Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 September 2012 11:45

የምር፤ “የህይወት ጥቅሙ ምንድነው?” - መቼም የማይሞት ሰው የለም

Written by 
Rate this item
(13 votes)

“በመልካም ስራው ሲታወስ ይኖራል” እንዳትሉ። ከሞተ በኋላ ታሪኩ ቢነገር መቼ ይሰማና!

“ስምና ስራ ከመቃብር በላይ ነው” እንዳትሉ። ከሞተ በኋላ አድናቆትና ክብር ምን ሊረባው!

“ድንቅ ስኬታቸው ዘላለማዊ ናቸው” አትበሉ። ከሞት በኋላ ምንም ነገር ትርጉም የለውም!

ጀግኖች፤ በህይወት እያሉ ነው በመልካም ስራና በድንቅ ስኬት ዘላለማዊነትን ያጣጣሙት!

የድፍረት አባባል እንዳይመስላችሁ። ርዕሱ ላይ፤ “የማይሞት ሰው የለም” ብዬ ስፅፍ፤ ... ዝግንን ብሎኛል። የተለመደ አባባል ስለሆነ፤ ብዙውን ጊዜ ያን ያህልም ስሜት ላይሰጣችሁ ይችላል። “ህይወት አላፊ ነው” ይባላል - እንደ ዋዛ። አንዳንዴ ግን፤ “የማይሞት ሰው የለም” ብላችሁ ስትናገሩ ወይም ስትሰሙ፤ ...የምር ውስጣችሁ ድረስ ጠልቆ ይሰማችኋል - ሰውነትን የሚያስፍቅ ሸካራ ስሜት። ሳይበርዳችሁ... ቆዳችሁ ተሸማቅቆ ፀጉራችሁ ይቆማል።

እስከ ዛሬ ያካበታችሁት እውቀትና ችሎታ፤ የሰራችሁትና ያፈራችሁት ነገር ሁሉ፤ ለወደፊት ያሰባችሁትና ያቀዳችሁት ሁሉ፤ የምታፈቅሩትና የምትሳሱለት፤ የሚያስደስታችሁና የሚያጓጓችሁ ነገር ሁሉ... ድንገት ትርጉም ሲያጣ ይታያችሁ። የምን ማየት! ከሞት በኋላ አንድ አፍታ ለማየትም እንኳ እድል የለም። ዛሬ አለሁ፤ ነገ የለሁም። ... አለቀ፤ እስከ መቼውም የለሁም። ለሞተ ሰው፤ “ከዚያ በኋላ....” የሚባል ነገር የለም። “ከዚያ በፊት... ከዚያ በኋላ” ብሎ ሊያስብና ሊናገር አይችልም። ጨርሶ የለማ። በቃ፤  ብን ብሎ ድንገት ጥፍት... ባዶ... ። ታዲያ የህይወት ትርጉም ምንድነው?

ሰው ቢሞትም፤ “ከዚያ በኋላ...” የሚባል ነገር ይኖረዋል ብሎ መሟገት እንደሚቻል አውቃለሁ። አሁን ግን፤ ጠያቂውና ተጠያቂው እኔ ራሴ ስለሆንኩ፤ መከራከሪያና ማሳመኛ አይሆነኝም። ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ ማየትና ማረጋገጥ ሳይቻል፤ ከራስ ጋር ተከራክሮ ማሳመን ከባድ ነው። ለነገሩ፤ ከዚህኛው ዓለም ባሻገር፤ ሌላ “የወዲያኛው ዓለም” ቢኖር እንኳ፤ እንዴት ማፅናኛ ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም።

