Saturday, 31 July 2021 00:00

“ስቶክ ኤክስቼንጅ” ወይም “ካፒታል ማርኬት” ምንድን ነው?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)


              ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ከሰዓት በኋላ በሸራተን ሆቴል የስቶክ ማርኬት (ካፒታል ማርኬት) ምንነትና ጥቅም ላይ ያተኮረ ሴሚናር ተካሂዷል። በእለቱም ባንኮች፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ታድመው ነበር። ይህንን ሴሚናር ያዘጋጁት ግራንት ቶርቶን ኢትዮጵያ (Grant Thornton ethiopa) እና ሴሉለር አማካሪዎች ሲሆኑ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ; የግራንት ቶርንተን ኢትዮጵያ መስራችና ባለቤት ከሆኑት ከአቶ ኤርሚያስ እሸቱ ጋር ተከታዩን ቃለምልስ አድርጋለች።


                  እስቲ ስለ ስቶክ ማርኬት (ካፒታል ማርኬት) ማብራሪያ ይስጡኝ?
ካፒታል ማርኬት ማለት የገንዘብ ገበያ ማለት ነው። ሌላ የተለየ ነገር የለውም። በተለምዶ ለምሳሌ ጎማ ተራ፣ በርበሬ ተራ ይባላል። ተራ ማለት አንድ እቃ የሚገኝበት ገበያ ማለት ነው። አሁን ደግሞ ወደ ዘመናዊ ስናመጣው ካፒታል ማርኬት፣ ገንዘብን የሚወክል ገበያ የሚካሄድበት ማለት ነው። የአክስዮን ገበያ ማለትም ነው። የአክስዮን ሀብት ነው። አክስዮን ገንዘብ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ቤት ወይም መኪና ሲገዛ፣  በቀላሉ ባለቤትነት ከአንዱ ወደ አንዱ እንደሚሸጋገረው ይሄ ደግሞ በጣም በፈጠነና በዘመነ መልኩ በቀናት፣ በሰዓታትና በሰኮንዶች አንድ የባለቤትነት መብት የሚሸጋገርበት ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ፤ ካፒታል ማርኬት ላይ ስንነጋገር፣ ከዚህ ጋር አብረው የተያያዙ የአክስዮን ገበያ ይኖራል፤ የቦንድ ገበያ ይኖራል። ሌሎችም ምርቶችና አገልግሎቶች ይኖራሉ። ስለዚህ እነዚህ ምርቶችና አገልግሎቶች የሚገበያዩበት ነው ካፒታል ማርኬት።
ይህ የምንነጋገርበት ጉዳይ ግን ለሀገራችን አዲስ ነው ልበል?
እስከ ዛሬ በሀገራችን ካፒታል ማርኬት (ስቶክ ኤክስቼንጅ) የለም እየተባለ ቆይቷል። አሁን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በቅርቡ በፓርላማ ይቀርባል፡፡ የካፒታል ገበያ ወይም የአክስዮን ዝውውር የሚደረግበት መድረክ እንዲቋቋም ህጉ ጸድቆ ያለበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል። ስለዚህ ገበያው ሲጀመር ምንድን ነው የሚደረገው? ምንስ ነው የሚሰራው? የሚለው ነገር ይመጣል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ እሱም አንድ፤ ገበያ ነው አይደለም? እሱ በሚቋቋምበት ጊዜ ምርት የሚያቀርብ አለ፣ ምርት የሚገዛ አለ፣ መሃል ላይ ደግሞ ሁለቱን የሚያስታርቅ - ኤክስቼንጅ የሚባለው አለ። እሱም ገበያ ማለት ነው። በአጠቃላይ እንግዲህ የተለያዩ ገበያዎች አሉ። እነዛን ገበያዎች ዲዛይን እያደረግን ነው ያለነው፤ በአገር ደረጃ፡፡ ስለዚህ ይህ የካፒታል ገበያ ወይም ገንዘብና የአክስዮን መለዋወጫ መድረክ ዲዛይን በሚደረግ ጊዜ አንደኛውና የመጀመሪያው ደረጃ የሚቆጣጠረው አካል ማን ነው? በምን ሁኔታ ነው የሚቆጣጠረው? የሚሉ ቀዳሚ ስራዎች አሉት። ከዛ ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊያን ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ አክስዮናቸውን ለመሸጥ ወደ ገበያው ዘልቀው የሚገቡበት መንገድ ይኖራል። ይሄ ደግሞ “IPO” ይባላል።
IPO ሲብራራ ምን ማለት ነው?
