Monday, 09 August 2021 20:13

እንግዳው ሰው

Written by  ድርሰት - ልዊስ ማኑኤል ኸርባኔጃ ኤቸልፖህል ትርጉም - ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(4 votes)

  በትልቁ መተላለፊያ መንገድ አካባቢ የተሰባሰቡ ሰዎች በተደጋጋሚ በማስጠንቀቂያ ድምጽ እያሰሙ ነበር፡፡ ‹‹ኦቬጆን! ኦቬጆን ይሆን እንዴ?››  ሆኖም የሚቦነውን አቧራ ወደ ወርቃማነት ከምትቀይረው ጸሐይ ጨረሮች በስተቀር በመንገዱ ላይ ምንም የሚታይ ነገር አልነበረም፡፡
ማንም የእርሱን ውልብታ ተመልክቶ አያውቅም፡፡ እስካሁንም እርሱን በመፈለግ የጋለ ፍላጎት፣ ከዛኑታ የመጣው የታጠቀው ጓድ እርሱ አብሮ ይኖራል በሚል የሚተላለፉ ሰዎችን ይበትናል፡፡ እነሆ አሁን በስፋት ማስጠንቀቂያው ተሰራጭቷል፡፡ አሁን እንደ የቆየው የከተማዋ የጉርብትና ይትብሃል በርን ገርገብ አድርገው የሚተኙበት ጊዜ አይደለም፡፡   
ኦቬጆን ጠላቶቹ ደረቱን እንደ ወንፊት ለመበሳሳት ቋምጠው ጣቶቻቸውን በሽጉጦቻቸው ምላጭ ላይ ለማኖር ሲያቆበቁቡ እንደተለመደው ከመቅጽበት ከእይታቸው እልም አለ፡፡ ሽፍታው ፊት ለፊታቸው እንደምንም የሚያጥበረብር ደመናው መስሎ ተሰወረ፡፡ ኦቬጆን በርካታ አስማቶችን ያውቃል፡፡
ፈላጊው ቡድን ወደ ቤት ተመልሶ ምን እንደተፈጠረ እየተወያየ ይገኛል፡፡ የተለመደ አሮጌ ታሪክ ነው፡፡ ፍለጋ፣ ማስጠንቀቂያ ከተለመዱ የኦቬጆን ማታለያዎች ጋር። አሁን ከአካባቢው በጣም ርቆ መሄድ ይኖርበታል።
በሰፊው አውላላ ሰማይ የምሽት ወርቃማ አብረቅራቂ ጨረሮች እየተሰባሰቡ ነበር፡፡ መላው ገጠራማ አካባቢ የተረጋጋና ጸጥታ የሰፈነበት ይመስላል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት በላይ የምሽቱ የአቅላላ ወጋገን ጭጋግ መስሎ ይታያል፡፡ እታች በወንዙና በመሻገሪያው በኩል የወንዙ ውሃ በአስደሳች ጉርምርምታና መልጎምጎም ታግዞ ይፈሳል፤ አብረቅራቂ የጨረር ፍንጣቂዎች በቀርቀሃ ተክሎችና በጥሻው ላይ ሁሉ አንጸባርቀዋል።
