Print this page
Saturday, 07 August 2021 14:10

በአፍሪካ የኮሮና ሟቾች ቁጥር በ89 በመቶ መጨመሩ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  - አለማቀፉ የኮሮና ሟቾች ቁጥር ከሚነገረው በ1 ሚሊዮን ይበልጣል ተባለ
                     - በጤና ተቋማት ጥቃቶች ከ2700 በላይ ባለሙያዎችና ታካሚዎች ተገድለዋል


              በአፍሪካ አህጉር በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ በ89 በመቶ ያህል መጨመሩንና ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው ዴልታ የሚል ስያሜ የተሰጠውና በፍጥነት በመሰራጨትም ሆነ በገዳይነት የከፋ እንደሆነ የሚነገርለት አደገኛው የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በስፋት መሰራጨቱ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ የክትባት ቢሮ ሃላፊ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፈው ወር በአህጉሪቱ የተመዘገበው የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር 24 ሺህ 987 ሲሆን ይህም ከአንድ ወር በፊት ከተመዘገበው የ89 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ሟቾች ቁጥር እስካለፈው ሳምንት በነበሩት ያለፉት አራት ተከታታይ ሳምንታት በሚገርም ሁኔታ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በሃምሌ አጋማሽ ከፍተኛው የአህጉሪቱ የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር 6 ሺህ 343 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በአፍሪካ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እስካለፈው ረቡዕ ከ6.8 ሚሊዮን ማለፉን፣ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 173 ሺህ  መድረሱን የዘገበው ኦል አፍሪካን ኒውስ፤ እስከተጠቀሰው ዕለት ድረስ በአህጉሪቱ በድምሩ ከ48.3 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች መሰጠታቸውን ጠቁሟል፡፡ በተያያዘ ዜና፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር በይፋ ከሚነገረው በ1 ሚሊዮን ያህል እንደሚበልጥ ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡
የእስራኤሉ ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በ103 የአለማችን አገራት ላይ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ በመላው አለም በኮሮና ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 4.22 ሚሊዮን ያህል ነው ቢባልም፣ ትክክለኛው ቁጥር ግን ከተባለው ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደሚበልጥ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
አንዳንድ መንግስታት፣ የኮሮና ቫይረስ ሟቾችን ቁጥር ሆን ብለው ቀንሰው ስለሚያሳውቁና አንዳንዶቹ ደግሞ የሟቾችን ቁጥር በአግባቡ ለመመዝገብ ባለመቻላቸው ሳቢያ፣ አለማቀፉ የቫይረሱ ሟቾች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተቀንሶ እንደሚነገርም ዩኒቨርሲቲው ባወጣው ጥናት አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል፤ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ለሁለት ዙር የወሰዱ ሰዎች ካልተከተቡ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸው በግማሽ ያህል ያነሰ እንደሆነ በብሪታኒያው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን የተሰራ አንድ ጥናት ማረጋገጡን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
በሌላ የጤናው መስክ ዜና ደግሞ፣ እስካለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በነበሩት ያለፉት 3 አመታት፣ በአለም ዙሪያ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ከ2700 በላይ የጤና ባለሙያዎችና ታካሚዎች መገደላቸውን አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ700 በላይ የጤና ባለሙያዎች ሲገደሉ፣ ከ2ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል።


Read 1692 times
Administrator

Latest from Administrator