Monday, 02 August 2021 20:43

ስድስተኛው ሃጢኣት

Written by  ኦ ‘ ታም ፑልቶ
Rate this item
(4 votes)

የሆነ ስህተት ኣለ! ከእያንዳንዷ አላፊ ቅፅበት ህማምን ወይም ሃሴትን ማግኘት ነበረብኝ። ደቂቃዎችን ማቆም ወይም አብሬአቸው መብረር ነበረብኝ። ሹክሹክታቸውን ማድመጥ ወይም ህልሜን ማጋራት ነበረብኝ። ከቶም እንደሌለሁ ቆጥረው የረጉ ከመሰሉ ግን ችግር አለ። አሻራ እንኳ ሳይተውብኝ ጥለውኝ ከበረሩ ስህተት አለ። ለምን ሰለቸኝ?
የህዝብ መዝናኛ ነው። የአትክልት ቦታው ይዞታ ለውበት በቅጡ መጨነቅ እንዳልጀመርን ያሳያል። (ጠየቅሁ፡- መንፈሳዊዋ ያበሻ ምድር የማያልፉ ነገሮችን - ውበትን፣ እውነትን፣ ንፅህናን፣ … እንዲህ ቸል ያለችው ለምን ይሆን?) መዝናኛው ቀልቤን አላረጋም። መፅሐፌም ከዘለዓለም ጋር ሊያነካካኝ አልቻለም። ሃሳቤ እንደ አውደልዳይ ነፍሶች፣ ያለ ዓላማ ይባክናል። ሰዓታቱ ዝም ብለው እያለፉኝ ይሄዳሉ፤ ወይም ቆመዋል፣ እኔ እንጃ!
ምን ያህል ቆየሁ? ብዙ ሰዎች አያዩኝም ደግነቱ። ልቅ ግቢ ነው። የተከረከሙ ፅዶች የፈጠሩት ግድግዳ ከልሎኛል። አስተናጋጆችም መጥተው አላናገሩኝም። አላዩኝም ወይም እንደማላዝ አውቀዋል። ከሌለህ እንደሌለህ መቆጠር ጥሩ ነው። ቢያንስ የልብህ ኩራት እንደተጠበቀ ይሆናል።
ለምንድነው እዚህ የመጣሁት? ሁለት ሶስቴ ለመሄድ ተነስቼ ቅር፣ ቅር ስላለኝ ሃሳቤን ቀየርኩ። ማንን እየጠበቅሁ እንደሆነ ገና ባይከሰትልኝም እየጠበቅሁ እንደሆነ ተሰምቶኛል። አለማወቅ ሲያሰለች! ለሰዓትም ቢሆን ልብህ ተሰቅሎ ይኑር ማለት እርግማን ነው መቼም።
ፀሃዩ ይፈናከታል። የዝናብ ፀሃይ የሚሉት ዓይነት ነው። ራስምታት ከለቀቀብኝ ቆይቷል። ራሴ በመዶሻ የተመታ ያህል ነው ስቃዩ። የሲሚንቶው መቀመጫ ስላደነዘዘኝ ሳሩ ላይ የእንግላል ተዘርግቼ ግንባሬንና ደረቴን ለፀሃዩ አመቻቸሁ። ስቃይን መሸሽ ከሌለብህ ራስህን ሳትቆጥብ ስጠው - በሚወጋህ ጦር ሌላኛው ጫፍ ላይ አርነትህ አለና። (ይሉ ነበር የድሮ መናኒያን። ይህ የነፃነት ኣቋራጭ ዛሬም ይሰራ እንደሁ ባላውቅም፣) ሙሉ ራሴን ለንዳዱ ሰጠሁ።
ማወቅ አለብኝ! ደቂቃዎች እንደተንጠብጣቢ ጤዛዎች ናቸው። በውስጣቸው የትየለሌ ምስጢር ደብቀዋል። ይህንን ምስጢር ማንበብ አልቻልኩም ማለት እየኖርኩ አይደለሁም እንደማለት ነው። በየደቂቃው ካልኖርኩ ደግሞ ሁሉም ደቂቃዎች አንድ ይሆናሉ - አያልፉም። ማወቅ አለብኝ። ቢያንስ፣ ማንን እየጠበቅሁ እንደሁ ሊነግሩኝ ይገባል።
(ይህ አዕምሮ እሚሉት ነገር ልክ እንደ ቀይ ሽንኩርት ድርብርብ የንቃት ዓለም አለው - ቢልጡት እማያልቅ። ይህንን ልብ አልኩ - ሰው በአንድ ጊዜ አንድ ነገር ብቻ አይደለም የሚያስበው። ሳያውቀው በአንድ ቅፅበት ውስጥ አዕላፍ ነገሮች ተሃሳብ ዓለሙ ይገባሉ። ሁዋላ፣ የአዕምሮውን ዕንቡጥ፣ ቅርፊት በቅርፊት ሲፈለቅቅ ያለ ንቃት ያሰላሰላቸውን ነገሮች ያገኛቸዋል። እዚያ መዝናኛ ውስጥ ተኝቼ አንጎሌ ማሰብ ያቃተው መስሎኝ ነበር። ከአይረቤ ነገሮች ባሻገር ማሰላሰሌ ትዝም አይለኝ። በዚያ የወጣቶች የጥበብ ምሽት ላይ ስላየሁዋት ልጅ በረጅሙ ሳስብ እንደነበር ያወቅሁት ቆይቶ ነው። ምናልባት ይህ ስላስተናጋጆች ወይም ስለ አትክልት ቦታው ወይም ደግሞ ስለ ስቃይ ባሰብኳቸው ሃሳቦች ተከልሎ የታሰበ ጉዳይ ይሆናል።)
ራሴን አልጠራጠርም። የነካኝ ስውር እጅ ህያውና እውነት ነው። እንዳየሁዋት ከጊዜና ከቦታ ጅረት ተነጥቄ ወጣሁ። በዓይኖቿ ውስጥ ሁሉም ነገር ነበር - የሆነውም፣ የሚሆነውም። ከአካሏ ነጥዬ ዓይኗን ብቻ እንዴት እንዳየሁ ነው ያልገባኝ። ዓይኖቿ እሳት ሆኑ። እሳቱ ብርሃን ወለደ። ብርሃኑ ፈውስን ሰጠኝ። (ባልንጀሬ ዕብደት ሰጠህ፣ ነው ያለኝ።) ስነቃ አጣሁዋት። ወደ ጊዜና ወደ ቦታ ጅረት ስመለስ፣ ከአላፊ ቅፅበቶችና ስሜቶች ጋር መፍሰስ ስጀምር አጣሁዋት። ሙታን መቃብር ፈንቅለው ሲነቁ የቀሰቀሳቸውን መንፈስ ያጣሉ? እኔ አጣሁዋት!
