Saturday, 07 August 2021 14:04

የጎንድር ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ምረቃ አዳዲስ ክስተቶች

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

     “ለልህቀት እንተጋለን” በሚል መርህ ይመራል። ከተመሰረተ ሰባት አስርት ዓመታት ገደማ አስቆጥሯል። ከመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርስቲዎች አንዱና ቀዳሚው ሲሆን በተለይ በጤና ሳይንስ ኮሌጁ  በርካታ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ቀዳሚው እንደሆነ ይነገርለታል ለዚህም በጎንደር ከተማ የሚገኘው የዩኒቨርስቲው ብቸኛው ሆስፒታሉ አንዱ ምስክሩ ነው። የሰላሙ የጎንደር ዩኒቨርስቲ፡፡
የዛሬ ሳምንት ሀምሌ 24 ረፋድ ላይ በዓመቱ ሁለተኛውን ዙር የተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓ ያካሄደ ሲሆን ጥር 15 ቀን 2013.ዓ.ም ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ፣የዛሬ ሳምንት ደግሞ በመደበኛ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ፣ በሶስተኛ ዲግሪና በስፔሻሊስት የትምህርት ደረጃዎች 6 ሺህ 574 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርስቲው የዘንድሮ ተማሪዎችን ሲያስመርቅ በመርሃ ግብሩ በርካታ አዳዲስ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ አንዱና ዋነኛው የተወዳጁና አንጋፋው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የክብር ዶክትሬት ዲግሪ መቀበሉ ሲሆን ከማናጀሩ፣ ከባለቤቱና ከአንዳንድ የቅርብ ወዳጆቹ ጋር በቦታው ተገኝቶ የክብር ዶክርሬት ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ ከሀሙስ ሀምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ላይ ለቴዲ አፍሮ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመስጠት በሰኔት መወሰኑ ይፋ ካደረገበት ቀን ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ ሳይቀር የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
“እኛ የአዲስቷ የኢትዮጵያ ትንሳኤ፤ የአባቶቻችን ልጆች፤ ሀይላችን ጉልበታችን መመኪያችን ፈጣሪያችን
እግዚአብሔር ነው”
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ሜዳማ ስታዲየም ጥቅጥቅ ብሎ ሞልቷል። ከስድስት ሺህ በላይ ተመራቂ ተማሪና ወላጆች፣ እንዲሁም በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። የዕለቱ የመክፈቻ ንግግር በዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ተጀምሯል፡፡ የ”ንጉሱ” መምጣት በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ አርፍዶም ቢሆን መጣ፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ ዶ/ር ኢ/ር ስልሺ በቀለ፤ ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ ዓባይ ወንዝ፣ ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብና ከግድቡ ጋር ተያይዞ ስለ ተፈጠረው ውጥረት ተናገሩ፣ ስለሚያከብሩት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ያላቸውን አድናቆት  ገልጸው “እንኳን ደስ አለህ ይገባሃል” ሲሉም አወደሱት።
ለተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ተመራቂዎቹ ለሀገራቸው በሙያቸው ስለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ገልፀው፤ ሀላፊነታቸውን በተጠሩበት ሁሉ ተቀብለው አገራቸውንና ወገናቸውን እንዲያገለግሉ አደራ ጭምር በማሳሰብ አመስግነው ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡
ቀጥሎም የክብር ዶክተሬት ዲግሪው  አሰጣጥ ሆነ፣ ሁኔታው አስደናቂ ነበር። ከነባለቤቱ በወርቀዘቦ የተጠለፈና   የተንቆጠቆጠ ካባ ለብሶ ስታዲየሙ እስኪንቀጠቀጥ እልልታና ጩኽት ቀለጠ፡፡ እጁን እያውለበለበ ጎንበስ እያለ፣ አክብሮትና ፍቅሩን ለህዝብ ገለፀና መደመነጋገሪያው አትሮንሱ ወረደ፡፡
