Wednesday, 04 August 2021 00:00

አቤቱታ ከአታሚው - ለአንባቢው

Written by  ቤንጃሚን ፍራንክሊን
Rate this item
(0 votes)

           አድማስ ትውስታ



         ቤንጃሚን ፍራንክሊን ያልሆነው ነገር የለም። ታዋቂው የአሜሪካ የልብወለድ ፀሐፊ ኸርማን ሜልቪሌ፤ “ሁሉንም ነገር-ከግጥም በስተቀር (Nothing but poetry)” ብሎለታል- የችሎታውን ስፋት ሲገልጽ። ወደ ኋላ የመጡ የፕሬስ ሰዎች “ቤንጃሚን ፍራንክሊን የፕሬስ ነጻነትን በምልአት የሚቀበል ሰው አልነበረም” ይሉታል። ሌሎች ደግሞ ለፕሬስ ነፃነት ቀዳሚ ተጠቃሽ ያደርጉታል።
ነቃፊዎቹ “ቤንጃሚን በጋዜጣው ላይ የተለያዩ (ተቃራኒ) አመለካከቶችን ያስተናግዳል፤ ግን የፕሬስ ነጻነትን የሀሳብ መሰረት ለማስያዝ ምሁራዊ አስተዋፅኦ አልነበረውም” ይላሉ። “በሁሉም ነገሮች የሰለጠነ ነው፣ ግን በርሱ ላይ  ምንም ነገር አልሰለጠንበትም” ይባልለታል። ይዞ ያስቀረው ሙያ  የለም  ለማለት ነው። ዘርፈ ብዙ ጠቢብ መሆኑን ለመግለፅ ነው። ከዚህ በታች የፕሬስ ሥራ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና የአንባቢያንን የግምት አስተያየትና ነቀፌታ አስመልክቶ የፃፈው ጽሁፍ ቀርቧል። አስተማሪነት ያለው ይመስለናል።
ሊታተም አይገባም ብለው የሚያስቡትን በማሳተሜ የተለያዩ ሰዎች በተደጋጋሚ ሲያነውሩኝና ሲያወግዙኝ አያለሁ። ስለዚህ የሆነ በዓመት አንድ ጊዜ የሚታተም፤ እንደ አስፈላጊነቱም ሊነበብ የሚችል ቋሚ አቤቱታ (ስሞታ) መፃፍ አስፈላጊ ሆኖ ይታሰበኛል፤ አልፎ-አልፎ።
እስካሁን አቅቦ የያዘኝ የሥራ ብዛት እንጂ ይህን ለማድረግ ካሰብኩ ቆየሁ። ነገር ግን  በቅርቡ፤ ከግርጌው `NB` (ማስታወሻ) የሚል ቃል የያዘ፣ አንድ ማስታወቂያ በማውጣቴ ኃይለኛ ቁጣ ስለተቀሰቀሰብኝ፤ በተለይ  እዚህ ደቂቃ ላይ ስሞታዬን ማሰማቱ ተገቢ ይመስለኛል።
እርግጥ፤ አሁን እንዲህ ያለን ነገር በወጉ ለመጻፍ የሚያስችል ፋታ ስለሌለኝ ልገልፀው የምፈልገውን ነገር እንደነገሩ አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
(በዚህ አጋጣሚ)፣ እንዲታተም የማይፈልጉትን ነገር በማሳተሜ የተነሳ የተቆጡብኝ ሰዎች የሚከተሉትን ነጥቦች በጥሞና እንዲያጤኑልኝ እጠይቃለሁ።
1. የሰዎች አስተያየት (አመለካከት) የመልካቸውን ያህል የተለያየ ነው። በጥቅሉ፣ ያለኝ አመለካከት እንደ ምሳሌያዊ አነጋገር አጠቃልሎ የሚይዘው፣ “So many men, so many minds.” የሚለው ነው።
2. የህትመት (የጋዜጣ) ስራ በእጅጉ ከሰዎች አመለካከት ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛዎቹ ለህትመት የሚበቁ ሥራዎች የአንዱን ወገን ሃሳብ የመደገፍ፣ የሌላውን ሀሳብ የመቃወም አዝማሚያ አላቸው።