ራስምታቱ እየለቀቀኝ ነው ወይም አንጎሌ እስኪበቃው ደንዝዟል። አይገርምም? ይህ ሁሉ አትክልት ኖሮ ነፋስ እንኳ አይነፍስም። ከርቀት የሰዎች ድምፅ ይሰማኛል። ድምፁ በተገተረው ጊዜ ውስጥ ሲስተጋባ ከሙታን ዓለም የሚመጣ ይመስላል። ወይም፣ የሞተው ጊዜ ወደ ሙታን ዓለም ይዞኝ ሄዷል።
ፍቅር ራሷን ታፈቅራለች፤ ይላሉ የሚያውቋት። ራሷን ማሞካሸትና ማናገስ ያስደስታታል አሉ። ሁሌ (እንደ ምፅዓት ቀን) በአስደንጋጭና አስደናቂ ትዕይንቶች ታጅባ እምትገለፀው ለራሷ ስትል መሆን አለበት። አሁን ዓይኖቼን በዚያች ልጅ ዓይኖች ላይ ሁለት ሰዓት ሙሉ ሰንቅሬ መልኳን ግን ማስታወስ አልቻልኩም ብል ማን ያምነኛል? እንግዳ ስለሆነ ብቻ ቅዠት ነው አይባልም መቼም። ያየሁት ለኔ እንደ እሳትና እንደ አበባ እውንና እውነት ነው። ለካስ የሴት ዓይን ቢሸሹትም እማይሸሽበት ጊዜ ኣለ!
ፍቅር ግን ደግ ናት! ቢያንስ አንዴ፣ ቢያንስ ለበራሪ ቅፅበት፣ እያንዳንዱን ልብ ትጎበኛለች። እኔም ዕጣው ሊደርሰኝ ነው። ይህን ባልንጀሬም ተረድቶልኛል።
ለመንኩት። እባክህን ልጅቱን አሳየኝ፣ አልኩት። እምቢ፣ አለኝ። “ሲሻልህ ፈልጋት፤” አለኝ። “አንተ ያየኸው ነፍሷን ነው፤ እኔ ስጋዋን ባሳይህም አታውቃትም፤” አለኝ። “አካሏንም አንተው ካገኘህ የፍቅርን መቅደስ ለመውረስ ዝግጁ ነህ ማለት ነው።” አለኝ። “ህመምህን ግን እጋራለሁ፤” አለኝ። ካለ ይጋራል። እሱ ለኔ ደግ ነው። ግን፣ ምን ማለቱ ነው ህመምህን እጋራልሃለሁ ሲል?
ጊዜ እንደ ባህር ዛጎል ነው። ስትፈለቅቀው ዕንቁ ታገኝበታለህ። እንደ ህቡዕ መዝገብም ነው። ስትገልጠው የማንነትህንም ሆነ የፍጥረትን ምስጢር ታነብበታለህ።
(ሰዓታቱ) “የጥበቃዬን ዓላማ ለዝንተዓለም ሊደብቁኝ አይገባም። ማወቅ አለብኝ!” አልኩ በልቤ። (ቢያንስ በልቤ መሰለኝ።)
ምናልባት እሚጮህ ሃሳብ አምልጦኝ ይሆናል። አንዳንዴ ለልብህ ያንጎራጎርክ ሲመስልህ ለካስ ዜማህ አድማስህን ጥሷል። አዝማሪ ነፍሴ ሃሳብንና ንግግርን ማምታታት ጀመረች ልበል? ወይም ደግሞ ሃሳቤን አድምጣም ይሆናል። አዎ፣ እንደ ብቁአን የሃሳቧን ቅኝት ተሃሳቤ ምት አስምራ ሳልናገር አድምጣኝም መሆን ኣለበት።
“አዋቂዎች ምን እንደሚሉ ታውቃለህ?” የሚል የሴት ድምፅ በረጋው ጊዜ ውስጥ የተንጣለለውን ህዋ ሰንጥቆ መጣ።
ለአርምሞ የሚሆን ጥቂት ዝምታ ፈጥራ ቀጠለች።
“‘የጊዜ ምስጢር በየልባችን ውስጥ ነው።’" የጥቅሷም የንግግሯም መጨረሻ።
አጠገቤ ነች። ጆሮዬን አቁሜ እንደ አዳኝ ድመት አደፈጥኩ። ቃሏ፣ በተሰነጠቀው ጊዜ ውስጥ እንደ ሽብልቅ ተቀርቅሮ ቀረ። ዓይኔን መክፈት ፈራሁ። ድንገት ዓይኗ ላይ ቢተከልስ? ምናልባት እሷው ትሆናለች። ግን፣ እንዴት አወቀች እዚህ እንዳለሁ? ለማንም አልነገርኩም!
የዓይኗ ጨረር በተጨፈነው ዓይኔ ላይ እንዳረፈ ተሰምቶኛል። ተይዣለሁ ማለት ነው። እንግዲህ ማምለጫም የለኝ። ማድፈጥ እንዴት ያዋጣል ታዲያ? ፍርሃት በተሞላው ድፍረት ዓይኔን ተግ! አደረግሁ። ብርሃኖቻችን ሲጋጩ መብረቅ የሚፈጠር መስሎኝ ነበር። እምሸበርም መስሎኝ ነበር። (ይህንን ልብ አልኩ - ስሜት ሁልጊዜም እንደ ደራሽ ውሃ ነው። ቀጥሎ ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅም፡- ፍርሃት ወይም ልበ-ሙሉነት፣ ሃዘን ወይም ደስታ።) ልቤ ውስጥ ሰላም ሲወርድ ተሰማኝ። እንደ ቦረና እርጎ እያቀዘቀዘ የሚያረካ ሰላም። ዓይኗ ታይኔ እንዳያመልጥ ተጠንቅቄ ከተንጋለልኩበት ተቃናሁ። የሲሚንቶው ወንበር ላይ ተቀምጣለች።
ማነች?