“ኢንሺያል ፐብሊክ ኦፈሪንግ” (የመጀመሪያ ህዝብ ለገበያ መቅረብ) ማለት ነው። አሁን ላይ ምናባልትም ካፒታል ማርኬቱ በጣም ሰፊና ኢኮ ሲስተሙ ለእኛ አዲስ ስለሆነ ህብረተሰቡ፣ ባለሙያው፣ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላውን ጉዳይ አብረን የምንሰራው ስለሆነ፣ የዕኛም ግራንት ቶረንተን የተባለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ከሴሉላር ኮንሰልታንሲ ጋር ሆነን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ይህን  ሴሚናር አዘጋጅተናል።
በዚህ ካፒታል ማርኬት ጉዳይ ላይ ዋና ዋና ባድርሻ አካላት እነማን ናቸው?
እንዳልኩሽ የካፒታል ማርኬት ቦታ ሰፊ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ባለስልጣኑ ወይም የሚቆጣጠረው ማነው? የሚለው ነውና፣ ዋናኛው ባለድርሻ “የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን” የተባለውና አሁን በህግ ፀድቆ እየተቋቋመ ያለው ዋኛው ባለድርሻ ነው። የህዝብን ጥቅም፣ የአክሲዮን ባለቤቶችን መብት ለማስጠበቅ ህጉን ተግባራዊ ከማድረግና ከማስጠበቅ አኳያ ትልቁና ዋናው ባለቤት የካፒታል ማርኬት ባለስልጣን ነው። በዛ ውስጥ ደግሞ ብዙ ባለሙያዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ የአካውንቲንግና ኦዲቲንግ፣ የሪስክ ማኔጅመንት፣ የኢንሹራንስና በተለያዩ የስራ ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ይኖራሉ። በዛሬው ዕለትም ወ/ሮ ሂክመት ከአካውንቲንግና ኦዲቲንግ ቦርድ ተገኝተዋል። ወ/ሮ ሂክመት በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳብራሩትም፤ በዚህ ካፒታል ማርኬት ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር ስላለ፣ ተጠያቂነትም ስላለው አንድ ሰው አክሲዮን ሲገዛ የማስተማመን ስራውን ሙሉ በሙሉ የሚሰራው አካውንቲንግና ኦዲቲንግ ቦርድ ነውና በዚህ ሴሚናር ላይ ተገኝተዋል፡፡ ባለድርሻነታቸውም ትልቅ ነው። ሌላው እንደኛ ተቋም አይነት “ግራንት ቶረንት ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያን” ስትወስጂ፣ በእንደዚህ አይነት ሥራ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የረጅም ጊዜ ልምድና እውቀት ነው ያለን።
ስለዚህ አንድ ድርጅት ራሱን አዘጋጅቶና ብቁ አድርጎ የሚያስፈልገውን ህጋዊ ቅድመ ዝግጅቶች አጠናቅቆ ወደ ገበያ ለመድረስ የሚያስፈልጉትን ድጋፎች የሚያገኘው እንደ እኛ ካሉ አማካሪ ድርጅቶች ነውና እኛም ዋነኛ ባለድርሻ ነን። ከዛ ደግሞ አክቹዋል ባለሙያው አለ። አካውንቲንግ ላይ ኦዲቲንግ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ማለቴ ነው። ከህግም በኩል አማካሪ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ዛሬ አንድ አክስዮን ቢሸጥ፣ ያለ የተሸጠበት ዋጋ፣ ትክክለኛ ዋጋ ነው ወይ? የገዛበት ሁኔታ ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን ሁሉ ገዢው ማረጋገጥ አለበት። ለምሳሌ  የሸጠለት ድርጅት መጀመሪያ ሲሸጥለት ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ሰጥቶት፣ ባልሆነ ዋጋ ሸጦለት ከሆነ ወደ ህግ ነው የሚሄደው ማለት ነው። ስለዚህ ለዚህ መፍትሄ የሚሰጡ የሕግ ባለሙያዎች ስለሆኑ እነሱም ባለ ድርሻ ናቸው። ሌላው ይህን ግንዛቤ ለማህበረሰቡ በማድረስ በኩል ዋናው ተዋናይ እንደ እናንተ ያለ ሚዲያ ወሳኝ ነው። በአጠቃላይ ይሄ ሁሉ ባለድርሻ በጋራ በመሆን ሰርቶ  ተዓማኒነትን ማምጣት ነው ዋናው ግብ።
ካነሱት አይቀር የአክሲዮን ገበያው ዘርፍ በተለይ ከተዓማኒነት ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ በተጨባጭ ብዙዎችን ለገንዘብ፣ ለጊዜና ለጉልበት ብክነት ብሎም ለብስጭት የሚዳርግ ዘርፍ ሆኖ ቆይቷል። ጥሩ ስምም የለውምና …ምናልባት የምንነጋገርበት ሂደት ይህን ችግር ሙሉ ለሙሉ ይቀርፈው ይሆን?
እውነት ነው። አሁን መንግስትም በዚህ ዙሪያ የሰራው ትልቁ ነገር ስርአት መዘርጋት ነው። ስርዓት በሌለበት ሁኔታ ገበያው ምን ይሁን? እኔ አክሲዮን ስሸጥ፣ “በዚህ ዋጋ ግዛኝ፤ በዚህ ዋጋ ሽጥልኝ” ብሎ ተደራድሮ በሚያደርገው ነገር ውስጥ ሁልጊዜ ገዢው ቢደሰት ሻጩ ሊከፋ ይችላል። ይህ ሁልጊዜ የሚከሰተው ስርዓት ስለሌለ ነው። አሁን ግን የተዘረጋው ስርዓት ውስጥ ሲገቡና ወደ አክሲዮን ገበያው ሲመጡ እርስ በእርስ እንዲተማመኑ የሚከፍሉት ዋጋ አስተማማኝ እንዲሆን፣ ወደፊት የሚያገኙት፣ ከማኔጅመንቱ ከCEO፣ ከቦርዱ የሚጠብቁት ነገር ስርዓት ያለውና በዚህ ስርአት ውስጥ የሚገዛ እንዲሆን የግዴታ ገበያው በዚያ መልክ የተቃኘና ዲዛይን የተደረገ ይሆናል ማለት ነው።
አሁን ለምሳሌ አንድ የመንግስት የስራ ድርጅት ያለውን የሰራተኞች የጡረታ ገንዘብ የሆነ ስራ ላይ ወስዶ ኢንቨስት ቢያደርግ፣ ነገ ጡረታ በተገቢው መንገድ መክፈል ስላለበት ኢንቨስት የሚያደርግበት ስራ አስተማማኝና ውጤታማ መሆን አለበት። ይሄ ሰው በህይወት እስካለ ድረስ በቋሚነት ጡረታ መክፈል አለብኝ። ለጡረታ ዘመኑ የተመጣጠነ ኑሮ እንዲኖር ገቢ ማግኘት አለብኝ ብሎና አስቦ ተጠንቅቆ መሆን አለበት  ኢንቨስት የሚያደርገው። ስለዚህ ለጡረተኛው አስተማማኝ የሆነ ክፍያና ይህ ድርጅት እያደገ ይሄዳል” ብሎ ቃል የገባው ነገር ሁሉ በትክክል ዕውን መሆን አለበት። “ይህ ካልሆነ ለጡረተኛው ከየት አምጥቶ ገንዘብ ይከፍለዋል? ኑሮ ሲወደድ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ፣ በዛው ልክ የሚስተካከል የጡረታ ዘመን እንዲኖራቸው የግድ እንደዚህ አይነት ገበያ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ዛሬ በሴሚናሩ ላይ ትልልቅ የባንክና የኢንሹራንሽ ኩባንያ ሀላፊዎችም ተገኝተዋል አይደል?
