Saturday, 07 August 2021 13:55

በሃገሪቱ ሁሉን አሳታፊ እርቀ ሰላም እንዲጀመር ህብር ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በትግራይ ጦርነት ቆሞ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱና በሃሪቱ ሁሉን አሳታፊ እርቀ ሰላም የመፍጠር ሂደቱ በአፋጣኝ እንዲጀመር ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር) ጥሪ አቀረበ።
ፓርቲው ሁሉም ወደ ውይይት መምጣት ተሸናፊነት ሳይሆን ሃገርን ከመበታተን ለማዳን የሚወስዱት ታላቅ የጋራ አሸናፊነት መንገድ ነው ብሏል የእርቀ ሰላምና ውይይት ጥሪ ባቀረበበት መግለጫው።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ለተጋረጡባት ውስብስብና ዘርፈ ብዙ አገራዊ ምስቅልቅሎሽ የገዢው ሃይልም ሆነ የግፋ በለው አጃቢ ሃይሎች በሚያደርጓቸው የጦር አውርድ እንቅስቃሴዎች መከራን ከማባባስ ባሻገር የሰላም መፍትሄ ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ በፍፁም አይታመንም ያለው የፓርቲው መግለጫ ጦርነቱ ዜጎችን ከማስጨረስ ባለፈ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ ለገጠማት ውስብስብ ተደራራቢና ተመጋጋቢ ችግሮች ዘላቂና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ ለማስገኘት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሁሉን አቀፉ አገራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ይካሄድ ዘንድምፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።
መንግስትም ሆነ ሌሎች ተቀናቃኝ ሃይሎች ሁሉ በዚህ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቀው ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ ሁሉም ጥሪውን ቢቀበሉና ለውይይት ቢቀመጡ ተሸናፊነት ሳይሆን ሃገርን ከመበታተን ለማዳን የሚወስዱት ታላቅ የጋራ አሸናፊ ነት መንገድ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል።

Read 11428 times