ያለችውን በሃሳቤ አንገዋልዬ አልኩ፡- “እምፈለቅቅ መስሎኝ ነበር። ጊዜን በመፈልቀቅ እማውቅ። ሲሳካልኝ ዕንቁዎቹ የፈለቁት ተልቤ ይሁን ተጊዜ ማህፀን አስቤበት ግን አላውቅም።” (ስናወራ የቆየን ያህል ተሰምቶኛል።)
“እንደመጋባት ቁጠረው።” አለችኝ፤ “ያንተነትህና የጊዜ መጋባት። ልጃችሁ ነው ዕንቁው። ከእያንዳንዱ በራሪ ቅፅበት ጋር ተክሊል የሚያስሩ እነርሱ ብፁኣን ናቸው።”
እርጋታዋ ተጋባብኝ። የበሰለ ቃሏ ከበሰለ አካሏ ጋር ይስማማል። ወጣት ሴት ጠብቄ ነበር። ጠይም ሴት፣ ቀጠን ያለች ሴት፣ እህቴን የመሰለች ሴት፣ ጠብቄ ነበር።
የፃድቃን ቀጠሮ እሚባል ነገር አለ። ፃድቃን’እኮ ሳይቃጠሩ የሚገናኙት በነፍስ ዓለም ስለሚነጋገሩ ነው። ለፍቅረኞችም እንዲያ መሆን አለበት። በአካል ሳይወያዩ ነፍሶቻቸው ይመሳጠራሉ፤ ይቀጣጠራሉ፤ ድንገትም ተፋቃሪ አካሎችን አገናኝተው አልነቄውን አካል “አጀብ!” ያስብላሉ።
እና፣ ተገናኘን ማለት ነው?
“ምን እያሰብክ ነው?” አለችኝ።
“ገርሞኛል። ከእያንዳንዱ በራሪ ቅፅበት ጋር ተክሊል የሚያስሩ ብፁኣን ናቸው።” ከማስባቸው ውስጥ ለመናገር የሚመቸውን መረጥኩ። “ቃልሽ የልቤን ሙዳይ ከፈተው። ለሟች ቅፅበቶች ዘለዓለማዊ ህይወት እምንሰጠው እኛ ነን ማለት ነው? የእርግጠኛነትን ቀለበት እያሰርንላቸው?”
“የተቀባህ ነህ!”
የሚደላ ሞገድ ነው ድምፅዋ! ነውጡና ሃሴቱ ባንድ ላይ ነው።
ልቤ ይህችን ተቀኘች፡- በእያንዳንዱ ኣላፊ ቅፅበት አንገት ላይ የዘለዓለማዊነት ዶቃ አሰርን ማለት፣ በአላፊ ቅፅበት ውስጥ ዘለዓለምን ፈጠርን ማለትም አይደል? ፍቅር የነካው ጊዜ አያልፍም፤ በወሰን አልባ ህያውነቱም ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን ያገናኛል።
“በእርግጠኛነት ሰገነት ላይ መኖር እንደምትፈልግ ጓደኛህ ነገረኝ።”
ስለኔ ጠይቃለች ማለት ነው። ለምን ልታውቀኝ ፈለገች? እውነቷን ነው ለነገሩ። በህይወቴ ወደ ዓለሜ ተወርውረው ተፈነዱ የመርሆ እንክብሎች ስግብግብ ብዬ ያነሳሁት ይህችን ፍንጣቂ ነው፡-
“እውነት የአርነት ጎዳና ናት።”
እምዬ እውነት ደግሞ፣ እርግጠኛነት ተልብህ ተሌለ እኔም የለሁም፤ አለችኝ። በየቅፅበቱ ለእርግጠኛነትና ለእውነት ብነቃ ጊዜ አብሮ-አደጎቼ፣ “መሰለኝ፤” እና “ሊሆን ይችላል፤” ጥለውኝ ሸሹ። ውለታቸውን ባልረሳም አልናፍቃቸውም!
ታባቶቻቸው የወረሱትን፣ ተየዋሉበት የዕውቀት አምባ የቃረሙትን፣ ተየህልማቸው ያነጠቡትን የጥበብ ቅንጥብጣቢ ፈጭተው፣ አልመው፣ በየወንፊታቸው አጥልለው፣ የየድርሻቸውን ለመጎንጨት የተጉ ወጣት ነፍሶች አሉ፤ መባሉን ሰምቼ፣ ተጀማው ብሰየም፣ ምን አየሁ? … ሴት! ምን አየሁ? … እሳት! ተጥበብ ጀማ እሷ ምን እንደዶላት ባይገባኝም ፍቅር ታድማሴ ስትነጋ ታወቀኝ። (ዕብደት ሰጠችህ፤ ቢለኝም ወዳጄ) ያጠናገረችኝ ፍቅርም ትሁን ልክፍት እፈልጋታለሁ!
እና፣ ይህች ናት ማለት ነው? እውን አሁን ያች ልጅ፣ ይህች ልጅ ናት ማለት ነው?
ዝምታዬን አድምጣ ነው መሰል፣ ቀጠለች፡-
“እነሆ የእርግጠኛነትን ቅብዓ-ቅዱስ አምጥቼልሃለሁ። ከንፈርህን ስጠኝ አርሳቸዋለሁ። እውነት፣ እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ለእርግጠኛነት ተፈጠረ፤ ለጥርጣሬ ግን አይደለም። ወደ ጥንቱ ክብርህ በመመለስህ የተባረክህ ነህ።”
በድፍርስ ስሜት ሳያት አርጅታብኝ ነበር። ሳውቃት ወጣት ሆነችብኝ። ስረዳት ደግሞ ልጅ - እንደ ጠቦት! ወደ ውስጧ እየገባሁ ነው ማለት ነው?  ለመሆኑ፣ ሰው ማለት ነፍስ ማለት ተሆነ፣ እርጅናስ ማለት ምንድነው? መቼም ነፍስ ኣታረጅ!
