Saturday, 08 September 2012 11:33

መንግስት ለሕዝብና ለተቋማት ይታመን፣ በሕዝብና ተቋማት ይተማመን

Written by  መጥምቁ ዮሐንስ
Rate this item
(0 votes)

የማክስ ዌበር ክላሲካል ሊደር ሺፕ ቲዎሪ(1947) የመሪዎችን ሚና አስመልክቶ የተናገሩት ጥቅስ ለጽሁፌ መነሻ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ እንደ ማክስ ዌበር እምነት መሪዎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ብቸኛ ሚና እንዲጫወቱ የሚያደርጋቸው ተጓዳኝ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሙያዊ ተቋማትና የሕዝቦች ሚና የቀጨጨ ሲሆን አሊያም ተቋማቱ ጨርሶ በማይኖሩበትና እንደሌሉ በሚቆጠሩበት ጊዜ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡የሃገሪቱና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ሰሞኑን በሰጧቸው ግለሰባዊም ሆነ ድርጅታዊ መግለጫዎችና ኢንተርቪዎች፣ በማያሻማ ቋንቋ ያረጋገጡትና የሰጡት ምስክርነት ቢኖር ከሃያ አንድ ዓመት አገዛዝ በኋላ ዛሬም  ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሌሏት መሆኑንና አሉ ከተባለም ተቋማቱ ያልተጠናከሩና ለይስሙላ የሚንቀሳቀሱ እንደነበር ሲሆን አገሪቱ በአጠቃላይና ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ምን ያህል በጠቅላይ ሚኒስትሩ መዳፍ ውስጥ እንደነበሩና በዚህም ምክንያት በቀጭን ክር ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ቀሪው የኢህአዴግ አመራርም ባለፉት ሃያ አንድ አመታት እራሱን ወደታች አውርዶ ከህዝብ ጋር ባለመወዳጀቱና ባለመተሳሰሩ በሕዝብና በሃገር ስም ከመማል ይልቅ በጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ እስከመማል ደርሷል፡፡ የሃገራችንም ሆነ የዓለማችን ነባራዊ ሁኔታ ከቶም የማይሻሻልና የማይለወጥ፣ አልፎ ተርፎም በዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ የማይመራ ይመስል ስለማይበረዝ፣ ስለማይከለስና ስለማይሻሻለው የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ፍልስፍና መሰብክ ግዴታችን ሆኗል፡፡

ከዚህ አኳያ ስንመዝነው ማክስ ዌበር ከ65 ዓመታት በፊት በተነበየው መሰረት፣ ዛሬ  የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እረፍት የጋረጠው ነገር  ቢኖር  የግለሰብን ሚና በተጋነነ መልኩ በማጠናከር አምልኮን ማስረጽ ወይም ጠንካራ ዴሞክራሲዊ ተቋማትን በመገንባትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በማስፈን መካከል ያለውን ግልጽ አደጋ ነው፡፡ ማክስ ዌበር  ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘበትን ይህንን ሃሳቡን በቅጡ ስንመዝነው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ የታየውን የባዶነት ስሜትና መደናገር፣ በሕዝባችን ውስጥ የነገሰውን የጭንቀትና የፍርሃት ስሜት መንስኤና ምክንያቱን እንድንረዳ ከማገዙም በላይ የኢህአዴግም ሆነ የሕዝባችን ፈተና በግለሰብ ተክለ-ሰውነት ላይ የተገነባ ስርዓትን እያመለኩ በመቀጠልና ሕዝባዊና ተቋማዊ ስርዓትን በመትከል መካከል የተደቀኑ ምርጫዎች ውጤት መሆኑን ያሳየናል፡፡