የሞተ ሰው፤ ወደ ወዲያኛው አለም ይሄዳል እንበል። ግን፤ ይሄኛውን አለም ተመልሶ ማየት አይችልም። የሚወደውን ስራ ተመልሶ ሊሰራ አይችልም። የሚወደውን ምግብ መቅመስ፣ ከሚያፈቅራቸው ሰዎች አጠገብ መሆንና ማነጋገር አይችልም። ምንም ማድረግ አይችልም። ሰዎችም ምንም አያደርጉለትም። ቢበዛ ቢበዛ፤ የትዝታቸው ቅንጣት ውስጥ ታሪኩን ያስታውሱ ይሆናል። እሱ ግን  ...የለም፤ ከእንግዲህ አይኖርም። ታዲያ፤ በህይወት ዘመኑ ውስጥ፤ እንዲያ ብዙ በሃሳብ መብሰልሰሉና ለነገ ማቀዱ፤ ማውጣትና ማውረዱ፣ ለስራ መድከሙና ለውጤት መጣጣሩ ምን ትርጉም አለው? የህይወት ፋይዳስ ምንድነው?

ዘመናዊ ማፅናኛዎቻችንን ሳላስባቸው የቀረሁ እንዳይመስላችሁ። “ሰው ይሞታል፤ ስራው ግን ህያው ነው” እንደሚባል አውቃለሁ። “ስምና ስራ ከመቃብር በላይ ናቸው” ሲባልም እሰማለሁ። “በአካል ብትለየንም በመንፈስ ከኛ ጋር ነህ” ይባላል። “ሰው በመልካም ስራውና በድንቅ ስኬቱ ህያው ይሆናል” ... ይህንንም ሰምቻለሁ፤ እንዲያውም እኔ ራሴ ብዙ ጊዜ የምለው ነገር ነው። “በሰራኸው መልካም ስራ ዘላለም ህያው ትሆናለህ፤ ዘላለም በክብር ታሪክህ ሲታወስ ይኖራል” ይባላል። ...አባባሎቹ የሆነ ደስ የሚል ነገር አላቸው። እኔም አባባሎቹን እወዳቸዋለሁ።

ነገር ግን፤ እንዲህ አይነት ሺህ እና ሺህ አባባሎች ተሰብስበው ቢደመሩ፤ ለሟች ነፍስ ሊዘሩና ህይወትን ሊመልሱ አይችሉም። በህይወት ያሉ ሰዎች፤ እነዚህን አባባሎች እንደመፅናኛ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። ምናልባትም መንፈሳቸው ይነቃቃ ይሆናል - በህይወት ካሉና አባባሎቹን ከሰሙ። በህይወት ለሌሉና መስማት ለማይችሉ ግን፤ እነዚያ እልፍ አባባሎች በሙሉ ትርጉም የላቸውም። ከሞተ በኋላ፤ “ታሪኬ እንዴት ይወራ ይሆን?” ብሎ የሚያስብ ሰው የለም። አላሰበም ወይም አያስብም ማለቴ አይደለም። ለማሰብ፤ በቅድሚያ በህይወት መኖር አለበት። ከሞት በኋላ ግን፤ ... በቃ ...የለም።

ከመኖር ወደ አለመኖር መሻገር... ከዚያ በኋላ ምንም የለም። ባዶ ነው። ምን ያህል ሰው በስራዬ ያደንቀኝ ይሆን? ስንቱስ በሞቴ ያዝንልኛል? የቀብሬ አከባበር እንዴት ይሆን? የጀመርኩትና የገነባሁት ቢፈርስስ? ያቀድኩትና የተለምኩትስ ይሳካ ይሆን? ታሪኬ ዘላለም ይቆያል ወይስ እረሳ ይሆን?... ከሞት በኋላ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ፋይዳ የላቸውም። ለማን ሊፈይዱ! ለማን ሊጠቅሙ! ከሌለህ የለህም። ሁሉም ነገር አብቅቷል። ታዲያ የህይወት ፋይዳው ምንድነው? የመንግስቱ ለማ ግጥም አይመጣባችሁም? (ስንኞቹ ውስጥ “ት” ጠበቅ ተደርጋ ስትነበብ ነው ቤት የሚመታው)

