዮን ሊትር (46 ቢሊዮን ሜትር ኩብ)፡፡
 የህዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ፏፏቴ፣ ከአዲስ አበባ የውሃ ፍጆታ፣... በሺህ እጥፍ ይበልጣል። ድንቅ ነው። ግድቡ ግዙፍ ነው። ለዋነኛው ግድብና ከጎን በኩል ለተሰራው የኮርቻ ግድብ የዋለው የኮንክሪትና የድንጋይ ብዛት፣ አጃኢብ ያስብላል።
1 ሜትር ውፍረት ያለው ሃይለኛ ግንብ ይታያችሁ። ተንጠራርተን የማንደርስበት የ4 ሜትር ቁመት ይኑረው። ግንቡ፣ ከጥግ እስከ ጥግ ኢትዮጵያን ዞሮ የሚመለስ ግንብ ቢሆን አስቡት። ለዚህ የሚበቃ ኮንክሪትና ድንጋይ ነው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የዋለው። እንዲያውም ይተርፋል፡፡
የውሃው ብዛት፣ የግድቡ ግዝፈት፣ የአዲስ ኃይቅ ልደት፣ የሰው ሰራሹ ጎርፍ ጉልበት፣... ድንቅ ናቸው። መደነቅና አድናቆት ደግሞ የመንፈስ ጣዕም ናቸው የህይወትን ትርጉም የሚያደምቁ፡፡ ነገር ግን፣ ግድቡ፣ ለመደነቅ ብቻ ታስቦ የተሰራ አይደለም።
ቁልቁል የሚምዘገዘገው ሰው ሰራሽ ፏፏቴ፣ ተርባይኖች ላይ ነው ጉልበቱን የሚያሳርፈው። ለአይን በሚያስቸግር ሃይለኛ ፍጥነት ያሽከረክራቸዋል። ተርባይኖቹ፣ በተራቸው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ዘንጎችን ያሽከረክራሉ።
ለስፌት መኪና እንደሚዘጋጅ ክር፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ዘንጎችም በሽቦ የተጠቀለሉ ናቸው። ያው፣ ሽቦ በማግኔት አጠገብ ሲንቀሳቀስ የኤሌክትሪክ ሃይል ይመነጫል። በሽቦ ውስጥ ኤሌክትሪክ ሲተላለፍ ደግሞ፣ የማግኔት ሃይል ይፈጠራል። ተመጋጋቢ ናቸው።
ነገሩ፣ የዚህን ያህል ቀላል ነው - እንደምትሃት። የዚያኑ ያህል ደግሞ ከባድ ነው። የማግኔቶቹ ጉልበትና፣ ቁጥር፣ ርቀትና አፈጣጠር፣ ...በዘፈቀደ የሚወሰን ነገር አይደለም፡፡ ከብዙ እውቀቶች፣ ከተራቀቁ ቀመሮች፣ ከድርብርብ ከጥልፍልፍ ስሌቶች፣ ከፍቱን ዲዛይኖችና ከአዳዲስ ፈጠራዎች፣ ሁሉ ነጥረውና ተጣርተው የሚወለዱ የጥበብ ውህደቶች ናቸው፡፡
ኤሌክትሪክ ማመንጫ ዘንጎች ላይ፣ ሽቦዎች ችምችም ብለው የሚጠቀለሉበት ስርዓት፣  ጌጠኛ ጥልፍ ይመስላል፡፡ ግን ለጌጥ አይደለም፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ለመፍጠር ከእውቀቶችና ከጥበቦች ህብር የሚመጣ ድንቅ ዘዴ ነው፡፡ የሽክርክሪቱ ፍጥነትና አቅጣጫም እንዲሁ።
ከመነሻው፣ የሽክርክሪት (የእንቅስቃሴ) ሃይልን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል መቀየር ነዋ - የማሽኑ ተግባር፡፡ በሃይል ሲሽከረከር፣ ነው ሀያል ኤሌክትሪክ የሚፈጠረው። አንዱ ከሌለ፣ ሌላኛውም አይኖርም።  ታዲያ፣ዘንጎቹን የሚያሽከረክር ሃይል ከየት ይምጣ? እንደመኪና በነዳጅ ማሽከርከር ይቻላል። ግን፣ ውድ ነው። በየአመቱ የሁለት የሶስት ቢሊዮን ዶላር ነዳጅ መግዛ እንዴት ተደርጎ።
እንደ ጥንቱ በሰው ጉልበት መጠቀምስ? ለሕዳሴ ግድብ ብቻ፣ የ20 ሚሊዮን ሰው ጉልበት? የማይሆን ነገር ነው፡፡ ቢሆን እንኳ የህይወት ብክነት እንጂ ቁም ነገር አይደለም። የጎርፍ የፏፏቴ ጉልበትስ? ይሄ፣ ሃያል ጉልበት ነው።
