Saturday, 08 September 2012 12:14

‘እኩይ ፋይሎች’ እና ‘ቶክሲክ ዌስት’…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡

ስሙኝማ…በብዙ መለኪያዎች እየጨረስነው ያለው ዓመት ጥሩ ዓመት አልነበረም፡፡ አንዱ ችግር በሌላው እየተተካ  ለወትሮው “የአዲስ ዓመት ዕቅድህ…” ምናምን የሚባሉ ነገሮች አሉ አይደል…ዘንድሮ ግን ለዓመት ምናምን ብቻ ማሰብ መተው ያለብን ይመስለኛል፡፡እናማ…ምን መሰላችሁ፣ በርካታ መዘጋት ያለባቸው ‘እኩይ’ ፋይሎች አሉ፡፡ ከዓመት ዓመት ውፍረታቸው እየጨመረ የሚሄድ፣ እንደ ጀርባ ላይ ምናምን ነክሰው የያዙን መዘጋት፣ መሽቀንጠር፣ መጥፋት ያለባቸው ፋይሎች፡፡  ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ ራስነ በደንብ ማየት አሪፍ ነው፡፡ በፋንታሲ ዓለም ስንኖር እንከርምና ድንገት ስንነቃ እውነተኛው ዓለም ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከጊዜ ብዛት አፈ ታሪኮች እንደ ታሪክ ይቆጥሩና የሌለውን ነገር እንዳለ ስንቆጥር ያለውን ግን የሚያየው ይጠፋል፡፡

መጀመሪያ ምን ነገር አለ መሰላችሁ… እግር ተወረች ሸቅቦ የያዘንን የግልጽና የስውር የምቀኝነት ፋይል መዘጋት አለበት፡፡

ደግሞላችሁ…አገሪቷን በታሪኳ ሁሉ እንኳን ሊዘጋ ጭርሱን እየወፈረ የሄደ ፋይል አለ-- የአስመሳይነት ፋይል! በፊት ለፊት ጥርሶቻችንን ብልጭ እያደረግን በጀርባችን ካራ የምንጨብጥ፣ ፊታችን ለማሳየት ካሜራ ፊት የምንጋፋ…ዘወር ብለን “ሠራሁላቸው!” አይነት የምንል በዝተን የአስመሳይነት ፋይል ለሸክምም እያስቸገረ ነው፡፡

ስሙኝማ…የሆነ ሰው በማይታወቅበት አካባቢ ሄዶ…አለ አይደል… “እግሬን በውሀ እጠቡ” አይነት ጉራ ምናምን ነገር ሲያበዛ… “ጅብ በማያውቁት አገር ቁርበት አንጥፉልኝ አለ…” ምናምን ነገር ይባላል፡፡ ዘንድሮ እንግዲህ ተረት እንኳን የተቀለበሰበት ዘመን አይደል…ሲገርማችሁ ይኑር ብሎን ጅብ ‘በሚያውቁት አገር’ እንኳን “ቁርበት አንጥፉልኝ” ሲል ይቺን ታክል እፍረት አይሰማውም፡፡ ቁርበት አስነጣፊ ሲበዛ…የተበላሸ ፋይል አለ ማለት ነው፡፡

ስሙኝማ…‘ፈረንጆች’…‘ኤ ኔው ቢጊኒንግ’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ በሁሉም በኩል የሚያስፈልገን ይኸው ነው፡፡ ‘ኤ ኔው ቢጊኒንግ’ ነገሮችን የማንሳትና የመጣል ጉዳይ ሳይሆን ይበልጡኑ መንፈስ የማደስ፣ የማከም፣ የማጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ውስጣችን ከተከማቹት ‘ቶክሲክ ዌስቶች’ (ፈረንጂኛ በአማርኛ ብዜት ይሏችኋል ይሄ ነው፡፡) ራሳችንን ማጽዳት ነው፡፡ ዓመት መጥቶ ዓመት ሲሄድ እንዲሁ እየተሸነጋገልን፡ በዘፈንና ከንፋሱ አቅጣጫ ጋር አቅጣጫውን በሚለዋውጥ ‘ፓትርዮቲዝም’ ዳሴ እያዥጎደጎድን… ‘ስንተዋወቅ እየተናነቅን’ ነው፡፡ የምር ያሳዝናል…የትናንቱን ችግር ሳንነቅል አዲስ ችግር እየተተከለብን… ‘ወስፌና ዋግምት’ ከመፈለግ ይልቅ እርስ በእርስ ጣት እየተቀሳሰርን ነገሮች ከወስፌና ዋግምት አቅም በላይ እንዳይሆኑ መፍራት ብልህነት ነው ፡፡