“አንቺ ማነሽ ለመሆኑ?” (ያበጠ ይፈንዳ!) (ሁዋላ ባልንጀሬ ሴት እንዲህ አትጠየቅም ብሎ ገስጦኛል።) እሷ ግን ኣለች፡-
“ይህ የእውነተኛ ባህረኞች ጥያቄ ነው። የእውነተኛ ፈላጊዎች!”
“? ? “ (በጥያቄ ባያት) አለች፡-
“መጥምቁ ዮሃንስን ‘አንተ ማነህ?’ ብለው ጠየቁት፤ ሱፍ ለባሹ የኤልሳቤጥ ልጅ መሆኑን እያወቁ። ክርስቶስንም ‘ማነህ?’ ጠየቁ፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደሆነ እያወቁ። ቡድሃንም ‘ማነህ?’ ኣሉት፤ የንጉሳቸው ልጅ ጉታማ መሆኑን ሳይረሱ። ሙሃመድንም፣ ባብንም ባሃኦላህንም እንዲህ ጠየቁ፤ ከሚያዩትና ከሚያውቁት ማንነት ባሻገር ሌላ ማንነት እንዳለ የጠረጠሩና የነቁ። በኣካል ተገናኝተን ነበር ኣይደል?”
ጥያቄዋ ብርሃን ቢያቀብለኝ፣ ፈራሁ። ኣዕምሮዬ ሊያሳምነኝ እሚጥረውን ልቤ መቀበል ኣቃተው። በግልፅ ብትነግረኝስ? “በ’ርግጥ እኔ እሷ ነኝ፤” ብትለኝስ?
“የወንድ ልብ አዳኝ ነው፤” ይላሉ የምዕራባዊያንን ጥበብ የቀመሱ። አድኖ ታልያዘ የቀረበለትን ግዳይ ንክችም አያደርግ! ሴት ልጅ ቀድማው፣ “እነሆ መጣሁልህ፤ እወድሃለሁ!” ብትለው ይበረግጋል። ሁዋላ ተእግሯ ስር ሊንበረከክ፤ በራሱ ጊዜ የሲኦልን አቀበት መውጣት ይመርጣል። ይህን ሁሉ ጥበብ ሰምቻለሁ። ለዚህ ይሆን ልቤ ሊቀበላት ያቃተው?
ድንበር የለሽ ነፍሴ ከምዕራቡም የሃሳብ ዓለም ታላዳቀለችኝ በቀር እኔስ አበቃቀሌ ተወደምስራቅ ነበር። ታዲያ ለምን አመነታሁ? በዕድሜዋ? ምን አለበት? ባለ35 ናት ምናልባት። ጠይቃኛለች። እውነቱን መናገር አለብኝ፡-
“አይቼሻለሁ። በአርቡ የጥበብ ምሽት ላይ መሆን አለበት። ድምፅሽም አዲሴ አይደለም።”
ደረቅ ነፋስ ደረቁን የፅድ ግድግዳ ነቀነቀ። የሚያጣጥረው የአትክልት ስፍራ ለልቤ ጮርቃ ጥበብ አቀበለ፡- ታላቅ መጠራጠር ተልብህ ታለ፣ ጠብቅ፤ ታላቅ መገለጥ ይከተለዋል።
*  *  *
“ጠብቅ፤” ማለት “ንፃ፤” ማለት ነው፤ ኣልሁ በልቤ። ሁሉም ሰው በየባህሉ “ጠብቅ፤” ተብሏል። የጥበብ ቀን ትነጋለች፣ ጠብቅ። መንግስተሰማይ ትወርዳለች፣ ጠብቅ። ንፃ ማለት ነው። እንጂ ጥበብማ መለኮታዊ ብርሃን አይደለች? ሁልጊዜም አብራን፣ ሁልጊዜም ቅርባችን፣ ሁልጊዜም ውስጣችን? እኛ ቢሳነን እንስሳትና ዕፅዋት በኛ ፈንታ ጥበብን ይናገራሉ። በመንፃት ውስጥ ሙሉ ሃላፊነት ኣለ፤ በመጠበቅ ግን ትንሽ። እናም፣ የተቀበልኩት ሹክታ ይህ መሆን አለበት፡- ታላቅ መጠራጠር ተልብህ ታለ፣ ንፃ፤ ታላቅ መገለጥ ይከተለዋል።
ለምን እንደደፈረስሁ ደግሞ አውቀዋለሁ። በራሴ የስሜት ንዳት ላያት ፈለግሁ። ራሴ በፈጠርኩት ተቃርኖ በተቀበል አትቀበል ተናጥሁ። ሳንቃጠር ተገናኘን፣ ስለኔ ልታውቅ ጠየቀች፣ ሰው ተሌለበት ቦታ ልታናግረኝ መጣች፤ ... ማለት በፍቅር መንገድ ፈልጋኛለች ማለት ብቻ ነው? ወንድ ብትሆን ኖሮ እንዲህ አስብ ነበር?
መስከን አለብኝ፤ እንደ ውሃ መጥለል። ያኔ ብቻ ነው ንፁህ እሷነቷ በንፁህ እኔነቴ ውስጥ እሚንፀባረቅ። ምነው ለእውነት ግርዶሽ አበጀሁ?
“ይህ ፅድ የሞተ መስሎ ነበር። ኣገር ሙሉ ፅድ በከንቱ ደርቆ ይቅር? ብዬ አዝኜ ነበር። ኣሁን ነፍስ እየዘራ ነው። በድርቀት ውስጥ ልምላሜ ተደብቆ ኖሯል! …”
በጥርጣሬ ውስጥ እርግጠኛነት ተደብቆ ኖሯል! ያለችኝ መሰለኝ። ከነፋሱ ጋር ኣንድ ነው ቃላቸው። እንዲህ ኣልኳት፡-
“ሶስተኛው ዓይንና ስድስተኛው ህዋስ ስለሚባሉ ነገሮች ምን ታስቢያለሽ?”
