Monday, 02 August 2021 20:22

ከሆስፒታል መውጣትና ስንብት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ከቀን ወደ ቀን የጤናዬ ሁኔታ  በትንሽ በትንሹ መሻሻል ማሳየት ቀጠለ፡፡ ትንሽ ትንሽ ፈሳሽም መውሰዴን ቀጠልኩ፡፡ በፊት ያስከፉኝ የነበሩትን አብዛኛዎቹን የህክምና ሂደቶችን እየተቀበልኳቸውና እየለመድኳቸው መጥቻለሁ፡፡ ኮሎስ ቶሚ ባግና ካቲተር መቀየር፣ የመኝታ አቅጣጫዎችን በየሁለት ሰዓት ልዩነት መለወጥ፣ ሰውነትን በሌላ ሰው እርዳታ መታጠብ ፣ልብስን በሰው እርዳታ መቀየር፣ በዊልቸር መንቀሳቀስ፣ ከአልጋ ወደ ዊልቸተር ከዊልቸር ወደ አልጋ በሰው እርዳታ መመላለስ ወዘተ…. ማድረግና መቀበል መማር ጀምርኩ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቦቼና ጓደኞቼም ይህንኑም መቀበልና መማር ጀመሩ፡፡
ያለሁብት ሁኔታ የመቀበል ሂደቱ እንዲህ እንደማወራው ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ህመምና መተናነቅ አለው፡፡ በመጀመሪያ መጽሐፌ ላይ ከሌሎች ታሪኮች ጋር በማያያዝ ፅፌዋለሁ፡፡ ይህንን ለሚያነብ ሰው አስረግጬ መናገር ይፈልግ ግን፣ ደስተኛ መሆን የጀመርኩት ያለሁበትን ሁኔታ መቀበል ስጀምር ነው፡፡ ማንነቴን፣ እኔነቴን፣ ያለሁበትን ሁኔታ፣ የደረሰብኘኝን አደጋና ሌሎች እውነታዎችን መቀበል መጀመሬ፣ የደስታ በር  ቁልፍን በቶሎ እንዲያገኝ ረድቶኛል፡፡ መደስት መጀመሬን ደግሞ፣ የውስጡን ቁስሌን ማሻልና ማዳን አሰችሎኛል፡፡ የውስጥ ቁስሌ መዳን ደግሞ፣የውጭውን አካላዊ ቁስል ቶሎ እንዲያድን አድርጎታል፡፡ ትልልቅ የሚመስሉት ችግሮችም፣ በመቀበል ብቻ ወደ ትንንሽ ተግዳሮቶች መቀየር ጀመሩ፡፡ ድፍን ጨለማ ከመሰለው ችግር ላይ ትንንሽ ብርሀናትን ማየትን ጀመርኩ፡፡
የእኔ ደስተኛ መሆን መጀምር ነርሶቼን፣ ጓደኞቼንና ቤተሰቦቼን ደስተኛ ማድረግ ጀመረ፡፡ እኔ ማገዝ፣መርዳና አብሮኝ መሆን የበለጠ ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ሆነ፡፡ ብዙ ጓደኞቼም እየተፈራረቁ እየገቡ ያጫውቱኝ፣ ያዋሩኝ፣ መዝሙር ይከፍቱልኝ፣ መጽሀፍ ቅዱስ ያቡልኝና ይፀልዩልኝ ጀመር። ሙሉቀን፣ መላከ፣ አሰግድ፣ በኤኔዘር፣ ስጦታው፣ ወሰን፣ ታግለህ፣ ህሊና፣ ብሩክታየት፣ አሌክስ፣ ሙና፣ ኩኩ፣ ውድድ፣ ፀጋ፣ ሉሲ፣ ናርዶስ፣ ፍፁም ሌሎችም ብዙ ጓደኞቼ እየመጡ ያጫውቱኛል፡፡
ሁኔታዎች እንደዚህ መስተካከል ሲጀምሩ፣ ሀኪሞቸና ነርሶቼ ከሆስፒታል መውጣትና በቤት ሆኜ ህክምና መከታተል ስለምችልበት ሁኔታ ሀሳብ ማምጣት ጀመሩ፡፡ ይህም በሌላ ቋንቋ “በደንብ ተሽሎኸል” ማለት ስለሆነ፣ አምላኬን አመሰገንኩት፡፡ በጣም ከምወዳትና ሲመደቡልኝ ደስተኛ ከሚያረጉኝ ነርሶች መካከል አንዷ ፅጌ እንዲህ አለችኝ፡፡