ሰሞኑን እንደተከታተልነው የልማቱና የእድገቱ ባለቤት ሕዝብ መሆኑ ተዘንግቶ፣ ልማትና እድገት  የዜጎች የማይገሰስ  መብትና የመንግስት ግዴታ መሆን ተረስቶ፤ ልማቱና እድገቱ ግለሰባዊ ተክለ-ሰውነትንና ሰብእና ተላብሶ ሲቀርብ የምንረዳው ነገር፤ በኢህአዴግ በኩል ጉዳዩ በዚህ መልክ እየተገፋበት ያለው የስልጣን ዘመናቸው ማስቀጠያ አይነተኛ ስልት አድርገው ስለወሰዱት  ነው ያስብላል፡፡ ምናልባትም  በጥሞና ላዳመጠና  በመስመሮቹ መካከል ማንበብ ለቻለ፤ ኢህአዴግ ለማስረገጥ የሚፈልገው በኛ ታድላችኋል፡፡ እኛ ባንሆን ኖሮ እጣ ፈንታችሁ ድህነትና ረሃብ ይሆን ነበር የሚል ዓይነት ዜማ ያለው ነው፡፡  ኢህአዴግ ይህንኑ ዜማውን ደጋግሞ ማዜምንና ስጋትን በዜጎች መካከል ማስፈኑን የስልጣን ዘመኑ ማራዘሚያና የመደላድሉ እርካብ አድርጎታል፡፡

ዜጎች ሃዘናቸው የምር እንደነበር ማንም አሌ አይለውም፡፡ ይህም ሆኖ ግን እራሳቸውን ከምንም በላይ ዝቅ አድርገው ልባቸውን በመስበር “በሕልማቸውም ቢሆን ያላለሙትን ተአምራዊ ልማት” ያቀዳጃቸውን መሪ  ማንነት ከፍ አድርገው እንዲዘምሩና የኢህአዴግን ወራሽነት እንዲያረጋግጡ በተዘዋዋሪ መንገድ የስነ-ልቦና ተጽእኖ ተደርጎባቸዋል፡፡ ቀሪዎቻችን ደግሞ የመሪ ሚና ምን እንደሆነና ምን እንደነበር እስኪጠፋንና እስኪደናገረን ድረስ  ተደናብረው በሚያደናብሩ “ትውፊቶች” ስንናጥ ከርመናል፡፡ የሃዘን ድባቡና ጫናው ቁልቁል ሰቅዞ ይዞን መንቃት አቅቶን ከርመናል፡፡

ታላላቅ የነበሩ መሪዎች ለዘመናት ስለ መሪነት  ያወሱትን በዚህ አጋጣሚ መመርመር ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ መሪዎች በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አንድ አይነተኛ ዜጋና በተለይ ደግሞ  በአደራ በሚሰጣቸው  ሃላፊነት ልክ የዜግነትና የተጣለባቸውን የመሪነት ሚና በቅጡ መጫወት እንዳለባቸው  ይታወቃል፡፡ ይህ ማለት ግን የሕዝብን  አጠቃላይ ሚና ይተካሉ ማለት አይደለም፡፡ ሃገር ዘላቂና ጥልቅ የሆኑ የብዙ ትውልዶች መስተጋብር ውጤት በመሆኑ ሃገር ከመሪም ሆነ  ከአንድ ትውልድ በላይ ለዘመናት የሚዘልቅ ነው፡፡  የልማት፣ የእድገት፣ የብልጽግናና የትልቅነት ጥያቄዎች መነሻቸው በነዚህ ዘመናት በተፈጠሩ መስተጋብሮች ውስጥ አልፎ በደማችን ውስጥ በሰረጸ እውነታ ላይ የተመሰረተ እንጂ በአንድ ዘመን በድንገት የተፈጠረ ብልጭታ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ እኛም በሀገሪቱ ላይ ዛሬ በድንገት የተከሰትን አዲስ ፍጡሮች አይደለንም፡፡ ከትወልድ የወረስንና ከትውልድ ጋር የተዋረስን ነን፡፡ ከዚህ አኳያ እንደልማትና እድገት ባሉና በሕዝብ ይሁንታና ባለቤትነት ብቻ ያለሰጭና ከልካይ ሊረጋገጡ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መሪዎች ሊሰጣቸው የሚገባው ሽፋን እኛነታችንን እንድንጠረጠርና ሁለንተናዊ ማንነታችንን ሊፈታተን ባልተገባ ነበር፡፡ መሪዎች ከሕዝባዊ አጀንዳዎች ሁሉ ልቀው መቀረጻቸውና ማጣፊያ እስኪያጥር ድረስ “ትውፊታቸው” ተጋኖ መቅረቡ ከታሪክም ሆነ ከዴሞክራሲያዊ ጽንሰ ሃሳብ ጋር የሚጋጭ  በመሆኑ  ሰሞኑን  በመገናኛ ብዙሃን ዙርያ የታየው ዝንባሌ በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ የተክለ-ሰውነት አምልኮ እስከዚህ ድረስ ስር ሲሰድ ትውልድን ለመቅረጽም ሆነ ትውልድን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ላይ ከባድ ተጽእኖ ሊፈጥር ስለሚችል ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰሞኑን በተደጋጋሚ የተደመጠው የእኔነትና የእኛነት ጉዳይ ሌላው አሳሳቢ ነጥብ ነው፡፡ “እኛ” የሚለው ቃል ለዘመናት “እኔነትን” ተክቶ  በአጼው ዘመን በሞላ፣ በተለይ ደግሞ በደርግ የመጨረሻ ዘመናት ላይ በማደናገርያነት በሰፊው ሲሰራበት ለማስተዋል እድል አግኝተናል፡፡ እውነተኛው እኛነት ግን የዘመናችን እኔነትን ከተካው አደናጋሪ የእኛነት መንፈስ ጋር በፍፁም እንደማይገናኝ በእኛነት ስም ከሚነገረው ይልቅ ባልተነገረውና በገሃድ ከተተገበረው ለመረዳት ይቻላል፡፡