ለምንድነው አልኩኝ

በምን ምክንያት

ህፃን መወለዱ

አርጅቶ ሊሞት

በጨላለመ ሃሳብና ስሜት የጀመርኩት ፅሁፍ፤ ድንገት የመጣ እንዳልሆነ መገመታችሁ አይቀርም። ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት ጋር ብዙ ሰዎች ብዙ ነገር አስበዋል። ስለ አገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ አውጠንጥነዋል። ፖለቲካውና የስልጣን ሽግግሩ አሳስቧቸዋል። የኢኮኖሚና የኑሮ ሁኔታ እንዴት ይቀጥል ይሆን ብለው አሰላስለዋል ... በአመዛኙም ስጋትና ጥርጣሬ በተሞላበት መንፈስ። ለየት የሚል መንፈስ የሚጫጫናቸው ግን፤ ስለ ህይወትና ስለ ሞት ሲያስቡ ነው - “የህይወት ፋይዳ ምንድነው?” ከሚል ጥያቄ ጋር ተጭኖ የሚመጣ የጨላለመ መንፈስ።

በእርግጥ፤ ይሄ ጨለማ መንፈስ፤ ከሃዘን ስሜት ጋር ስለሚደባለቅና ስለሚቀየጥ፤ ሁለቱን በግልፅ ለይቶ ለማውጣትና ለማየት ያስቸግራል። ግን፤ ጨለማው መንፈስ ከሃዘን ስሜት ይለያል፤ ይብሳል። የሃዘን ስሜት፤ “አንዳች ነገር ማጣት”ን የሚያመለክት ነው - ተፈጥሯዊና ተገቢ የሆነ ስሜት። “የህይወት ፋይዳ ምንድነው? ምን ትርጉም አለው?” ከሚለው ጥያቄ ጋር አብሮ የሚከሰተው ጨለማ መንፈስ ግን፤ “ራስን ከማጣት” ስሜት ጋር የተያያዘ ነው - ከተሳሳተ አስተሳሰብ የሚመነጭና ተገቢ ያልሆነ ጨለማ መንፈስ።

ማጣትና ማዘን - ከትንሽ እስከ ትልቅ

አቤት የሃዘን አይነትና መጠን አበዛዙ! ለነገሩ የደስታ አይነትና መጠንም እጅግ ብዙ ነው። አይነታቸው ይብዛ እንጂ ከሁለት ምንጮች የሚፈልቁ ናቸው። ደስታ የሚመነጨው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ ከ”ስኬት” ነው። “ማጣት” ደግሞ ሃዘንን ያስከትላል። ደስታና ሃዘን የእለት ተእለት ህይወታችን ቢሆኑም፤ ከስኬትና ከእጦት የሚመነጩ መሆናቸው በግልፅ ይታየናል ማለት አይደለም። ባይታየን ደግሞ አይገርምም። የብዙዎቻችን ህይወት በአርቴፊሻል “ደስታ እና ሃዘን” ሲበረዝ ውሎ የሚያድር ነውና። እንዴት በሉ።

የውሸት “ደስታ”ን እያውለበለብን መፈንጠዝ ያምረናል - ያልደረስንበትን ስኬት እንዳገኘነው እየቆጠርን። ወይም አላስፈላጊ “ሃዘን” ተከናንበን ትካዜ ውስጥ እንነከራለን - አላግባብ በጥፋተኝነት ስሜት ራሳችንን እየወቀስን። በመጠጥ ሞቅታ የሚገኘው ደስታ ከየትም የሚመጣ አይደለም። ሰዎች ሞቅ ሲላቸው ሃብታም ወይም ጀግና፤ አዋቂ ወይም ትልቅ የሆኑ ሲመስላቸውኮ፡፡ “ስኬታማ ነኝ” ብለው አሰቡ ማለት ነው። “ስኬት” ደግሞ ደስታን ይፈጥራል - ጊዜያዊ አርቴፊሻል ደስታ። የአስመሳዮች ደስታም ተመሳሳይ ነው። ባልሰሩትና ባልፈጠሩት ስኬት፤ በአስመሳይነታቸው የሰው አድናቆትና ሙገሳ የሚጎርፍላቸው ሰዎች በደስታ የሚሆኑትን ሊያጡ ይችላሉ። በሙገሳ ሲሰክሩ፤ ስኬታማ የሆኑ ይመስላቸውና፤ ደስታ ይሰማቸዋል።