በዚያው ቅጽበት ከወንዙ በኩል ቅርጽየለሽ እድፋም ያበጠ ፊትና ስስ ከንፈሮች ያለው ባለ ቢጫ አኮፋዳ ለማኝ በተነፋፋ እግሩ ለመራመድ እራሱን እየጎተተ ነበር፡፡ በአረንጓዴና የሚንጸባርቁት ድንጋዮች ላይ እየተራመደ ለመሻገር ይታገላል፡፡ ረጅም ቀጭን በትር ተደግፏል፡፡ የለማኝ አኮፋዳው መጠነኛ እብጠት ከሰጣት ቡናማ ቂጣ ጋር ከእርምጃው ጋር ውን ውን ትላለች፡፡ ለማኙ ባልረጉና ሲረግጧቸው በሚንሸራተቱ ድንጋዮች ላይ የተነፋፋ እግሩን በጥንቃቄ እያሳረፈ ቀርፋፋ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ በሚያጥበረብር ብርሃን ውስጥ ያልተስተካከለ ሚዛንን ጠብቆ መራመድ አስቸጋሪ ሆኖበታል፡፡ ለማኙ ድንገት ጅው ብሎ ድንጋዮቹ ላይ ተዘረረ፡፡
ጥሻው ውስጥ የነበረ ሰው አሳዛኝ ጩኸት አሰምቶ ተንደርድሮ አጠገቡ ደረሰ። ሰውዬው ንቁ ዓይኖችና መካከለኛ ቁመት አለው፡፡ የማይመች አደገኛ ሰው ቢመስልም ከከናፍሮቹ ስስ ጫፍ ላይ ደግ የሆነ ፈገግታ ይነበብበት ነበር፡፡ ሰውየው ወደ ወንዙ ዘሎ ከገባ በኋላ ልክ ለማኙ ሕጻን ልጅ እንደሆነ ሁሉ ክንዱን ይዞ ተሸክሞ ወደ ወንዙ ዳር አወጣው፡፡ ለማኙ ማቃሰቱን፣ ማቋረሩን ቀጥሏል፡፡ የተጎዳውን እግሩን ምርቅዝ ቁስል ለመንከባከብ የሚቻል አይመስልም። የአበጠው ጉልበቱም እየደማ ነበር፡፡ ስስ የእንባ ዘለላዎች ወደ ዓይኖቹ ቆቦች ተንቆረዘዙ፡፡  
እንግዳው ሰው ቀና ብሎ ዙሪያ ገባውን ተመለከተ፡፡ ምልከታው የታሰበበትና ጥንቃቄ የታከለበት ይመስላል፡፡ ሁሉም ነገር የምሽት ጸጥታና ስክነት ረብቦበት ነበር፡፡ ቀጥሎ እንግዳው ሰው ወደ ለማኙ ጠጋ ብሎ ልክ እናት ጨቅላ ልጇን በምትንከባከብበት የላቀ ጥንቃቄ ዓይነት፣ ቁስሉን በወንዙ ውኃ ማጠብ ጀመረ፡፡ ከቁስሉ የሚመረቅዘው ደም የሚያቆም አይመስልም፡፡ ደሙ በኃይል የሚንፎለፎል ባይሆንም ቀስ እያለ ይወርዳል፡፡ እንግዳው ሰው ፈጠን ብሎ ወደ ጥሻው ገባ፡፡ አጎንብሶ ከቁጥቋጦዎች መሃል የሆነ ነገር የሚፈልግ ይመስላል፡፡ በጣቱ የሆነ ምንነቱ የማይታወቅ አረንጓዴ አገዳ እየሰባበረ ከጉንብሱ ቀና አለ፡፡ በጠንካራ ጣቶቹ አረንጓዴ አገዳዎቹን እያላመ ተመለሰ፡፡  
ያላመውን ነገር በቁስሉ ላይ አደረገለት። ለማኙ ለቁስል መጠቅለያ ፋሻነት የሚያገለግል ንጹህ ልብስ ስላልነበረው እንግዳው ሰው የለበሰውን ከካናሪ ደሴት የሚመጡ ሰዎች ለቀራጮች በመታያነት የሚሰጡት ከምርጥ ሀር የተሰራውን ሽርጥ ቀዶ ፋሻ አዘጋጀ፡፡ ለማኙ እንግዳው ሰው የሚያደርገውን ያለ አንዳች ንግግር በጽሞና ይከታተላል፡፡ እንግዳው ሰው ሙሉ አትኩሮቱ ቁስሉ ላይ ብቻ ነው፡፡ ደሙ መንጠባጠቡ እንዳበቃ ፋሻውን ቁስሉ ላይ አሰረው፡፡ በነጩ የሀር ፋሻ ላይ ምንም የነተበ የደም ጠብታ ባለመታየቱ እንግዳው ሰው ረካ፡፡ እርካታውን በፈገግታ በከናፍሮቹ ስስ ጫፍ አንጸባረቀ፡፡