3. የስራው አስቸጋሪነት (አስከፊነት) የሚጀምረው ከዚሁ ነው። በሌሎች የሥራ መስኮች የማያጋጥም ችግር በዚህ አለ። የህትመት ስራ በሌላ መንገድ እንጀራ ለማግኘት ሲያቅተን የምንገባበት መሆን አለበት። ስራችን ጥቂት ሰዎችን ምናልባት የማያስከፋ ሆኖ ቢገኝ እንኳን ብዙዎችን ያስቀይማል። በአንፃሩ እንደ ወርቅ ሰሪ፣ ጫማ ሰፊ፣ አናጢ ወይም በማናቸውም ሌላ የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሰዎች አመለካከት ምንም-ሆነ-ምን አንዳችም ተፅዕኖ ሳያመጣብን ሁሉንም ሰዎች ልናገለግል እንችላለን። የትኛውንም ሰው ሳያስቀይሙ መሥራት ይቻላል። ከነጋዴው፤ ከአይሁዱ፤ ከቱርኩ፣ ሀሳቡ ከማንም ከማይገጥመው ሰው ጋር፣ ከመናፍቁም (Heretic) እየተገበያየ ከሁሉም ትርፍ ሊያገኝ ይላል። በማንኛውም ነገር እጅግ ወግ አጥባቂ የሆነውንም ሰው የሚያስቀይሙበት ሁኔታ የለም። ከማናቸውም ሰው ማንነት ጋር ተያይዞ በሚመጣ ነገር የመወገዝና በክፉ አይን የመታየት ችግር አይገጥማቸውም።
4. በማናቸውም በሚታተም ነገር ለመደሰት የሚፈልግ ሰው (ቡድን) በጣም የተሳሳተ ነው። ይህ ማለት፣ እኔ (እኛ) ብቻ እንጂ ሌላ ሰው ሊደሰት አይገባም ብሎ ማሰብ ነው።
5. አሳታሚዎች፣ ሰዎች በእምነት የተለያዩ ሆነው ሲገኙ በየወገኑ ያሉት ሰዎች ድምፃቸውን ለህዝቡ እንዲያሰሙ እኩል ዕድል የመስጠት እምነት ያዳበሩ ናቸው። በማንኛውም ጊዜ፣ እውነትና ውሸት የሚጋጠሙበት ስፍራ ከተሰጣቸው፣ መቼም ቢሆን እውነት ማየሉ አይቀርም። ስለዚህ በወጉ ተፋላሚ ሆነው የሚመጡ ፀሐፊዎችን “እኔ ከየትኛው ወገን ጋር ነው የምወግነው?” የሚል ነገር ሳያነሱ ሁለቱንም በደስታ ያስተናግዳሉ።
6. እናም፣ አሳታሚዎች ያለማቋረጥ የሁለት ወገን ሃሳቦችን በማስተናገድ ስራ ተጠምደው ስለሚቆዩ፣ በሚያትሙት ነገር ውስጥ ትክክለኛው አመለካከት ያለው ከየትኛው ወገን እንደሆነ የመለየቱን ነገር ከቀን-ወደ ቀን ቸል የማለት ዓመል እያዳበሩ ይመጣሉ። ትክክልና ስህተት  ለሚል ነገር መጨነቁን እርግፍ አድርገው ይተውትና ስራቸው የመጣውን ነገር ማተም ብቻ ይሆናል። በዘለፋና ቁጣ ታጭቀው የሚመጡ ፅሁፎችን በአስገራሚ ዕርጋታና ከስሜታዊነት ውጪ ሆነው ያትማሉ። በእነዚህ ፅሑፎች ለተጠቀሰው ሰው አንዳችም መጥፎ አመለካከት አይኖራቸውም። ስማቸው የተነሳው ሰዎች ግን አሳታሚውን ከፀሐፊው እኩል በጠላትነት ያዩታል፤ ያስቡታል።
7. እንዲሁም፣ አሳታሚዎች የሚያትሙትን ነገር ሁሉ የሚቀበሉትና የሚደግፉት መስሎ የሚታያቸው ሰዎች ተሳስተዋል። ታትመው የሚወጡትን በዚህ አንፃር እያዩ ውግዘት የሚያወርዱ ተሳስተዋል። ምክንያቱም፣ ከሥራቸው ጠባይ የተነሳ፣ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑና የሚጣሉ እጅግ በርካታ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ያትማሉ።