“ዳጊ አሁን በደንብ እየተሻለህ ነው። በህይወትህ  የሚያሰጉ ነገሮች በሙሉ አሁን የሉም፡፡ አንተ ከፈለክና ሁኔታዎች የሚመቻቹ ከሆነ፣በቤትህ ሆነህ ህክምናህን መከታተል ትችላለህ፡፡ እዚህ የሚደረጉልህን አብዛኞቹን ህክምናዎች በቤት ውስጥ ነርስ ተቀጥሮልህ  ወይም ቤተሰብ በኩል ሊደግልህ ይችላል፡፡ ደግሞም ብፁህ ዶ/ር ናት፤ ናቲ ነርስ ናት  እነሱ ቤት ውጥ በደንብ ቢከታተሉህ ይችላሉ፡፡ አንደኛ ብዙ ወጪ ማትረፍ ትችላለህ፡፡ ሁለተኛ እዚህ ሆስፒታል በመቆየት  ሊይዙህ የሚችሉ ኒሞኒያ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ከእነሱም ትድናለህ። ደግሞም ይሔ ሁሉ ቤተሰብና ጓደኛ ከአዋሳ እዚህ ድረስ እየተመላለሰ ከሚቸገር፣ አንተ እዛው ብትሆን የተሻለ ነው፡፡ ምናልባት ቤት መሆንን ከፈራህ ወይም ካልተመቸህም፣ሀዋሳ ላይ ጥሩ ሆስፒታል ሆነህ ክትትልህን  መቀጠል ትችላለህ። እስኪ ከቤተሰቦችህ ጋር ተነጋገሩ፡፡”  አለችኝ፡፡
እኔ በሀሳቡ ስለተስማማሁ ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸው፡፡ በሀሳቡ ዙሪያ እንዲመካከሩበትና  የተሻለ ሀሳብ እንዲያመጡ አሳሰብኳቸው፡፡ ከጓደኞቼም ጋር በሀሳቡ ዙሪያ  በደንብ ተነጋገርንበት። ነገር ግን በሆስፒታል ለመውጣት ሲታሰብ ፊት ለፊት ያሉ ብዙ ችግሮች ነበሩ። አንደኛው ወደ ቤት ከሄድኩ በኋላ፣ የምተነፍስበት የብረት ትቦ በድንገት ቢታፈን በምን ሊፀዳ ይችላል?  ለዚህ ደግሞ የመምጠጫና የማጽጃ ማሽን (ሳክሽን ማሽን) ማግኘት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማሽን የማይኖር ከሆነ ወደ ቤት መሄዱ ትርፉ ሞት ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር ኦክሲጅን ነው፡፡ በእርግጥ ምንም ዓይነት  ኦክስጅን መጠቀም ካቆምኩ ወር አልፎኛል፡፡   ስለዚህ  ኦክስጅን አያስፈልገኝም፡፡ ነገር ግን ምናልባት የአየር እጥረት ቢፈጠርብኝ  መዘጋጀት ስለሚያስፈልግ፣ ስለ ኦክስጅንም ማሰብ ነበረብኝ፡፡ ከዚህም ካለፈ በቅርቤ ካሉት የህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ ቤት መተው የሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎችን መቅጠር እንችላለን፡፡ ሌሎችም ችግር ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እያነሳሁ፣ከሆስፒታሉ ከመውጣቴ በፊት ቀድመን ለማስተካከልና ለማዘጃገት ጥረታችንን ቀጠልን፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ነበር ያ በመጀመሪያው መፅሀፌ ላይ የጠቀስኩት ዶ/ር፤ ከእንቅልፌ ቀስቅሶ ያናገረኝ፡፡ ንግግሩ እስከ ዛሬ ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡ “ዳጊ ስላለው ነገር ለፋዘር ነግሬያቸዋለሁ፡፡ አልነገሩህም? ከዚህ በኋላ እድናለሁ ብለህ ብዙም ተስፋ አታድርግ፡፡ እጅህ  እግርህ እንደበፊቱ መሆን አይችልም፡፡ ምናልባት በወዲያኛው ዓለም ካልሆነ እዚህ ያለኸው ሌሎች ቁስሎችን ለማከም እንጂ፣ ዋናውን የአለርጂ ችግር ለማከም አይደለም፡፡ ለእሱም በዙም ተስፋ አታድርግ፡፡” ነበር ያለኝ፡፡ በነበረኝ ተስፋ፣ ደስታና መነሳሳት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸለስ ንግግር ነበር፡፡