ችግሩ፤ ማታ ሰው ሁሉ ተኝቶ ሙገሳው ሲቋረጥ ወይም በማግስቱ ሞቅታው ሲበርድ፤ “ስኬታማ ነኝ” የሚለው የስካር ሃሳብም አብሮ ይጠፋል፤ “የውሸት ደስታውም” እንዲሁ። በእውነተኛ ስኬት ላይ የተመሰረተ እውነተኛ ደስታ ግን፤ በአንድ ሌሊት እንቅልፍና በአድናቂ እጦት በኖ አይጠፋም። የሆነ ሆኖ፤ ማንኛውም የደስታ አይነት፤ የውሸትም ይሁን የእውነት ደስታ፤ ዞሮ ዞሮ ከ”ስኬት” ጋር የተቆራኘ ነው (የእውነትና የውሸት ስኬት)።

የሃዘን ምንጭም፤ (ሃዘኑ ተገቢም ይሁን አላስፈላጊ)፤ ከ”ማጣት” ጋር የተያያዘ ነው - (የእውነትና የውሸት እጦት)። ያስቀመጥነውን ውድ እቃ ፈልገን ካላገኘነው፤ የጠፋና ያጣነው እየመሰለን እናዝናለን። ግን ጊዜያዊ ስለሆነ ብዙም አይጎዳም። መጥፎነቱ እጅግ ጎጂ የሆኑ አላስፈላጊ ሃዘኖችም አሉ። ከፍተኛ የፈተና ውጤት በማስመዝገቡ እየተደሰተ፤ ነገር ግን ከጓደኞቹ በመብለጡ የጥፋተኝነት ስሜት የሚፈጠርበት ተማሪ አለ - ጓደኝነታቸውን የሚያጣ እየመሰለው። በቢዝነስ ስራው ስኬታማ እየሆነ ደስታ ቢያገኝም፤ ገዳም የመግባት ፍላጎት በማጣቱ ራሱን እንደጥፋተኛ የሚቆጥርም ጥቂት አይደለም። እነዚህ አላስፈላጊ ሃዘኖች ናቸው።

ከ”ማጣት” (ከመጎዳት) የሚመነጩ እውነተኛ ሃዘኖችም ቢሆኑ አስፈላጊ ናቸው ማለቴ አይደለም። ግን ተፈጥሯዊ ናቸው። አንድን ነገር መውደድና ማክበር ማለት፤ ያስደስትሃል ማለት ነው፤ ስታጣው ደግሞ ያሳዝንሃል... የግድ ነው። ሁሉም ሃዘኖች ከማጣት የሚመነጩ ቢሆንም፤ ስፋትና ክብደታቸው ግን... የትና የት! የሚያኮማትር፣ እየቆየ የሚያስደነግጥና ግራ የሚያጋባ ሃዘን እንዳለ ሁሉ፤ ከአፍታ ብልጭታ የማያልፍ ሃዘንም ይኖራል።