በተመሳሳይ መንገድ “አሳታሚዎች ተገቢ የመሰላቸውን ነገር እንጂ ማንኛውንም ነገር ማተም የለባቸውም” የሚሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ይህም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። አሳታሚዎች እንደዚህ አይነት ውሳኔ ላይ ከደረሱና በዚህ ውሳኔያቸው ከተገዙ ሀሳብን በፅሑፍ የመግለፅ ነፃነት አበቃለት ማለት ነው። ያን ጊዜ ዓለም፣ አሳታሚዎች ከተቀበሉት አመለካከት በቀር ሌላ ሊያነበው የሚችለው አንዳችም ነገር አይኖርም።
8. አሳታሚዎች፤ ያገኙትን ኢንፎርሜሽን (ተባለ ከማለት ተጠብቀው) በአስተማማኝ ካላረጋገጡ በቀር ላለማተም ቢወስኑ ሰውን የሚያስከፋ ነገር አይፈጠርም ይሆናል። ግን በዚያ ሁኔታ ማተም የሚቻለው ነገር በጣም ትንሽ ነው።
9. ለንባብ ሊበቁ የማይችሉ ተራ ሸፍጠኛ፣ መርዘኛ ነገሮች አንዳንድ ጊዜ ታትመው ብታዩ፤ አሳታሚዎች ራሳቸው እንደዚህ ዓይነት ነገሮች መውጣታቸውን ስለሚደግፉ አይምሰላችሁ። ህዝቡ ደህና ጣዕም አጥቷል። ጥሩ ነገሮችን የሚያበረታታ ሰው የለም። እኛም በዚህ መንገድ ለመሄድ ተገደናል።
10. የሰውን ልጅ ደህንነት አስመልክቶ ሊነሱ የሚችሉት ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አንድ ሰው በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ገንዘብ ሊያስገኙለት የሚችሉትን ማናቸውንም ነገሮች እንዲሰራ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ አሳታሚዎች ብዙ ብልሹ ነገሮች እንዳይታተሙ ሳያሰልሱ ይጣጣራሉ። ጎጂ ውጤት ያላቸው ነገሮች በእንጭጩ እንዲቀሩ ያደርጋሉ። እኔ ራሴ፣ ነውረኛ ጉዳዮችን (Vice) የሚያደፋፍሩና የስነ-ምግባር ውድቀትን የሚያስከትሉ ነገሮች እንዳይታተሙ ለማድረግ ሁልጊዜም እጣጣራለሁ።
ይሁንና፣ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ከያዘው የተበላሸ የስነ-ምግባር ጣዕም ጋር ተጎዳኝቼ ለመሄድ መሞከሬ ብዙ ገንዘብ እንዳገኝ ረድቶኛል።
ነገር ግን ሁልጊዜም በየትኛውም ሰው ላይ ተጨባጭ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች እንዳይታተሙ አደርጋለሁ። የቱንም ያህል የሚያስጎመዥ ጥቅም ቢታየኝ፤ ማባበያ የሚሆን ከፍ ያለ የገንዘብ ስጦታ ቢቀርብልኝ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በማግለሌ ሥራ ሊፈጥሩልኝ የሚችሉት ሰዎች ሁሉ በክፉ አይን ይዩኝ እንጂ አላደርገውም። የአንድን ቡድን ወይም ግለሰብ አቋም ለማተም ባለመፍቀዴ በብዙ ሰዎች ዘንድ ጥላቻን አትርፌአለሁ። በብዙ አካሄዴ በራሴ ላይ ብዙ ጠላት አፍርቼአለሁ። ይሁንና፣ እነዚህን የመሰሉ ነገሮች የማያየው ህዝብ //አንባቢ/፤ አሳታሚው ካለማወቅ ወይም በበርካታ ውትወታ በብዙዎች ዘንድ ተነቃፊ የሆነን ነገር ያሳተመ እንደሆነ፣ ለምስኪኑ አሳታሚ አዘኔታ የሚኖረው አይገኝም።