ለማኙ ዝግ ባለ ድምጽ አጉተመተመ፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ! ድኛለሁ፡፡››
እንግዳው ሰው መለሰ፡፡ ‹‹አትጨነቅ… ይሄ ዕጽ ቁስልህን ይደፍንልሃል፡፡››
ለማኙ ሰው ለመነሳት ተውተረተረ፡፡ እንግዳው ሰው በደግነት ሁለቱንም እጆቹን ዘርግቶ ለማኙን እንዲነሳ ረዳው፡፡ የምስኪኑ ሰው ልብስ በውኃው ረጥቦ ከሰውነቱ ጋር ተጣብቋል፡፡ እንግዳው ሰው የለበሰውን ልብስ አውልቆ ሰጠው፡፡ ለማኙ ተደንቆ ተመለከተው፡፡ እንግዳው ሰው ከውስጥ የሚያምር የናይለን ሙሉ ልብስ ለብሶ ነበር። ሸሚዙን በማውለቅ ላይ እያለ ለማኙ፣ ሰውየውን በጥንቃቄ አጠናው፡፡ ሁለት ነገሮች በአዕምሮው ተቀረጹ፡፡ የሰውየው ንቁና አንጸባራቂ ዓይኖችና የተጠቀለለ ቡናማ ጸጉሩ…
ሰውዬው ለማኙን፣ የሚመረኮዝባትን በትርና አኮፋዳውን ያዘ፡፡ የአኮፋዳውን ባዶ መሆን ሲመለከት ሰፊውን ቀበቶውን ፈታ። ጩቤውና አፈሙዙ ሰፊ የሆነው ሽጉጡ ወዲያው ብቅ አሉ፡፡ ሰውየው ከውስጠኛው ሱሪው ኪስ የብር ሳንቲሞችን አወጣ፡፡ ከመካከላቸው አንዲት የቬንዚዌላ የወርቅ  ሳንቲምም ነበረች፡፡ እንግዳው ሰው ለአፍታ ከተመለከታቸው በኋላ ወደ ለማኙ አኮፋዳ ወረወራቸው፡፡ ‹‹በራሱ ፈቃድ ስለወጣ ላንተ አስፈላጊ መሆን አለበት፡፡›› አለ፡፡
ለማኙ የእንግዳውን ሰው እጆች ለመሳም ሞከረ፡፡ ገንዘቡ አስቦት የማያውቀው ሀብት ሆነበት፡፡ የሰውየው ከልክ በላይ የሆነ ውለታ እያሰበ እየተሰናከለ ሲራመድ፣ ምስጋናና ምርቃት እያጉተመተመ ነበር፡፡ እንግዳው ዙሪያ ገባውን ከተመለከተ በኋላ ‹‹ዛሬ አንተን የመርዳት ተራ የእኔ ነው፡፡ ነገ ምናልባት አንተ እኔን የምትረዳበት ተራህ ይሆናል፡፡››
ጸሐይዋ ከዚያ ወዲያ የለማኙን ዓይን አታጥበረብረውም፡፡ ከተማው ለመድረስ ብዙ መንገድ ይቀራል፡፡ ለጋስ፣ ለስለስ ያለ የጸሐይ ጨረር የመኸሩን አመሻሽ ድምቀት አልብሶታል፡፡ ለማኙ የተነፋፋ እግሩን ችላ ብሎ በደስታ ለብቻው ማዝገሙን ቀጠለ፡፡
