Monday, 09 August 2021 18:02

እግዜርን በጀርባ ማዘል

Written by  ያ.ብርሃኑ
Rate this item
(4 votes)

 ‹‹ሊሊ የደጃፌን መከፈት ልትጠቁምበት በማትደፍራቸው እህቶቼን እያለፈች ትመላለስ ጀመር፡፡ አንድ ቀን ሲያለቅስ ሰምቼው የማላውቀውን ልጅ እያባበለች። አንድ ቀን ነቅቶ ያላየሁትን ልጅ ለማስተኛት እየወዘወዘች፡፡ ረሀብተኛ አይኖቿ ያስፈራሉ። እኔን ለማፍቀር ሳይሆን ለመብላት የጎመጀች ያስመስሉባታል፡፡ በበሬ እንዳለፈች ሳትመለስ በፊት መለስ አደረግኩት፡፡ በእኔ መጨነቅ እግዚአብሔር እየሳቀ ነው፡፡ እንዴት ከእኔ ከፍጡሩ ያንሳል? እንደ ልጅ ኢያሱ በልጅነቱ በውርስ የተሾመብን ሌላ አምላክ ይኖር ይሆን? የፈጠረን የሚያውቀንስ በዚህ ድክመታችን አይሳለቅም፡፡ እኔን ይተው ሊሊን አያይም? አሁን የእርሷ ኑሮ ፍቅር የሚያሻው ነው? እኔ ያየሁትን እንዴት እግዚአብሔር ሳያይ ቀረ?…››
የዓለማየሁ ገላጋይን "ታለ-በዕውነት ስም"ን ካነበብኩ እነሆ ሣምንታትን አሳብሬ ወራትን መቁጠር ጀምሬያለሁ፡፡ ዓለማየሁ በዚህ መጽሐፉ ልርሳሽ ብል እንኳን መቼም የማረሳት፣ ነፍሴን ቀስፋ ይዛ ዘወትር በጽሞና ሰዓቴ የማብሰለስላት አንዲት ገጸ ባህሪ አለችው፡፡ ስለዚህች ገጸባህሪው እንዲያው ላመል ያህል ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ፈልጌ በርከት ላሉ ቀናት ሳመነታ ነበር፡፡ ምናልባት ያኔ መርሳቱ ቢቀር እንኳን ልዘነጋት ቢቻለኝ በሚል… ይህች ገጸ ባህሪ ሊሊ ናት። ያቺ ወንድሟንና እግዚአብሔርን በጀርባዋ የተሸከመችው ሊሊ…
ዓለማየሁ ገላጋይ በሌሎቹ መጻሕፍቱ (ቅበላ፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ወሪሳ፣ አጥቢያ…) እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህም መጽሐፉ በቀላሉ ልንረሳቸው የማንችላቸውን እንግዳ ገጸባህሪያትን ያስነብበናል፡፡ ምናልባት በዚህ ጥበብ ተወዳዳሪ የለውም መሰለኝ። የአልበርት ካሙን ሞገደኛ ገጸ ባህሪያት የሚመስለው ረድ ሰርዌ፣ ወትሮውንም ለወዲያኛው ዓለም የቀረበች የምትመስለውና እንደ ቢራቢሮ ሽልምልሟ ረቂቅ፣ የምሁርና የፊውዳል ድቅል መልክ የሚታይበት ጠና ጋሻው… ከእነዚህ ሁሉ በላይ ምናልባትም በቀደሙት መጻሕፍቱ ሁሉ ካነበብኳቸው ሙና፣ ቹቹ፣ አንጰርጵር፣ ሽትርገጥ፣ ጦጤ፣ ሲፈን በላይ ሊሊ ግን ትለያለች፡፡