የኦስትርያ ተወላጅ የነበረውና የአስተዳደር ፍልስፍና ኤክስፐርቱ ፒተር ድራከር  “ታላላቅ መሪዎች “እኔ” አይሉም፡፡” ይላል፤ ሲቀጥልም ታላላቅ መሪዎች “እኔ” ማለትን የማይፈቅዱት ቃሉን መሸሽ ስለሚፈልጉ ሳይሆን “እኔ” የሚለውን ቃል ስለማይቀበሉትና “እኛ” የሚለውን ቃል ከእምነታቸው በመነጨ [በልባቸው] ውስጥ ስለተከሉት ነው፡

የስኮትላንዱ ደራሲና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ስቴትስማን ጆን ቢከን በተራው “የመሪዎች ሚና መሆን ያለበት በሕዝቦች ላይ አዲስ ታላቅነት መጫን ሳይሆን በውስጣቸው የነበረውን ታላቅነት መቆስቆስ ነው፡፡” ይላል

ላኦ ሱ የተባለው የጥንታዊ ቻይና ፈላስፋም “ታላላቅ መሪዎች ከሕዝባቸው ጋር መሳ ገጥመው ጎን ለጎን በአብሮነት ስለሚጓዙ፣ ሕዝቦቸውም የራሱ እኩሌታ አድርጎ ስለሚወስዳቸው እንደልዩ ዜጋ አይመለከታቸውም ፡፡ ታላቅነቱ ያልሞላላቸው ሌሎቹ መሪዎች ደግሞ አድራጊና ፈጣሪ ተደርገው ስለሚሳሉ ሕዝቡ አለቅጥ ያወድሷቸዋል፡፡ አምባገነን መሪዎችን ግን ሕዝቦች ስለሚፈሯቸው፣… ይጠራጠሯቸዋል… የሚያዟቸውንም ያደርጋሉ፡፡ ታላላቆቹ መሪዎች ሚናቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ሕዝቦች በተሰራው ሁሉ ስለሚኮሩና የባለቤትነት መንፈስ ስለሚያድርባቸው ስራውን የሰራነው “እኛ ሕዝቦች” ነን ይላሉ፡፡” በማለት የታላቅ መሪዎች ሚና መነሻና መድረሻው ሕዝብ የሃገሩና የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ ሳይሆን ባለቤት ማድረግ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡

መሪዎች እስከዛሬ ካደረጓቸው የስልጣን ሽግግሮች መካከል በተለይ በተፈጥሮ ህመም ወይም በአደጋ ያረፉ 57 መሪዎችን መርጠው ጥናት ያደረጉት ሃውስማን፤ ጆንና ኦኪን (Haussmann et al. 2005, Jones and Olken 2008) ልማትና እድገት ከግለሰብ መሪዎች ሰብእና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው መስክረዋል፡፡ ልማትና እድገት ከግለሰብ መሪዎች ጋር ከተሳሰረም ማክስ ዌበር እንደጠቀሱት ጠንካራ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ሙያዊ ተቋማት ባለመኖራቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግለሰብ መሪዎችም ያልተገደበ ስልጣንና ባለቤትነትን ያለተቀናቃኝና ከልካይ ስለሚቆጣጠሩት ሃገርንም ሆነ ሕዝብን ማንኛውንም ዋጋ አስከፍለው የልማቱና የእድገቱ አምጭና አከፋፋይ ይሆናሉ፡፡ ለጥቆም በከባድ ዋጋ የተገኘው ልማት ባለቤት መሆናቸው ተረጋግጦ ይሞገሱበታል፣ ይወደሱበታል፡፡ ደም ተፍቶ፣ አፈር ግጦ የሰራው ሕዝብ ሚናው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ይወርዳል፡፡ ምናልባትም አስከሬናቸው በሙዚየም እንዲቀመጥ መመኘትም ይከተላል፡፡ ሕዝቡም የልማቱ ግንባር ቀደም ባለቤት ሳይሆን ተራ ተጠቃሚ ሆኖ ይቀራል፡፡ ሕዝባዊ ባለቤትነት የሌለው ልማትም ሆነ እድገት እንደአስፈላጊነቱ በየወቅቱ ለሚታቀድለት መደብ እንዲያድር እየተደረገ ልማቱ ሂያጅና መጭ ይሆናል፡፡የአንድ አገር ልማትና እድገት መሰረቱ ሶስቱ የኢኮኖሚ ግብአቶች ናቸው፡፡ መሬት (Land)፣ የማምረቻ መሳሪያ፣ ጥሬ ገንዘብ (capital, capital goods), ጉልበት (labor) እና ለእድገትና ለልማት የተመቻቹ ፖሊሲዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች መሪዎች በሚከተሏቸው ርዕዮተ ዓለሞች ምክንያት ተቀይደው ሲያዙ፣ ለልማትና ለእድገት አይነተኛ ሚናና አቅም ያላቸው ወይም መፍጠር የሚችሉ ዜጎች መሰረታዊ ከሆኑ የኢኮኖሚ ግብአቶች ጋር እንዳይቀራረቡና እንዳይታረቁ ይሆናሉ፡፡ ዜጎችን መሰረት ያደረጉ የልማትና የእድገት ጥያቄዎች አደጋ ይጋረጥባቸዋል፡፡ ለጥቆም መንግስት የሚባለው ተቋም በውክልና ካገኘው ስልጣን በላይ ርቆ በመሄድና ሁሉን እወክላለሁ በሚል  ፍፁማዊነት   እራሱን በባለቤትነት አግዝፎ  ሁሉን ሰጭና ከልካይ ይሆናል፡፡ እጦትና ጉድለት ደግሞ  ሰጭና ከልካዩን ሽቅብ እንዲያዩ ያስገድዳል፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተውም ይኸው ነው፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር የመንግስት ነው፡፡ ሰሞኑን ከሰማነው ምስክርነት ተነስተን ስናጤን፣ የኢትዮጵያን ለየት የሚያደርገው ደግሞ  መንግስት ማለት በአብላጫው፣ ምናልባትም በብቸኝነት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደነበሩ መረዳታችን ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ዴሞክራሲን ያሰፈኑ ስርዓቶችን እንመልከት በነዚህ ስርዓቶች ውስጥ ትክክለኛውን ርዕዮተ ዓለም በመከትል  ልማትንና እድገትን ማስፈን፣ የሚያተጋና የሚያሰራ ፖሊሲ ማመንጨትና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት የመሪዎች የእለት ተዕለት ስራቸው ነው፡፡ ስራቸውንም የሚሰሩት ብቃት ባላቸው ኢክስፐርቶቻቸው አማካኝነት ይሆናሉ፡፡ ለምን ቢባል መሪው ሁሉንም ነገር ሊያውቁ እንደማይችሉና አውቃለሁ ብለው ቢያስቡም መስራት እንደሌለባቸው እሙን ነው፡፡ መሪዎች ትክክለኛውን ርዕዮተ ዓለም በመከተላቸው ምክንያት ተክለ-ሰውነታቸውን የሚገነቡበት አንዳችም እድል የሚሰጣቸው አሰራር የለም፡፡ ልማትና እድገት ከመጣም መሰራት ያለበትን በትክክል ለመስራታቸው ማረጋገጫ ከመሆን አያልፍም፡፡ ከልማቱና እድገቱ በኋላ የሚገኝ ሽልማት ካለም ሽልማቱ የሚሆነው በድጋሚ መመረጥና ከ21 ዓመት እጅግ በጣም ላነሰ ጊዜ ሃገርንና ሕዝብን ማገልገል ብቻ ነው፡፡