ወደ መጠጥ ቤቱ ሲደርስ መብራት ያዢው አሁንም ድረስ መብራቱን አለኮሰም። መሰላሉ ግድግዳውን ተደግፎ ቆሟል፡፡ ከስር ዘወትር እርሱ የሚለኩሰው ፋኖሱ ተንጠልጥሏል፡፡ በመሸታ ቤቱ ውስጥ በጠጭዎች መሃል በቅርቡ ኦቬጆን ስለፈጸመው የጀግንነት ተግባር የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ይሰማሉ፡፡ ዛውታ በተባለ ቦታ የከብት እርባታ ጣቢያን ዘርፎ አንድ ሰው በጩቤ ወግቶ መግደሉ ተሰምቷል፡፡ በመጠጥ ቤቱ በር በኩል የጠጭዎቹ ሰፋፊ ፊቶች ይታያሉ፡፡ የለማኙን የተነፋፋ እግር በጨረፍታ ሲመለከቱ አሳዛኝ ድምፁን እያንቋረረ፣ አዳፋ ባርኔጣውን ዘርግቶ እንደሚለምናቸው በመጠበቅ ሁሉም ዝም ዝም አሉ፡፡
ለማኙ እንደተለመደው በመለመን ፋንታ እያነከሰ፣ ወደ አንደኛው ጥግ ሄዶ ከተቀመጠ በኋላ መጠጥ አዘዘ፡፡ ከሸሚዙ በታች የልብሱ እርጥበት አሁንም ድረስ ይሰማዋል። እርቦታል፤ በርዶታል፡፡ ጣፋጩን መጠጥ ከተጎነጨ በኋላ የቂጣ ድርቆሹን በትዕግስት ማድቀቅ ጀመረ፡፡
ሌሎቹ ጠጪዎችም እርሱን መመልከቱን አቁመው ወደ ቀደመ ወሬያቸው ተመለሱ፡፡ መብራት ያዢው ‹‹የምትሃት ኃይሎቹ ከሆነ የሚያሳስቡን፣ አሁንም በርካታ ጥበቦች እንዳሉት እናገራለሁ፡፡›› አለ፡፡
የመጠጥ ቤቱ ጠባቂ፣ ተጠራጣሪው ወደ ወሬው ተመልሶ፣ ‹‹ሁለት አፈሙዝ ባለው ጠብመንጃዬ ባገኘው ምትሃቱ ሁሉ በኖ ይጠፋ ነበር፡፡››
ግዙፍ ጥሩ ቁመና ያለው ክልስ ‹‹ኦቬንጆ ምን እንደሚመስል ማወቅና ጭንቅላቱን ሰጥቻቸው 500 ፔሶ መሸለም እፈልጋለሁ፡፡ ሞቶም ይሁን በሕይወት እያለ ኦቬንጆን ይዞ ለሚያስረክብ 500 ፔሶ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል እኮ፡፡››
ጥቁሩ ሰው ቀጠለ፤ ‹‹እሱማ ቀላል ነው። ፈዛዛ ቢጫ ቀለም ያለው፣ ግዙፍ፣ ሳንቲም የመሰሉ አንጸባራቂ ዓይኖች ያሉት ባለ ቡናማ ጸጉር ሰው ነው፡፡ አሁን ወደ ተራራ ሂድና ይዘኸው ና፡፡ ይዘኸው ስትመጣ የመጠጤን ትከፍልልኛለህ፡፡››
ለማኙ ደረቁን ምግቡን በምራቁ ለማራስ እየተጣጣረ አውጠነጠነ፡፡ ‹‹ወንዙ ጋ ያገኘሁት ሰው ኦቬጆን ነበር፡፡ 500 ፔሶ እሱን በሕይወትም ይሁን ሞቶ ለመያዝ ለሚረዳ ሰው፡፡ ይሄ ጠንቋይ ኦቬጆን ነፍሱን ለሳጥናዔል ሸጧል፡፡ ካጋለጥኩት ከዚህ ወዲያ ከልመና እወጣለሁ፡፡ እራሴን በእነዚያ ጎዳናዎች ላይ ሁሉ መጎተቴ ያበቃል፡፡ 500 ፔሶ! ገንዘቡን ካገኘሁት ደህና እሆናለሁ፡፡››