ሃዘን የሚለውን ቃል በየጊዜው ምን ያህል እንደምንጠቀምበት አስቡት። ልብሷን ጭቃ ሲነካት አሳዘነችኝ ይላል። አዳልጦት ስለወደቀ አሳዘነኝ ትላለች። ካልተጎዳ ተመልሶ ይነሳል። ጭቃ የነካው ልብስም፤ ታጥቦ ይነፃል። ያጣነውን ነገር ቶሎ መልሰን የምናገኘው ከሆነ፤ ለሃዘን ፊት አንሰጠውም - ከወደቅንበት እንነሳለን፤ የጨቀየውን እናጥባለን። ግብዣ ጠርተውት ሳይመጣ በመቅረቱ፤ ብርጭቆው ስለተሰበረ፣ የልጅነቱ ፎቶ ስለተቃጠለ፣ የቤቱ ጣሪያ ስለተገነጠለ፣ በፈተና የማለፊያ ውጤት ስላጣ፣ የአሜሪካ ቪዛ ስለተከለከለ፣ ገንዘብ ከቦርሳው ስለተሰረቀ.... ያዝናል። ከፍቅረኛው ጋር ስለተጣላ፣ የሚወደው ሰው ስለደኸየ፣ የራሱ ንብረት በጎርፍ ስለተወሰደ፣ ጓደኛው በመኪና ስለተገጨ፣ የራሱ አካል በአደጋ ስለጎደለ፣ የሚያደንቀው ሰው ስለታመመ ... በጣም ያዝናል። የሚያከብረው ሰው ስለሞተ... እጅግ አዝኖ ያለቅሳል።

ደረጃቸው የሰማይና የምድር ያህል ቢራራቅም፤ ሁሉም አይነት ሃዘኖች፤ ኮምጣጣውም ሆነ መራራው ሃዘን ... ከ”ማጣት” የሚመነጩ ናቸው። አንዳንዶቹ ሃዘኖች እጅግ መራራ የማይሆኑት፤ ያጣነውን ነገር መልሰን ልናገኘው ስለምንችል ነው። ጊዜና ጥረት ያስፈልገው ይሆናል እንጂ፤ በተቃጠለብን ንብረት ምትክ ሌላ ንብረት የማፍራት እድል ይኖረናል። የለመድነው ወይም የምንወደው፤ የምናውቀው ወይም የምናከብረው ሰው ሲሞት ግን... መልሰን ልናገኘው አንችልም። ትዝታው ብቻ ነው የሚቀረን። የድሮውን ከማስታወስ በስተቀር፤ የድሮው ህይወት ተመልሶ እውን አይሆንም።

የሞት ሃዘን እጅግ መራራ ነው። በተለይ ከእለት ተእለት ህይወታችን ጋር የዘወትር ወይም የቅርብ ትስስር ያለው ሰው ሲሞት፤ ከሃዘኑ በተጨማሪ እየቆየ ድንግጥ ድንግጥ ያሰኛል። ቤት ስንገባና ስንወጣ፤ ድንገት እንድንገጣጠምና ድምፁን እንድንሰማ እንጠብቃለን። በየእለቱ የለመድነውና እንደ ቋሚ የተፈጥሮ ኡደት የምንቆጥረው ነገር ነዋ። ከብዙ ሃሳቦቻችንና ተግባራችን ጋር የተሳሰረ ነዋ። እናም፤ እንደለመድነው እንጠብቃለን።

ግን፤ ከእንግዲህ በአካል አናየውም፤ ድምፁንም አንሰማውም። ከእንግዲህ ጨርሶ የማይሆንና የማይቻል ነገር መሆኑ ብልጭ ሲልብን ድንግጥ እንላለን። ጭራሽ፤ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሃዘናችን እየበረታ ይሄዳል - በሞት ያጣነውን ሰው መልሰን ልናገኘው እንደማንችል በደንብ እየገባን ይመጣል። ከዘወትር የእለት ተእለት ልምዳችን ጋር የማይገጥም እውነታ ተፈጥሯል። ከዚህ እውነታ ጋር ስንፋጠጥ ድንግጥ እንላለን።

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በቲቪ ሲናገሩ ማየት ምን ያህል ከህይወታችን ጋር እንደተሳሰረ አስቡት። አሁንም ድንገት ቲቪ ከፍተን ስንመለከት... የጠ/ሚ መለስ ንግግር ስናይ... የምናውቀውና የለመድነው ነገር ነው። ... ግን ወዲያው ድንግጥ እንላለን። ለካ፤ ከእንግዲህ በጭራሽ ፓርላማ ውስጥ ንግግር ሲያደርጉ በቲቪ መከታተል አንችልም፤ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ... ለወትሮው እንደ ነባር ስንቆጥረው የነበረ ነገር፤ አሁን ፈፅሞ የማይቻልና የማይሆን ነገር ... ከእንደዚህ አይነት ነገር ጋር ስንፋጠጥ ነው ድንጋጤ የተቀላቀለው ሃዘን የሚሰማን - ከ”ማጣት” የመነጨ ሃዘን።

