Print this page
Saturday, 07 August 2021 14:08

ሕወሓት እንዴት ዳግም አንሰራራ?

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)


               ማስፈንጠሪያ
ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን፣ አፈር ልሶ ተነስቶ፣ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት፤ ለዜጎች ሞትና መፈናቀል መንስኤ መሆን ከጀመረ፣ ሰነበተ፡፡ ከማእከላዊው መንግሥት ጋር የሚተካከል ወታደራዊ ቁመናን ይዞ፤ ሦስት ሳምንት በቅጡ እንኳን መገዳደር ሳይችል፣ አከርካሪውን የተሰበረው ድርጅት፣ እንዴት ዳግም የሥጋት ምንጭ ሊሆን እንደቻለ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡
ለመሆኑ ሕወሓት እንዴት አንሰራራ?
የጊዜያዊ አስተዳደሩ አሻጥር
በሕወሓት ውድቀት ማግሥት፣ ትግራይን እንዲያስተዳድር የተሰየመው አካል፣ ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ነበር፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የሕወሓት ጉዳይ አስፈጻሚ እንደነበረ፤ በመስተዳደሩ ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ቦታ የሰሩ ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ናቸው፡፡
ሌ/ኮሎኔል ፍሰሀ በርሔ፣ የትግራይ ክልል የጤና ምርምር ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የሕግ ማስከበር ዘመቻው፣ ለመቀልበሱ በዋናነት መጠየቅ ያለበት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ነው ይላሉ፡፡
መስተዳደሩ ውስጥ የነበሩት አመራሮች፣ ከሰብአዊ ድጋፍ በዘለለ፤ የፖለቲካ ሥራን መሬት ላይ ወርደው ለመሥራት ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ የሰብአዊ  ድጋፉም ቢሆን፤ በተጎጂዎች ፈንታ፣ ለጥፋት ኃይሉ  ሲሳይ እንዲሆን፤ ትልቅ ሴራ ሲጎነጎን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ሌላው ቀርቶ፤ ከካቢኔ አባላቱ ወደ 8 የሚጠጉ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሽብርተኛውን ሕወሓትን መቀላቀላቸውን ስንመለከት፣ መስተዳደሩ የጥፋት ኃይሉ አጀንዳ አስፈጻሚ እንደነበረ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፤ ብለዋል፡፡
አቶ መሰለ ሰለሞን፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር፣ የእንደርታ ዞን ም/አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል፤ በመስተዳደሩ ውስጥ የተሰገሰጉት አመራሮች፣ የአቅም ችግር ቢኖርባቸውም፤ የጥፋት ኃይሉን ተልእኮ ለማስፈጸም ግን፤ ግንባራቸውን አያጥፉም ነበር ፡፡ ይኽ ሁኔታ ውሎ አድሮ፣ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቅሬታን የፈጠረ ሲሆን ከመንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነትም የበለጠ እያሻከረው መሄዱን ያስረዳሉ፤ አቶ መሰለ ሰለሞን፡፡
ምንም እንኳን፤ የቀድሞ አመራሮች ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለምልልስ፤ ለሕወሓት ዳግም ማንሰራራት ጊዜያዊ አስተዳደሩን በምክንያትነት ቢጠቅሱም፤ በሌላ አንጻር መንግሥት በተረፈ ሕወሓት ላይ፣ በጸረ ሽምቅ ውጊያ እግር በእግር በመከታተል የመደምሰስ ሥራ አለመሥራቱ፤ አጥፊው ቡድን ትንፋሽ እንዲሰብሰብ ትልቅ እገዛ እንዳደረገለት፤ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይደመጣል፡፡
የምእራባዊያን ጫና
ሕወሓት በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የወሰደውን የሽብር ጥቃት፣ በወቅቱ በይፋ ለማውገዝ የደፈረ የምእራቡ አለም ሀገር አልነበረም፡፡ በተቃራኒው፤ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የአጻፋ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኋላ፣ በክልሉ የዘር ማጥፋትና ጅምላ ጭፈጨፋ ተፈጽሟል በሚል ጭምብል፣ ማእከላዊው መንግሥት ላይ ጭፍን ፕሮፓጋንዳ ማሰማት የጀመሩት ገና በጠዋቱ ነው፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ታዛቢዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ምእራባዊያን በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ምስቅልቅል የተረዱበት አግባብ የሚመነጨው፣ ከብሔራዊ ጥቅማቸው ነው፡፡
በምዕራባዊያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ፣ ሰብኣዊ ቀውስ የሚለው ቋንቋ ጭምብል ነው፡፡ ሀገራቱ በርግጥም ይኽ ግድ የሚላቸው ቢሆን ኖር፤ ሕወሓት በወልቃይት ሕዝብ ላይ ከአፓርታይድ ያልተናነሰ እጅግ አሰቃቂ አገዛዝን ሲዘረጋ ድምጻቸውን ባሰሙ ነበር፡፡ ዜጎች የተለየ አመለካከት በማንጸባራቀቸው ብቻ፤ ላለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት፣ ሰብኣዊ ፍጡር ሊሸከመው የማይችለው ግፍ በጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን ሲፈጸምባቸው፤ የሀገራቱ ምላሽ ዝምታ ባልሆነ ነበር፡፡
ልእለ ኃያሏ አሜሪካ፣ ሕወሓትን እንዲህ ያለቅጥ እሽሩሩ ማለቷና ማእከላዊ መንግሥት ላይ ከልክ በላይ ጫና ማሳደሯ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን ታሳቢ አድርጋ እንጂ፤ ሰብኣዊ ቀውስ አሳስቧት አይደለም፡፡ ለዚህም በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የተነሳ በሶሪያ፣ የመንንና ሊቢያ የተከሰተውን ምስቅለቅል  በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
"ቲፋይግሎባል" ለተባለ የመረጃ ምንጭ፣ የፖለቲካ ትንታኔን በመስጠት የሚታወቁት ሶህል ሲናህ፣ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እያንጻበረቀ ያለው አቋም፣ በቀጥታ የሚያያዘው፤ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጸሐፊው በትንታኔያቸው እንደዳሰሱት፤ አሜሪካ በትግራይ ከተከሰተው ሰብኣዊ ቀውስ የበለጠ የሚያሳስባት ቀጠናው ላይ ያላት ተሰሚነት ነው፡፡ "የአፍሪቃ ቀንድ፣ በርካታ የንግድ መርከቦች የሚተላለፍባቸውን ቀይ ባሕርና የስዊዝ ቦይን የሚገኝበት ወሳኝ ቀጠና እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ አካባቢ ያለውን የኃይል ሚዛን፣ ምእራባዊያን በቅርበት ነው የሚከታተሉት፡፡" ብለዋል፤ ጸሐፊው፡፡
"የምእራብ ኃያላን አገራት፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የፈጠረችው የኢኮኖሚ ግንኙነት፣ በአፍሪቃ ቀንድ ያላቸውን ተሰሚነት ይቀንስዋል፤ ብለው ይሰጋሉ" ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ "ይህንንም አደጋ ለማስቀረት፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሰብኣዊ ቀውስ፣ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፤ በከፍተኛ ሁኔታ እየተረባረቡ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡  