የዚያን ቀን ተረኛ ሆኖ አጠገቤ ያደረው ጓደኛዬ ታግለህ ነበር፡፡ ገና ንግግሩን ሲሳማ መላ ሰውነቱ በቁጣ ተንቀጠቀጠ፡፡ እኔ ፊት ምንም  ላለማድረግና ላለመናገር እንደምንም ራሱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ይታየኛል፡፡ ዐይኞቹ ደም መስለው የግንባሩ ደም ስሮች ሲወጣጠሩ ይታየኛል፡፡ አንዴ እኔን አንዴ ዶክተሩን ያያል፡፡ ከንዴቱ የተነሳ ግንባሩን ማላብ ጀመረው፡፡ ዶክተሩ ግን ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት ጨረሶ ወደ ውጪ መውጣ ጀመረ፡፡ ቀና በዬ ታግለህን አየሁትና
“ወንድሜ ለምንድን ነው የተበሳጨኸው? ዶክተሩ ያለውን ሰምተህ ነው? አይዞህ እኔ አልሰማሁምትም፡፡ አንተም አትስማው። ከእሱ ቃል ይልቅ እኔን ነው የማምነው እግዚአብሔር ነው፡፡ “አልኩት ረጋ ብዬ፡፡
(“ከማዕዘኑ ወዲህ” ከተሰኘው ዳግማዊ አሰፋ መጽሃፍ የተቀነጨበ)
“እሺ አልሰማውም” አለኝና ፈጠረኖ ካጠገቤ ሄደ፡፡ ዶክተሩን ተከትሎ ወደ ውጭ ሲወጣ አባቴ፣ እናቴ ወንድሜና ቤቢ በር ላይ አገኙት  እጅግ በጣም ተቆጥቶ በንዴት በግኗል፡፡ እነሱም ሁኔታን አይተው ስለደነገጡ፣ የተፈጠረውን ጠየቁት፡፡ እሱም በንዴት እንባ እየተናነቀው ዶክተሩ ያለኝን ነገር ነገራቸው፡፡ አካባቢው ተደበላለቀ፡ ሁሉም ተቆጡ፡፡ ሀኪሙን ጠርተው በቁጣ አናገሩት፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደር ድረስ ክስ አስገቡ፡፡ ፈፅሞ  አጠገቤ እንዳይደርስ  አመለከቱ፡፡ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ አልፎ ነርሶቼን በሀኪሙ ንግግር በጣም ተበሳጩ። አውቆም ይሁን ሳያውቅ አስቦትም ይሁን ሳያስብ በተናገረው ነገር ሁሉንም ሰው አሳዘነ፡፡ የሁሉንም ሰው ስሜት የጎዳ የሁሉንም ተስፋ አጨለመ፡፡
ነገሩ የሰመማ ሰው ሁሉ እየተፈራረቀ እየመጣ ምንም እንዳይሰማንና ተስፋ እንዳልቆርጥ አጽናናኝ፡፡ የሰይጣን ፈተና መሆኑን እየነገሩ እንደልሸነፍ መከሩኝ፡፡ በተቻላቸው መጠን ሁሉ ከጎኔ መሆናቸውን ነገሩኝ፡፡ የሁሉም ሰው ጭንቀት ገብቶኛል፡፡ በሀኪሙ ንግግር ተስፋ ቆርጬ እንዳልሸነፍ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ካለሁበት ችግር ወደ ከፋ በስጭት፣ሀዘንና ተስፋ መቁረጥ እንዳልገባ ነው፡፡
ውስጤ ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ እንዴት እንደሆነ ባልገባኝ ሁኔታ ምንም ዓይነት መከፋት ማዘንና ተስፋ መቁረጥ አልተሰማኝም፡፡ እንዲያውም ሀኪሙ ያንን ሲናገር እዚያው ነበር የሳኩት፡፡ የተናገረውን ንግግር በጆሮዬም ሰማሁት እንጂ አንዱም ቃል ወደ ውስጤ አላስገባሁትም፡፡ በፍፁም ልቤን ለሀዘን፣ውስጤንም ለመከፋፋት አልከፈትኩም፡፡