አሁን ከላይ ወደ ጠቀስኩት የ`N.B` ጉዳይ ልመልሳችሁ። በማናቸውም ጉዳይ እንዲህ ያለ ሰፊ ቁጣ ተቀስቅሶብኝ አያውቅም። በሌሎች ሥራዎች ላይ እየተጣደፍኩ ሳለ የሆኑ ሰዎች አንድ ማስታወቂያ እንዳወጣላቸው ይዘው ይመጣሉ።
በዚህ ማስታወቂያ ውስጥ “በእንዲህ ያለ ወደብ… እንዲህ ያለ መርከብ ይገኛል፤ በእንዲህ ያለ ሰዓት ወደ ባርባራዶስ ይሄዳል፤ ዕቃ አስተላላፊዎች ወይም ተጓዦች የሆናችሁ ከእንዲህ ያለ ቦታ ከካፒቴኑ ጋር መነጋገርና መዋዋል ትችላላችሁ” ይላል። እዚህ ድረስ ያለው ነገር የተለመደ ነው። ነገር ግን በስተግርጌው አንድ ያልተለመደ እንግዳ ነገር ተጨምሯል። “N.B (ማስታወሻ)፣ የባህር ዶሮዎች እንዲሁም ባለ ጥቁር ካባዎች በምንም ዐይነት ሁኔታ ተቀባይነት አያገኙም”
(`N.B No SEA HENS NOR BLACK GOWNS WILL BE ADMITTED ON ANY TERMS) ይላል። አተምኩት። ገንዘቤን ተቀበልኩ። ማስታወቂያውም እንደ ተለመደው የመነጋገሪያ ነጥብ ሆነ። ያን ጊዜ ብዙ አትኩሬ “የዚህ ቃል ትርጉም ምንድነው?” ብዬ አልጠየቅሁም። እንደዚህ ሊያስቆጣ የሚችል መሆኑንም ማሰብ አልቻኩም። ሰዎች ጉዳዩን ባለማወቅ፤ “እንግዲህ እንደዚህ የሚያስብ ሰው ነው!” እያሉ በየሄዱበት ያወራሉ። ብዙ ጥሩ ሰዎች በዚህ አጋጣሚ ተቆጥተውብኛል። እነሱ አሳታሚ ቢሆኑ እንዲህ ያለ ነገር  ሊሰሩ አይችሉም ይሆናል። የዚህች ቁጣ መነሻ ግን ሌላ ነች። ለሃይማኖትና ለካህናት ያለኝን ጥላቻ በመንተራስ የመጣ ጉዳይ አድርገውታል። ከዚህ በኋላ የኔን ጋዜጣ በእጃቸው ላይነኳት ምለዋል።
በምንም ነገር፣ ከኔ ጋር ለመሥራት እንደማይዳዳቸው እየተናገሩ ነው። ከኔ ጋር ያላቸውን ደንበኝነት ለመግታት እንዳሰቡ ይናገራሉ። ይኸ ሁሉ እጅግ አስቸጋሪ ነው።
ይኸን የተባለውን ማስታወቂያ አላትምም ብዬ ብመልሰው ኖሮ የተሻለ እንደነበር ይሰማኛል። ይሁንና፣ አንድ ጊዜ ሆኗል። የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ! ከእንግዲህ ሊመለስ አይችልም። አሁን ሊደረግ የሚችለው ከዚህ በታች ያሉትን ነጥቦች መናገር ብቻ ነው። አንዳንዶቹ፣ የተፈጠረውን ቁጣ ለማቀዝቀዝ  እንዲያግዙ ስለ ራሴ በመጨነቅ ያቀረብኳቸው ናቸው። ሌሎቹ ግን ከዚህ የተለዩና ስለ አጠቃላዩ ሁኔታ ለመናገር የቀረቡ ናቸው። ነገር ግን፣ የትኞቹንም ቢሆን አንባቢው ጥሩ የመጫወት/የመቀለድ ስልት ይዞ (Sense of humour) ቢያነባቸው እወድዳለሁ።”
(ቤንጃሚን ፍራንክሊን ይቀጥላል። እንግዲህ የኛም ቦታ ከዚህ በላይ አያስኬደንም። ጋዜጣ አይደል?! ከተቻለ እንመለስበታለን።)
(ምንጭ፡- አዲስ አድማስ በመጋቢት 23 ቀን 1992 ዓ.ም ዕትሙ ካወጣውለትውስታ በድጋሚ ተመርጦ የቀረበ)


Read 6713 times