ያልተጠበቀ ጥያቄዬ እኔን እንጂ እሷን ኣላስደነቃትም።
“ይህ ስያሜ ብቻ ነው። ከስያሜው ጀርባ ትልቅ እውነት አለ። ሰው ከስጋዊ ህዋሶች ባሻገር ሌሎች ሃይሎችም ኣሉት - ይህን አውቃለሁ።” አለች ስክነት ተሞልታ።
“በፍቅር ውስጥ ይህ ምን ማለት ነው?”
እኛ ባንጠይቅም በራሳቸው ፈቃድ ዘለው የሚጠየቁ አንዳንድ ጥያቄዎች ኣሉ። ይህንን ልብ ኣልሁ፡- እውነትን እኛ ኣንገልጣትም። እውነት ራሷን ትገልጣለች።
“አንተ ንገረኝ።” አለች በፈገግታ። መጠየቄ እሷንም ሳያስደስታት ኣልቀረም። ስለ ፍቅር ማውራት እማይፈልግ ማን ኣለ?
“እንቺ ንገሪኝ።”
“አንተን ልከተል።” (ደስ የሚል ድምፅ።)
“የሆነ የፍቅር መገለጥ ኣለ - ድንገት ዓይኖቻችሁ ሲጋጩ - ድ.ን.ግ.ጥ! ወዲያውም ፍርሃት ፍርሃት፣ ሳቅ ሳቅ፣ ዕብደት ዕብደት፣ … ይልሻል። ወይም በራስ መርሳት ትጠፊያለሽ። ባንድ መተያየት’ኮ ነው! ይህ ምንድነው?”
“መጠራት!” ፊቷ ለምን እንደምትጠይቀኝ ኣውቄኣለሁ። የሚል ፈገግታ ለብሷል።
“መጠራት?”
“ጴጥሮስ ባልጠበቀው ሰዓት ክርስቶስ መጣና ተከተለኝ፤ ኣለው። ይህ መጠራት ነው። እያንዳንዱ ሰው ለተፈቃሪው ጴጥሮስ ነው። እያንዳንዱም ሰው ቢያንስ አንድ መጠራት ኣለው።”
ይህ ለኔ ብጤው የተስፋ ቃል ነው። ሁሉም ሰው ቢያንስ አንዴ ያፈቅራል። ይህን ተስፋ በማድረግ ነበር ለዘመናት የጠበቅሁት። ዛሬ ተጠራሁ። ግን …
“ግን፣ ፍቅር ድንገት በሚበረገድ ልብ ብቻ ነው’ንዴ እምትገባ? እንደ ወንዝ እያዋዛች አትወስድም?” ባልንጀሬ ከካሊል ጂብራን ጣዝማዎች፣ ያቀመሰኝን ጠብታ አቀመስኳት፡-  
‘ፍቅር ከመላመድና ከረጅም ጓደኝነት ትመጣለች ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ፍቅር የመንፈሳዊ መሳሳብ ልጅ ነች፤ ይህ መሳሳብ በቅፅበት ውስጥ ካልተፈጠረ በዓመታት ውስጥ ኣይፈጠርም፣ በዘመናት ውስጥም ቢሆን።’ ይላል ጂብራን።
“ጂብራን ግማሹን እውነት ብቻ ተናገረ። የፍቅር እጆች ሁሌም እንደተዘረጉ ናቸው - ስትዘጋጅ ያቅፉሃል። ራስህን እንደ መስተዋት አስበው፤ ፍቅር ደግሞ ፀሃይ ናት። መስተዋቱ ድንገት ፀሃዩን ሲጋፈጥ አስደንጋጭ መጠራት ይሆናል። በቀስታም ወደ ፀሃይዋ ቢመለስ ይዘግይ እንጂ መስተዋቱ ብርሃኑን ማንፀባረቁ የማይቀር ነው። ጴጥሮስ ድንገት ተጠራ ማለት ለመጠራት ኣልተዘጋጀም ነበር ማለት ኣይደለም። ባለመንቃቱና ባለማወቁ ውስጥ ታላቅ እሾት፣ ታላቅ ጥማት ነበር። እንዲህ ያሉ የፍቅር ጴጥሮሶች ብዙ ኣሉ፤ ሳያስቡት በፍላፃው የሚወጉ። ብዙዎቻችን ግን በዓመታት መፈተግ ተወልውለን እንነፃለን። ጳውሎሶች ልትለን ትችላለህ። ከፍቅር ዓይን የሚሰውር የለምና የተዘጋጀውን ታውቃለች። ያኔ ትገለፃለች። እንግዲህ ሶስተኛው ዓይንና ስድስተኛው ህዋስ ማለት፣ የፍቅር ዓይን ሁሉን ታያለች፤ ማለትም ነው።”
ጴጥሮስ ታላቅ መንፃጽ ነበረው፤ አልሁ ለልቤ።
ግቢው መተንፈስ ጀምሯል። ከሁለታችን ድምፅ በቀር በአትክልት ስፍራው ውስጥ ፍፁም ፀጥታ ቢነግስም በፀጥታው ውስጥ ግን ህይወት ነበር። ዓይኖቿን አየሁዋቸው። አየችኝ። ቢያንስ ነፍሶቻችን ተጣጥመዋል። ጠየቅሁዋት፡-  
“አያብልም ግን ይህ ድንገት መጠራት?”