 ነገር ግን፣ የወንዝ ጎርፍ ወይም የገደል ፏፏቴ፣ “ያኛውን ተርባይን ላሽከርክር” ብሎ፣ አቅጣጫና ፍጥነቱን አነጣጥሮ አይጎርፍም። ቁልቁለቱን እየተከተለ ይነጉዳል። አመቱን ሙሉ ላገልግላቸው ብሎ የጎርፍ መጠኑን አይቆጣጠርም። እንዳመጣጡ እንደ ዝናቡ ሁኔታ እየተንደረደረ ጥርግ ይላል - ቁልቁለቱን ተከትሎ። የቁልቁለቱን ግፊት፣ ወይም የመሬትን ስበትን ለመቋቋም ነው የግድብ አስፈላጊነት። እንዳይፈስ  ውሃውን ተሸክሞ እንደመያዝ ቁጠሩት - የግድብ አገልግሎት። ይዞ ተሸክሞ ለመቅረት አይደለም። የቁልቁለቱን ጎርፍና ፏፏቴውን እየገታ ውሃውን አጠራቅም ይይዝና፤ በአሸንዳ ውስጥ አዲስና እጅግ ኃይለኛ ጎርፍ ይፈጥራል። እስከ 140 ሜትር ከፍታ የተጠራቀመው የተከመረው ውሃ፣ አሸንዳዎች ሲከፈቱለት፣ ቁልቁል መንደርደሩ፣ ተፈጥሮው ነው። በአሸንዳ ውስጥ ሲሆን  ጉልበቱ ይጨምራል። አቅጣጫውም ሄዶ ሄዶ ተርባይኖች ላይ ያነጣጠረ ይሆናል።
በአጭሩ፣ የዘፈቀደ የቁልቁለት ጎርፍን ለመግታትና ወደ ተርባይን የተነጣጠረ ሃይለኛ የቁልቁለት ጎርፍ ለመፍጠር ነው  የግድቡ አገልግሎት።
የሕዳሴ ግድብ እንደ ጠፈር ሮኬት ነው፡፡
ነገሩ እንደጠፈር ጉዞ ነው። ከመሬት ስበት ለማምለጥ፤ ነው ሮኬቶች አገር ምድሩን የሚያንቀጠቅጡት፡፡ ከመሬት ስበት ጋር ነው ትግሉ። ዛሬ በአገልግሎት ላይ ካሉት መንኮራኩሮች መካከል፣ በጣም ሃያሉን መንኮራኩር ተመልከቱ።
ከመሬት ለመነሳት፣ ከአውሮፕላኖች ሞተር የበለጠ ጉልበት ያላቸው 27 ሞተሮችን ይለኩሳል። አጠቃላይ የመንኮራኩሩ ክብደት 14,700 ኩንታል ነው። ከዚህ ውስጥ 13,400 ኩንታሉ ነዳጅና ነዳጁን የሚቀጣጥል ኦክስጅን ነው።
4,000 ኩንታል የሮኬት ነዳጅ፣ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ቤንዚን እንደማለት ነው። ሮኬቱ ከምድር በተነሳ በ5 ደቂቃ ውስጥ፣ ነዳጁ ያልቃል ማለት ይቻላል። ሩብ ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን፣ በ5ደቂቃ ፉት ብሎ የሚጨርስ ማሽን...
ይሄ ሁሉ፣ የምድር ስበትን አሸንፎ ወደ ህዋ ለመጓዝ ነው ለ10 ደቂቃ ሽርሽር ወይም ሳተላይት ለማምጠቅ ሊሆን ይችላል። ከምድር 400 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ የደረሰው ሳተላይት፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚምዘገዘግ ነው - በሰዓት ከ28ሺ ኪሎ ሜትር በላይ እየተወነጨፈ ነው። በዚያ ፍጥነት፣ ከምድር ርቆ፣ማብቂያ በሌላው ግልቢያ እየሸመጠጠ ጠፍቶ እንዳይቀር፣ መላው ምንድ ነው?
ሳተላይቱ፣ ከመሬት ያለውን ርቀት ጠብቆ የሚሸከረከረው፤ በሌላ ምክንያት ሳይሆን፣ በመሬት ስበት አማካኝነት ነው። የመሬት ስበት ነው መተማመኛው። ከመሬት ሲነሳ፣ ትልቁ ፈተና ከመሬት ስበት ጋር ታግሎ ማሸነፍ ነው።
ህዋ ውስጥ በመሬት ዙሪያ ርቀቱን ጠብቆ ለመሽከርከር ደግሞ፣ ዋና መተማመኛው የመሬት ስበት ነው።
የግድቡም ተፈጥሮ ተመሳሳይ ነው። በመሬት ስበት አማካኝነት ቁልቁል የሚነጉደውን ጎርፍ ይገታል፤ በአሸንዳ ውስጥ ብቻ፣ወደ ተርባይን አነጣጥሮ፣ ሰው ሰራሽ ጎርፍን ይፈጥራል፡፡ በመሬት ስበት አማካኝነት፣ ሃያል ግፊት እንደሚፈጠር በመተማመን፡፡ ታዲያ የግድቡ ግንባታ፣ የኃይቅ ልደት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማንጨት፣ ሮኬት መስራት፣ ወደ ጠፈር ተስፈንጥሮ መመለስ፣ ሳተላይት ማምጠቅ…. ማንኛውም ኑሮ ለማደላደል፣ እንዲሁም አዲስ ምዕራፍ ለመክፈትና ወደ ከፍታ ለመጓዝ የሚከናውን ቅዱስ ተግባር፣ ሁሉ እጅግ ክቡር እና ድንቅ የመሆኑ ያህል፤ የሁሉም ምንጭ፣የሰው ልጅ ድንቅ ብቃት ነው፡፡
የሰው ልጅ ድንቅ ብቃትና ልህቀትን በማሳየት መንፈስን “ማደስ ደግሞ፣ የኦሎምፒክ ድርሻ ነው። የብቃት ልህቀት በአደባባይና በእውን የሚታይበት፣ እንዲሁም የሚከበርበት ድግስ ነው- ኦሎምፒክ የብቃት የልህቀት ንግስ!

Read 7867 times