እንዲያውም ሀኪሙን ንግግር እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ለመሆኑ እንደ ማረጋገጫ አድርጌ ወሰድኩት። ምክንያቱም ፈተናና መከራ ሲበዛ፣ እግዚአብሔር የፈተነውን ሰው ለመርዳት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚቀርብ አውቃለሁ፤ አምናለሁም፡፡ በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ከተፃፉት የተፈተኑ ለሚፈተኑ ሰዎች እግዚአብሔር ቅርብ እንደሆነ ነው። ለዚህ ብዙ ማሳያ የሚሆኑ  ታሪኮች መጥቀስ ቢቻልም፣ መጀመሪያው መፅሀፌ ላይ ስላካተትኩት ያንን እንዲያነቡበ አጋባዛለሁ።
በሁለተኛ ደረጃ የተረዳሁት ነገር ሰይጣን የሚችለውን ሰይፍ ሁሉ ወደ እኔ እየወረወረ እንደሆነ ነው፡፡ በመጀመሪያ መፅሐፌና ከዚያም በላይ ባሉት ምዕራፎች እንደገልጽኩት ከስድስት ጊዜ በላይ ለሞት ያበቁ ሁኔታዎች ተከስተውብኝ ነበር፡፡ በእግዚአብሔር እርዳታ አምልጫለሁ፡፡
ሰይጣንም በተለያየ መንገድ ሊገድለኝ የሞከረው መንገድ አልተሳካም፡፡ የአሁኑን የሀኪሙን ንግግር ደግሞ ተስፋዬንና መንፈሴን ለመግደል እንደተወረረ ሰይፍ ቆጠርኩት፡፡ ለዚህ መድሃኒቱ ደግሞ ንግግሩን ችላ ብሎ ወደ እግዚአብሔር በመጠጋትና እርዳታ መለመን ነው፡፡ እኔም አደረኩት፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ለራሴ ፈተናው የሚበዛው ጠንካራ ስከሆንኩ እንደሆነና መሸነፍ እንደሌለብኝ ደጋሜ ነገርኩት። ምንም ቢመጣ በህይወት እስካለሁ ደረስ መጋፈጥና መታገል ብሎም ማሸነፍ እንደለብኝ ነገርኩት፡፡ አቅሙ እንዳለኝና ይልቁንም ይህን ፈተና አሸንፌ ወጥቼ ሀኪሙ ፊት በእግሬ መምጣት እንደለብኝ ራሴን አሳመንኩት።
እግዚአብሔር እስከረዳኝ፣ እኔም አስከበረታሁና እስካልተሸነፍኩ ድረስ የማይታለፍ ፈተና፣ የማይናድም ተራራ እንደሌለ ውስጤን አሳመንኩት፡፡ እንዲያውም ትግል የሚበዛበት ጠንካራ ሰው ብቻ እንደሆነ ለራሴ እየነገርኩ ውስጤን አጠነከርኩት፡፡ ከዚያም ያለቀሱ ዐይኖቿን ጠራርጋ ልታበረታተኝ የመጣቸው እናቴን እንዲህ አልኳት፡፡
“አይዟችሁ አትበሳጩ፡፡ ይሄ የሰይጣን ፈተና እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ የሀኪሙ ንግግር ዓላማው ሁለት ነው፡፡ ከተሳካ እኔን ተስፋ ማስቆረጥና ጥንካሬዬን መግደል ነው። ውስጤ ከተሸነፈና ብርታቴ ከወደቀ ደግሞ፤ ሞትኩኝ ማለት ነው፡፡ ይህ ካልተሳካ ደግሞ፤ እናንተ ተቆጥታችሁ ሆስፒታሉን እንድትበጠብጡ ወይም ሀኪሙን እንድትደበደቡና እኔ ከሆስፒታሉ እንድባረር ነው፡፡
እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ሌላ ሆስፒታል ለመፈለግ ላይ ታች  ስንል ሰይጣን ሌላ አደጋ ይፈጥርና ድጋሚ ሊገድለኝ ይሞክራል ማለት ነው፡፡ የዶክተሩ ንግግር ዓላማ ይሄ ነው፡፡ እኔ ምንም አልተሰማኝም። ያለውንም አልሰማሁትም። እናንተም አትበሳጩ

Read 2222 times