“በማፍቀር ፍርሃት ማፈግፈግ ይኖራል። በመጠራጠር ባህር ውስጥ መስጠምም ይኖራል። ጨርሶ ወደ ሁዋላ መመለስ ግን የለም። አያብልም፤ ሙሉ መቀበል ነው እውነተኛ መጠራት። ምልክቱም፣ ግቡም ያ ነው። ይህ ካልሆነ ልብህ በፅሉም እሾት ተወርሮ ነበር ማለት ነው። መደንገጥህም ለከንቱ ነው።”
በሚኮንን መልኩ ንግግሯ ከኔ ጋር የተያያዘ መሰለኝ። እኔ እሷ ነኝ፤ ካለችኝ በርግጥ ልቤ ይከፈላል። ሙሉ መቀበል ኣይኖርም። ፅሉም ስሜት ግን በልቤ የለም። የሆነ ያልገጠመ ኮከብ ይኖራል፡-
“በደነገጥሽላት ሴት ውስጥ ህልምሽ ባይኖርስ?” ኣልኳት።
“እምታልማትን እንደተዘጋጀ ሸማ ተሰርታና አልቃ እምታገኛት ከመሰለህ በርሷ ውስጥ ሳቅህ እንጂ ዕንባህና ደምህ ኣይኖርምና ያንተ ኣይደለችም። የትኛዋም ኣፍቃሪ ነፍስ ራሷ ባላነፀችው መቅደስ ውስጥ ተደላድላ ኣትተኛም። ኣልም። ህልምህን ስጋ እምታለብሳት ራስህ እንደሆንክ ግን እወቅ። ልብህ በደነገጠላት ሴት ውስጥ ህልምህ ኣለች፤ ባንተም ውስጥ የርሷ። በዘር መልክ እንጂ በጎመራ ፍሬ መልክ ግን ኣይደለም። ዕጣችሁ ሲያገናኛችሁ የፍቅርን ድንግል አፈር በሰላው የመተዋወቅ ሞፈር ታርሱታላችሁ። የየህልማችሁንም ዘር በመላቀቅ እጆች ትዘሩበታላችሁ። በትዕግስት፣ በይቅርባይነትና በታማኝነት ቅዱስ ውሃም ትመግቡታላችሁ። የቀኖቻችሁ መዓዛና የመርካት ፍሬዎቻችሁ በረከት ለፍጡራን ሁሉ ይዳረሳል። ሙሉ ህይወቱን ለዚህ ቅዱስ ግብርና የሰጠ የህይወትን ዓላማ ኣገኘ። መቅደሱን ኣልቆ ለማግኘት የሚኳትን ግን ፍለጋው ሁሌም ኣያበቃም። ኣገኘሁ ቢልም እንኳ ባገኘው ከቶም አይረካም። በዚህ ስንጥቅ ውስጥ አመንዝራነት አንገቷን ታስገባለች።”
ታላቅ መጠራጠር በልብ ታለ፣ ንፃ … የመገለጡ ክፍል የጀመረ መሰለኝ። የሰው ልጅ ስውር የጥበብ መዝገብ ርዕሱ ይህ ነው፡- ፈልግ! ያወገገብኝ ብርሃን ይህችን ጥበብ ተምላሴ ላይ አስቀመጠ፡- ፍለጋ ከጥያቄ ይጀመራል፤ የመጠራጠርን ደዌ በጥያቄ ዋግምት ንቀል!
ሁለት ጥያቄዎች ከቋጥኙ ልቤ ትርታር ፈለቁ፡- ይህ መዝናኛ እንዲህ ለምን ፀጥ ኣለ? ለወትሮው እሚተራመስበት የኣዳም ዘር ከዚህች ሴት ወይን ለመቋደስ ብቅ እማይለው ለምንድነው? ይህን በልቤ ቋጥሬ ሁለተኛውን ጥያቄዬን ኣቀበልኳት፡-
“መጠራቱ ከአንድ ወገን ቢሆንስ? የክርስቶስ ጥሪ የኣንድ ወገን ጥሪ ነበር። ጴጥሮስ ግን ተከተለው። ይህ በፆታዊ ፍቅር ውስጥ ቢሆን ጎደሎ አይሆንም?”
ልብ በሚነካ ድምፅ፣ “የክርስቶስ ጥሪ የኣንድ ወገን ጥሪ ነው?” አለች። ዝምታ። ቀጥላም፡- “ነውም፣ አይደለምም። ፍቅር ፍፁም ከሆነ ከአንድ አቅጣጫም ቢሆን በቂ ነው። እውነተኛ ፍቅር፣ ሙሉ ፍቅር፣ በተፈቃሪው ልብም ውስጥ እሳት የመጫር ሃይል ኣለው። ይህ ከተሳነው ቀድሞም ፍቅር ኣይደለም።”
ብዙ፣ ብዙ ልጠይቃት ፈለግሁ፤ ጥያቄዎቼ ሁሉ ደካማ መስለው ቢሰሙኝ፣ ጥያቄዎቼ ሁሉ መልሶቿን እሚወስኑብኝ መስለው ቢሰሙኝ፣ በደፈናው፡-
“ንገሪኝ፣ እማላውቀውን ሁሉ ኣሳውቂኝ። ልቦናዬን በቃልሽ ወይን አጥምቂልኝ።” ኣልኳት።
ከሱባዔ መሳይ አርምሞ በሁዋላ፡-
“ወሲብ መስጠት ኣይደለም፤ መሰጠት ነው።” ብላ ስትጀምር ልቤን እንዳነበበችው ኣወቅሁ። ሙሉ ቀልቤንም ሰጠሁዋት።
“ወሲብ መሰጠት ነው - ለፍጡራን ሁሉ እንደተሰጠችው ፀሃይ፣ ለኣፍቃሪዎች ሁሉ እንደተሰጠችው ጨረቃ፣ ለንቦች ሁሉ እንደተሰጡት አበቦች፣ ያለ ሙሉ መሰጠት። እልሃለሁ - ወሲብን ችሮታ ያደረግኸው ‘ለት ታጣዋለህ፤ ሙሉ መሰጠት መሆኑን ባወቅህ ሰዓት ታገኘዋለህ።
“በዋሽንት ውስጥ የምትንቆረቆር ዜማ ለፍቅረኞች ትፍስህትን፣ ለእናቶች ርህራሄን፣ ለተዋጊዎች ወኔን፣ ለፀበኞች ቁጣን፣ ለለማኞች ደግሞ ዕምባን ትሰጣለች።  ዋሽንት ዜማ ያፈልቃል፤ ዜማ ወደ ህዋ ይለቀቃል። የለም! የዜማው ዕጣ-ፈንታ በዋሽንቱ ኣይወሰንም። እንጉርጉሮው ወደ ህዋ ከመስገሩ በፊትም፣ ለዜማው ኣድራጊነት የዋሽንቱ ድርሻ ኢምንት ነው። በዜማው ውስጥ እንከን ካለ ዋሽንቱን ብቻ ለማረም መድከም ስንኩል መላ ነው። እውነቱ ይህ ነውና፡- የዜማው ምንጭ ባለዋሽንቱ-’ንጂ ሸንበቆው ኣይደለም። ሸንበቆው ዘለዓለማዊው የውበት ጣት በባለዋሽንቱ ነፍስ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ቅዱስ ኣውሎነፋስ የሚያስተላልፍ ኣሸንዳ ብቻ ነው። በወሲብ ወቅት ኣንተም እንደሸንበቆ የህይወት ህያው ሙቀት የሚተላለፍብህ ቦይ ብቻ ነህ።