የኃይላን አገራትን ጥቅምና ፍላጎት፣ በስውርም ሆነ በግልጽ ለማስጠበቅ የተቋቋሙት የመገናኛ ብዙኅን፣ የሙያው ሥነምግባርን በጣሰ መልኩ፤ ለአንድ ወገን ያላቸውን ጥብቅና በገሀድ አስመስክረዋል። በመገናኛ ብዙኃኑ እንደ ልባቸው የሚፈነጩት እነ ማርቲን ፕላውት፣ አሌክስ ዳዋል፣ ትሮንቮልና ዊሊያም ዳቪድሰን ናቸው፡፡ እነዚህ "ነጭ ወያኔዎች" & የአጥፊውን ቡድን አጀንዳ በአደባባይ ሲከላከሉ ነው የሚስተዋለው። ተቋማቱም መረጃዎቹን ሳይፈትሹ፤ እንደ ወረደ በማቅረብ፣ ከግምት ላይ የሚጥል ስህተትን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ በብዙዎች ዘንድ፤ መነጋገሪያ የሆነውን የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ በዋቢነት ማንሳት ይቻላል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ፣ ህውሓት ካሰማራቸው ሕጻናት ወታደሮች ጋር በተያያዘ የሰራው ዘገባ ግርምትን የሚያጭር ነው። በግዳጅ የተሠማሩትን ልጆች፣ “a highly motivated young recruits” ("እንደ ተርብ የተነቃቁ ብላቴና ተዋጊዎች”) በሚል ርዕስ ሥር ባቀረበው ሐተታ፤ ቡድኑን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት በወንጀል ለሚያስጠይቀው ድርጊት፣ ድጋፍ ማሳየቱን መመልከት እንችላለን፡፡
የምእራባዊያን ሚዲያ ግጭቱን አስመልክተው የሚዘግቡበት አግባብ፣ ከመስመር የወጣ መሆኑ ሊደንቀን አይገባም። ሚዲያዎቹ የዘገባዎችን ተአማኒነት ለማረጋገጥ፤ የምርምራ ሥራ ለመሥራትም ሆነ፤ የግጭቱን ሙሉ ስእል ለማሳየት ደፍረው አያውቁም፡፡ ሕወሓት፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ እያደረሰ ያለውን ጥፋት በማሳወቅ ፋንታ፤ በሰብኣዊ ቀውስ ሽፋን ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻን መክፈታቸው፤ የገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስነሳ ይሆናል፡፡ ይህም የተቀነባበረ ዘመቻ፣ አጥፊው በድን ከቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ወጥቶ ዳግም ለሽብር ድርጊት እንዲሰማራ ብርታት ሆኖታል፡፡
ማሰሪያ ነጥብ
ለሀገርም ሆነ ለቀጠናው ጠንቅ የሆነውን ሽብርተኛ ድርጅት፣ በነፍጥ ማንበርከክ፤ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። ይኽንንም እውን ለማድረግ፤ መንግሥት ከበቂ በላይ ኃይል እንዳለው ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተከተለው ሥልት፣ የሕወሓት ታጣቂዎችን ወደፊት መግፋት ላይ ያተኮረ ነበረ፡፡ በዚህ ስልት ፈንታ፤ እየቆረጠ ደምስሷቸው ቢሆን ኖሮ፤ዳግም ለማንሰራራት የሚኖራቸው ዕድል፣ ይመነምን እንደነበረ፤ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙዎች ይገልጻሉ፡፡
የኃይል መሳሳት ባለበት በራያ ግንባር፣ ሕወሓት በከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት ቀና ማለት ጀምሯል፡፡ እጅግ አስፈላጊውን የወልቃይት ኮሪደርን፣ በእጁ ለማሰገባት ቢፍጨረጭርም፤ ከአቅሙ በላይ ስለሆነበት የምዕራባዊያን ሸሪኮቹን ጫና እንደ ምጽአት ቀን በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡
የአሸባሪው ድርጅት የጥፋት አድማስ ከዚህ በላይ እንዳይሰፋ፤ የመንግሥት የተቀናጀ ወታደራዊ እርምጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ፤ ሀገር ወዳድ ወገኖች በመወትወት ላይ ናቸው፡፡ በእርግጥ፤ ውትወታው ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ ወታደራዊው ስኬት ብቻውን ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፡፡  ከወታደራዊው ዘመቻ ጎን ለጎን፣ የፖለቲካ ሥራው  በእጅጉ መታሰብ ይኖርበታል፡፡
ጀርመኖች በናዚዝም እምነት ላይ ከበቀለው ብሔርተኝነት ቀስ በቀስ መላቀቅ የቻሉት፣ ሂትለር በጥምር ጦር ድብቃ ከተመታ በኋላ፣ ዘረኝነትን ማሟሟት በሚችል  ፍትሓዊ የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ሕወሓት አምጦ የወለደው አደገኛው የትግራይ ብሔርተኝነት፤ ከወታደራዊ ድል በኋላ በጊዜ ሒደት ለማጥፋት፣ እኩልነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እጅግ በጣም ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

Read 11932 times