Tuesday, 03 August 2021 17:25

"ፊትህን ወደ ሀገርህ ሥነጽሁፍ አዙር"

Written by  መክብብ ፍቃዱ
Rate this item
(0 votes)


               እና...
እባክህ መንግስት ሆይ! አንዳንዴ ከአይሁድ መጽሐፍ (ቅዱስ) ፊትህን አዙርና የሀገርህን ስነ-ጽሑፍ አንብብ። ሃዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብራቸው፣ በፊት አውራሪ መሸሻ የግብር እልፍኝ የተገኘው በዛብህ ቦጋለ፣ በ”ማህሌተ ገንቦው”፣ እመቤቲቱንና ጌቶችን ሲያወድስ፣ ፊታውራሪ መሸሻ ግምጃ ቤታቸውን ጠርተው “ንሳ ንሳ ይሄንን ድማም ተማሪ  ሙሉ ልብስ ሸልመህ አምጣልኝ።” እስከ ማለት ያደረሳቸውን ትዕዛዝ ያሰጣቸውን ውዳሴ ያገኙት መጠጥ ከጠጣ የቅኔ ተማሪ ነበር። (ፍቅር እስከ መቃብር ገጽ 81-82)
የአዳም ረታችን “ግራጫ ቃጭሎች” ያ እምቦሳው መዝገቡ፣ የእእን ቁጣ ግልምጫና አቃጣሪነት፣ የአባቱን የዱቤን እርግጫና ኩርኩም ከቁብ እንዳይቆጥር ያደረገውና ያስረሳው ጉዳይ፣ የማንቆርቆራ ጠጅ መሆኑን አለማንበብህም ጎድቶሃል። (ግራጫ ቃጭሎች ገጽ 41-43)
አለማየሁ ገላጋያችንም “ቅበላ” በተሰኘ መጽሐፉ፤ “ሕይወት አሰልቺና አታካች መሆኑ የሚታወቀው መጠጥ በጠጡ ሰዓት ነው።” ይለናልም። (ገጹ ጠፍቶኛል)
በእውቄያችንም “አዳምኤል” በተሰኘች መድበሉ ማህሌተ ገንቦ የተሰኘች ግጥም አለችው። ጽዋችንን ከፍ አድርገን ቸር የዋሉልንን ስለማወደስ የምታወሳ ግጥም ናት። እንዲህ ትሰኛለች።
ማህሌተ ገንቦ
ባጭር ቀረን ስንል - እድሜ ላበደሩን
ቀርፀው ላሳመሩን
ለኩሰው ላበሩን
ቺርስ!!
ፊታችንን ዐይተው
እንደተቸገርን - ካይናችን ላወቁ
ስለማርያም ብለን
እስክንለምናቸው - ቆመው ላልጠበቁ
ቺርስ!!!
ወድቀው ለማይጥሉ -ነግሰው ለሚያነግሱ
ነውራችንን ዐይተው
ልክ እንደ ድመት ኩስ ፣ ለሚያለባብሱ
ብድር አበድረው ፈጥነው ለሚረሱ
ቺርስ!!!!
ላባ ላረጉልን ፣ የመከራ ሸክሙን
ቀልደው ላሳቁን ፣ ተጫውተው ላከሙን
በቸከ ዘመን ላይ-
ስጋ ለበስ ትንግርት -ሆነው ላስደመሙን
ቺርስ!!!!!
(አዳምኤል ገጽ 21)
መጠጣት የምንፈልግበትን ብዙ ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። እነዚህ የሥነ-ጽሑፍ ፊታውራሪዎቻችንን ካነበብክ ግን በበቂ ይነግሩሃልና አንብብና እኛን ፍታን። እንጠጣበት።


Read 1862 times