Wednesday, 04 August 2021 00:00

አውሮፓ ለ70 በመቶ ህዝብ የኮሮና ክትባት የመስጠት ዕቅዷን አሳካች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሳዑዲ ወደተከለከሉ አገራት የሄዱ ዜጎችን ለ3 አመታት ከጉዞ ልታግድ ነው


             የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን እስከ ሃምሌ ወር መጀመሪያ ድረስ ከአጠቃላይ አዋቂ ዜጎቻቸው ለ70 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ዙር ለመስጠት የያዙትን ዕቅድ ማሳካታቸውን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
ህብረቱ ባለፈው ማክሰኞ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳስነበበው፣ በአሁኑ ሰዓት በየዕለቱ በአማካይ 3.1 ሚሊዮን ያህል ክትባቶችን በመስጠት ላይ የሚገኙት አባል አገራቱ 70 በመቶ ያህል ዜጎቻቸውን ቢያንስ ለአንድ ዙር ለመከተብ የያዙትን ዕቅድ ሲያሳኩ፣ አንከተብም የሚሉ ዜጎቿን ለማሳመን ጊዜ የፈጀባት አሜሪካ በበኩሏ፤ 69 በመቶ ያህል ዜጎቿን ብቻ ነው ለመከተብ የቻለችው፡፡
የአውሮፓ ህብረት አገራት 70 በመቶ ዜጎችን በመከተብ ከአሜሪካ ቀዳሚ ቢሆኑም፣ በሁለት ዙር ሙሉ ክትባት በመስጠት ረገድ ግን አሜሪካ የበለጠ ውጤታማ መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ ሙሉ ክትባት ያገኘው 49.1 በመቶ ያህሉ ሲሆን በአውሮፓ ግን 47.3 በመቶው ብቻ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ በአለማቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ለመከተብ ከቻሉ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መካከል ዴንማርክ፣ ማልታ፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስና ስፔን እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች እንዳይስፋፉ ለመከላከል ያቀደው የሳዑዲ አረቢያ መንግስት፤ ኢትዮጵያ፣ አፍጋኒስታን፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካና ቱርክን ጨምሮ የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ የጉዞ ክልከላ ወደጣለባቸው የተወሰኑ አገራት የተጓዙ ዜጎቹን ለ3 አመታት ያህል ከአገር እንዳይወጡ እንደሚከለክልና ሌሎች ከፍተኛ ቅጣቶችን እንደሚጥልባቸው ማስጠንቀቁ ተዘግቧል፡፡
የሳዑዲ አረቢያ የአገር ውስጥ ሚኒስቴርን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ጠቅሶ አረብ ኒውስ ባለፈው ማክሰኞ እንደዘገበው፣ የአገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ ወደለያቸውና ዜጎቹን እንዳይጓዙባቸው ወይም እንዳይመጡባቸው ወደከለከላቸው አገራት የተጓዙ ዜጎች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልባቸውና ለ3 አመታት ያህል ከአገር እንዳይወጡ እንደሚከለከሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአገሪቱ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ስጋት አለባቸው ብሎ የዘረዘራቸውና የጉዞ ክልከላ ገደብ የጣለባቸው ሌሎች አገራት አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ሊባኖስ፣ ፓኪስታን፣ ቬትናም እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡


Read 6198 times