Monday, 02 August 2021 20:44

ርዕስ አልባ ግጥም እና ሥዕል

Written by  ተፈሪ ዘ ካዛንቺስ
Rate this item
(6 votes)

“ርዕስ የሌለው ግጥም ያልተቋጨ ሥራ ነው”
                              
             ከሁለት ሣምንት በፊት በአንድ የቅርብ ወዳጄ ግብዣ በኤልያስ ሽታሁን የተደረሰ ርእስ የለውም የተሰኘ የግጥም ሥራ ምረቃ ሥነ- ሥርአት ላይ ለመታደም ወደ አንጋፋው ብሔራዊ ቴአትር አቀናሁ። ከላይ እንደገለፅኩት የግጥሙ ድርሰት ርእስ ርእስ፡- የለውም ነው፡፡ በእዚህ አግባብ መጽሐፉ ርእስ ያለው ሥራ ነው፡፡ በእዚህ ርእሱ አማካኝነት መጽሐፉ የራሱ የሆነ ሙሉ ህልውና ያለው ነገር መሆን ችሏል፡፡ መጽሐፉ ሙሉ ህልውናውን ይዞ በመገኘቱም ይህን ሥራ ከሌሎች የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ለይተን ማንበብ፣ መተንተን፣ ማወደስ፣ መተቸት…ወዘተ እንችላለን፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ ያጨቃቸው የግጥም ሥራዎች ርእስ አልባ ሥራዎች ናቸው፡፡ ማንኛውም የጥበብ ሥራ በምልአት ተሠርቶ ቀርቧል ተብሎ እውቅና ሊሰጠው የሚችለው ርእስ ሲኖረውና ርእሱን ተከትሎ የተወለደው የከያኒው የምናብ ፈጠራ በአግባቡ ተጠናቆ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አንድን ጥበባዊ ሥራ ሙሉ ሥራ ሆኖ እንዲገኝ የሚያደርገው  (ሙሉ ህልውና ይዞ እንዲፀና የሚያደርገው) ለጥበብ ሥራው ህልውና ዋልታ የሆነው ርእሱና ይኸው ርእስ የወለደው የከያኒው የምናብ የፈጠራ ሥራ ተሰናስሎ ሲገኝ ብቻ፡፡
በግልፅ እንደሚታወቀው በማንኛውም የጥበብ ሥራ ርእሱና ርእሱ በሚያትተው ጉዳይ መካከል ጥብቅ ቁርኝት አለ፡፡ ይህ ጥብቅ ቁርኝት የጥበብ ሥራው በሙሉነት እንዲገኝ መሠረት ይሆነዋል፡፡ በሌላ አገላለፅ፣ ማንኛውም ድርሰት (compostion) (ግጥምም ይሁን ሥዕል) የሚወለደው ከርእስ ነው፡፡ ይህ አካሄድ አንዳንዴ ቢሻር እንኳ የጥበብ ሥራው ርእስ ወጥቶለት ተቋጭቶ መቅረብ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ድርሰቱ ጎደሎ ሥራ ሆኖ ከመቅረት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ማንኛውም የጥበብ ሐሳብ የራሱ የሆነ የተዋቀረና የሠመረ ሂደትና ዐቢይ ግብ (purpose) አለው፡፡ የጥበብ ሥራ በወጉ የተዋቀረና የሠመረ ካልሆነ እብደት ወይም ቅዠት ነው የሚሰኘው፡፡ ዓለም ላይ በህልውና ያለ ነገር ሁሉ ቋሚ የሆነ ሕግን (fixed principle) ተከትሎ የፀና ነው። የዚህ ስርአት መኖር የነገሮች ውበትም ፅኑ መደላድል ነው፡፡ ሥነ-ግጥም በቤት ይመሰላል፡፡ አንድ ቤት ቤት ተብሎ እውቅና የሚያገኘው የቤትነት ቅርፅና ጥቅም (utility) አሰናስሎ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ የተሟላ የተባለ ቤት ሙሉ ህልውና (essence) ያለው ቤት ግድግዳውና ጣሪያው በትክክለኛ ልኬት ተሠርቶ የቀረበ ነው፡፡ አንድን ቤት ቤት የሚያደርጉት ንዑስ ግብአቶች ቢጎድሉ (ጣሪያው ወይም ግድግዳው) ቤቱ ሙሉ ሆኖ በህልውና አይቆምም፡፡ በሌላ አነጋገር ቤቱ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ባለመሆኑ ትክክለኛ ቤት ተብሎ እውቅና አይሰጠውም፡፡ ቤቱም ጅምር ቤት በመሆኑ የቤትነት ፋይዳ (end) የለውም፡፡ የድህረ-ዘመናዊነት (postmodernism) መስፋፋት ወደ ኪነ-ህንፃውም ተሻግሮ ያመጣው አብዮት የህንፃ ዲዛይን እንጂ የአሠራር መዋቅር አልነበረም፡፡ በሌላ አነጋገር የቤቶች ዲዛይን ቢለዋወጥም የቤቱ ካስማ ግድግዳውና የቤቱ መቋጫ ጣሪያው የቤቱ ህልውና ሆነው በቋሚነት የሚዘልቁ ነገሮች ናቸው፡፡ በሥነ-ግጥምም በርእስና በዐቢይ ድርሰቱ መካከል ያለው ቁርኝት ከቤት ህልውና ጋር ተመሳሳይ ነው። የአንድ ግጥም ርእስና ርእሱን ተከትሎ የሚመጣው የግጥሙ ዐቢይ ሐተታ መሰናሰል የግጥሙ ህልውና እና ውበት መሠረት ነው፡፡ አንድን የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ሥነ-ግጥም ተብሎ የሚፈረጀው የርእሱ እና የዐቢይ ሐተታው ጥብቅ ተዋህዶ በፈጠራ ሥራው ላይ ሲገለጥ ብቻ ነው፡፡ ግጥምን የመጻፍ ሂደት (process) የገጣሚውን ግላዊ ንሸጣ የማብራራት ወይም የማተት ሂደት (expostion)እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ይህን ሸጣ (immediate artistic provoke) በአንድ ዐቢይ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡  ይህ ንሸጣ ወደ ግጥም ህልውና የሚመጣው የተጻፈው ግላዊ ስሜት በአንድ ዐቢይ ርእስ ተቋጥሮ ሲቀርብ ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ከያኒ የጥበብ ሥራውን ርእስ ብቻ ደርሶ ቢመጣ፣ የሁሉም መሳለቂያ ከመሆን በዘለለ ለሠራው ሥራ እውቅና የሚሰጠው አንድም ሰው እንደማይኖር እሙን ነው፡፡ ግጥምንም ደርሶ ርእስ አለመሰየም ተመሳሳይ ነው። ከላይ እንደገለፅኩት ርእስ የማኝኛውም ፈጠራ ድርሰት ካስማ ነው፡፡
ተጠናቆ ያልቀረበን ጎደሎ ሥራ ማንበብም ከንቱ ተግባር በመሆኑ ስለ ኤልያስ ግጥም ሐሳብ ሂስ መጻፍ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ አንባቢም የቀረበለትን ግጥም ሐሳብ አንብቦ ከመገንዘብ በዘለለ ርእስ የመሰየም ግዴታም የለበትም፡፡ ይህን እንዲያደርግም የሥነ-ጽሑፍ ሂደት አይፈቅድም፡፡ ምክንያቱም የጸሐፊና የአንባቢ ሚና ለየቅል ነው፡፡
ለጥበብ ሥራ ርእስ ሳይሰይሙ ሥራን ማቅረብ፣ በሥነ-ጥበቡ ዘርፍ እየተለመደ የመጣ ግን የተሳሳተ ብሂል ነው። በአገራችንም ታላቁን ሠዓሊ ዘሪሁን የትምጌታን ጨምሮ ርእስ አልባ የሥዕል ሥራ ያላቸው ሠዓሊያን በርካታ ናቸው። በእርግጥ በሥነ-ጥበብና በሥነ-ግጥም መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡
ብዙ ደራሲያን የፈጠራ ሥራቸውን ሠርተው ካገባደዱ በኋላ የሠሩትን የጥበብ ሥራ ገላጭ ወይም ወካይ የሆነ ርእስ ለማበጀት እጅግ ሲጠበቡ ይስተዋላል። ለምንቢሉ፣ የሠሩት የድርሰት ሥራ ርእስ ካልወጣለት ያልተቋጨ ሥራ ሆኖ ስለሚቀር ነው፡፡
እንደ አጠቃላይ፣ ተሠርቶ ያላለቀ ፈጠራን ጠርዞ መሸጥም ሆነ በአደባባይ ማስመረቅ ከንቱ ተግባር ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ መንገድ የጥበብ ፈጠራ ሥራን ምንነትና አላማ በጥልቀት ያለ መገንዘብ ውጤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም፣ እንዲህ አይነቱም ልማድ ፍፁም የተሳሳተ ስለሆነ መታረም ይገባዋል፡፡

Read 1096 times