አዎ በሚገባ! ምናልባት ባንኮች ትልቁና የመጀመሪያው ወደ ገበያ የሚገቡትና ወደ ካፒታል ማርኬት የሚገቡት ተዋናዮች ናቸው። ባንኮች ኢንሹራንሶች፣ በብሄራዊ ባንክ የቁጥጥር ስርዓት ውስጥ ቀድሞውኑም የዘመኑ ስለሆኑ ምልባትም የተወሰነ ማስተካከያና ቅድመ ዝግጅት አድርገው ቀዳሚ ተዋናዮች ይሆናሉ። እናም ቅድም ወዳነሳሽው ነጥብ ስንመጣ፣ እስከዛሬ የነበሩት ከስርዓት ውጭ የነበሩ አሰራሮች ይቀሩና የግብያት ስርአቱ እንደገና ትክክለኛ ዋጋ እንዲከፈልበት ይሆናል። ክፍያውም ሲከናወን ትክክለኛ የክፍያ የምስክር ወረቀት በትክክል እንዲሰጠው ይደረጋል። ይሄ ሁሉ ነገር ታዲያ በኢኮ ሲስተሙ ውስጥ ታቅፎ ይሄዳል ማለት ነው። ጥርጣሬውም ይቀራል። ገዢና ሻጭንም የሚገዛቸው ህግና ስርዓት ይሆናል ማለት ነው። በገበያው ላይ መተማመንና ተጠያቂነት ሲፈጠር ደግሞ በየትራሱ ስር ተደበቀው ገንዘብ ይወጣና ወደ ሲስተም ይገባና፣ እቤት ከሚቀመጥ ኢንቨስትመንት ይደረግበታል ወይም ደግሞ ባንክ ውስጥ ተቀምጦ ትንንሽ ወለድ ከሚያመጣ ጥሩ ጥሩ የኢንቨስት ሀሳቦች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችል መድረክ ለህብረተሰቡ ይፈጥራል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የውስጥ ለውስጥ የኢኮኖሚ መቀጣጠልን ያመጣል ማለት ነው።
እንዲህ አይነት አዳዲስና ዘመናዊ ሀሳቦች ሲመጡ በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙ ጊዜ ተቀባይነት የማጣት ተዳዳሮቶች ይገጥማሉ። ይህንን ተግዳሮት ተቋቁሞና  አሳምኖ በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረፁ ከፍተኛ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ይጠይቃል። በተለይ ለእንደ እናንተ አይነት አማካሪ ድርጅቶች። ስለዚህ  ይህንን ተግዳሮት ለመቋቋም ምን አይነት ዝግጁነት አለ?
እውነት ነው።  የሰው ልጅ በባህሪው የለመደውንና የኖረበትን ነገር ቶሎ ጥሎ ወደ አዲስ አይነት ሀሳብና ቴክኖሎጂ ለመግባት ይቸገራል። ይሄ ደግሞ መብት ስለሆነ ቀስ በቀስ ጥቅሙን እያሳዩ፣ ትዕግስት ተጨምሮበት ካልሆነ ማስገደድ አይቻልም። እናም ትልቁ ሥራ ያለው እዚህ ላይ ነው። ይሄ ደግሞ “ Change Management” ይባላል፡፡ ከባዱም ስራ ይሄው ነው። አንድ ሰው ከልጅነት እስከ እውቀት ትክክል ነው ብሎ የሚያምነው ነገር ላይ “አይ ሌላ የተሻለ አማራጭኮ አለ” ሲባል ቶሎ መቀበል ይቸግረዋል። ስለዚህ እዚህ ላይ ከፍተኛ ስራ ለመስራት ጊዜም አቅምም ያስፈልጋል። ቼንጅ ማኔጅመንት ከባድ ሥራ ነው። ለምሳሌ ከተማ ውስጥ ዘመናዊ እና ንፁህ ሞሎች ውስጥ ሄዶ መጠቀም አማራጭ ቀርቦለት “አይ እኔ እዛው የለመድኩት መርካቶ እሄዳለሁ” ይልና ይሄዳል። ምክንያቱ በቅናሽ ማግኘት ይፈልግ ይሆናል፡፡ ወይ የለመደው ቦታ ላይ የሚፈግለውን ቶሎ ማግኘት ይሆናል ብቻ የተለያየ ምክንያችን ያስቀምጣል። ይሄ የግለሰቡ መብት ይሆናል። ነገር ግን በዚያ ውስጥ ሁልጊዜ ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት የግድ አለበት። ለምሳሌ ራይድ ያነሳሽው አለ፤ እንደገና ላዳ አለ። ላዳ ከራይድ ጋር  ተወዳዳሪ ካልሆነና በለመድኩት እቀጥላለሁ ካለ ምን ይሆናል፤ ከጫዋታ ይወጣል ይወድቃል። ስለዚህ ሁልጊዜ በገበያ አሸናፊ ሆኖ የሚመጣውን በኢኮኖሚው በህብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ እንዲሆን ራሱን አዘጋጅና ልቆ መገኘት ሲችል ብቻ ነው። አማዞንን ተመልከቺ። በዓለም ለምን ተመራጭ ሆነ? የሰውን ችግር ሁሉ እየፈታ እየፈታ ስለመጣ ነው። ላዳ እየነዳሁ ነውና እንደ ድሮው 500 ብር ካልተከፈለኝ ብሎ ቁጭ ካለ፣ ቁጭ ብሎ መቅረቱ ነው። ምክንያም እዚህ ጋ ደግሞ ራይድ መጣ። አንደኛ በቀላሉ በስልክ መጥራት ተቻለ። ሁለተኛ ተመጣጣኝ ዋጋ በተፈለገው አቅጣቻና ፍጥነት ማገልግል ቻሉ። ሶስተኛ ተጠቃሚውን ከስጋት ነፃ ማድረግ ቻለ። አራና ደግሞ ከድርድርና ከንትርክ ነፃ አደረገ። በዚህ ምክንያት አገልግሎቱን ያገኘና የተመቸው ለጓደኛው፣ ለጎረቤቱ፣ ለስራ ባልደረባው ሲናገር፤ አብዛኛው ተጠቃሚ ፊቱን ወደ ዘመናዊነት ያዞራል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ይሄ ነው።
ስለዚህ በዛሬው ሴሚናር እስካሁን ከተነጋገርናቸው በየትኛው ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው? ሌላው እንዲህ አይነት ሴሚናሮች፣ የግንዛቤ ስራዎች ብዙ ጊዜ በዋናው ከተሞች ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ነገር ግን በየክፍሎች ተመሳሳይ ሴሚናሮችን የሚፈልጉ ተመሳሳይ ዘርፎች አሉና ምን የታሰበ ነገር አለ?
የሴሚናሩ ትኩረት እንግዲህ መንግስት ለዚህ አዲስ ነገር መድረኩን አዘጋጅቶ፣ ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው ብሏል።  ከዚህ በኋላ መንግስት ለብቻው የሚሰራው ነገር የለም። ተዋናዮቹ ፈረሰኞቹ ወደተዘረጋው ሜዳ መግባት አለባቸው። ሥራው ከባድ ነው። መሰራት አለበት። ስለዚህ እኛ እንደ ባለሙያ፣ ነገ ወደ ገበያው የሚመጡት ባንከችና ኢንሹራንሶች የህግ ባለሙያዎች፣ አካውንታንትና ኦዲተሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሰብስበን “መንግስት ይህንን ፍሬም ወርክ አዘጋጀ” ይህ የተዘጋ ፍሬም ወርክ ለእኛና ለማህበረሰቡ በሚጠቅም መልኩ እየተቃኘ እንዲሄድ የኛ አስተዋፅኦ ምን መሆን አለበት በሚለው ላይ ለመመካከር የተዘጋጀ ነው።  ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዴት ነው ላልሽው ጉዳዩ ገና አዲስ ነው። በጅምር ላይ ያለ ነው፤ ቀስ በቀስ ጉዳዩ መድረስ ያለበት ድረስ ይሄዳል። ምክንያም አገር አቀፍ የሆነ ፍሬም ወርክ ስለሆነ ማለቴ ነው።

Read 2855 times