“ሙሉ መስጠት እንደምን ያለች ነች? አትበለኝ። ሙዚቃን ለተጠማች ነፍስ ሸንበቆን የሚወረውር እርሱ በርግጥ ተሰጥዖውን ኣነወረ። ለምታፈቅራት ሄዋን ስጋህን ብቻ በችሮታ ብታቀርብ ከቁንፅሉ የመስጠት ግብህ እንኳ ልትደርስ ኣይቻልህም - ሙሉ መሰጠት የነፍስና የስጋ ህብር ነችና። የወሲብ እንከንህን በስጋህ ላይ ብቻም አትፈልጋት። ወደ ልብህም አሸንቁረህ እያት።”
ነጎድጓድ ሰማሁ ልበል? በነዚህ የሚሞቁ ቃላት ውስጥ ቅዝቃዜ የተሰማኝስ እንዴት ሆኖ ነው? ጥቂት ቅፅበቶችን ዝምታ የዋጣቸው መሰለ። እንደገናም የሚሞቅ ቃሏን ከሚፈስሱት ደቂቃዎች ጋር ኣዋሃደች።
“ሙዚቃ ሰማያዊት ነች። በወርቅና በዝና፣ በግብ-ኣልቦነትና በከንቱ ምናብ ምኩራቦች ውስጥ የምትካድም ከሆነ እሷ ሰስናለች። እውነተኛ ሙዚቃ ለመለኮታዊው የውበት ኣምላክ ታማኝ ነች። ሙሉ መሰጠቷም ያለው በርሱ በኩል ብቻ ነው። ያንተም ሙሉ መሰጠት ያለው ሚስትህ በሆነች ሴት በኩል ብቻ ነው። በወሲብ ኣንተ ለሚስትህ ትሰጣለህ፤ እሷም ላንተ ትሰጣለች። እውነቱ ግን ይህ ነው፡- ሁለታችሁም በእያንዳንዳችሁ በኩል የምትሰጡት ለዓለሙ በሙሉ ነው። ያንተም ሆነ የ’ሷ ሙሉ መሰጠት ባንተም ሆነ በ’ሷ ውስጥ፣ ቅዱስ ቤተሰብ፣ ደስተኛ ልጆችና እውነተኛ እርካታ ሆኖ ለሰው ዘር ሁሉ ይሰጣል - ላሉትም፣ ለሚመጡትም። የፍጥረት ሁሉ ደህንነት መሰረት ይህ ነው። የሰው ዘር ብቻም ኣይደለም፤ የፍጥረት ሁሉ ደህንነት። በሙዚቃና በወሲብ ሃይል የማይቻል ይቻልሃል፡- በኣላፊ የቅፅበታት ጠብታዎች ውስጥ እንደተሳፈርክ በዘለዓለማዊነት ባህር ውስጥ ትዋኛለህ። ከጥበብ ፅዋ በተጎነጩ ብቁኣን ዘንድ ሁለትነት የለምና፣ ሙዚቃና ወሲብ ኣንድ ናቸው።”
ለልቤም እንዲህ ኣልሁ፡- ይህች ኣፍቃሪ ሴት ብቻም ኣይደለች፤ የፍቅርን መቅደስ እንደከርቤ ጭስ ለማወድ በየልቡ የምትተነፈስ ሽቱ ነች።
ታላቅ የዝምታ ሰማይ ተዘረጋ። ከዝምታው ቅዝቃዜ ተወለደ። በቅዝቃዜው ውስጥ ኣብረክራኪ ነጎድጓድ ተስተጋባ። በመብረክረኩ ውስጥ እኔ ነቃሁ። (ከህይወት ወደ ሞት ተነሳሁ ልበል?) ኣትክልቶቹ መጠለያ እንዳጣ ፈረስ ኣንገታቸውን ደፍተው ዶፉን ይቀበላሉ። እኔም ኣንገቴን ደፋሁ። ፊቴን እያጠበ የሚወርደው ውሃ እንደ ፅጌረዳ ቀልሟል። ነስሮኝ ነበር ማለት ነው። (ራስምታትና ፀሃይ ሲፈራረቁብኝ ያነስረኛል።) ኣካሌን ኣደመጥኩት። ህመም ወርሮታል። መንቀሳቀስ ግን እንደምችል ኣረጋገጥሁ። ጎርፉ ያለበሰኝን ኣፈር ዶፉ እንዲያጥብልኝ ትንሽ ቆየሁ። እንዴት ይህን ያህል ደነዘዝኩ? (ህልሜን ሊነጥቁኝ ያልፈለጉ የቸርነት እጆች ከኔ ጋር ነበሩ መሰል።)
ከግቢው ስወጣ ማንም ኣላየኝም። ቢያዩኝም ሰክሬ የነበር ይመስላቸዋል። እንደኔ ባህር ውስጥ ቆይተው ዓሳ መሆንን ባወቁ፣ ኣልሁ። ያኔ ወደ ሁለተኛው ምንቃት ተሸጋገርኩ። ኣልሜ ነበር። በህልሜ ውስጥ ሴት ነበረች። በርሷ ውስጥ ደግሞ ጥበብ። ያለችኝን ለማስታወስ ሞከርኩ። በትውስታዬ ውስጥ ኣንድ ቃል ደምቆ ተስተጋባ፡- ታላቅ መጠራጠር ተልብህ ታለ፣ ንፃ፤ ታላቅ መገለጥ ይከተለዋል።
ምናልባት ያለምኩት ለደቂቃ ይሆናል። በነፍሴ ውስጥ ግን አድማስ አልባ የጥበብ ባህር ተዘርግቷል። መጀመሪያው ሁሉም ቦታ፤ ማለቂያውም ሁሉም ቦታ የሆነ ባህር። ይህ የዘለዓለም ባህር ነው፤ ኣልሁ ለልቤ። ግን፣ የዘመናት ሁሉ ህልም በደቂቃ ውስጥ እንዴት ሊታመቅ ይችላል? ሁሉም እውነት፣ ሁሉም ውበት፣ በቅፅበት ውስጥ እንዴት? ይህን ለልቤ ነገርሁ፡- በቅፅበት ውስጥ ዘለዓለምን ማየት ከቻልክ ለሰዓታትም ኣለምክ ለዓመታት ልዩነት የለውም። ህልሜን ሳልጨርስ ነቃሁ የሚል ቁጭት በውስጤ ነበርና በዚህ ተፅናናሁ። የተቋረጠ ህልም አልነበረም። (ጎርፉ ሳይውጠኝ እንኳን ነቃሁ!)