ከላይ ለመረዳት እንደሚቻለው ልማትና እድገትን ለማስፈን የመሪዎች ሚና መሆን የሚገባው ሁሉን ተቆጣጥሮ ሰጭና ከልካይ መሆን ሳይሆን ሃገርን ወደ ውድቀት ከሚወስዱ እንደጦርነት ካሉ መንገዶች መራቅ፣ ዜጎች ለልማትና ለእድገት እንዲተጉ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን ማመንጨትና ሰላምና ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ሲሆን ሊያደሙት የሚችሉትን ስራ መርጠው በመስራት፣ ሌላውን ስራ ለሚሰሩት ኤክስፐርቶች መተውና በግምገማውና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ መሳተፍ ነው፡፡ ልማትና እድገቱን ማምጣትና ቀጣይነቱንም ማረጋገጥ የመሪዎች ስራ ሳይሆን የዜጎች ጉዳይ መሆን ይገባዋል፡፡ በመውረስና በመቆጣጠር፣ በማከፋፈልና በማዳረስ ላይ የተመሰረት ልማትና እድገት ዘለቄታ የሌለው ከመሆኑም በላይ የሌላውን ሃብት በመቀራመት ላይ ስለሚመሰረት የአደረግሁልህና  የእኔነት አሻራ አያጣውም፡፡ እኔነት ደግሞ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደርና በራስ የመተማመን ጠንቅ ነው፡፡

በርካታ መሪዎቻችን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲፈጥሩና ለሺህ ዓመታት የዘለቀውን ኢትዮጵያዊ ታላቅነት ሲከልሱና ሲበርዙ፤ ከሃገሪቱና ከሕዝቡም በላይ ገዝፈውና ሰፍነው ሲወደሱ መኖራቸው አሌ የማይባል መራራ እውነታ ነው፡፡ ዛሬም ታሪክ እራሱን እንዳይደግም ስጋት አለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አምባገነኑን የደርግ ስርዓትን ታግሎ መጣል የቻለ ድርጅት ለድል ከማብቃት ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በዘለቀ የአመራር ዘመናቸው ይጠቅማል ብለው ያመኑበትን ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ባደረጉት ገንቢ አስተዋጽኦ ምክንያት በታሪክ የሚዘከሩትን ያህል ዴሞክራሲንና ሰብአዊ መብትን ከማረጋገጥና ተቃዋሚውን  ከማዋከብና ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ በቂ ስራ አልሰሩምና በእኔ በኩል በታሪክ ተወቃሽ ናቸው እላለሁ፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ከማስከበር አኳያ ትልቅ እርምጃ የተራመዱትን ያህል ኢትዮጵያን ለብተና የሚዳርግ የመንግስት አከላለል ስርዕትን በመገንባታቸው ይወቀሳሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስን በእያንዳንዱ ጉዳይ ታሪክ ሊዘክራቸው የሚገባው በአንጻራዊነትና በዚህ መንገድ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ከቀለሙ ቀነስ ከእውነታው በርከት አድርጎ ሰብእናቸውን መዘከር ለሳቸውም ክብር ለታሪካቸውም መሰረት መጣል ያስችላል፤ መጭውን ትውልድም “ነበር እንዴ?” ከማለትና ከመደናገር እንታደገዋለን፡፡