ሊሊ አስራ ስድስት ዓመት የሆናት ታዳጊ ነች፡፡ ወንድሞቿን ሁሉ አዝላ ያሳደገቻቸው እሷ ነች፡፡ ታለ መኖሪያውን ቀይሮ እነ ሊሊ ሰፈር ሰባራ ባቡር ሲገባ በዕይታ ብቻ ወደደችው፡፡ ወንድሟን እንዳዘለች የታለን አንዲት ውልብታ ለማየት ያህል በር በሩን ስትመለከት ትውላለች፡፡ ነገሩ ለየት ያለ የሚያነውር የሚመስል እንግዳ መልክ አለው፡፡ ከተወለደች ጀምሮ ከቤት ወጥታም ሆነ ትምህርት ቤት ሄዳ አታውቅም፡፡
ሊሊ እስከ ጽንፍ በተዘረጋው ህዋ ውስጥ እየኖረች፣ አንድ ቀን ብቻ ልጅ ሳታዝል፣ ከሰባራ ባቡር ወደ ሞንተራሌ ሄዳለች፡፡ የመደመጥ ዕድል ባገኘች ቁጥር ያችኑ የአንድ ቀን ጀብዷን፣ የአንዲት ዕለት ነጻነቷን ትደጋግማታለች፡፡ ‹‹ጉድጓድ ውስጥ የምትኖር እንቁራሪት በቀዳዳ የምታየው ሰማይ መላው ዓለም ይመስላታል›› እንዲሉ አበው፣ የሊሊ ዓለም ከሰባራ ባቡር እስከ ሞንትራሌ ብቻ ይመስላል፡፡ ጉስቁልናዋ፣ መገፋቷ፣ መገደቧ ብዙ ነው፡፡ ነገር ግን እግሮቿ፣ አካሏ ቢታሰርም ቅሉ ልቧን ማንም ማሰር አልተቻለውም፡፡ እናም ዘመኗን ቆጥራ መውደድን ተመኘች። ግንችሬ ወንድሟን በጀርባዋ እንዳዘለች በነፍሷ የተሸከመችውን የመውደድ ሲቃ ለማስታመም ተፍገመገመች፡፡ በጀርባዋ አንድ ወንድሟ ብቻ ሳይሆን ታለ፣ እግዜሩ ራሱ፣ እኔ እናንተ ሁላችንም በየተራ ታዘልን።  በዚህ ሁሉ የሚያሰቅቅ ትዕይንት መሀል እግዜር አምላክነቱን ትቶ በፍጡራኑ ላይ ከንቱ ብሽሽቅ የሚጫወት ጅላጅል ሸክላ ሰሪ ሆኖ ቀረበ፡፡ እንከኑ የራሱም መሆኑን ረስቶ በፍጡራኑ ጉድለት የሚያላግጥ ….
‹‹እግዚአብሔር ቀልድ ሲያምረው እኔን በሊሊ እንድፈቀር አደረገ፡፡ ወደ ሕይወት የሚጓዝና ከሕይወት መልስ ለታከተ ሰው አንዲት የኑሮ መገናኛ ነጥብ አለች፡፡ ይህች ነጥብ ናት የእግዚአብሔር ቀልድ፡፡ ሊሊ በሬን ስትፋጭር እግዜሩ (እ) ላይ ሆኖ ይስቅ ይሆን? እንዴት ያለ ቀልድ ነው? ቢያንስ ለሰው ልጅ ይሄ ቀልድ እንዳልሆነ መናገር እችላለሁ።”
እናስ ዓለማየሁ በሊሊ መነፅር ሊነግረን የፈለገው ምንድን ነው? የታዘለው አንድም ቀን ተንቀሳቅሶም ሆነ አልቅሶ የማያውቀው ልጅ ምስለት (symbolism) ምንድን ነው?