 

“የህይወት ትርጉም - ዘላለማዊነትን ማጣጣም”

ሰውን በሞት ከማጣት የሚመነጭ የሃዘን ስሜት፤ ከሌሎቹ የሃዘን ስሜቶች ለየት ይላል። ብዙውን ጊዜ ሌላ ተጨማሪ ስሜት ይጭንብናል። “የማይሞት ሰው የለም” ከሚለው ሃሳብ ጋር፤ “ታድያ የህይወት ፋይዳው ምንድነው?” የሚል ጥያቄና ጨለማ መንፈስ ይፈታተነናል። ህይወት ትርጉም የሚያገኘው፤ ሞት የሚባል ነገር ከሌለ ነው ብለን ስለምናስብ ይሆን? ህይወትን ስለማናጣጥማትም ሊሆን ይችላል። እናም፤ ከሞት ባሻገር ከሞት ወዲያ ማዶ እንቃኛለን - የህይወትን ትርጉም ለማግኘት።

አንዳንዴ፤ በሌላ የወዲያኛው አለም፤ ሌላ የወዲያኛው ህይወት እንዳለ በማመን፤ ከጨለማው መንፈስ ለመገላገል እንጥራለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ “የሞተው ሰው፤ በስራው ህያውና ዘላለማዊ ሆኗል” በማለት ራሳችንን እናፅናናለን - የህይወት ትርጉም ታሪካዊ ስራ አከናውኖ ማለፍ እንደሆነ በማመን። ከሞት በኋላ ሌላ የወዲያኛው ህይወት ባይኖር እንኳ፤ “የታሪክ ህይወት” የሚባል ምናባዊ የህልውና አለም እንፈጥራለን - “በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ሰው” እንላለን።

እንግዲህ፤ መሞት ማለት ዘላለማዊ ፍፃሜ መሆኑን ላለማመን ነው መፍጨርጨራችን። በዚህም፤ ጨለማውን መንፈስ አሽቀንጥረን የምንጥል ይመስለናል። መሞት ግን፤ ዘላለማዊ ፍፃሜ ነው (ቢያንስ ቢያንስ በዚህ በምናውቀው ዓለም ውስጥ)። እንዲያም ሆኖ፤ ከጨለማ መንፈስ ለማምለጥ ዘዴ መፈለጋችን አይቀርም። ሟቹ፤ ሃዘናችንንና አክብሮታችንን በማየት እንደሚደሰት አድርገን እናስባለን - ከሞተ በኋላም ህያው እንደሚሆን እያስመሰልን።

“ያሰብከውን እናሳካለን፤ ራዕይህን እውን እናደርጋለን” በማለት ቃል እንገባለታለን። ነገር ግን፤ ቃላችንን መስማት አይችልም። ሲያስብ የነበረውን ብናሳካና ባናሳካ፤ ይዞት የነበረውን ራዕይ ብንፈፅምና ባንፈፅም ለኛ ለራሳችን ካልሆነ በቀር፤ ለሟቹ ትርጉም አይኖረውም። ሊያስደስተውም ሆነ ሊያሳዝነው አይችልም። በህይወት የለማ።

