Saturday, 07 August 2021 13:50

በ32ኛው ኦሎምፒያድ የመገባደጃ ቀናት የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ይደምቃሉ

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በጃፓን እየተካሄደ በሚገኘው 32ኛው ኦሎምፒያድ  ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያዶች ለሜዳሊያ ድሎች የሚጠበቁባቸው የረዥም ርቀት ሩጫዎች ከትናት ሌሊት ጀምሮ እየተካሄዱ ናቸው፡፡ በሴቶች በሚካሄደው የኦልምፒክ ማራቶን ትዕግስት ግርማ፣ብርሃኔ ዲባባና ሮዛ ደረጄ ሲሳተፉ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በሴቶች ከ10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ወድድር ለተሰንበተ ግደይ ፣ጽጌ ገብረሰላማ እና ፀሀይ ገመቹ ይወዳደራሉ፡፡ እንዲሁም በወንዶች የኦሎምፒክ ማራቶን ሹራቂጣታ፣ሌሊሳ ዴሲሳ እና ሲሳይ ለማ ተሳታፊ ናቸው፡፡ በአራት የኦሎምፒክ ስፖረቶች በአተሌቲክስ፤ በርምጃ ውድድር፤ በውሀ ዋናና በብስክሌት 38 ኦሎምፒያኖችን ያሰለፈችው ኢትዮጵያ እስከ ትናንት ድረስ አንድ ወርቅ፤አንድ ብርና፤አንድ የነሀስ ሜዳሊያዎችን በማስመሰገብ 3ኛ ደረጃን ይዛ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በ5ሺ ሜትር ወንዶች
ትናንት በወንዶች 5ሺ ሜትር የፍፃሜው ውድድር ተካሂዶ የነበረ ሲሆን 18 የዓለማችን ምርጥ ኦሎምፒያኖች በተሳተፉበት ከባድ ውድድር ኢትዮጵያዊው ኦሎምፒያን ሚልኬሳ መንገሻ ለፍፃሜው የሜዳሊያ ድልለ ማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ  አልተሳካለም፡፡
በ5ሺ ሜትር ወንዶች ኢትዮጵያ   ባለፉት 13 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ  3 የወርቅ፤ 2 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ የመጀመርያውን የሜዳልያ ክብር በወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበው በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡ ከዚያም በ1992 እኤአ ባርሴሎና ኦሎምፒክ ፊጣ  ባይሳ የነሐስ፤ በ2000 እኤአ በሲድኒ ኦሎምፒክ ሚሊዮን ወልዴ የወርቅ፤ በ2004 እኤአ በአቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የብር፤ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ደጀን ገብረመስቀል የብር ሜዳልያዎችን አግኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ10ሺ ሜትር ሴቶች
በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ሁለት የዓለም ሪከርዶችን ያስመዘገበችው  የ22 ዓመቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ10ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር የኢትዮጵያ ክብር ለማስጠበቅ የምትሰለፍ ይሆናል፡፡
በ10ሺ ሜትር ሴቶች የኦሎምፒክ ውድድር  ከ1988 እኤአ በሲኦል ኦሎምፒክ ተጀምሯል፡፡  ኢትዮጵያ   ባለፉት 7 ኦሎምፒያዶች በነበራት ተሳትፎ  4 የወርቅና 2 የብር  2 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ የመጀመርያን የሜዳልያ ክብር በወርቅ ሜዳልያ ያሳካችው በ1992 እኤአ  በባርሴሎና ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ ነበረች፡፡በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2000 እኤአ  በሲድኒ ኦሎምፒክ ኦሎምፒክ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ እና ጌጤ ዋሚ የብር ፤ በ2004 እኤአ  በአቴንስ ኦሎምፒክ እጅጋየሁ ዲባባ የብር እና ደራርቱ ቱሉ የነሐስ፤ በ2008 እኤአ  በቤጂንግ ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ  እንዲሁም በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡  
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ማራቶን
በቶኪዮ ኦሊምፒክ  በሁለቱም ፆታዎች የሚካሄዱት የማራቶን ውድድሮች የሽልማት ስነስርዓት ከመዝጊያው ስነስርዓት ጋር ተያይዞ መካሄዱ የኢትዮጵያ ማራቶን ቡድን የሚያስመዘግበውን ውጤት አጓጊ ያደርገዋል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለኢትዮጵያ የሚሰለፉትን የማራቶን ኦሎምፒያኖች ለስምንት ወራት በጥሩ ዝግጅት ሲያሰሩ የቆዩት ዋና አሰልጣኞች ሃጂ አደሎና ገመዱ ደደፎ  ምርጥ ውጤት እንደሚገኝ ተስፋ አድርገዋል፡፡
ባለፉት 31 ኦሎምፒያዶች ላይ ኢትዮጵያ 6 የወርቅ ሜዳልያዎችን በማስመዝገብ ብቸኛዋ አገር ስትሆን 4 የወርቅ ሜዳልያዎች በወንዶች በ1960 እና በ1964 አበበ ቢቂላ፤ በ1968 እኤአ ማሞ ወልዴ እንዲሁም በ2000 እኤአ ገዛሐኝ አበራ እንዲሁም ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በሴቶች በ1996 እኤአ ላይ በፋጡማ ሮባ እና በ2012 እኤአ ላይ ቲኪ ገላና በማሸነፋቸው ነው፡፡
ከ32ኛው የቶኪዮ ኦሎምፒያድ በፊት ኢትዮጵያ ባለፉት 31 ኦሎምፒያዶች በወንዶች ከፍተኛውን ውጤት 4 የወርቅ፤ 1 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች እንዲሁም በሴ ቶች ከጃፓን ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ 2 የወርቅ እና 1 የነሐስ በድምሩ 12 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡


Read 11563 times