በታሪካዊቷና የገናናው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ትውልድ ሀገር በሆነችው የጎንደር ከተማ በተዘጋጀው የምረቃ በዓል ላይ ለመታደምና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶችና እንኳን ደህና መጣችሁ ካለ በኋላ ከብዙ ድካም በኋላ ለፍሬ የበቁትን ተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ። ቀጠለናም “በተሰማራሁበት የኪነ- ጥበብ ዘርፍ  ይህ የክብር ሽልማት ይገባሃል ብሎ በዛሬው ዕለት በእናንተ ፊት እንድንቆም ምክንያት ለሆነኝ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በማስከተልም የህይወት አጋሬ ለሆነችው ለባለቤቴ አምለሰት ሙጬ እና ለወላጅ አባቴ ካሳሁን ገርማሞ እንዲሁም ለወላጅ እናቴ ለወ/ሮ ጥላዬ አራጌ እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በሙሉ ከፍ ያለ የአክብሮት ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ። ከዚህ በማስከተልም በማስተላልፈው አጭር መልዕክት ንግግሬን  እቋጫለሁ” አለ፡፡ በአጭር መልዕክቱም “ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገባችበት ከባድ አጣብቂኝና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ፣በሁሉም ዘንድ የታወቀ ቢሆንም እንኳ ነገር ግን እናት ከመጨረሻው አስጨናቂ ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰት ሁሉ ሀገራችንም ከገጠማትና ሊገጥማት ከሚችለው ማንኛውም ከባድ አደጋ በድል ወጥታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር  የለውም፡፡
ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጎሳ ፖለቲካ ሐሳብ እንደማንኛውም ፍልስፍና ሃሳብ ተወልዶ፣ አድጎ፣ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል፡፡   ስለዚህ ከዚህ በኋላ መላው የሀጋራችን ህዝብ በተለይም ወጣቶች  በጎሳ፣ በዘርና በሀይማኖት ልዩነት ሳትናወፁ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በፍጹም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜት ፀንታችሁ መቆም ያለባችሁ ወይም ያለብን መሆኑን በአንጽኦት ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ እኛ የአዲስቷ የኢትዮጵያ ትንሳኤ የአባቶቻችን ልጆች ሃይላችን፣ ጉልበታችንና መመኪያችን እግዚአብሔር ነው ራዕያችንም፣ ፍቅር ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ታላቅ እና ገናና አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ፍቅር ያሸንፋል፡፡” የሚል ሁሉንም ያስገረመ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ሊተገብሩት የሚገባ “የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት”
እሁድ ሀምሌ 25 በሁለተኛው ቀንም የጎንደር ዩኒቨርስቲ በዓል በድምቀት እንደቀጠለ ነው፡፡ ለምን ቢባል? ባለፈው ዓመት ሞክሮት ውጤት ያመጣበት “የቃልኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክት” በዚሁ ዕለት ቀጥሏል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በየዓመቱ ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች፣ በጎንደር ከተማ ውስጥ ከሚኖሩ ነዋሪዎች ተገቢውን ፍቅርና እንክብካቤ የሚያገኙበት ብሎም ለትምህርትና ስልጠና በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ጊዜ ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን  ቤተሰባዊ ክትትልና ድጋፍ እንዲያገኙ መሰረት ያደረገ ታልሞ የተቀረፀ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዕለቱም የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ የቃልኪዳን ልጆቻቸውን ተረክበዋል በሌላ በኩል ደግሞ በዩኒቨርስቲው በከፍተኛ ሀላፊነት የሚሰሩት ዶ/ር መሰረት  የቃልኪዳን ወላጅ ሆነው ያስተማሯትን አንዲት የአዲስ አበባ ልጅ በከፍተኛ ውጤት መመረቋን ምክንያት በማድረግ፣ የተማሪዋ የተፈጠሮ ወላጆች ከአዲስ አበባ ለዩንቨርስቲውና ለቃል ኪዳን ቤተሰቧ ዶ/ር የእውቅና ሽልማት ማበርከታቸው አነጋጋሪ ነበረ (የእነዚህን ወላጆች ድንቅ ተሞክሮ ሳምንት  የምናቀርብላችሁ ይሆናል)፡፡ በዚሁ ስነ-ስርዓ ላይ ትኩረት የሳበ ነበር። ይህ ቀን ድምፃዊ ታሪኩ  ክንጊሲ (ዲሽታ ጊና)፤ በጎንደር ህዝብ ፍቅር ያበደበት ዕለት ነበር። ድምጻዊው ወደ መድረክ ሲወጣ ህዝቡ ባደረገለት ታላቅ አቀባበል በእጅጉ የሰከረው ታሪኩ ከመድረኩ ዘልሎ ወደ ተማሪው በመግባት ለተወሰነ ደቂቃ ግርግርና ትርምስ ተፈጥሮ እንደነበር በቦታው ሆነን ታዝበናል። “ከዚህ በኋላ የትም ብሔድ ከዚህ የበለጠ ፍቅር የማገኝ አይመስለኝም” ሲል ታሪኩ ለጎንደር ህዝብና ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አድናቆቱን ገልቷል።