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ደግሞላችሁ ጊዜ መጠኑን እየጨመረው የሄደው ነገሮችን ሁሉ በ‘አገርና በወንዝ ልጅነት’ የመመልከት ‘ቶክሲክ ዌስት’ ከውስጣችን አልወጣ ብሎ ‘ዝም አየነቅዝም’ በሚል ብሂል አፋችንን እየተመተምን ተአምር እስኪወርድ እየጠበቅን ይመስላል፡፡  ሰው የምንገምተውና አግልግሎት የምንሰጠውና የምንንፈገው በአገር ልጅነት እየሆነ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ የ‘አገር ልጅነት’ እየጠበበች፣ እየሟሸሸች ወደ መንደር ደረጃ ስታቆለቁል ስናይ የምር የጎጠኝነት ‘ቶሲክ ዌስት’ ምን ያህል የእያንዳንዳችንን አእምሮ ሰርስሮ ሊገባ እንደ ደረሰ ስናይ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡

ደግሞላችሁ…አእምሯችንን ከላይ እሰከታች ያጥለቀለቀው ሌላ ‘ቶክሲክ ዌስት’ ምን መሰላችሁ…ሀሜት! ወሬ! ወሬ!  ወሬ! የምር ነው የምላቸሁ… እዚህ አገር ወሬ በምን ያህል ፍጥነት እየተፈጠረ፣ ‘ኤዲት’ እየተደረገ፣ እንዴት ይዘቱን ለውጦ እንደሚመጣ ባለፉት ጥቂት ወራት ያየነውን ያህል መቼም አይተን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ የእኛ ነገር አንዳንዴ እኮ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የእኛ የጆሮ ህዋሳቶች ከሌላው የሰው ልጅ ተለይተው ‘መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ፊልተር እንዲያደርጉ’ የተፈጠሩ ይመስላሉ፡፡

ችግሩ ምን መሳለችሁ…“ለምን?” “እንዴት?” “በምን ምክንያት?” የሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎችን የሚጠይቅ ቢንኖር በጣም፣ ‘እጅግ በጣም’ ጥቂት ናቸው፡፡ እነኚህ ጥያቄዎች ባለመጠየቃቸው እነ ስቴፈን ኪንግ እንኳን ሊያስቧቸው የማይችሏቸውን ታሪኮች ስንሰማ ከርመናል፡፡ አሀ…ሳይንስ ፊክሽን እንኳን እኮ መነሻ አለው፡፡

እናላችሁ…ሌላው ደግሞ በማህበራዊ ኑሮም፣ በሥራም፣ በሌሎች ከሰዎች ጋር ባሉ ግንኙነቶችም  ያስቸገረ ‘ቶክሲክ ዌስት’ ምን መሰላችሁ-- ሀሜት! ብዙ መሥሪያ ቤት እንኳን ሠራተኛው… አይደለም ከማን ጋር ኛይ እንደሚጠጣ፣ ማንን አጥብቆ ሰላም እንደሚል፣ ማንን ከአንገት በላይ በምልክት እንደሚያልፍ እየታየ በዛው ልክ የተለየየዩ ቦከስ ፋይሎች ይዘጋጁለታል፡፡