‹‹እግዚአብሔር ቀልድ ሲያምረው እኔን በሊሊ እንድፈቀር አደረገ፡፡… ሊሊ በሬን ስትፋጭር እግዜሩ (እ) ላይ ሆኖ ይስቅ ይሆን? እንዴት ያለ ቀልድ ነው?…››
በዓለማየሁ የብዕር ፍትጊያ እግዜር ዘመኑን ጨርሶ ጃጅቶ ቀረበ፡፡ ገጣሚ ነቢይ መኮንን ‹ስውር ስፌት› ቁጥር የግጥም መጽሐፋቸው ላይ ‹ጊዜም ቀን ይጎድልበታል› በሚል ከቋጠሯት ግጥም ስንኞችን ቀንጭቤ ልጥቀስ፡፡
‹‹… የሚገርመው
ጊዜም እኮ እንደሰው ፊት
ሲያረጅ ይጨማደድና
ገጹን ማዲያት ይወራዋል
  …
…እና አትርሱ
ጊዜም ቀን ይጎድልበታል
ጥቁር መስታውት እንደሚያይ ልቡን ጽልመት ይሞላዋል፡፡
አትመኑት እንደኛው ነው
ሰባራም ሙሉም ፊት አለው፡፡›› ገጽ 52
ጉደኞቹ እኛ ዘመናችን አጃጀን፤ እግዜርንም እንደኛው አስረጀን፡፡ በእነዚህ ገፆች መሃል ጊዜን ጊዜ ሲያጥጥበት እግዜርም ዘመኑን ጨርሶ ጨርጭሶ ታየ፡፡ ለእኛም ጊዜ እንደ ሸሚዝ እንደ ካኒተራ እላያችን ላይ አለቀ። ዘመናችን ከመገርጀፉ የተነሳ የትናንት በጎነታችን ዓይናችን እያየ ዛሬ ነውር ሆኗል። እግዜርም እንደኛ ከዘመኑ ጋር መታደስ ተስኖት ‹ፋሽኑ› ሊያልፍበት ይመስላል፡፡ እግዚአብሔርን እዚያ ከደመና በላይ በሩቅ ሰማይ ሰቅለው አጉል የሚጎናበሱ እነሱ ምንኛ ጅሎች ናቸው፡፡ እግዜር እኮ እኛው ነን፡፡ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ… እግዜርን ማየት ስትፈልግ ስለ ምን ወደ መቅደስና ምኩራብ ትኳትናለህ? ይልቅስ መስታወት ፊት ቅረብ። እሱ ስትከፋ ክፉ ነው፤ ስትለግስ ለጋስ…  
የሆነስ ሆነና ዓለማየሁ፤ በሊሊ መነጽር ሊነግረን የፈለገው ምንድን ነው? አንድም ቀን ተንቀሳቅሶም ሆነ አልቆሶ የማያውቀው የታዘለው ልጅ ምስለቱ ምንድን ነው? ሁላችንንም ልባችንን ገልጦ ማየት ለሚችል ሰው እንደ ሊሊ የሆነ የማንፈልገውን በዓድ ክቡድ ሬሳ ተሸክመን የምንከረፈፍ ፍጥረቶች አይደለንምን? እውነትስ የሚፋጅ እሳት አስታቅፎና ሮጦ ማምለጫ እግር ነስቶ የሚፈጥር አምላክ፣ ጅላጅል ሸክላ ሰሪ ካልሆነ ምን ሊሆን ነው?
ከአስር ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያሳትመው ‹ሰላምታ› መጽሔት ላይ ባነበብኩት አንድ ትንታኔ መሰረት፣ ‹ሊሊ› ከጥንታዊ ግብጻዊያን ዘመን ጀምሮ እንደ ብርቅ የሚታዩ፣ ለአማልክት የሚበረከቱ የአበባ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ሊሊ አበቦች በአብዛኛው ውኃ ባቆሩ አካባቢዎች እንደ አልጌ ውኃው ላይ እየተንሳፈፉ ይበቅላሉ፡፡ እነዚህ ሚጢጢ ጌጠኛ አበቦች የድንግልና፣ የንጽህና፣ የውበት፣ የጥንካሬ መገለጫዎች ናቸው፡፡
እናስ ካልጠፋ ስም ለዚህች መከራን ሁሉ ጠቅልላ በጀርባዋ የተሸከመች ጉስቁል ታዳጊ፣ ይህንን ስም ማከናነብ ምን ዓይነት መራር ምጸት ነው?! እንጃ!


Read 1074 times