Saturday, 14 August 2021 10:58

መንግስት የአምነስቲ ሪፖርት በተሳሳቱ መረጃዎች የተሞላ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በትግራይ ጦርነቱን ተከትሎ የተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን አስመልክቶ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ያወጣው የምርመራ ሪፖርት በተሳሳቱ መረጃዎችና የጥናት ስልት ላይ የተመሰረተ ነው ሲል የኢትዮጵያ  መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱን አጣጥሎታል።
አምነስቲ ጥናቱን ያከናወነው  በሱዳን የስደተኛ መጠለያ ካምፖች ውስጥ በርቀት በተደረጉቃለ-ምልልሶች መሆኑን በመጠቆምም፤ ድርጊቱ በስፋት ተፈጽሟል የተባለበት መንገድ አስተማማኝና በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አይደለም ብሏል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማክሰኞ እለት ይፋ ባደረገው ባለ 39 ገጾች ሪፖርቱ ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ባሉ ሶስት ወራት 1288 ሴቶች ስለመደፈራቸውን ከጤና ተቋማት ባሰባሰብኩት መረጃዎች አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህ ጥናት ቃለ ምልልስ ከተደረገላቸው 68 የጥቃቱ ሰለባዎች ውስጥ አብዛኞቹ  ወደ ጤና ተቋማት አለመሄዳቸውን ያመለከተው ተቋሙ ወደ ህክምና ተቋማት የሄዱ የተጠቂዎች ቁጥር  የጥቃቱን ስፋት አያሳይም፤ አብላጫው የጥቃቱ ሰለባዎች ወደ ህክምና ተቋማት አልሄዱም ብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የአምነስቲን ሪፖርቱን  በተቸበት መግለጫው፣ የመረጃ ምንጮቹ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ እንዳለውና የመረጃ አሰባሰብ ስልቶቹ ሳይንሳዊ እንዳልሆኑ አመልክቷል።
ተቋሙ በአመዛኙ በሱዳን ስደተኛ ጣቢያ የተጠለሉና ሳምሪ በተባለ ቡድን ውስጥ ተሳትፎ አላቸው ተብለው በወንጀል ከተጠረጠሩ አካላት ጋር በተደረገ ቃለምልልስ ላይ የተመሰረተ መረጃን ይዞ ጥልቅ ድምዳሜ ላይ መድረሱም አግባብ አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቁሟል- በመግለጫው።
አምነስቲ በዚህ ሪፖርቱ፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ክልል ሃይሎች አስገድዶ የመድፈር ጥቃት እንዲሁም የወሲብ ባርያነትና እገታን መፈጸማቸውን አመልክቷል።
በዚህም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ባለሙያዎች ምርመራ ተካሂዶ አጥፊዎች ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው አሳስቧል።
የአምነስቲን ሪፖርት ክፉኛ የተቸው መንግስት በበኩሉ፤ ሪፖርቱ የመንግስትን ጥረቶች እውቅና ያልሰጠ ውንጀላ ላይ ብቻ የተመሰረተ፣ በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ እንዲሁም ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ የጥቃት ሪፖርቶች፣ በመንግስት ላይ ስም ማጥፋትን ያለመ ነው ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በአምነስቲ የምስራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት ውስጥ ስላሉ አንዳንድ ሰራተኞቹ ገለልተኛነትና ሙያዊ ብቃት አሁንም ፍተሻ እንዲያደርግ መንግስት ጠይቋል።

Read 12868 times