ገፅዋ በልቤ ተቀርፆ ቀርቷል። አካሏ እንደሚዳሰስ አበባ፣ ቃሏም እንደሚፋጅ እሳት እውን ነበር። የነፍሷ ንፃት ነው ሁሉን የነገረኝ መምህሬ። ባህሬም እሱው ነበር። እንደዓሳ ተነጥቄ ስወጣ ትዝታዋ ጅረት ሆነ። ሞገደኛ ቃሏን ቃሌ ላደርገው ብሞክር ሻከረብኝ። ተኣዕምሮዬ ሙዳይ ልደብቀው ባስብም ሻከረብኝ። በቃ፣ ተትዝታ በላይ፣ ተኣዕምሮም በላይ ትቀመጥ። ህልሜ ነች፤ ህልሜን ኣምጣ የወለደች ህልሜ! ዓለሟም ተዓለሜ ኣይደለም። እኔ ወዳለሟ ልሂድ እንጂ እሷስ ተዓለሜ ኣትምጣ! የለመኑትን እማይነሳው የቀን ህልሜን እንዳይነሳኝ ልለምን። ህልሜን እንድትወልድ ልማጠናት። ተራሷም ሌላ ሌላ ህልም እንዳትፈጥር ደጅ ልጥና።
እየቃዠሁ ነው? ይህ ቅዠት ተሆነስ ሌላ እውነት የት ይኖራል?
*  *  *
ይህ በሆነ በማግስቱ ተ’ንቅልፍ ዓለም ማልጄ ተመለስሁ። ከመኝታዬ እንደተነሳሁም ያው እንደወትሮዬ ቀድሜ ወደ መዝገበ-ውሎኣችን ኣመራሁ። ባልንጀሬ እኔ ስለትናንት ውሎዬ ከፃፍኩት ማስታወሻ በታች የፃፈውን ሳይ ሶስተኛው መንቃት ሆነ። እንዲህ ይላል የ’ሱ ቃል፡-  
ኣንዳንዴ ግራ ያጋባኛል። የጤናማነት መለኪያው ምን ይሆን? የዕብደትስ መስፈሪያው ምን? እላለሁ።
ባልንጀሬ የዕውኑና የህልሙ ዓለም ድንበር ተሳክሮበት በሁለቱም ዓለማት ሲዋትት ኣያለሁ።
ግን፣ የህልም ዓለሙ ከዕውኑ ይበልጥ ዕውን መሆኑ፣ የ’ሱን በህልም ዓለም መኳተን ጤናማ ያደርገዋል?  በዕውን ዓለም የሆነንስ ህልም ዓለም ይዞ መሄድ በሽታ ይሆን? ዕውኗ ህይወት ህልም ስትሆን ውበቷ ይበልጥ፣ ሚስጢሯም ይበልጥ፣ የሚገለጥ ከሆነስ?    
ጨቀጨቀኝ። በዚያ የዓርቡ ምሽት ላይ ለሁለት ሰዓት ያህል ኣፍጦባት መልኳን እንኳ ያላያትን ልጅ እንዳሳየው ወተወተኝ። ላሳየው ኣልፈለግሁም። እሱ ለዚያን ያህል ጊዜ ዓይኖቿ ውስጥ ዓይኖቹን ተክሎ ኣካሏን ማወቅ ከተሳነው፣ እኔ ኣንድ ኣካል ባሳየው ለሱ ምን ትርጉም ይኖረዋል?  ‘ኣንተ ያየኸው መንፈሷን ነው፣ ስጋዋንም ኣንተው ፈልገህ ኣግኝ፤’ ኣልኩት። ያ ኣላቆመውም። እንዲያው ቢተወኝ ብዬ፣ ስለልጂቱ እማውቀውን እውነት ብቻ ነገርኩት፡- እሷ የሰው ሚስት እንደሆነች፣ ሰዓሊ እንደሆነች፣ ስዕሎቿን ብዙውን ጊዜ እሰፈራችን ካለው የቀበሌ መዝናኛ ውስጥ እንደምትስል፣ … ወዘተ። ኣሁን ታዲያ የነገርኩትን የዕውን ቃሌን ረስቶ፣ ከህልም ዓለሙ እንዳገኘው፣ ቀበሌም የሄደው በኣጋጣሚ፣ ስለሷም ያለመው እንዲሁ፣ እንደሆነ ያስባል።
አመነታሁ። ወደ ዕውኑ ዓለም ኣምጥቼው ያመነውን የህልም ዕውን ከምነጥቅበት፣ እዚያ እህልም ዓለም ውስጥ በትህፍስት እንዲኖር ልተወው ይሆን?  ብዬ ኣመነታሁ። ግን፣ ያ እውነት ኣይሆንም። እውነት ታልሆነ ደግሞ ውበቱ ምኑ ላይ ነው?  ቢያንስ እውነቱን ይወቅና ያሻውን ዓለም ይምረጥ።…
“አታመንዝር!” ይላል የመልካሙ መፅሃፍ ስድስተኛው ትዕዛዝ። “ያየም፣ የተመኘም አመነዘረ፤” ብሎም የትዕዛዙን ካቴና ያጠብቃል። ባላይም ተመኘሁ። ስድስተኛው ትዕዛዝ ስድስተኛ ሃጢዓት ሆኖ በመፈረጃዬ መዝገብ ላይ በደማቁ ተፃፈብኝ። ... ያ መተላለፍ እንዲፋቅ እፈልግ ይሆን?  
(ምንጭ:- "ጉራማይሌ" የዘመናችን አጫጭር ታሪኮች)


Read 1890 times