ለማኙ የሚበላው ሌላ የደረቀ ቂጣ ለማውጣት እጁን ወደ አኮፋዳው ሲልክ ከሳንቲሙ ጋር ተገጣጠመ፡፡ ወዲያው የወርቅ የቬንዚዌላ ሳንቲሟን አስታወሳት፡፡ ማሰቡን ቀጠለ፡፡ ‹‹ኦቬጆን ሌሎች በርካታ የቬንዚዌላ ሳንቲሞች ሊኖሩት ይችላል። ሲሰጠኝ ቅርም አላለውም፡፡ ደግ ሰው ነው፡፡ ችሮታ ለማድረግ ከሆነ የሚዘርፈው ይደንቀኛል፡፡ ምክንያቱም እርዳታ መስጠት ይወዳል፡፡ እነዚህ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይጠሉኛል፤ ይጸየፉኛል፤ እናም አንድም ቀን እግሬን ሊያጥቡልኝ አይችሉም። ደረጃው ከፍ ያለ ሰው ሆኖ ሳለ ለምን እርሱ ብቻ ሀዘኔታ ሊያሳየኝ ቻለ?›› ዓይኖቹን፣ ፈገግታውን፣ ጸጉሩን አስታወሰ፡፡
በመንገዱ ላይ የተለመዱ የፈረስ ኮቴዎች ሲሰሙ ለማኙ ማን እንደሆነ ለማየት ወጣ፡፡ ዥጉርጉር ፈረስ የኮርቻው የፊተኛው ክፍል ከበግ ለምድ የተሰራ ጌጥ ነገር ለብሷል። ሰውየው ረጅም ቡትስ ጫማ አድርጓል። በፈጣን ግልቢያ ላይ ያለው ሰው ድንገት ወደ መጠጥ ቤቱ ዘወር ሲል ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ፡፡ ለማኙ አንገቱን ደፍቶ ድምጹን አጠፋ፡፡ የመጠጥ ቤት ጠባቂው ምን እንደሆነ ለማየት ቢቅበዘበዝም፣ ጋላቢው ሰው ገና ድሮ ሄዷል፡፡
ለማኙ ለራሱ አጉተመተመ፡፡ ‹‹ኦቬጆን ነበር፡፡ ዓይኖቹን አይቻቸዋለሁ፡፡ ዓይኖቹ ልክ እንደ ጩቤ ዓይኖቼን ወግተዋቸዋል፡፡››
መብራት ያዢው፤ ‹‹መብራቶችን ላበራቸው ነው፡፡›› አለ፡፡
የሚያብለጨልጨው ጥቁር ሰው ሕንዶቹ ላይ ቀልድ እየፈጠረ ነበር፡፡ ‹‹ደህና ለምን ኦቬጆንን ፍለጋ አትወጡም? ልብ አደርጉ፤ ዛሬ ማታ ኦቬጆንን ከያዛችሁት በሽርሽር ዛፍ ላይ ተንጠልጣይ አልጋችሁ ላይ መተኛት ትችላላችሁ፡፡ ውጡና ፖኤብሎንን  ዙሩዋት፡፡ አሁን የመፈለጊያ ግዴታችሁ ሰዓት ነው፡፡ ኦቬጆንን አድኑ፡፡››
ለማኙ ለራሱ ማንሾካሾኩን ቀጥሏል፡፡ ‹‹እራሱ ነበር፡፡ በትክክል ራሱ ነበር፡፡ እየሸሸ ነው፡፡ የሆነ ሰውን ገድሏል ወይም ዘርፏል፡፡ ማንን ይሆን?››
 ወዲያው አራት የታጠቁ ሰዎች እየሮጡ መጥተው ወደ መጠጥ ቤቱ ገቡ፡፡
‹‹ሲያልፍ ያየው ሰው አለ?›› ጠጪዎቹ ላይ አፈጠጡ፡፡
‹‹ማንን? ማንን?››
‹‹ኦቬጆን? ኦቬጆን?››
ሁሉም በመገረም እርስ በእርስ ተያዩ፡፡
‹‹ኦቬጆን! ኦቬጆን!›› ደጋገሙት፡፡
ወታደሮቹ ቀጠሉ፤ ‹‹ዥጉርጉሯ ባዝራ ተሰርቃለች፡፡ የጀኔራሉ ኮርቻና ጫማም አብሮ ተወስዷል፡፡››
‹‹ያየው ሰው ይኖር ይሆን?››
የመጠጥ ቤቱ ጠባቂ ተናገረ፤ ‹‹የሆነ ሰው እየጋለበ አልፏል፡፡››
ሰዎቹ አከሉ፤ ‹‹አዎ፤ በነጭና ጥቁር ዥጉርጉር ባዝራ ላይ የሆነ ሰው አልፏል››


Read 1675 times