ዛሬ ላይ ሆኜ መነሻው ከየት እንደሆነ በቅጡ ለማወቅ ቢያዳግተኝም፤ ነፍስ ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ የሃገርና የመሪዎች ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ለረጅም ጊዜ ከአዕምሮዬ ልፍቀው ያልቻልኩት አንድ ትንግርት ነበር፡፡ ከአካባቢዬ ይሁን ከመምህራኖቼ፣ ከቤተሰብ ይሁን ከዘመድ አዝማድ እርግጠኛ መሆን ባልችልም አጼ ሐይለስላሴ ከሞቱ ፀሃይ እንደምትጠልቅ፣ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳችን እንደምንጨራረስና ለጥቆም ኢትዮጵያ እንደሃገር እንደምትፈራርስ  እንዳምን ተደርጌ ኖርያለሁ፡፡ ነፍስ ማወቅ ደጉ፤ ዛሬ ያን ጽንሰ ሃሳብ ስሰማ እጅግ የኮረኮሩት ያህል የሚያስቀኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ሰዎች እገሌ ወይም እገሊት የሚባለው መሪ፣ አስተዳዳሪ፣ ሃላፊ፣ ገዢ…  ወዘተ ከሃላፊነታቸው ከወረዱ፣ ከስራቸው ከለቀቁ፣ ከተባረሩ ወይም ከሞቱ ሰማይ ይደፋል፤ ሕይወት ይቆማል በማለት ሊያስረዱኝ ሲሞክሩ ሳቄ ይመጣል፤ አበክረው ሲወተውቱኝ  ደግሞ  ስሜቴ ወደ ሃዘኔታ ይለወጣል፡፡ በተለይ ደግሞ በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ መሪዎች እንዲህ አይነቱን ጉዳዩ አለቅጥ አጋነው የሰው ዘርን አይምሮ በፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ፣  ተጽእኖ ሲያዋክቡትና ግራ ሲያጋቡት በመጨረሻም እጁን ሲሰጥና አሜን ብሎ ሲቀበል ማየት ያስደነግጣል፤ ያሳስባልም፡፡ ጉዞው ወዴት ነው እንድንል ያስገድደናል፡፡

ፕሮፓጋንዳን ዘመናዊ ካደረጉት ግለሰቦች መካከል በሰፊው የሚወራለት አንድ ግለሰብ የተዛባ መረጃን ደጋግሞና ያለማቋረጥ በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ እንዲያቃጭል በማድረግ፣ እያሳደጉና እያጎለበቱ ደጋግሞ በማዛመት የሃሰት መረጃው ተቀባይነትን እንዲያገኝ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለጉዳዩ ባይተዋር የነበረውን ጭምር የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል፡፡ የሰሞኑ ኢትዮጵያ ሁኔታ ከዚህ ጋር ምን ያህል እንደሚጣጣም ባላውቅም ሃገሩ  ሁሉ ለኢቴቪ ከተለቀቀ የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ መጨረሻ እስከምን ድረስ ሊለጠጥ እንደሚችል ገላጭ ምሳሌ መሆኑን ግን አልጠራጠርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፤ ዜና እረፍታቸው ከተሰማ ጀምሮ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች  የነበራቸውን  የግል ሚና ዘክሯል፡፡ ሊለመድና ሊወደስ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የሉምና ምን ይውጠናል በሚል ቀቢጸ ተስፋ መብከንከንና  ሰማይና ምድር እንደተደፋብን፣ ቀኑ እንደጨለመበን እየዘከሩ  ሕዝብን ለመምራት መከጀል በራስ ላይ እባብ እንደመጠምጠም የሚቆጠር አባዜ ነው፡፡ ህዝብ አጥብቆ በያዘው፣ በቅጡ በተረዳውና ቀና ደፋ በሚልበት ጉዳይ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ መጋበዝ፣ መጨረሻው አቻ የማይገኝለት ውድቀት እንደሚያስከትል ከወዲሁ መማር የግድ ይላል፡፡ኢህአዴግ ከሃዘኑ በስተጀርባ ተቀምጦ ሲያቀነባብረውና ሲለቀው የከረመው ረጅም፣ ዘለቄታ የሌለው፣ አንዳንዴም እርስ በርሱ የሚጋጭ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያስገነዘበን ነገር ቢኖር ድርጅቱ ሕዝባዊ ተቀባይነቱ በግለሰብ ሰብእና ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በቂ ምስክርነትን ከከፍተኛ አመራሮቹ ያለወትዋች ተገንዝበናል፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ስጋቱ በተጨማሪ  የተረዳንለት ነገር  ቢኖር በድርጅታዊ ቅርጹ ላይ ያለው ክፍተት  እንደተጠበቀ ሆኖ  ስርዓቱ በፈጠራቸው  ሕገ-መንግስታዊ ተቋማት ላይ ምን ያህል የእምነት ችግር እንዳለበት ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ አሳዛኝ የነበረው ጉዳይ በሃዘኑ ስርዓት ውስጥ የኢህአዴግን ተቀባይነትና የራዕይ ወራሽነት ለማረጋገጥ በማሰብ ሂደቱ እጅግ እንዲራዘም መደረጉና አንዳንዴም በፕሮፓጋንዳ የተበተበ ከመሆኑ የተነሳ እውነትነቱና ሃሰቱን ለመለየት እጅግ አዳጋች ሆኖ መክረሙ ነው፡፡