የጎርጎራ መሪ እቅድና ዲዛይን ርክክብ
የጎንደር ዩኒቨርስቲ በ“ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት” ከተካተቱ ውስጥ አንዱ የሆነው የጎርጎራ ከተማን በርካታ ዘርፍ ያገለግላል ከነዚህም መካከል በጎርጎራ የግብር የጤና ምርምር ማዕከሉ ለማህበረሰቡ ጤና ጣቢያ በመክፈትና ለከተማው ብቸኛ በሆነው በዚሁ ጤና ጣቢያ ማህበረሰቡን ከማገልገሉም በተጨማሪ በግብርና ምርምር ማዕከሉ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር በመስጠት ለምርምር ያመረተውን ምርት በዝቅተኛ ዋጋ በመሸጥ፣ገበሬውን የዘመነ ግብርና እንዲከተል በማንቃትና በበርካታ ዘርፎች ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
አሁን ደግሞ ጎርጎራ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውስጥ ሲካተት የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉም በላይ በዲዛይን ስራ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጎና ባለብዙ ገፅ የከተማዋን መሪ እቅድ አዘጋጅቶ በዚሁ ዕለት ለጎርጎራ ከተማ ከንቲባ አስረክቧል፡፡ ከንቲባውም ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስራት አፀደ ወይን (ዶ/ር) እጅ የጎንደር ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በክብር እንግድነት በተገኙበት ተረክበዋል፡፡
የሱዳን ምሁራን ልዑካን ቡድን በጎንደር
የጎንደር ዩኒቨርስቲን የዘንድሮ የምረቃ ሥነ ስርዓት ለየት ከሚያደርጉት አንዱና አዲሱ ጉዳይ የሱዳን የምሁራን ልዑካን ቡድን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መጋበዛቸው ነው፡፡ እነዚህ የሱዳን ዩኒቨርስቲዎች ፕሮፌሰሮች በምረቃ በዓሉ ላይ ከመታደማቸውም ባለፈ በምረቃው በሶስተኛው ቀን ማለትም ሰኞ ሀምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ረፋድ ላይ ዩኒቨርስቲው በማራኪ ግቢ አልሙኒየም አዳራሽ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ምሁራን ጋር በመሰብሰብ በሁለቱ ሀገራት ወቅታዊ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ውይይትና ምክክር አድርገዋል፡፡
በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን  ማጠናከር ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑ የተነሳ ሲሆን፣ ሁለቱ ሀገራት ከጥንት ጀምሮ ያላቸውን ታሪካዊ የባህል ትስስር የሚገልፁ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎችም በሱዳናዊ ፕሮፌሰሮች ቀርበዋል። የሁለቱን ሀገራት ምሁራን በማስተባበርም ከአባይ ወንዝና ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የምርምር ተቋማትን በኢትዮጵያና በሱዳን በመመስረት የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንዲሚገኝ የጎንደር ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ተገኝ (ዶ/ር) በመድረኩ ተገኝተው ከማብራራታቸውም ባለፈ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታም ገልጸዋል፡፡

የጎዳናዎች ስያሜ
 በከያኒ የክብር ዶ/ር ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮና) የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቀድሞ ፕሮጀክት ማናጀር በነበሩትና ከሶስት ዓመት በፊት ህይወታቸው ባለፈው ኢ/ር ስመኘው በቀለ ስም በተለምዶ ኮሌጅ ማዞሪያ (18) እየተባለ ከሚጠራው ቦታ እስከ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ማራኪ ግቢ ድረስ “ቴዲ አፍሮ ጎዳና” ሲባል ከዚሁ የኮሌጅ ማዞሪያ “ሸንታ” እስከሚባለው ድረስ ያለው ደሞ “ኢ/ር ስመኘው ጎዳና” ተብሎ ተሰይሟል። የሁለቱንም የጎዳና ስያሜዎች ታፔላ ሪቫን የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ እና ቴዲ አፍሮ ቆርጠዋል፡፡ ሀምሌ 26 ቀን ጠዋት በማራኪ ግቢ በርካታ የዩኒቨርስቲው ሰራተኞችና ተማሪዎች ችግኞችን የተከሉ ሲሆን ረፋዱ ላይ ቴዲ አፍሮን ወደ አዲስ አበባ በመሸኘት መርሃ ግብሩ በሰላም ተጠናቋል፡፡ ጎንደርም ከምረቃ ቀኑ ቀደም ብለው ካሉ ቀናት ጀምሮ በእንግዶች ተጨናንቃ የጥምቀት አይነት ድባብ ተላብሳ መሰንበቷን በቦታው ተገኝተን ለመመልከት ችለናል፡፡


Read 1353 times