ወዳጅነቶች እየተንኮታኮቱ፣ ትዳሮች እየፈረሱ፣ የጋራ ስብስቦች እየተነኑ ያሉት በአብዛኛው ሀሜት በሚሉት ‘ቶክሲክ ዌስት’ ነው፡፡

ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በትንሹም በትልቁም የኃላፊነት ወንበር መቀመጥን “ሥዩመ እግዚአብሔር…” ተብሎ እንደ መቀባት የሚቆጥሩ ሰዎች እየበዙ የስልጣን ‘ቶክሲክ ዌስት’ አገር እያመሰ ነው፡፡ የማን ኃላፊነት የትኛው ጥግ ድረስ እንደሚሄድ፣ ማን ምን ማድረግ… ምን አለማደረግ እንደሚችል፣ ‘ትንሹ’ ቢበድለን “የፍርድ ያለህ! የባንዲራ ያለህ!” የምንልበት ‘ትልቁ’ የትኛው እንደሆነ ግራ እየገባን የሚነግረን እያጣን…የመጥረጊያ ቁራጭ ከያዘው የ‘ጎልድ ሌብል ብርጭቆ’ እስከጨበጠው ሁሉም የማርያም ጠላት ነገር ሲያደርገን… አሪፍ አይደለም፡፡

ምን መሰላቸሁ…ሁልጊዜም በሆነ ምክንያት አቧራ ሲነሳ ‘ተመሳስለን’ ቁጭ ነው! የእያንዳንዳችንን እውነተኛ መልክ ለማየት አቧራው እስኪረጋ መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ደግሞም እመኑኝ… ‘የማይረጋ አቧራ’ የለም፡፡ ያኔ አየሩ ሲጠራ ነው ከ‘አንድ ወንዝ የተቀዳን’ እንመስል የነበርነው ሁሉ ከስንት ወንዝ እንደተቀዳን የሚታየው፡፡

እናላችሁ…ድፍን አገርን ትንፋሽ እያሳጣ ያለ ከሁሉም እየባሰ የመጣ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ኑሮ ተወዷል የሚለው ቃል ብቻ ሊገልጸው የማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ ይህን፣ ውፍረቱ ሙሉ መዝገብ ቤቱን ሊሞላ ምንም ያልቀረውን ፋይል ወይ ካልጠፋን ወይ ካልቀነስን መጪው ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው የሚጠብቀን፡፡

እናማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ተሽቀንጥሮ መጣል’ የሚገባውን አሽቀንጥረው እየጣሉ፣ ‘መሻሻል’ የሚገባውን እያሻሻሉ፡ ‘ባለበት መቀጠል’ የሚገባውን ከእነወንዙ እየያዙ፣ አዲስ ለሚያስፈልገው አዲስ ነገር እየፈለጉ መሄድ ካልተቻለ…አለ አይደል… ነገራችን “ጸጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል…” ነው፡፡ የምርም… አብዛኛው የዘንድሮ ነገራችን የ‘ጸጉራም ውሻው’ ነገር አይነት ነው፡፡

ስሙኝማ… ለዘመናት ስር እየሰደደ የቆየ ረጃጅም ስሮች ያሉት ‘ቶክሲክ ዌስት’ አለ-- “ሰው ለምን ደስ ይበለው!” የሚሉት  በባዶ ሆዳችን ቁንጣን ያስቸገረን እንድንመስል የሚያደርገን፡፡ ቢርበንም ሸሽገን፣ ቢቸግረንም ሸሽገን፣ ቢከፋንም ሸሽገን፣ ብንበደል ሸሽገን… በ“ሰው ለምን ደስ ይበለው!” ‘ቶክሲክ ዌስት’ ጸጉራም ውሻ ነገር የሆንን ብዙዎች ነን፡፡

እናላችሁ…ዘላለም ወደኋላ እየተመለስን አቧራ የምናራግፍባቸውን ፋይሎች እስከ ወዲያኛው ለመዝጋት ዝግጁነቱ ከሌለን፣… በአይነትና በብዛት ሲስተማችንን ሁሉ የበከሉትን ‘ቶክሲክ ዌስቶች’ ጠራርገን ለማስወጣት ፈቃደኛ ካለሆንን፣…‘ኤ ኒው ቢጊኒንግ’ የሚሉት ነገሮችን በማንሳትና በመጣል ላይ ሳይሆን አእምሮን ሙሉ ለሙሉ የማጥራት መንገድ እንዳለ ለማመን ፍቃደኛ ካልሆንን…አለ አይደል…በእርግጥም “እውነት የእኛ መጨረሻ ምን ይሆን!” ያሰኘናል፡፡

መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡

ሸገሮችን ልዋስና… ‘ኢትዮዽያ ለዘለአለም ትኑር!’

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

 

Read 1938 times Last modified on Saturday, 08 September 2012 12:18