እናም፤ ሃሳብና እቅዳችን፤ ጥረትና ተግባራችን ሁሉ የታለመው፤ ሟቹን ለማስደሰት ከሆነ፤ በከንቱ ደከምን - ቅንጣት አናስደስተውም። ሃዘንና ድንጋጤያችንን፤ ክብርና አድናቆታችንን መግለፃችን ለሟቹ ይጠቅመዋል ብለን ካመንን፤ በከንቱ ባከንን - ቅንጣት አንጠቅመውም። “ዘላለማዊ ነህ፤ ህያው ነህ፤ መንፈስህ ከኛው ጋር ነው” የምንለው፤ ለሟቹ በማሰብ ከሆነ፤ በከንቱ ለፋን - ቅንጣት እድሜ አንጨምርለትም።

ሃዘኑም ሆነ አክብሮቱ፤ ድንጋጤውም ሆነ አድናቆቱ፤ ትርጉም የሚኖረው፤ በህይወት ላሉ ሰዎች ነው። መልካም ስራንና ሰሪዎችን ማክበር፤ ስኬትንና ስኬታማዎችን ማድነቅ፤ እነዚህ ጀግኖች በህልውና ሲገኙ መደሰትና በህልፈታቸው ሲታጡ ማዘን... ይሄው ነው ቁምነገሩ። መልካም ስራንና ስኬታማዎችን ማድነቅ ለራስ ነው - ለራስ የስብእና ጤንነት።

ሟቾቹማ፤ ከማንም ምንም አይፈልጉም። ለሟቾች፤ ምንም ቢሆን ምንም ትርጉም የለውም - በህልውና የሉምና። “ህያው ናችሁ፤ ዘላለማዊ ናችሁ” ብንል ለነሱ ዋጋ የለውም። እኛ ስለተናገርን ወይም ስላልተናገርን አይደለም። አለማወቃችን እንጂ፤ ጀግኖችና የስኬት ሰዎች ዘላለማዊ ህልውናን የሚያጣጥሙት፤ ከሞት በኋላ ሳይሆን፤ በህይወት ዘመናቸው ውስጥ ነው - በእያንዳንዷ መልካም ስራና ድንቅ ስኬት ውስጥ ነው ዘላለማዊ ህልውናን የሚያጣጥሙት።

ጀግኖች፤ በአስተዋይነት ያመነጩት ሃሳባቸው ትክክለኛ መሆኑን ሲያውቁ፤ ትክክለኛነቱ መቼም የማይሻር ዘላለማዊ እንደሆነ ያውቃሉ፤ በዚህም ዘላለማዊነትን ያጣጥማሉ። አርስቶትል የሎጂክ መርሆችን ሲቀምር፤ የሃሳቦቹ ትክክለኛነት ዘላለማዊ መሆናቸውን በማወቅ ነው። አንድ ነገር፤ በአንድ ጊዜ ድንጋይ መሆንና ድንጋይ አለመሆን አይችልም።

ኮፐርኒከስና ጋሊልዮ፤ መሬት በፀሃይ ዙሪያ ትሽከረከራለች ሲሉ፤ ሃሳባቸው ትክክለኛነት ዘላለማዊ እንደሆነ ያውቃሉ። ያኔ ነው፤ ዘላለማዊ ህልውናን የሚያጣጥሙት። በህይወት ዘመናቸው ስለሚያጣጥሙትም፤ ከሞት በኋላ አሻግረው ሌላ የህይወት ትርጉም ለማግኘት በከንቱ መድከም አያስፈልጋቸውም። በእውነታ ላይ የተመሰረተች እያንዳንዷ እውቀት፤ በመረጃ ላይ የተመሰረተች እያንዳንዷ ሃሳብ፤ የዘላለማዊ ህልውና መስኮት ነች። በጀግኖች አርአያነት መንፈሳችንን እያነቃቃን፤ እውነታ ታማኝ በመሆንና በቅንነት በማሰብ ነው፤ በህይወት ዘመናችን ዘላለማዊ ህልውናን የምናጣጥመው።