በአጠቃላይ ትናንትን ከዛሬ አወዳድረንና ትንፋሽ ወስደን ሂደቱን በቅጡ ስናጤነው፣ ከዚህ በኋላስ ማለታችን ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እንደ ሃገር ምን ተማርን? እንደ ሕዝብስ ምን እንማራለን? እዚህ ጋ የአንድ መበለትን የጾም ተረት በምሳሌነት ማውሳቱ ጠቃሚ መስሎኛል፡፡መበለቷ ለጾም መያዢያ ስክን ያለ ዶሮ ወጥ ሰርተው በማዘጋጀት በሂደቱ ስለደከማቸው ሳይበሉት ሌቱ ይነጋል፡፡ በጠዋት ተነስተው ጉዳቸውን ሲረዱ ቤተ ክርስትያን ሄደው ቄሰ ገበዙ የገጠማቸውን ዘርዝረው ዶሮውን ስለበሉት እንዲጠብሏቸው ይጠይቃሉ፡፡ ቄሰ ገበዙም አጉረምርመው ይጸብሉና ጾሙን ይቀጥላሉ፡፡

ፍልሰታ ሲደርስም መበለቷ እንደለመዱት ስክን ያለ ዶሮ ያዘጋጁና ከመአዛውና ከአምሮቱ የተነሳ እጅግ ቋምጠው ቄሰ ገበዙ ጋር ይሄዱና አምሮቱ አላስተነፍስ እንዳላቸውና እንደበሉ፣ ለዚህም እንዲጠብሏቸው ይማጸናሉ፡፡ እርስ በርሱ በሚጋጨው ተጽኖአቸው የተበሳጩት ቄሰ ገበዝም “ምነው እርሶ ደግሞ ጾሙ ሲገባ አላስገባ ሲወጣም አላስወጣ ነው የሚሉት እንዴ? ይሄማ ለእግዚአብሔርም አለመመቸት ነው” በማለት ገሰፁዋቸው፡፡ስልጣን እንደዶሮ ወጡ ያጓጓል፡፡

ተቋማትን በማጠናከር ሕዝብን የስልጣን ባለቤት ማድረግ ደግሞ ለስርዓት መገዛትን የግድ ይላል፡፡  ለስርዓት መገዛት ደግሞ በስልጣን ላይ ሆነን መስራት የምንፈልገውንና በስልጣን ላይ መቆየት የምንሻውን ዘመን ይገድባል፡፡ ስርዓቱ የሚገነባቸውንና እውቅና የሰጣቸው ተቋማት እንዲጠናከሩ ማድረግ፤ ሰሞኑን እንደታየው በስጋት ተወጥሮ  ጭንቀት ከወለደው መንፈስ በመነጨ መደናበር ተሸብቦና ተሸብሮ አሳዛኝ በሆነ መልኩ “ወዮ ለኔ” በማለት የሚያነባ ሕዝብ ከማየት ያድነናል፡፡የሕዝብ እንባ ክፉ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲም በሕዝብ ካለመታመንና በሕዝብ ያለመታመን ችግሩ እስካልተላቀቀ ድረስ በግለሰብ ተክለ-ሰውነት ላይ ተመስርቶ “ካለ እርሶ አይሆንልንም” ከማለት ለመታቀብ እድል ያገኛል፡፡

በሕዝብ ፊትም ባይተዋር ከመሆን ያድናል፡፡ በአጠቃላይ መሪ ባረፈ ቁጥር ምርር ብለን ከምናለቅስ መረዎቻችንን በክብር ቀብርን እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ሕዝብ በቀጣዩ ሂደት ላይ እርግጠኛ እንድንሆንና ከእንደዚህ አይነት መራራ ጭንቅ ለመዳንና ለመፈታት፣ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ተሰልፈን ለዲሞክራሲያዊ ተቋማት እንታመን፣ ለተቋማቱ ጥንካሬ እንታገል፡፡ ገዢውም ፓርቲ ለዚሁ ተግባር ይትጋ፣ ፓርቲዎች ገዢዎችንም ጨምሮ በግለሰብ ተክለ ሰውነት ላይ ሳይሆን ለሕዝብና ለተቋማት ድርጅታዊ ጥንካሬ  እንታመን፤ በሕዝብና በተቋማት እንተማመን፡፡

 

 

 

Read 2336 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:46