Saturday, 07 August 2021 13:57

ዓላማውን ያላሳካው የሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ ጉዞ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(9 votes)

   በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፎች ገደብ ሳይደረግባቸው ለተረጂዎች በሚደርሱበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ለመወያየትና ጫና ለማሳደር አቅደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር፤ ዓላማቸውን ሳያሳኩ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተጠቆመ።
በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት አድርገው የተመለሱት ሳማንታ፤ በጉብኝታቸው ማጠናቀቂያ ላይ በሰጡት መግለጫ፤  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ለመነጋገር አቅደው የመጡ ቢሆንም ዕቅዳቸው አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ሳማንታ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ጠቅላይ ሚ/ኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ማግኘት እንዳማይችሉ ተገልፆላቸዋል ተብሏል።
ከኢትዮጵያ በፊት በሱዳን ጉብኝት ያደረጉት ዳይሬክተሯ፤ ከትግራይ ክልል ጦርነት ሸሽተው በስደት ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን ማነጋገራቸው ተጠቁሟል፡፡
በሱዳንና በኢትዮጵያ ስላካሄዱት ጉብኝት መግለጫ የሰጡት ሳማንታ ፓወር፤ ሱዳንን “በቋፍ ላይ ያለ የዲሞክራሲ መንገድ ላይ ያለች አገር” ሲሉ የገለጿት ሲሆን ኢትዮጵያን “በግጭት ማጥ ውስጥ ያለችና የረሃብ አደጋ የተደቀነባት አገር” በማለት ገልፀዋታል፡፡
የኤርትራ መንግስት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ያሰፈረውን የጦር ሰራዊቱን በአስቸኳይ እንዲያስወጣ አጥብቀው ያሳሰቡት ዳይሬክተሯ፤ ላለፉት ወራት የኢትዮጵያን መሬት በሃይል ወርራ ስለያዘችው ሱዳን ምንም ነገር አለማለታቸው ጥያቄ አስነስቶባቸዋል።
በወልዲያ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ መምህር የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ ታመነ በሰጡት አስተያየት፤ ሴትየዋ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እንደ አንድ የእርዳታ ድርጅት ኃላፊ፣ በእርዳታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ሳይሆን ቀጥተኛ ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር እንዲሁም የኢትዮጵያን መንግስት እጅ ለመጠምዘዝና ለአሜሪካ ፍላጎትና ጫና ተገዥ ለማድረግ ነው” ብለዋል።
በተደጋጋሚ “በትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል የምትወቅሰው አሜሪካ፤ በማይካድራ እንደ በግ የታረዱትን ዜጎች ግን ከቁብ አልቆጠረቻቸውም፤ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ ነው” ሲሉ ተችተዋል-መምህሩ፡፡
ሳማንታ ፓወር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ባለማግኘታቸውና ባለማነጋገራቸው ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማቸው የጠቆሙት የፖለቲካ ምሁሩ፤ “አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሟል ያለችው የሰብአዊ መብት ጥሰትና የረሃብ አደጋ አሳስቧትና ለዚያም መፍትሔ ለመስጠት አይደለም፤  ሴትየዋን የላከችው። ይልቁንም ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ውስጥ የቀበሩት የዘር ፖለቲካ እየተጠላ መምጣቱና ያሉትን ሁሉ እየተቀበለ የሚያስፈጽም ተላላኪ መንግስት መጥፋቱ አሳስቧቸው ነው ብለዋል፡፡
“በእርዳታ ስም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሊሚያሴሩ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ጥሩ ምላሽ ነው፡፡ ለነገሩ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሴትየዋን ያላነጋገሯቸው እንደተባለው በሌሎች ስራዎች ተጠምደው ወይንም ሴትየዋ በስልጣን ደረጃ ስለማይመጥናቸው አይደለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት ከሳቸው ያነሰ ስልጣን ያላቸውን በርካታ እንግዶችን አነጋግረው ያውቃሉ፡፡ ይህ መልዕክት  ግን ምዕራባውያን  ይልቁንም አሜሪካ በኢትዮጵያ  ላይ እያራመደችው ያለው አቋም ያልተመቻት መሆኑን ለማሳወቅና  የኢትዮጵያውያንን ስነልቦና ለማስገንዘብ ነው” ሲሉ ስሞታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምሁሩ አክለውም፤ “ኢትዮጵያውያን በቀኝ ያልተገዙ ኩሩ ማንንት ያላቸው ዜጎች ናቸው፤ በቅኝ ያልተገዛ ሰው ደግሞ እኛ ያልነውን ብቻ አድርግ ቢሉት አይሰማም፡፡ እንዲያ ቢሆንማ ኖሮ አድዋ የሚባለው ታሪክ የኢትዮጵያውያን ታሪክ አይሆንም ነበር፡፡ እናም የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ይኸው ይመስለኛል” ብለዋል፡፡
በአገሪቱ ታላላቅ የመገናኛ ብዙሀን እምብዛም ትኩረት የተነፈገው የሳማንታ ጉብኝት የኢትዮጵያ መንግስት በሱዳን በኩል ያለውን ኮሪደር እንዲከፍትና ሰብአዊ እርዳታዎች ያለምንም ገደብ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ለማድረግ ያለመ ነው ቢባልም፤ የሴትየዋ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከዚህም የዘለለ ዓላማ እንደነበረው  የፖለቲካ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ የሱዳንን ኮሪደር ለማስከፈት ጥረት እየተደረገ ያለው ለህወኃት ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ እንደልብ ለማስገባት ታቅዶ ነው ይላሉ-ምሁሩ፡፡ ዓላማው ሰብአዊ እርዳታዎችን ወደ ትግራይ ለማስገባት ብቻ ከሆነ ከሱዳኑ ኮሪደር የበለጠ ለክልሉ የቀረቡና አስተማማኝ የሆኑ ሌሎች ኮሪደሮች አሉ፡፡ ከፖርት ሱዳን መቀሌ ድረስ ርቀቱ 1.306 ኪ.ሎ ሜትር ነው በተሸከርካሪ በአማካይ ከ17 ሰዓታት በላይ ይወስዳል፡፡ ከጅቡቲ መቀሌ ደግሞ 779.1 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን በተሸከርካሪ በአማካይ 12 ሰዓት ይወስዳል፡፡ ከምጽዋ መቀሌ 398 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው፡፡ ይህም በአማካይ 5 ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜን ይወስዳል እንግዲህ ዓላማው እርዳታን ለተረጂዎች በአፋጣኝ ማድረስ ብቻ ከሆነ፣ የትኛው ኮሪደር ለትግራይ የበለጠ ቅርብ ነው? አሜሪካስ ረዥሙን ኮሪደር ለምን መረጠች? በእኔ በኩል ጉዳዩ ከሰብአዊ እርዳታ ያለፈ ነገር ነው፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ካለችው  ከሱዳን ጋር በመሆን የጦር መሳሪያን ለማስገባትና ታጣቂ ቡድኑን ለመደገፍ ነው ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ አብራርተው ይናገራሉ፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በተደጋጋሚ መታየታቸው የሚነገረው ሳማንታ፤ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የአገራቸው ፍላጎት ከኢትዮጵያውያንና ከመንግስታቸው ጋር በመሆን አሁን በአገሪቱ ግጭት ላስከተለው ሰብአዊ ቀውስ እልባት መስጠት እንደሆነ ጠቁመው፤ ስለዚሁ ጉዳይ ከጠቅላይ  ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ለመነጋገር ዕቅድ ይዘው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው መቅረቱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሳማንታ ፓወር ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝተው ለማናገር እንደማይችሉ ተነግሯቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡


Read 12293 times