ጀግኖች፤ በችግርና በእንቅፋት ብዛት ሳይበገሩ፤ ለአላማቸውና ለሃሳባቸው በፅናት በመቆም በድንቅ ብቃት መልካም ተግባር ይፈፅማሉ። ብቃትና ተግባራቸውም፤ ድንቅና ጠቃሚ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ መቼም ለዘላለም እንደማይሻር ይገባቸዋል፤ እናም ዘላለማዊነትን ያጣጥማሉ። ተፈጥሮን መመርመርና ለእውቀት መትጋት፤ መማርና ማስተማር፤ ምርጥ የእህል ዘር መፍጠርና ወንዝ መገደብ፤ ማሽንና ቴሌፎን፣ ክትባትና መድሃኒት ለመስራት ሙከራና ጥናት ማካሄድ... እነዚህ ብቃትና ተግባሮቻቸው እጅግ ድንቅና ጠቃሚ መሆናቸው፤ መቼም ቢሆን እስከዘላለሙም አይሻርም። የኛ ማወቅና አለማወቅ፤ የኛ ማጨብጨብና አለማጨብጨብ አይደለም። ብናውቅና ብናጨበጭብ ጥሩ ነው። ግን፤ ባናውቅና ባናጨበጭብም እንኳ፤ የጀግኖቹ ተግባር ጠቃሚ ሆኑን ልንሽረው አንችልም። እውነት ነውና። ዘላለማዊ ነው። ይህንን የሚያውቁ ጀግኖች፤ በህይወት ዘመናቸው ውስጥ በእያንዳንዱ ድንቅ ብቃትና መልካም ተግባር ዘላለማዊ የህይወት ደስታን ያጣጥማሉ።

ጀግኖች፤ ስኬታቸውና ራዕያቸው፤ እውነተኛና ብሩህ መሆኑን ሲያውቁ፤ እውነተኛነቱና ብሩህነቱ በየትኛውም ጊዜ እንደማይሰረዝ እንደማይደለዝ ይገነዘቡታል፤ እናም በዚያው ልክ ዘላለማዊ ህልውናንን ያጣጥማሉ። ከሊዊ ፓስተር ፔኒሲሊን፤ ከአርኪሜደስ የፈሳሽ ነገሮች ህግ፤ ከአንስታይን የኢነርጂ ቀመር ጀምሮ፤ እያንዳንዷ የእውቀት ግኝት፤ የቴክኖሎጂ ፈጠራና የምርት ውጤት፤ በብሩህ ራዕይ የታጀበች እውነተኛ ስኬት መሆኗ... ለዘላለም እውነት ነው።  መሞት ይህንን አይሰርዘውም።

የህይወት ትርጉምም ይሄው ነው - እንዲህ መቼም ዘላለምም ሊሰረዝና ሊሻር በማይችል፤ ከአስተዋይነት በመነጨ ትክክለኛ ሃሳብ፤ በድንቅ ብቃትና በመልካም ተግባር፤ በድንቅ ስኬትና በብሩህ ራዕይ ህይወትን ማጣጣም ነው የህይወት ትርጉም። ጨለማውን መንፈስ አሽቀንጥረን መጣል የምንችለው፤ ከሞት በኋላና ከሞት ወዲያ ማዶ አሻግረን ለመቃኘት በመፍጨርጨር አይደለም። ዘላለማዊ ህልውናና የህይወት ትርጉም ያለው፤ እዚሁ በህይወት ዘመን በምናሳልፋቸው ደቂቃዎችና ሰዓታት፤ ቀናትና አመታት ውስጥ ነው።

ህይወትና ሞት የግል ነው። መጋራት አይቻልም። ሁሉም ሰው በየግሉ ይሞታል፤ በዚህ በዚህ ሁላችንም እንመሳሰላለን። ነገር ግን፤ ሁሉም ሰው ህይወትን አያጣጥምም። የምናደንቃቸው ጀግና ሰዎች፤ ዘላለማዊ የህይወት ደስታን አጣጥመዋል። አድናቆታችን ትርጉም የሚኖረው፤ እኛም እንደየአቅማችን ያንን የህይወት ጣእም ለማጣጣም ስንነቃቃ ነው።

 

 

 

 

Read 12213 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 11:51